Sunday, 22 April 2018 00:00

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ - በምሁር ዕይታ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የ150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ካቀረቡ ምሁራን አንዱ ሲሆኑ “ዘመን የማያደበዝዘው የቴዎድሮስ አሻራ” የሚል ርዕስ የሰጡት የጥናት ጽሁፋቸው አድናቆት ተችሮታል፡፡ ለመሆኑ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ምን ዓይነት መሪ ነበሩ? ራዕያቸውን እንዳያሳኩ ተግዳሮት የሆነባቸው ምንድን ነው? ለምን እንግሊዝን ማሸነፍ ተሳናቸው? ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገስታት በምን ይለያሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን አነጋግራቸዋለች፡፡


    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተነሳሽነቱን ወስዶ የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓልን አዘጋጅቷል። ዝክረ በዓሉን  እንዴት አገኙት?
ባቀረብኩት ጽሁፍ መግቢያም ላይ ጠቅሼዋለሁ። ዝግጅቱን በከፍተኛ አድናቆት ነው ያየሁት፡፡ አንደኛ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ፣ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ ሰፊ ፕሮግራም በማዘጋጀታቸው፣ ሁለተኛም ይህ ዝግጅት ከጉባኤነት ባለፈ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከሰዉ በኋላ የተዘረፉ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ኃይል ከመፍጠር ጋር የተዛመደ በመሆኑ፣ ሌላው ወቅታዊ ከሆነው የአንድነት ጥያቄ አንፃር ስለ አገር አንድነት ከ150 ዓመት በፊት መስዋዕት የሆኑ ባለታሪክን ለማሰብና ለመዘከር በመነሳታቸው  ምስጋና ይገባቸዋል - አዘጋጆቹ፡፡ እኔም እንደ ታሪክ ምሁር፣ በዝግጅቱ  ደስተኛ ነኝ፡፡
በዚህች አገር ላይ የተለያዩ ነገስታት ተፈራርቀዋል። ነገር ግን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከሞቱ ከ150 ዓመታት በኋላም በድምቀት እየታወሱ  ነው፡፡ በንጉሱ ታሪክ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎችም ሆኑ የፈጠራ ሥራዎች አሁንም እየተሰሩ ነው፡፡ ይሄ የአፄው መንፈስ ከሌሎቹ ነገስታት የበለጠ እስካሁን የዘለቀበት ምክንያት ምንድን ነው?
ምን መሰለሽ---ዝም ብለሽ አፄ ቴዎድሮስን እንደ ገፀ ባህሪ ያየሽው እንደሆነ የሚስብ ነው። ከምንም ተነስቶ ነው አገር እስከ መምራት የደረሰው፡፡ እሱም “ከትቢያ አንስቶኝ” ነው የሚለው፡፡ በንግግሮቹና ለተለያዩ ጉዳዮች በሚፅፋቸው ደብዳቤዎች መጨረሻ ላይ በተደጋጋሚ  “በእግዚአብሔር ኃይል” ይላል። በእንግሊዝኛው “A man of Destiny” ወይም ለአንድ ትልቅ ነገር የታጨ ሰው መሆኑ ይሰማው ነበር። በዚያ ሁኔታና ራዕይ ይንቀሳቀስ የነበረ ሰው ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ የተነሳባቸውን አላማዎች ስትመለከቺ፣ ቋሚ የሆኑ አላማዎች ስለሆኑ ከሌላው የበለጠ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ የተዋጣላቸው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒሊክ ናቸው፡፡ ምንጊዜም ይወደሳሉ ይሞገሳሉ፡፡
