Saturday, 07 April 2018 00:00

የቅኔና የፍልስፍና ፉክክር (፬)፡- ሊቁ አርስቶትል

Written by  በካሣሁን ዓለሙ (የ‹ቅኔ ዘፍልሱፍ› መጽሐፍ ደራሲ)
Rate this item
(2 votes)


    “--አርስቶትል ቅኔን ከታሪክ የተሻለ ፍልስፍናዊ ጥበብ በማለት ትምህርትን ሲከፋፍልም የተግባራዊ ሳይንስ ጥበብ አድርጎታል፡፡ የእሱ ዋናው ግቡም መልካምነትን ማስፈን ስለኾነ፣ ሕሊናዊ ተግባር መልካም ሕይወትን ያስመርጣል፤ ይህም የተሻለ ኑሮን ለመኖር ያስችላል፤ ቅኔም ደግነትን የሚያስገኝ መኾን አለበት ብሎ ተከራክሯል፡፡--”
      በካሣሁን ዓለሙ (የ‹ቅኔ ዘፍልሱፍ› መጽሐፍ ደራሲ)

   ባለፈው ጽሁፌ ከግሪክ ፈላስፎች መካከል የሶቅራጥስና የፕሌቶን የቅኔ ዕይታ ተመልክተናል፤ በዛሬ መጣጥፌ ከአርስቶትል እስከ አውጉስጢን ያለውን የቅኔ ዕይታ ለማቅረብ ቃል ብገባም ሊቁ አርስቶትል ነገር አስረዝሞ አለቀኝ ስላለ፣ የእሱን ዕይታ ብቻ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡፡፡
ከፕሌቶ ያላነሰ በአውሮጳ አስተምህሮ ተፅዕኖ ፈጣሪ የኾነው ተማሪው አርስቶትል፤ በቅኔና በፍልስፍና አታካራ ላይ ያለው ተፅእኖ በመምህሩ ቦይ ውስጥ የሚፈስ ቢኾንም ለቅኔ በሰጠው ደረጃ፣ ዋጋ እና መነሻ ይለያል፡፡ ቅኔን የሚመዝነው በሚሠጠው ጥቅምና ባለው ዋጋ ሲኾን እንደ ፍልስፍና የሚመሠረተው በመደነቅ ላይ መኾኑን ይስማማል፤ ደረጃ ሲሰጥም ቅኔን የታሪክ ታላቅ ወንድም፣ የፍልስፍና ተከታይ ያደርገዋል፡፡
አርስቶትል ቅኔና ፍልስፍና በመደነቅ ላይ እንደሚመሠረት በመግለጽ፣ ከፕሌቶ ብዙም የራቀ አይደለም፤ ልዩነታቸው የሚፈጠረው ኹለቱ ጥበባት ካላቸው ደራጃና ከተረት ጋር ካላቸው ግንኙት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የቅኔን ደረጃ ሲያስቀምጥም፤ የሥነ መለኮት ቅኔን (Theological Poetry) ከምሥጢረ ፍጥረት (Metaphysics) አያይዞ እንደ መነሻ ይወስደዋል፤ ባለቅኔ በምሥጢረ ፍጥረት ዕሳቤ በሥነ-መለኮት ቅኔ መጀመሩ ብቻ ሳይኾን ፈላስፋም ቢኾን እስከተወሰነ ደረጃ ተረትን እንደሚወድና እንደሚተርት ይሞግታል፤ ተረት ተጠየቃዊ (አመክንዮአዊ) አስተሳሰብ የሚፈጥር ባይኾንም መገረምን ግን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ በሥነ መለኮት ቅኔ የማይንቀሳቀስ አንቀሳቃሽን አንሥቶ፣ ይህ አንቀሳቃሽ ወይ በራሱ እየተንቀሳቀሰ ያንቀሳቅሳል፤ ወይም ምንም የማይንቀሳቀስ ኃይል ኾኖ እየኖረ ያንቀሳቅሳል፤ መኖሪያውንም ወይ በዓለም ክፍል ውስጥ ኾኖ ወይም ከዓለሙ ውጪ በመኾን ያንቀሳቅሳል፤ የአርስቶትል መልስ ከዓለሙ ውጭ የሚያደርግ ነው የሚል ነው፡፡ ይህም አትላስ መሬትን ተሸክሞና በእጆቹ እንደ ምሰሶ ደግፎ ይኖራል ከሚለው ተረት ጋር ይመሳሰላል፤ ዕንቆቅልሻዊ ተፈጥሮም አለው፤ ዕንቆቅልሹም ድንቀትን ይፈጥራል፡፡
በዚህ መልክ ተረት የድንቀቶች ጥርቅም ስለኾነም የተረት አፍቃሪ የኾነ ሰው፤ የጥበብ አፍቃሪነት ስሜት ይኖረዋል፤ መደነቅ ደግሞ ሰዎችን እንዲፈላሰፉ የሚቀሰቅስ ኃይል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ባለቅኔውና ፈላስፋው መደነቅን ይጋሩታል፤ ስለኾነም ቅኔና ፍልስፍና ከተረት ጋር ተዋሕደው ይገኛሉ ብሎ ይከራከራል፡፡ የፈላስፋም ተግባር በቀድሞው ባለቅኔዎች የተደበላለቁትን ሐሳቦች እንደ ቢላ በተሳለ ጥያቄ መሞረድ፣ በጥልቀት በሚመረምር አስተውሎትና የወደፊቱን ጭምር በሚገምት በአብሰልስሎሽ ማጥራት ነው ይለናል፡፡
ሕሊናዊ ግንዛቤና ጥበብ ቢገናዘቡም አንድ ዓይነት አለመኾናቸውን ይገልጻል፡፡ የጥበብን መሠረት ሲገልጽም የማይለወጥ፣ አስደናቂና መለኮታዊ እያለ በመጥቀስ የምሥጢረ ፍጥረት ጥናት (Metaphysics) መኾኑን ሞግቷል፤ ኾኖም ‹ይህ ከግንዛቤ ጋር ሲያያዝ ለሰዎች ምን ይፈይዳል?› ብሎ ሲጠይቅ፤ ምሥጢረ-ፍጥረት የሰው ልጅን መልካምነት (ደግነትን) የማይቀርጽ ስለኾነ ፋይዳው ዝቅተኛ ነው ይላል፡፡ ‹ይህ ማለት ግን› እንዲል ካድሬ፣ የምሥጢረ ፍጥረት ጥናትን አጣጥሏል ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ‹የላቀ ክብር ያለው ሳይንስ›፣ መለኮታዊ መገለጫ የኾኑትን የመጀመሪያ መንሥኤንና ቀዳሚያን መርሆዎች የሚያጠና ጥበብ መኾኑን ይከራከራል፡፡ ከተግባራዊ ሳይንስ ጋር ሲያይዘው ነው ፋይዳው ያልታየው፤ ፅንሰ ሐሳባዊ ሳይንስ ያለው ውስጥ የሚካተት ነውና፡፡ እንዲሁም ምሥጢረ ፍጥረት ዕንቆቅልሻዊነትንና አእምሯችን ምክንያቱን አቅርቦ ሊያጠይቃቸው የሚችሉ ፅንሳተ ሐሳባትን የሚያጠና ስለኾነ እና ተረታዊ አስተሳሰቦችን ስለሚያካትት የተግባራዊነት ጥቅሙ ዝቅተኛ ነው፡- ምሥጢረ ፍጥረት።
