Saturday, 07 April 2018 00:00

ጲላጦስ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

(የፍርደ ገምድሎች እንጦሮጦስ!)
            
    1 - ንጉሥ?!
ክቡር እም ክቡራኑ፡ ለበርካታ ዓመታት ያብሰለሰላቸው ክስተት ፡ በኃይል አንበርክከው በሚያስተዳድሩት ቅኝ ግዛታቸው ይሁዳ ከተማ፡ ከእነርሱ ሌላ ደምቆ እናም ልቆ የታየው ‹‹ሰው›› ጉዳይ  ነበር፡፡ (እርሱ ግን አስቀድሞም ነበረ፡፡)
 
ከ33 ዓመታት በፊት - ልደት
... ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ፣ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ... (ማቴ.2፡1-3)
ከ33 ዓመታት በኋላ - ስቅለት
በስቅለቱ ድርሣንም አራቱም ወንጌላዊያን ይህንኑ ይመሰክሩታል . . .
ማቴዎስ - ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ ፤ ገዢውም የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። (ማቴ.27፡11)
ማርቆስ - ጲላጦስም አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። (ማር. 15፡2)
ሉቃስ - ጲላጦስም አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ፦ አንተ አልህ አለው። (ሉቃ. 23፡3)
ዮሐንስ - ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህን? አለው። (ዮሐ. 18፡33-34)
ለጲላጦስ ዋንኛ ጉዳዩ፡ ንጉሥ ነህ ወይ? በሚለው ጥያቄ ማጥመድና ‹‹ለማይቀረው›› የፍርዱ ውሳኔ የሚያበቃው የተረጋገጠ ማስረጃ ማግኘት ብቻ ነበር! አዎን! የሚል ምላሽ ለማግኘት እንደጓጓ ቀረ እንጂ፡፡ ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ (1ኛ ጢሞ. 6፡13)የታሪክ ተመራማሪው ፒኒ pini በEusebius ዜና መዋዕሉ ውስጥ እኒህን መሰል ጥያቄዎች ጥንታዊያኑን ክርስቲያን ሰማዕታት ለመወንጀል በሚደረጉ የምርመራ ጥያቄዎች ውስጥም ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ይገልፃል . . . Pilate’s repeated questioning of Jesus about His alleged kingship was in a form regularly employed to determine the guilt of a prisoner who refused to plead: Christian martyrs were questioned in this way in the earliest recorded trials.
2 - ጲላጦስ
አበው ለአማርኛ አቻ ትርጉሙ፤ጴንጤናዊው ጲላጦስ ሲሉ የሰየሙት PILATE, PONTIUS በጢባርዮስ ቄሣር የንጉሠ ነገሥትነት ዘመን ከ26/27 -36 ዓ.ም ለአስር ዓመታት ያህል የይሁዳ ሀገረ ገዢ ሹም ነበር፡፡ የቤተሰቡ ስም Pontius በመካከለኛና ሰሜናዊው ሮማዊያን ሕዝቦች ዘንድ የሚዘወተር መጠሪያ ሲሆን፤ የእርሱ ስም Pilate  ‹‹ጦር ታጣቂ›› ወይም ‹‹መላጣ›› ወደ ስርወ ቃሉ መነሻ ሲጠልቁ ደግሞ ‹‹የተመሰቃቀለ›› የሚል አይነት ትርጓሜ አለው፡፡ ይኸውም ጲላጦስ በኢየሱስ ችሎት ላይ ከነበረው መንገጫገጭ/ወላዋይነት uncertainity ጋር ይመሳሰላል ይላል፤ ኹነቱን Excecution of