Print this page
Saturday, 21 April 2018 11:36

“ለራስህ ነው” የሙዚቃ ኮንሰርት ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የጃኖ ባንድ አባላት፤ በቅርቡ ባወጡት “ለራስህ ነው” በተሰኘው አዲስ አልበም መጠሪያ የተሰየመ የሙዚቃ ኮንሰርት ሚያዚያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂዱ የባንዱ ማኔጀር አቶ ሳሙኤል ተፈራ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡ ኮንሰርቱ በሚሊኒየም አዳራሽ ግቢ ውስጥ በልዩ የመድረክ ዝግጅት ከአዳራሽ ውጭ እንደሚካሄድም ማናጀሩ ተናግረዋል፡፡
የአልበሙን መውጣትና ተቀባይነት ማግኘት ተከትሎ በሚያቀርቡት በዚህ ኮንሰርት መክፈቻ ላይ ልጅ ሚካኤል፣ ሳሚ ዳንና ስካት ናቲ በተጋባዥነት እንደሚያቀነቅኑም ታውቋል፡፡ የኮንሰርቱ መግቢያ ለተማሪዎች 200 ብር፣ ለመደበኛው 400 ብር እና ለቪአይፒ 1000 ብር መሆኑ ተነግሯል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ ከ15-20 ሺህ የሚደርስ ታዳሚ እንደሚጠበቅ ማናጀሩ ገልፀዋል፡፡ የአዳራሹ በር ከምሽቱ 1፡00 ጀምሮ ክፍት ሲሆን ዲጄ ሼሪና ዲጄ ኢዩ ታዳሚውን በሙዚቃ እንደሚያዝናኑም ታውቋል፡፡ የኮንሰርቱ አዘጋጅ በኩሪፍቱ ሪዞርቶች የሙዚቃ ድግስና ሌሎች ሁነቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው “ክስተት ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንት ሲሆን ኮንሰርቱ በብዙ ድካም የተዘጋጀ በመሆኑ የሙዚቃ አፍቃሪውን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያዝናና የገለፁት የባንዱ ማናጀር፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከመንግሥት አካል ተገቢውን ማግኘት የሚገባቸውን ፈቃድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባንዱ በተከታታይ ቀጣይ ሳምንታት በመቀሌና በሃዋሳ ኮንሰርት የሚያካሂድ ሲሆን በመቀጠልም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችም እየተዘዋወረ የኮንሰርት ሥራዎቹን ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ማናጀሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 1262 times