በሌላ በኩል አፄ ቴዎድሮስ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ አነሳሱም አወዳደቁም እንዳይረሳ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ አንበሳ፤ የማታ ማታ ሁሉ ነገር ከሽፎበት ብቻውን ከዚያ ምድረ በዳ ላይ (አፄ ቴዎድሮስ ራሱ ምድረ በዳ ነው የሚለው መቅደላን) መሽጎ፣ በመጨረሻ ራሱን መሰዋቱ ህይወቱን በድራማ የታጀበ ያደርገዋል፡፡ እንዳልኩሽ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግና የማዘመን ዓላማው ደግሞ ቋሚና ዘላቂ ናቸው፡፡ እስካሁንም ሁለቱም አላማዎች አግባብነት አላቸው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአገሪቷ የእድገት ማገር ነው እንላለን፤ አይደለም? በመሳሪያ መልክ ቢሆንም የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት እሱ ያወቀው ያን ጊዜ ነው፡፡ በመሳሪያ መልክ ያወቀውም በወቅቱ መሳሪያው አንገብጋቢና አስፈላጊ ስለነበረ ነው፡፡ እነዚህ የአገር አንድነትና አገርን የማዘመን ርዕዮቹ እስከዚህ ዘመን ቋሚ የሆኑ፣ ወደፊትም የሚቀጥሉ በመሆናቸው መንፈሱም ምግባሩም ሊረሳ አልቻለም፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በስፋት በመፃፍ ንጉሱ ይበልጥ ጎልተው እንዲታወቁ አስተዋጽኦ ከአደረጉ  ምሁራን አንዱ መሆንዎ ይነገራል---?
እኔ ግን አላምንበትም፡፡ ምክንያቱም ከኔ በላይ ስለ አፄ ቴዎድሮስ በእጅጉ ብዙ የፃፉ አሉ፡፡ እኔ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በምፅፍበት ጊዜ የተወሰነ ምዕራፍ ለቴዎድሮስ መስጠት ነበረብኝ፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እንግዲህ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሬ እስከ አብዮቱ … እንዲያውም ሁለተኛው መፅሐፌ እትም እስከ ኢህአዴግ ድረስ ነው የተሰራው፡፡ እናም የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ የተወሰነ ክፍል ነው ያለው፡፡ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ስምና ታሪክ በደንብ እንዲታወቅና እንዲወጣ ያደረገው የታሪክ መምህራችን ፕሮፌሰር ስቬን ሩቤንሰን ነው፡፡ እንዲያውም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የቴዎድሮስ ስም ብዙ ገንኖ እንዳይወጣ ይፈለግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሰሎሞኒክ ዳይናስቲ የማይወለዱ ናቸው የሚባል ነገር ስላለ፣ ስማቸው እንዲገንን አይፈለግም ነበር፡፡
ያንን ሁሉ ተቋቁሞ ነው እንግዲህ ፕሮፌሰር ሩቤንሰን፣ ስለ ቴዎድሮስ ማስተማርና መቶ ገፅ የምታክል ትንሽ የመጀመሪያ መፅሐፍ ያዘጋጀው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ዳጎስ ያለውንና “The Survival of Ethiopian Independence” የተሰኘውን በቴዎድሮስ ዘመን ዙሪያ የሚያጠነጥን ዲፕሎማሲያዊ ታሪክን ፅፏል፡፡ በሶስተኛ ደረጃም (ባቀረብኩት ፅሑፍ ላይ የጠቀስኳቸውን) ቴዎድሮስ ለተለያዩ ጉዳዮች የፃፋቸውን ደብዳቤዎች አሳትሞ ያወጣውም ይሄው አንጋፋ መምህራችን ነው። ከአምስት ነው ከስድስት ዓመት በፊት ነው ያረፈው። አንጋፋ የሚባሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁራንን ያስተማረ ትልቅ መምህር ነው። እናም አፄ ቴዎድሮስን በማሳወቅ ረገድ ምስጋና የሚገባው ሰው ቢኖር፣ ፕሮፌሰር ሩቤንሰን እንጂ እኔ አይደለሁም፤ የኔ በመጠኑ ነው። የሩቤንሰንንም የሌሎችንም ጨምቄ፣ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የቴዎድሮስ ሚና ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ነው የሞከርኩት፡፡
በዝክረ በዓሉ ላይ የተለያዩ ምሁራን ጥናታዊ ፅሑፎችን አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው “የጀግኖች ሽሚያ” በሚል ርዕስ፣ ሌሎች ደግሞ ለአፄ ቴዎድሮስ በተገጠሙ ግጥሞች ላይ  ፅሁፎች አቅርበዋል፡፡ የቀረቡትን ፅሑፎች እርስዎ እንዴት አገኟቸው?