ሊቁ አርስቶትል የዕውቀትን ክፍሎች በየፈርጅ ከፋፍሎ በመበየን የመጀመሪያ ፈላስፋ (ሳይንቲስትም) ነው፤ እንደ ግዕዝ የሰዋሰው (የእርባ ቅምር) ሥርዓት፣ ዕውቀትን በአለቃና በምንዝር (በሠራዊት) እየመደበ አሰልፎታል (ቦታ ቦታውን አስይዟል)፤ የእነ ፕሌቶ እና የእነ ሶቅራጥስን የእሰጥ አገባ ሙግት ገሸሽ አድርጎም ትኩረቱንና ልፋቱን አከፋፍሎ በሰደሩ ላይ አድርጓል፤ በዚህም ሳይንሳዊ የትምህርት አከፋፋይ ተብሏል፡፡
ይህን ሲያደርግም አበው አዕማዳተ ሰዋሰውን አድራጊ እና ተደራጊ ብለው ለኹለት እንደሚመድቡት፤ እሱም ጽንሰ-ሐሳባዊ ሳይንስ እና ተግባራዊ ሳይንስ በሚል ለኹለት ከፍሎታል፤ በዚህ ክፍፍል ስልቱ ቅኔን ለፍልስፍና ከሰጠውና ከነበረበት ደረጃ አወርዶ በተግባራዊ ሳይንስ (Practical Science) ውስጥ መድቦታል፡፡ ይህንን ያደረገው ግን ቅኔን ካለው ፋይዳ እና ከሰው ልጅ ሰብዕና ጋር በማያይዝ ነው፤ የቅኔ ዓይነቶችንም ኢፒክ፣ ትራጀዲ፣ ኮሚክና ዲቲራምቢክ በሚሉ ዘርፎች ለያይቶ አስቀምጧቸዋል፤ ከእነዚያም ውስጥ ለትራጀዲያዊ ቅኔ ልዩ ሥፍራ ሰጥቶታል፡፡
ዕውቀትን በደረጃ ሲከፋፍልም ፍልስፍናን የዕውቀቶች ሊቀመንበር አድርጎ አቅርቧታል፣ ከዚያም ቅኔን ሻል ያለ ደረጃ በመስጠት፣ታሪክና ሥነ-ተረት ደግሞ ያስከትላቸዋል (ይህንን poetics በሚለው መጽሐፉ በምዕራፍ 1፣ 9፣ ከ23-25 ላይ አብራርቶ ጽፎታል)፡፡ ቅኔን በዚህ ደረጃ ለማስቀመጥ የተጠቀመው መስፈርትም ጥቅል ሐሳብን መያዝ ከመቻላቸው አንጻር ነው፤ በእርግጥ በቅኔ ውስጥ ጥቅል ሐሳቦች ይካተታሉ፤ ፍልስፍና ግን ከቅኔ ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ረቂቅና ጥቅል ሐሳቦችን የመግለፅ ችሎታ አለው፤ ታሪክ ግን የሚገለጸው በዝርዝር ነገሮች ነው፡፡ ስለዚህ ከሌሎች የዕውቀት ክፍሎች አንጻር ለቅኔ ደረጃ ሲሰጥ ከታሪክ ትረካ የተሻለ ፍልስፍና አለበት (ባዘኔታ ይመስላል¡)፡፡
ይህንን ቨረኔ የተባለው ጸሐፊ Man and Culture በሚለው መጽሐፉ በገጽ 11 እና 12፡-
‹ምንም እንኳ አርስቶትል ቅኔን ከመዋቅር ልምድ መንገዶቹ አንድ ብቸኛው ስልት አድርጎ ቢያስበውም ስልቱ ተግዳሮት ነበረበት፤ የቅኔ ዓይነቶችንና አስተያየቶችን በቅኔ ገለጻ በአመክንዮአዊነት ከፋፍሏልም፤ ቅኔ ከታሪክ የበለጠ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ መሆኑን በመሞገትም፣ በቅኔና በታሪክ መካከል ልዩነት እንዳለ አሳይቷል› ብሎ አስቀምጦታል፡፡
