Print this page
Monday, 23 April 2018 00:00

ስምህ ማነው? “What is in a name?”

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

‹‹ሰው በመወለድ ማደግና መሞት መካከል ሦስት ስሞችን ያስተናግዳል፡፡›› ይላሉ፡፡ ቤተሰቡ የሚያወጣለት፡ ማሕበረሰቡ እርሱን የሚያውቅበትና በህይወት ዘመኑ መጨረሻ የሚያገኘው ስሙ፡፡ ‹‹ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል።›› እንዲል መጽሐፍ፡፡
የአስቆሮቱ ይሁዳ
ወላጆቹ ‹‹ይሁዳ›› የሚለውን የተከበረ ስም አወጡለት።
በሐዋርያት የገንዘብ (ከረጢት) ያዥነት ታወቀ፡፡
ኢየሱስን በ30 ዲናር አሳልፎ ሰጥቶ ከሀዲ ሆነ፡፡
በነገራችን ላይ ይሁዳና የአስቆሮቱ ይሁዳን የማምታታት ግንዛቤ በስፋት ይታያልና ለማስተዋል ብንሞክር . . .
ይሁዳ እጅግ የተከበረ ታላቅ ስም ነው። ትርጉሙም ‹‹ማመስገን›› ማለት ነው፡፡ ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት 4ኛ ልጅ፡፡ ከእስራኤል ነገዶች የአንዱ አባት የሆነ፡፡ በስሙም ነገደ ይሁዳ ተብሎ የተጠራ፡፡ በያዕቆብ በአንበሳ የተመሰለ፡፡ አለቅነት ከይሁዳ እንዲሁም አሕዛብ የሚገዙለት ገዢ ከይሁዳ እንደሚመጣ የተተነበየለት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የተወለደበት፤የይሁዳ ወገንና የዳዊት ቤት ነገሥታት የነገሡበት የይሁዳ መንግሥት። የእስራኤላዊያን ምድርና ሕዝብ አይሁዳዊያን መጠሪያ...ነው፡፡ክርስቶስም ከይሁዳ ወገን ተወለደ፡፡
በአዲስ ኪዳን ይሁዳ በሚለው ስም የተጠሩ ብዙ አሉ፡፡ ከሐዋርያት አንዱ የያዕቆብ ልጅ (ታዴዎስ/ልብድዮስ) ይሁዳ፤ በ6ኛው ዓ.ም በሮማዊያን ላይ አምጾ የተገደለው ይሁዳ፤ ጳውሎስን በቤቱ ያስተናገደው የደማስቆው ይሁዳ፤ የኢየሩሳሌምን ውሳኔ ያወጀው በርስያን የተባለው ይሁዳ፤ የጌታ ወንድም የሚባለው የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤እናም ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ....ናቸው፡፡ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው፣ ከአስቆሮት የይሁዳ አውራጃ ከነበረችው ቂርያትሐጾር የመጣ ስለነበር ነው፡፡
መቋጫውን፤ የያኔውን ኩነት ከአሁን ጊዜ ትዝብቱ አሰናስሎ በቋጠረልን በገጣሚ አማኑኤል መኻሪ የ‹‹ጥለት›› ስንኝ እንሸምነው  . . .
‹‹.ቅልስልሱ ይሁዳ››
ይሁዳማ ቅልስልስ ነው
አቅፎና ደግፎ
ክርስቶስን ሰጠ ለሞት አሳልፎ፡፡
የኛ ዘመን ሰው ግን
ሰቅሏችሁ ሲያበቃ በፈገግታው ክቦ
አቅፎ ይስማችኋል ዓይኑን በጨው አጥቦ፡፡
ማርያም መግደላዊት
ወላጆቿ ማርያም ብለው ስም አወጡላት፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ ክፉ መናፍስት የተጠናወቷት ሆና ታወቀች፡፡
ምህረቱን ታደለችና የኢየሱስ አገልጋይ ሆነች።
ማርያም መግደላዊት ሰባት አጋንንት ከወጣላት በኋላ ኢየሱስን ለማገልገልና ለኢየሱስ መሰቀልና መቀበሩ ምስክር ሆነች፡፡እንዲሁም ከትንሣኤው በኋላ በአትክልት ቦታ ለብቻዋ የተገለጠላት እድለኛ ሴት፡፡ እርሷም እንዲሁ መግደላዊት ተብላ መጠራቷ ምናልባት ከገሊላ ከተማ ከመጌዶል ስለመጣች ይሆናል፡፡ ልክ እንደ ይሁዳ ሁሉ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማርያም በሚል መጠሪያ ብዙዎች ይጠሩበታል፡፡ የኢየሱስን እናት ድንግል ማርያምን ጨምሮ የአልዐዛርና ማርታ እህት ማርያምና የቀለዮጳ ሚስት፡ የያዕቆብ የዮሳም እናት፡ የማርቆስ እናት . . .፡፡
የሰውን ሶስት ስሞች እስቲ ደግሞ በፈጠራ ገጽ እንመልከተው፡፡ በደራሲ አበራ ለማ ‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› አጭር ልቦለድ ገጸ ባሕርይ  . . .