እንደነዚህ አይነት ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ፅሑፎች እንግዲህ ፍፁም አይደሉም፡፡ ግን ለውይይት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ በውይይት ዳብረው የተሻለ ጥሩ መልክ ይይዛሉ፡፡ ጉባኤ ላይ የሚቀርብ ፅሁፍ ዘላለማዊና ፍፁም ነው፤የመጨረሻውን ፍርድ ይሰጣል ብለን አናስብም፤ አቅራቢውም ታዳሚውም አያስብም፡፡ ፅሁፉ ከቀረበ በኋላ አንዳንዱ “አይ ይሄ ገና ብዙ ይቀረዋል” ይባላል። ሌላው “በጣም የተዋጣለት ነው፤ ነገር ግን እዚህ ቦታ ላይ ማስተካከያ ይደረግበት” ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዋ ዶ/ር ፍሬህይወት ያቀረበችው የተሟላ ነው፤ ግን የሚጎድሉት ነገሮች አሉት፤ ይሄ ይጨመር” ተብሎ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የመማሪያ መድረክም ጭምር ነው ማለት ይቻላል?
ትክክል! መማሪያም ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት ጉባኤ የማያውቀው ይማራል፡፡ አውቃለሁ ብሎ ያቀረበውም ከሚሰጡት ገንቢ አስተያየቶች ተምሮ የተሻለ ፅሁፍ ይፅፋል፡፡ ለምሳሌ ፅሁፎች ለህትመት ሲቀርቡ ፀሐፊዎቹ ተመልሰው እንዲያስተካክሉ የሚደረጉበት ሁኔታ አለ። እንዲህ አይነት ጉባኤ ላይ የመሳተፍ ልምድ የሌለው ሰው፣ የሚያቀርበው ፅሁፍ ፍፁም ሊመስለው ይችላል ግን አይደለም፡፡ እኔ ለምሳሌ ያቀረብኩትን ፅሁፍ መልሼ እመረምራለሁ፤ ህዝብ ከተናገረውም ካልተናገረውም የሚሰሙኝ ነገሮች አሉ፡፡ አይ ይህቺ ብትስተካከል እላለሁ፡፡ የጉባኤ ባህል እንግዲህ ይህን ይመስላል፡፡
እርስዎ ባቀረቡት ፅሁፍ ላይ ቴዎድሮስ ትልቅ ራዕይ ቢያነግብም ራዕይና ህልሙን እውን ለማድረግ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ይጎድለዋል ብለዋል፡፡ እስኪ ይህን ያሉበትን ምክንያት ያብራሩልኝ?
እንግዲህ ቴዎድሮስ ያነሳው አላማ ከባድ ነው፡፡ የዓላማውን ከባድነት መረዳት ነበረበት ነው የምለው። ከባድነቱን እሱ ተረድቶ አንዳንድ ሰዎች ካልተረዱም ለማስረዳት የሚችልበትን ስልት መፈለግ ነበረበት እንጂ አንተ ካልተረዳህ፣ ያሰብኩትን የማትቀበል ከሆነ … እያለ መግደልና ማስወገድ አልነበረበትም ለማለት ነው።
አሁን የጠቀሱት ዓይነት ችግር እስከ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡ ከዚህ አንፃር የችግሩ መሰረት የቴዎድሮስ ዘመን ነው ማለት ይቻላል?