አርስቶትል ባለቅኔዎች አማልክትን ቀናተኛ፣ ስግብግብ፣… እያደረጉ መግለጻቸውን ይነቅፋል፤ በዚህም ‹ባለቅኔዎች ብዙ ውሸት ያወራሉ› ይሏችኋል በሚል ያሸማቅቃቸዋል፤ ባለቅኔዎቹን በዚህ መልክ ቢወርፋቸውም ቅኔን ፕሌቶ ‹አደገኛ ሥጋት!› ብሎ በመሳሉ ግን አይስማማም፤ ይልቁንም የኢፒክ እና የትራጄዲ ታላላቅ ቅኔዎችን እንዲቀኙ ያበረታታቸዋል፤ በተለይም የተሻለ ትራጄዲን ለተቀኘ ባለቅኔ ልዩ ክብር አለው፤ የደግነት ድርጊቶችንና መልካም ኑሮን በመቅዳት ማቅረብ ይችላል በማለት ጥብቅና ይቆምለታል፡፡
ፕሌቶ ቅኔን በቅጅ ቅጅ አደገኛነት ከሶ ነበር፤ ለዚህም ቅኔ ፩) በቀጥታ እውን ነገርን አለመወከሉን፣ ፪) የሚጠቀምባቸው ቃላት እውነትን የመግለጽ ብቃት ወይም ዋስትና የሌላቸው መኾኑን፣ £) ሕሊናን መሠረታዊ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንዲመራመር አለማድረጉን፣ ፬) በውበት፣ በዜማ፣ በለዛ፣… ውስጥ ወሽቆ በአርት እንድንታለል የሚያደርገን መኾኑን በመከራከሪያነት አቅርቦ ነበር፡- ሊቁ ፕሌቶ፡፡
ለአርስቶትል ግን እውነተኛ ማስመሰል የቅኔ ሐሳብ መሠረት ነው፤ አስመስሎ በመቅዳትም የተሟላና እውነተኛ ሰብዕናን ማግኘት ያስችላል ብሎ ይሟገታል። ስለዚህ የቅኔ ምንጭ የሚፈልቀውም ከሰዎች ሰብዕና ውስጥ ነው፤ ቅኔን ማየትና መረዳት ያለብንም ለሕዝቦች በሚሰጠው የተሻለ ነገር እና በሚያስገኘው የደስታ ዕርካታ መኾን አለበት ይለናል፡፡ ከፕሌቶ በተቃራኒም ቅኔ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምረው መልካም ጠባያትን አስመስለው በመቅዳት አንዲያጎለምሱ መሠረት የሚጥል ጥበብ መኾኑን ይሞግታል (ፕሌቶ ተረትን ያበላሻቸዋል በሚል ልጆች በማይደርሱበት ሥፍራ ይቀመጥ ብሎ ነበር)፡፡ እንዲሁም መልካም የቅኔ ቅጅ ተፈጥሮን እንዳለች ለማወቅ ጠቃሚ መኾኑን ተከራክሯል፡፡  
አርስቶትል ከፕሌቶ የሚለየው አስመስሎ በመቅዳት ብቻ ሳይኾን በቅኔ እና በሥነምግባር ግንኙነት ላይ ባቀረበው መከራከሪያም ነው፡፡ ይህም ክርክሩም Nichomachean Ethics፣ Politics እና Poetics በሚሉ መጽሐፎቹ በሰፊው ተገልጸዋል፡፡ በዚህም ቅኔን በቅኔነቱ እንጂ በሥነምግባር ቀዳሚነቱ መመዘን የለበትም፤ ዕርካታንም አስገኝው ራሱ ነውና ይለናል፡፡ ‹በቅድሚያ ራስን ማወቅ› በሚለው በሶቅራጥስ ሐሳብም በመስማማት የሰው ልጅ ራሱን ለማወቅ የሚያስፈልገው ከከፍተኛው፣ ከረቂቁ፣ ከሰፊው እና ከጥልቁ ከመለኮት ወይም ከምሥጢር-ፍጥረት ጥናት መጀመር አይደለም ይልቁንም  ከራሱ ‹እኔ ማን ነኝ› እና ‹ምን ማድረግ ይገባኛል› በማለት እንጂ! በሚል የደግነት ሚዛንንና የዕርካታን ውጤት ይዞ ‹መደረግ ያለበትንና የሌለበትን› ወደ መበየን ያዘነብላል፡፡