ሞገደኛው ነውጤ
ወላጁ/ደራሲው ሞገደኛው ነውጤ የሚል ስም/ርዕስ አወጣለት፡፡
በማህበረሰቡ በባለ እጅ/አንጥረኛነት ሙያው፣ ኋላም ያለ ግብሩ ተወንጅሎ ታወቀ፡፡
ፍርድ ቤት ከተጠረጠረበት የሀሰት ክስ ነጻ መሆኑን አረጋግጦለት እንደ ቀድሞው ነጻ ሰው ሆነ፡፡
ችሎት ላይ ከክቡር ዳኛው ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ . . .
ዳኛ - ስምህ ?
ነውጤ - ነውጤ ደስታ
ዳኛ - ስራህ ?
ነውጤ - አንጣሪ
ዳኛ - ምንድነው እምታነጥር ?
ነውጤ - እህ! ‹‹ወርቅ›› ነውዪ ቅቤ አላነጥር!
(ሞገደኛው ነውጤ ደስታ ምን ግዱ! የዠማ ወንዝ ደራሽ ማዕበልም አልበገረው እንኳንስ a storm in a tea-cup. በንጽህናው ይተማመናላ፡፡)
ከሰው ሦስት ስሞች አንጻር ሀገርንም ለማየት ያህል . . .
እናት ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ የሚል የሉዐላዊ፣ ገናና. . . ትልቅ ሕዝብና የጥንታዊ ምድርነቷ መለያ እጅግ ክቡር ስም፡፡
አዱኛ ከዳትና በዓለሙ ሁሉ ዘንድ በሀፍረት በሚያሸማቅቅ መልኳ ታወቀች፡፡
? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ? ?  . . . . . . . . ሆነች፡፡/ትሆናለች፡፡
(እኮ ምን? ሆነች/ትሆናለች? ... በዚህ መረጃ ከነፋስ በቀጠነበት፣ አንዳች ገመና ላይሸሸግ አደባባይ ወጥቶ በሚሰጣበት የስልጣኔ ዘመን፤ የቢትልስን Lucy on the sky with diamonds እየቀወጡ መጥተው፤  ‹‹የሰው ዘር ሁሉ መገኛ እኛ ነን ብላችሁናል!›› ወይም ‹‹ተድቦልቡለን የተሰራንበት አፈር ከዬህ ዘንድ ነው ተብለናል!›› የሚሉ የመላው ዓለም ዜጎች ዙሪያህን አፍጥጠውብህ፤ ከኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ በየዘመኑ አሰባስበው ካቆዩትና አቧራውን እያራገፉ ሲያገላብጡት ከኖሩት የታሪክ ማህደራችን ጥልቅ ግንዛቤያቸው በመነሳት፤ ከቋንቋም ሁሉ መርጠው (Geez is the future እያሉ ነውና) ለነባሩ እና አለም ወደ ፊት ሊሸመጥጥበት ለተፈናጠጠው (በተለይ የሳባ ፊደል ለተራቀቀ ቴክኖሎጂ ቁልፍ በመግባቢያ ምልክትነት ሲውል በBlack Panther ፊልም ውስጥ ግዘፍ ነስቶ ማየታችንን ልብ ይሏል፤ ከሌሎቹም ለምስል ወ ድምጽ ግብዐትነት ከዋሉት እጅግ ብዙ አንጡራ የታሪክና የባህል ቅርሶቻችን መልኮች በተጨማሪ፡፡) ለጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ከሚቀርቡት ቋንቋዎቻችን መካከል በአንዱ የተዜመውን ስምን/ማንነትን የሚያጠይቀውን ውብ ዜማ ተውሰው፤ የቱባ ባህሉን የጭፈራ ስልትና ውበትም ጠብቀው፤ ቀስ በቀስ እየሰፋ እየሰፋ እየሰፋ ሄዶ፣ ሕዋውን ሊያክል ምንም እማይቀረው ትልቅ ክብ እየሰሩ፤ አታሞ እየመቱ፤ ‹‹ስምህ ማነው? ወንድም ስምህ ማነው?