እርግጥ ነው እኛ ከቴዎድሮስ ዘመን ምንድነው የምንማረው የሚለው ነገር አለ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ሽብሩ ከአፄ ቴዎድሮስ የጀመረ ባለመሆኑ መሰረት ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ የዘርዓ ያዕቆብን፣ የሱስኒዮስን እንዲሁም በቅርቡ የቀይ ሽብርን ክስተት ስትመለከቺ፤ ይሄ ሁሉ የሚመነጨው “እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው” ከሚል ነው፡፡ አልቀበልም የሚልን አካል ከማስረዳትና ከማሳመን ይልቅ ማስወገድ ነው እርምጃው፤ ይሄ ደግሞ መቅረት አለበት፡፡ ችግሩ ከነገርኩሽ ነገስታት ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ የመጣ የኢትዮጵያ ቋሚ በሽታ ነው፡፡ ለትልቅ ኪሳራ እየዳረገን ያለ ትልቁ ህመማችን ነው፡፡
አንድ ሰው ሀሳቡን ለሌላው ለማስረዳትና ለማሳመን ሆደ ሰፊ፣ ታጋሽና ብልሃተኛ መሆን አለበት፡፡ ያ ሰው የሌላውን ሃሳብ ካልተቀበለም በቃ አልተቀበለም፡፡ አለቀ፡፡ መሳሪያ ይዞ የሚነሳበትንም ሰው ቢሆን ከማስወገድ ይልቅ በሌላ መንገድ ማሸነፍ አለበት፡፡ ቴዎድሮስ ዓላማውን ለማሳካት ማሸነፍ ነበረበት፡፡ ካሸነፈ በኋላ ግን የሚቃወሙትን ማስወገድም ሆነ እጅና እግር መቁረጥ አልነበረበትም። ዝክረ በዓል በሆነበት በዚህ መድረክ፣ የፖለቲካ ሽብር ማውራት ባያስፈልግም፣ ችግሩ በዘላቂነት የቀጠለ በመሆኑ መቅረት አለበት ብያለሁ - በፅሁፌ፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለበት፡፡ የኔን ሀሳብ አልተቀበልክም ብሎ በሀይልና በጭካኔ፣ የሰውን ህይወት መቅሰፍ መቅረት ይገባዋል፡፡  
ቴዎድሮስ እንግሊዞችን የማሸነፍ ዕድል ነበራቸው ብለው ያስባሉ? ወይስ ከእነ አካቴው እንግሊዞችን መግጠም አልነበረባቸውም?
እርግጥ ነው ጦርነቱን መግጠም ነበረበት፡፡ መጨረሻ ላይ አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ መግጠም ይኖርበታል፡፡ እንግሊዞች እዚያ ድረስ ከመጡ በኋላ ግን በምንም መልኩ ተሸንፈው ሊሄዱ አይችሉም ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ቀድሞ የነበረው የሰራዊት ብዛትና ተቀባይነት ቢኖረው ኖሮ ሊቋቋማቸው ይችል ነበር፡፡ ያለ አንዳች ችግርና እንቅፋት ሰተት ብለው ነው መቅደላ ድረስ የገቡት፡፡ የቴዎድሮስ ሰራዊት በጣም ጥቂት ስለነበረ ከእንግሊዝ ሰራዊት ቆስለው የሞቱት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ከእኛ ወገን ብዙ የቴዎድሮስ ወታደሮች አልቀዋል፡፡ ስለሆነም የማሸነፍ እድሉ ጠባብ ነበር፡፡
ቴዎድሮስ ራሳቸውን ባይገድሉ ኖሮስ ---?
አሁን ወሳኙ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ ራሱን ባያጠፋ ኖሮ ምን ይሆን ነበር? እንግሊዞች ይዘውት ይሄዳሉ፡፡ ለንደን አደባባይ እየጎተቱ፣ “ከአፍሪካ የመጣ እምቢተኛ፣ ነጮችን ለማገት የሚደፍር ቀበጥ ተመልከቱ፣ እግራችን ስር ወደቀ” እያሉ ይዘባበቱበት ነበር፡፡ ይሄ ለእርሱም ለኢትዮጵያም ትልቅ ውርደት ነው፡፡ ራሱን በመግደሉ ትልቅ ኪሳራ ነው ያደረሰባቸው፡፡
ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው፡፡ …
--የሚለው ግጥም የተገጠመው በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል …?
