Saturday, 07 April 2018 00:00

የተራራው ላይ ዛፎች ምኞት!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ካልጠፋ ሁሉ ከምድር
እንዴት ይገዟል የገባር ፣
በሔዋንማ በናታችሁ
ግንደ በል ነበራችሁ፡፡ (ዘፍጥ 3፣6) (… ወዳጄ ልቤና ሌሎችም … ገጽ 36 … ዛፍ በልታችሁ እንደሞታችሁ … በዛፍ ደግሞ ዳናችሁ! … ሲሉ አስተማሩን!)
*   *   *
በተራራው አናት ያሉ 3 ዛፎች ገና እንደተተከሉ፣ በችግኝ ዘመናቸው ሲወያዩ…. ተስፋቸውንና ህልማቸውን ሲነጋገሩ ለሰማቸው በጣም ይገርሙ ነበር፡፡ ከበታቻቸው ባለው ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ካሉት ዘመዶቻቸው በተለየ መልኩ የተለየ ህልምና ምኞት ነበራቸው …  
*   *   *
የመጀመሪያ ዛፍ ችግኝ እንዲህ አለ … ‹‹.. እንግዲህ የሆነ ቀን አድጌ ስቆረጥ የከበሩ ዕቃዎች ማስቀመጫ እንዲሰሩብኝ እመኛለሁ፡፡ ዘናጭና ምርጥ በዓለም ካሉት ነገሮች ሁሉ የከበረ ነገር ማስቀመጫ ሳጥን መሆን ምኞቴ ነው፡፡ ይህ ካልተሳካልኝ ምኑን ኖርኩት … እኔ በተስማሚ ሁኔታ ለማደግ እሞክራለሁ … ቀሪውን ተካይና ተንከባካቢያችን ይጨነቅበት…››
ሁለተኛው ችግኝ እንዲህ አለ ‹‹…እኔ ግን ወደፊት የሆነ ግዜ ታላቅ መርከብ እንዲሰራብኝ እመኛለሁ፡፡ ምርጥና ውብ እንዲሁም ጠንካራ መርከብ ሆኜና ከንጉሶች ሁሉ ታላቅ የሆነውን ንጉስ ጭኜ በዓለም ዙሪያ መዞር … በእኔ ጥንካሬ ሰዎች ሁሉ እንዲተማመኑብኝና በእኔም መልካም ነገር እንዲሰሩብኝ እመኛለሁ …››
ሶስተኛው ዛፍ እንዲህ ሲል ምኞቱን አስቀመጠ ‹‹… እኔ የምመኘው በጣም ትልቅ፣ ረጅምና መለሎ ሆኜ ማደግ ነው፡፡ ሰዎች ሲመጡ ገና ከሩቁ ያዩኝና ይህስ ወደ መንግስተ ሰማያት ሊደርስ ምን ቀረው! እያሉ ያደንቁኛል፡፡ ከዛፎቹ ሁሉ ድንቅ እሆናለሁ፣ እናም ሰዎች በድንቅነቴ ያስታውሱኛል … ሲያስታውሱኝም … ‹… ያ! ዛፍ የሰማይ መክፈቻ ቁልፍ ቢኖረው ከፍቶ በገባ ነበር … ዳመናዎችን ወሽሟል … ዝናብን ይስማል …› …. ይሉኛል …››
ለምኞታቸው መሳካትም በየዕለቱ መትጋት ጀመሩ …
*   *   *
ከአመታት ጸሎት በኋላ ህልሞቻቸው እውን የሚሆንበት ወቅት መጣ፡፡ እነሆ በአንድ የጸደይ ማለዳ ጥቂት ዛፍ ቆራጮች ተሰብስበው ወደ ተራራው መጡ፡፡ አንደኛውም ወደ መጀመሪያው ዛፍ እየተጠጋና ግንዱን እየደባበሰው እንዲህ አለ …
‹‹ይህ ጠንካራ ዛፍ ይመስላል ስለዚህ ለአናጺው ወዳጃችን እንሸጥለታለን፡፡ እርሱም ሳጥን ይሰራበት ይሆናል…›› እናም መጥረቢያውን ይዞ ይቆርጠው ጀመር፡፡ ዛፉም እየተቆረጠ … ደስ አለው፡፡ ትክክል! እንደ ምኞቴና ህልሜ አናጺው የከበሩ ዕቃዎች ማስቀመጫ ሳጥን አድርጎ ይሰራኛል ሲል አሰበ፡፡
ሁለተኛውን ዛፍ እየደባበሰ ሌላው ዛፍ ቆራጩ እንዲህ አለ … ‹‹ይህም ጠንካራ ዛፍ ይመስላል፤ ይህንን ደግሞ ለመርከብ ሰሪው እሸጠዋለሁ… ጥሩ መርከብ የሚገነባበት ይመስለኛል …›› ሁለተኛውም ዛፍ እጅግ ደስ ብሎት ነበር፡፡ እነሆ ታላቅ መርከብ ሊገነባብኝና በመጨረሻም ህልሜ እውን ሊሆን ነው ሲል አሰበ፡፡
ወደ ሶስተኛው ዛፍ ሲመጡ ዛፉ በድንጋጤ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ቁመቴ ገና ሁሉን የሚበልጥ እጅግ ግዙፍ አልሆንኩምና አሁን ከቆረጡኝ ህልሜ አይሳክልኝም ሲል አስቦ ነበር፡፡ ከዛፍ ቆራጮቹ አንዱ እንዲህ አለ፡- ‹‹ከዚህ ዛፍ ምንም የተለየ ነገር አላየሁበትም፤ ሆኖም ቆርጬ ልውሰደው… መቼም ለሆነ ነገር ማገልገሉ አይቀርም…!›› አለና ቆረጠው፡፡
እነሆ ዛፎቻችን ተቆረጡ፤ ተጫኑ፤ ወደ ሰፈሩም ተጋዙ፡፡
የመጀመሪያውም ለአናጺው ተሰጠ፡፡ በእርግጥም አናጺው ሳጥን ሰራበት፡፡ ሆኖም ሳጥኑ የተሸጠው ለከበሩ ዕቃዎች ማስቀመጫ እንዲያገለግል ሳይሆን በበረት ውስጥ ለበጎች መመገቢያ ነበር፡፡ ዛፉም… ለዚህ አልነበረም የጸለይኩት ሲል አሰበና አዘነ፡፡
በሁለተኛውም ዛፍ የመርከብ ሰሪው ትንሽዬ የአሳ አስጋሪዎች የሚጠቀሙበት ታንኳ ሰራበት። ታላቅ መርከብ የመሆን ምኞቱ ድቅቅ አለ፡፡ ሆኖም ምን ይደረጋል! ሲል አሰበ፡፡ መርከብ መሆኔ ቢቀር … ታንኳም ቢሆን ሆኜ ልኑር የወደፊቱ አይታወቅምና…  ሲል ተቀበለው፡፡
ሶስተኛው ዛፍ ግን በረጃጅሙ እንደተቆረጠና ጥቂት እንደተስተካከለ ምንም ነገር ሳይሰራበት ከቆራጩ ዕቃ ቤት ተቀመጠ፡፡ እነሆ ወደ ጨለማው ዕቃ ቤት ተጣለና አቧራውን እየለበሰ … አዝኖ ቁጭ አለ፡፡ ተፀፀተ…
‹ምነው ጥቂት ጊዜ ቢተውኝ ኖሮ … ሁሉንም በልጬ አድግ ነበር!› ሲል አሰበ….