በዚህ የሥነ ምግባር መስፈርትም የባለቅኔንና የፈላስፋን ግንኙነትና ድርሻ ይሞግታል፡፡ ለአርስጣጣሊስ ደግነት ስሜትን ከመግለፅና ውሳኔ ከመተግበር ጋር የተቆራኘ ነው፤ ከሰዎች ጠባያትና ሕይወት ጋር በመያያዙም ሰዎች ስሜታቸውን ሲገልፁ፤ በድርጊቱ መልካም ወይም መጥፎ ውጤትን ያስገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ደግነት ለራስ ነው፤ መጥፎነትም እንደዚሁ፤ ይህንን በትክክለኛ ግንዛቤ ስንተገብረው ውጤቱ መልካም ወይም መጥፎ ይኾናል፤ የበጎነት ተግባርም ከተግባራዊ ሳይንስ ጋር ይያያዛል፤ ቅኔም የተግባር ሳይንስ ስለኾነ የራሱን የደስታ ዕርካታ ያስገኛል፡፡
ለአርስቶትል የኹሉም መዳረሻ ደግነትን ማምጣት፣መልካምነትን ማስፈን ወይም አስደሳች ዕርካታን ማስገኘት ነው፡፡ አርስቶትል መርጠን የምንተገብረው ነገር በተወሰነ ደረጃም ቢኾን መልካምና አስደሳች መኾን አለበት የሚል መከራከሪያ አለው። በዚህም መደነቅ፣ ዕርካታና የስሜት ነፀብራቆችን በማያያዝ የዕርካታ ስሜት ማካተት ባለበት ግንዛቤ ላይ ከሶቅራጥስ አይስማማም፡፡ ‹ዕርካታ በሚሰማን ስሜት ነፀብራቆች የሚገኝ ግንዛቤ ነው› በማለት ከመደነቅ፣ ከመማር እና ከመጥፎ ነገሮች መንፃት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይሞግታል፡፡ ይህን ክርክሩንም ከትራጀዲያዊ ቅኔና ከንግግር ጥበብ ጋር አገናኝቶ ምርጫችን በሚያስደስተን ነገር ይገናኛል ይለናል፡፡
ከላይ በሳይንሳዊ የዕውቀት ክፍፍሉ እንዳየነው አርስቶትል ተግባራዊ ፈላስፋ ነው፤ ዓላማውም ሰዎች ትክክለኛ ግንዛቤ ይዘው ደጋግ ዜጎች እንዲኾኑ፣ ትክክለኛ ፍርድን መስጠት እንዲችሉ እና መልካም ነገርን እንዲሠሩ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ትኩረቱም ከፕሌቶ ይለያል፤ ‹መልካሞች ሳንኾን በዕውቀት ብንራቀቅ ትርጉም የለውም› የሚል ሙግት ማጠንጠኛው ነው። የኹሉም ነገር መዳረሻ ግቡ መልካም መኾን ስለኾነ በዓለም ላይ የሚገኝ ዕውቀት ኹሉ በዚህ ግብ መሠረት ይለካል፡፡ ስለዚህ የደግነት ተግባራት መልካም ውጤትን የሚያስገኙ ናቸው ይለናል፡፡    