አዎ! ይሄው ነው እውነታው፡፡ ስቆባቸው ነው የሞተው፡፡ የምፀት ሳቅ ስቆ እንደተሰዋ ታሪክ ይናገራል። ለነገሩማ ቴዎድሮስን ቴዎድሮስ ያደረገውኮ ስንብቱ ነው፡፡ ለምንድን ነው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያንን የመሰለ “የቴዎድሮስ ስንብት” የተሰኘ ተውኔት የጻፈው፡፡ መቼም ለፀጋዬ ገ/መድህን እግዚአብሔር ይስጠው፤ ችሎታ ስላለው ስንብቱን በደንብ ሰርቶታል። አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ደግሞ በደንብ አድርጎ ተጫውቶታል፡፡ የቴዎድሮስ ትልቁ ታሪክ መጨረሻ ላይ የወሰደው እርምጃ ነው፡፡
በተወለዱበት ቋራ ደለጎ ከተማ እሳቸውን የሚገልፅ ምልክት የለም፡፡ ለሀውልት ግንባታ የተቀመጠው የመሰረት ድንጋይ 10 ዓመት አልፎታል፡፡ መቃብራቸው ያለበት መቅደላ አምባ ላይ እንዲሁ 10 ዓመት ያለፈው የመሰረት ድንጋይ በስተቀር አፄውን በጉልህ የሚያሳይ ነገር የለም፡፡ መንገድም ቢሆን በዚያው መጠን የለም፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ከቋራ እስከ መቅደላ ሄጃለሁ ብለሻል፡፡ ለመሆኑ መቅደላ በየት በኩል ሄዳችሁ?
ከደብረ ታቦር ወልዲያ፣ ከወልዲያ ደሴ፣ ከደሴ በኩታበር በበሻሌ ወንድ አድርገን ነው መቅደላ አምባ የደረስነው፡፡
ተመልከቺ፤ አፄ ቴዎድሮስ ከ150 ዓመታት በፊት ያንን የሚያክል መድፍ እየጎተተ የሄደው፣ ከደብረ ታቦር መቅደላ ቀጥታ በጠረገው መንገድ ነው፡፡ ያ መንገድ አሁን ዱካው ይኑር አይኑር አላውቅም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰራ መንገድ የለም፡፡ መንገድ መስራት አገራችን ላይ እንደ ልብ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ሰው መቅደላን ለመጎብኘት ዙሪያ ጥምጥም መሄድ ነበረበት? ይሄ በጣም የሚያሳፍር ጉዳይ ነው። በጣምም ያሳዝናል፡፡ እንዴት ይህን የሚያህል ታሪክ ይዘን፣መንገድ ሰርተን ማስጎብኘት ዳገት ይሆንብናል፡፡ በዚህ ረገድ ይሄን ዝክረ በዓል ያዘጋጁ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ ሚዲያው መረባረብና ተፅዕኖ መፍጠር አለባቸው። ይሄ ጉዳይ አጠቃላይ የአገራችን ችግር ነው፡፡ እኔ አሁን በቅርቡ በአድዋ ጉዳይ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አካል ሆኛለሁ፡፡ እንቅስቃሴው ሙዚየም ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡
አድዋን የሚያክል ግዙፍ ገድል፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ የሆነ አኩሪ ታሪክ ይዘን፣ ገድሉ የተፈፀመበት ቦታ ላይ ግን ምንም አይነት መታሰቢያም ሆነ ሙዚየም የለም፡፡ የውጊያ አውዶቹም ለጉብኝት እንዳይበቁ የተሰራ ጥርጊያ መንገድ የለም። ይሄ ቋሚና አጠቃላይ ችግራችን በመሆኑ ጠንካራ ርብርብ ይጠይቃል፡፡
ከምኒልክ ህይወትና ታሪክ ጋር የተቆራኙት አንኮበር፣ አንጎለላና ሌሎችም ቦታዎች ቅርስ ናቸው። ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ አሻራ ትተው ያለፉ መሪዎች ህይወታቸው ያለፈበትን ታሪክ የሰሩበትን ቦታ አሳምረንና አስተካክለን ለሚመጣ ጎብኚ፤ “እዚህ ቦታ ነው የነገሰው፣ በዚህ አካባቢ ነው የተዋጋው” ለማለት የማንችልበት ደረጃ ላይ መሆናችን ያሳዝናል ያሳፍራልም፡፡ ይሄን ለመለወጥ በትብብር መስራት ይኖርብናል፡፡  