አመታት ነጎዱ፡፡ ዛፎቹም ህልማቸውን ዘንግተውና ረስተው መኖር ጀመሩ፡፡ ጸጥ ብለው ስራቸውን ይሰሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን አንዲት ሴትና አንድ ሰውዬ ወደዚያ የበጎች በረት መጡ፡፡ ሴትየዋም በምጥ ተይዛ ነበር፡፡ ቆይታም ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ህጻኑንም ከመጀመሪያው ዛፍ በተሰራው በበጎቹ የመመገቢያ ሳጥን ውስጥ አስተኙት፡፡ እነሆም የመጀመሪያው ዛፍ ከዓለም ድንቅ ነገሮች ሁሉ የላቀው ድንቅ ማረፊያ ሆነ። በቤተልሄም ከተማ የከብቶች ግርግም የኖረ ቢሆንም፣ የዓለምን ታላቅ ስጦታ አቀፈ፡፡ አማኑኤልን፡፡
(የማቴዎስ ወንጌል 2፣ 1 -)
*ከሌላ ዓመታት በኋላ በሁለተኛው ዛፍ በተሰራው ታንኳ ሆነው ባህሩን ያቋርጡ ዘንድ ሰዎች ነበሩ … በባህሩ ላይ ታላቅ መናወጥ ሆነ፣ ታላቅ ማዕበልም ተነስቶ ታንኳይቱን ያንገላታት ያዘ፡፡  ያቺ ትንሽ ታንኳ ታላቁን ወጀብ ተቋቁማ ሳትሰባበር ታገለች፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ ተነስቶ ‹‹ሰላም ይሁን!›› ብሎ ወጀቡንና ንፋሱን ገስፆ እስኪያቆመው ድረስ ያቺ ታንኳ ታላቅ ስራ ሰራች። ያ የተሸከመችውና ወጀቡን የገሰፀው ሰውም የንጉሶች ሁሉ ንጉስ የሆነው መሆኑን ባወቀች ግዜ ተደሰተች፡፡ እኛም የሁለተኛው ዛፍ ምኞት መሳካቱን አወቅን ….
(የማቴዎስ ወንጌል 8፣ 23 -)
*በመጨረሻም ከሶስተኛው ዛፍ ተቆርጦ ወደተቀመጠበት ጭለማ ክፍል አንድ ሰው መጣ፡፡ እነዚያን ቀጥ ያሉ የሶስተኛው ዛፍ ግንዶች አወጡ … መስቀልያ ሰርተውም ካጣመሯቸው በኋላ ለአንድ ምስኪን ሰው አሸክመው ያንገላቱት ጀመር፡፡ ስምኦን የተባለው የቀሬና ሰው ሲመጣ በእርሱ አህያ ጭነው ከዚያ የወጀብና የማዕበል አዛዥ ኋላ አስከትለው አስጓዙት፡፡ዋይ ዋይ የሚሉ እናቶች በሞሉበት መንገድ አቋርጠው ሲሄዱ ሰውየው ‹ለራሳችሁ አልቅሱ!› እያለ ይመክራቸው ነበር … ሰውየው በደም አበላ ታጥቦና በስቃይ ውስጥ ሆኖ ይጓዝም ነበር … ከቀራንዮ ተራሮች ላይ አወጡና በመስቀሉ ላይ ከሁለት ወንጀለኞች መሃል  ቸነከሩት፡፡
(የሉቃስ ወንጌል 23፣ 25 -)
ሶስተኛውም ዛፍ አለ ‹‹ … እነሆም በመጨረሻው በታላቁ ተራራ ላይ ታላቁን የሰማየ ሰማያት ልጅ ተሸከምኩ!... ምኞቴም ልክ መጣ … የሰማያትን ሁሉ መክፈቻ ቁልፍ በእኔ ላይ አኑረዋልና … ›› ሲል አሰበ፡፡
*   *   *
እንግዲህ የህልማችንን መፈቻ ወቅት መጠበቅ ግድ ነው … ለህልማችንም መሳካት መስራትና ቀሪውን ለተተኪያችን መተው ይገባል፡፡ የተመኘሁት አልተሰጠኝም፣  በወቅቱም አላገኘሁትም ልትል ትችላለህ፡፡  እመነኝ ላንተ የተባለ ዘግይቶም ቢሆን ወዳንተ ይመጣል፡፡
ዘግይቶም ቢሆን ግን በጣም ይፈጥናልና አይዘገይም፡፡
በርትቼ ብነሳ አውርጄም ባየው
ለካ ምግብ ኖሯል የተሰቀለው … (የሉቃስ ወንጌል 22፣ 19) (…ወዳጄ ልቤና ሌሎችም … ገጽ 69)
*   *   *
 (…የሃሳቡ አመንጪና እውነተኛ ፀሃፊው ያልታወቀ ሰው፡፡ ተሻሽሎ የተተረጎመ የ3ቱ ዛፎች ታሪክ …)
መልካም የትንሳኤ በዓል!

Read 3765 times