አርስቶትል ባለቅኔዎች ትራጀዲን ሲጽፉ እና ገጸባሕርያቱን ከእኛ እየቀዱ፣ራሳችንን ሲያሳዩን የምናለቅሰው፣ የምንደሰተው ወይም የምናዝነው የፈጠሯቸው ገጸባሕርያት፤ ከእኛ ጋር ስለተዛመዱ ወይም ቤተሰባዊነትን መፍጠር ስለቻሉ እንደኾነ ይከራከራል። ግን መጥፎ ገጸባሕርያትን (ሌባ፣ ቀማኛ፣ ውሸታም፣ ዕድለቢስ፣ መናጢ፣…) መላመድና ከእነሱም ጠባያት ጋር መስማማት የለብንም፤ ከሰብዕና ተፈጥሯችን ጋር አብሮ አይሄድምና፡፡ ኑሮን መካከለኛ በኾነ ደረጃ እየኖርን፣ በየትኛውም መንገድና ደረጃ ደስታን ማግኘት አለብን ይለናል፡፡
‹ቅኔ እንዴትና በምን ማሳያ መገለጽ አለበት?› ለሚል ጥያቄም የሚሰጠው መልስ፤ ‹ቅኔን ለመግለፅ የሚጠቅም ትልቁ መሣሪያ ዘይቤያዊ አነጋገር› መኾኑን በመሞገት ነው፡፡ ‹ትልቁ ነገር ብቁ የዘይቤያዊ ግንዛቤ ነው፤ ይህ ግንዛቤ ከሌለ ሊማሩት የማይቻልና በተፈጥሮ የተቸረ የአስተውሎት ምልክት ነው፤ የማይመሳሰሉ ነገሮችን በማመሳሰል፣ የአስተውሎት ግንዛቤን ይገልጻልና› ይላል። ዘይቤያዊ አነጋገር ዐዲስ ሐሳብን ገልጾ ለማሳየትና የምናውቀውንም እንድንከልሰው በማድረግ ትልቅ አቅም ነው፤ ለፈላስፎችም በአመሳስሎሽ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። በዚህ ላይ ግን ችግር ብሎ የሚገልፀው የዘይቤያዊ ዕውቀት ግንዛቤ በተፈጥሮ የሚቸሩት እንጂ ሊማሩት ስለማይቻል ‹ካልተሰጠህ አልተሰጠህም› በማለቱ ተስፋ እንዳይቆርጡ ‹ተፈጥሮ ብትቆጣጠረንም በአርት እናሸንፋታለን› ይላል፤ እንዲሁም በዘይቤያዊና ፈሊጣዊ አገላለፆች ቃላትን ወስኖ ማስቀመጥ ስለማይቻል ለመከራከር አያስችልም ይለናል፡፡  
ይህ ብቻ ሳይኾን ቅኔን የሚገልጽበትን ቋንቋ ከሙዚቃ ጋርም ያመሳስለዋል፤ ምክንያቱም ሙዚቃ በትምህርትነት ይጠናል፤ አእምሮን ለማንቃት ይውላል፤ ያዝናናል፤ የደስታ ዕርካታን ይፈጥራል። በተመሳሳይ መልኩ የትራጀዲያዊ ቅኔም እንደ ሙዚቃ የአስተሳሰብ መድኃኒት ነው፤ ከሕክምናም ጋር ይዛመዳል፤ ደስታንም ያመጣል ይላል፡፡
አርስቶትል ባለቅኔ አልነበረም፤ ለባለቅኔዎች ግን ወዳጃቸው ነው፡፡ እንዲሁም ለእሱ ፍልስፍና እና ቅኔ በፀጋነት የሚገኙ ናቸው፡፡ በተለይ ቅኔ ለእሱ በፀጋ መሰጠትን ወይም ከዕብደት ጋር መነካካትን ይፈልጋል (‹የጥበብ ዛር› እንዲሉ)፡፡
በአጠቃላይ አርስቶትል ቅኔን ከታሪክ የተሻለ ፍልስፍናዊ ጥበብ በማለት ትምህርትን ሲከፋፍልም የተግባራዊ ሳይንስ ጥበብ አድርጎታል፡፡ የእሱ ዋናው ግቡም መልካምነትን ማስፈን ስለኾነ ሕሊናዊ ተግባር መልካም ሕይወትን ያስመርጣል፤ ይህም የተሻለ ኑሮን ለመኖር ያስችላል፤ ቅኔም ደግነትን የሚያስገኝ መኾን አለበት ብሎ ተከራክሯል፡፡

Read 3293 times