ሌላው አስቸጋሪ እየሆነ የመጣው  የታሪክ ሽሚያና ቅርምት ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሳቸውን ሰውተው የተቀበሩበት ነው የተባለው ቦታ፣ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦበት ይጎበኛል፡፡ በሌላ በኩል መቅደላ አምባ ላይ ከተቀበሩ ከ7 ዓመት በኋላ ቀድሞ በተማሩበት መተማ በሚገኝ ማህበረ ሥላሴ ገዳም፣ አፅማቸው ተወስዶ መቀበሩ ይነገራል፡፡ የአፄው ዘመዶችም አብዛኞቹ ይህንን ያምናሉ፡፡  እውነቱን ለማረጋገጥ  ምን ቢደረግ ይሻላል ይላሉ?
ይሄ ከፍተኛ ምርምር ይጠይቃል፡፡ ጊዜው በሄደ ቁጥር የቃል ምስክር ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን የፅሑፍ መረጃዎችን የበለጠ መመርመርና ማመሳከር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ከባድ ነገር ነው፤ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
አሁን እናንተ የታሪክ ምሁራን፣ የቴዎድሮስ መቃብር የት ነው ብላችሁ ነው የምታምኑት?
በእውነቱ እኔ እዚህ ላይ መልስ ልሰጥሽ አልችልም፤ አላውቀውም፡፡ ነገር ግን አንድ አወዛጋቢ ነገር ሲነሳ መፍትሄው ጥልቅ ምርምር ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ያሉትን የምርምር መሳሪያዎች ተጠቅሞ፣ ጊዜ ወስዶ በመመርመር፣ እውነታው ላይ መድረስ ነው ብቸኛው መፍትሄ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከሰዉ በኋላ በእንግሊዞች የተዘረፉ ወደ 2 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ ቅርሶቻችን በቪክቶሪያ አልበርት ሙዚየምና በየቦታው በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል የእንግሊዝ መንግሥት በረጅም ጊዜ ውሰት ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቢያቅድም የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤”የራሴን ቅርስ በውሰት አልወስድም” በሚል ውድቅ አድርጎታል፡፡ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ ያሉት ሌሎች አማራጮች ምንድን ናቸው? “የረጅም ጊዜ ውሰት” የሚለውስ  ምን ማለት ነው?
ቅርሶቹ የራሳችን ናቸው፤ እነሱ ይሄን “የረጅም ጊዜ ውሰት” የሚለውን ያመጡበት ምክንያት ምንድን ነው፣ ከጀርባው ምን የታሰበ ነገር አለ የሚለውን ነገር መመርመር ያስፈልግ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው እነሱ ቅርሶቹን ሊመልሱ አይችሉም። ሁሉንም ቅርሶቻችንን ከመለሱ ሙዚየማቸው ይፈርሳል፡፡ መቶ በመቶ ባዶ ነዋ የሚሆነው። ይሄ የረጅም ጊዜ ውሰት የሚሉት የማምለጫ ስልታቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ቅርሶቹን ለማስመለስ ያለው አማራጭ፤ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመፍትሄዎቹ ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ምክክር ማድረግ ነው፡፡ ያለ ምክክር የሚመጣ መፍትሄ የለም ባይ ነኝ፡፡

Read 4639 times