›› እያሉ መሀል ተገትረህ ጥያቄ በዜማ ሲያቀርቡልህ፤ አንተ ሆዬ፤ የገዛ ስምህንም መናገር ቸግሮህ፤ እከሌ ነኝ ለማለት እርግጠኝነት ነጥፎብህ፤ ወኔ ከድቶህ፤ ‹‹እኛኮ የሰው ዘር መገኛ ነን›› በሚል አጉል መደገግ (vain pride) ብቻ ዘመንህን በከንቱ አባክነህ፤ እንኳንስ ‹ወደ መነሻችን፣ወደ ምንጅላታችን ጎጆ› ብለው ከምድር ዙሪያ የመጡቱን እንግዶች የጥያቄ ቋት በቅጡ በተደራጀና በተትረፈረፈ የመረጃ ስንቅ ልትሞላ ቀርቶ፤ ለራስህም ተማምነህ እምትደገፈውም ሆነ ለነግ ትውልድ አወርሰዋለሁ እምትለው የጽኑ ማንነትን የወል ካስማ ለማቆም ሳትታትር ስለመርፈዱ፤ በዝንጋኤ ፀፀት አንተም እንደ ከበሮው ቆዳ ክፉኛ ስትወጠር ላፍታ ‹‹አስበው እስቲ!›› የሚል ሀሳብ ሽው አለኝ።  በበኩሌ . . . መቸም ‹‹ስሜ/ማችንን አላ/ናውቀውም›› ከሚል አንገት እሚያስደፋ ምላሽ፤ ወይም የተጋነነ ስም ሰይሜ ‹‹ዝኻያፍር ድሙ-ገብረ ማርያም ሽሙ!›› ከመባልም ለመትረፍ፤ ‹‹ዜማን በዜማ ሕብር የማዋሀድ ‹ሉላዊ ቅኝት›› ምናምን ... የሚል አጠር ያለ የ3 ሰአት መንደርደሪያ አስቀድሜ፣ በማስከተል የእጅጋየሁ ሽባባውን ቅኔ ተውሼ አንጎራጉር ይሆናል . . . ‹‹ስም የለኝ ስም የለኝ በቤቴ›› . . .) ብዙ ነው ለማለት - የስም ብዛት!!!
ይህን የሰውን ሦስት ስሞች ማያ መስተዋት ያቀበሉን አይሁዳዊያን፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መጠሪያ ስሞች ሁሉ በፍቺያቸው፤ በስም የጠባይ፣ ግብር እና ሁኔታ ገላጭነት ላይ እንደተመሰረቱም ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ ምን ነክቶት ነው እንግሊዛዊው ባለቅኔ ዊልያም ሼክስፒር፤ ‹‹ስም ከቶ ምንድነው?›› ሲል በልበ ሙሉነት ስምን ዋጋ ማሳጣቱ!
ምናልባት፤ ከላይ ከዘረዘርናቸው ምሳሌዎች መካከል ቋሚ ተፈጥሮውን ይዞ እንደዘለቀው እንደ ሞገደኛው ነውጤ ደስታ ላሉ የንጹህ ሰብእና መገለጫ ባሕርያትና በየትየለሌ ምክንያቶች አስገዳጅነት ከነባር ክብሯ ብትናጋም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሸርሸር በመሸራረፍ ስጋት፣ በቋፍ ላይ ያለውን ለብዙ ሺህ ዘመናት በጽናት ጠብቃ ያኖረችውን መሰረታዊ ማንነቷን፣ እጹብ ድንቅ አፈጣጠሯን ላለማጣት ለምትፍጨረጨረው እናም ተግዳሮቶቿን ሁሉ ድል ነስታ፣ ነግ ወደ ቀደመው ታላቅነቷ እንድትመለስ ተስፋ ለምናደርጋት እናት ሀገራችን የሚስማማ ሊሆን ይችላል፡፡ (‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ትንቢቱ ቃልን አምነን፡፡ እናም ተግባር አክለንበት፡፡) What is in a name ? That we call a rose, by any other name would smell as sweet. ጽጌረዳ አበባን በሌላ በምንም አይነት ስም ብንጠራት መዐዛዋ ያው ጣፋጭ ነው፡፡ (ያው እንግዲህ ጽጌረዳነቷ እስካልተለወጠ ድረስ ማለት ነው፡፡) to be or not to be , that is the question እንዲል መልሶ እርሱው ራሱ ብዕረኛው ጦር Shake ነቅንቅ Spear... ‹‹መሆን ወይም አለመሆን - ጥያቄው ይኸው ነው፡፡›› ግና፤ ያገርንም ሆነ የሰውን ገና ያልተደረሰበትን ሦስተኛ ስም በምን ለመገመት፣ ለማወቅ፣ ለመለየት፣ ለማረጋገጥ ይችሏል?!
እነሆ፤ ከስም የጠባይ፣ ግብር እና ሁኔታ መገለጫ አንዱ ምላሽ... ‹‹በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ!››

Read 1186 times