Christus በሚል አርዕስት የከተበው የላቲኑ የታሪክ አጥኚ Tacitus ታኪተስ፡፡ (ኢትዮጵያዊያን ስምን መልዐክ ያወጣዋል እንደምንለው፡፡) ሌላው የታሪክ ተመራማሪ ፊሎ Philo በበኩሉ፤ ጲላጦስ ከመኳንንትና መሳፍንቱ በተለይ ከንጉሡ ጋር ጥብቅ ፖለቲካዊ ቁርኝት እንደ ነበረውና ለሀገረ ገዢነት ከመመልመሉ በፊት ያሳለፈው የውትድርና ውሎ ብቃቱም፤ ጢባርዮስ ቄሳር በንግሥና ዘመኑ በጲላጦስ ታዛዥነት ላስከበረውና ከእርሱም በኋላ ለቀጠሉት ገዢዎች አመቺ ሆኖ ለዘለቀው ሰጥ! ለጥ! አድርጎ በኃይል አንበርክኮ የመግዛት ስልት መሰረት የጣለ ነው፡፡ለዚህም ነበር በየጊዜው ብዙ ስሞታዎች እየጎረፉለትምንኳ ጲላጦስን አስር ዓመታት በገዢነት እንዲቀጥል ንጉሡ የተወው ይላል፡፡ እንጂ የጲላጦስ ሀገረ ገዢነት ቆይታ ሮማዊያን ከቅድስቲቱ ምድር ሕዝቦች ጋር ክፉኛ የተፋጠጡባቸው ዓመታት እና ያንንም ተከትሎ ጲላጦስም እጅግ ብዙ ተግዳሮቶችን ያስተናገደባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ወንጌላዊያኑ ባበረከቱልን ድርሳናት ውስጥ ከምናገኘው ባሻገር፤ እንደ ፊሎ ሁሉ የጲላጦስን ህይወት በስፋት ዳስሷል የሚባለው እውቁ የታሪክ ጸሐፊ ጆሴፊየስ Josephius እንደዘገበው . . .
ጲላጦስ፡ በቤተ መቅደስ ውስጥ የቄሣሩን ሀውልት ለማቆም እስከመከጀልና መሞከርም ድረስ የሮማን ንጉሠ ነገሥት በታማኝነት በማገልገል ከፍ ከፍ ብሎ ለመመስገን ፍዳውን አይቷል፡፡ ይህንኑም በተግባር ለማሳየት በሚል ያልተገደበ አምባገነንነቱን ተጠቅሞ ቅድስቲቱን የኢየሩሳሌም ከተማ በኃይል ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ ነዋሪዎቿን ክፉኛ ያሳዘነና ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ፡የንጉሠ ነገሥቱን ስም ያጎደፈ፡ከነባሩ የሮማዊያኑ ያገዛዝ ጠባይም ሆነ ከአይሁድ ህግና ስርአት አለቅጥ ያፈነገጠ ነበርና ከያቅጣጫው ብርቱ ወቀሳና ትችቶች ዘንበውበታል፡፡ ውሎ አድሮም ጲላጦስ የውኃ አገልግሎትና የጥቃቅን ጥቅማ ጥቅሞችን ወጪ በመበጀት የኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎችን ለመደለልና ለማግባባት ቢሞክርም አልተሳካለትም፡፡ በየግዛቶቹ ያልተቋረጡትን አመጾች ለማረጋጋትም፤ ወታደሮቹ ከእንግዲህ ከሰይፋቸው ይልቅ ቆመጦቻቸውን ብቻ እንዲጠቀሙ ቀጭን ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም፤ ትዕዛዙ ሰሚ በማጣቱ፤ አመራሩ ለበርካቶች ህይወት መቀጠፍ በተጠያቂነት ከመጋለጥ አልዳነም፡፡ ይህም በገሊላ ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን በድብቅ የተደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ ይጨምራል፡፡ (ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች (ሉቃስ 13፡1) ሀይ ባይ በማጣቱም በሀገረ ገዢነት በተሾመ በአስረኛው ዓመት ሲመቱ በሰማርያ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተመላበት ዘግናኝ ድርጊት ከወትሮው የገነነ ተቃውሞንና የገሊላ ከተማ ሸንጎ ለበላዩ ሀገረ ገዢ ያቀረበውን አቤቱታ ጨምሮ፤ በአውሮጳ የሚኖሩ የአይሁዳዊያን ልዑካን ቡድንም ሮማ ቤተ መንግሥት ዘልቀው አቤት ያሉበት ከፍተኛ ውግዘት ስላደረሰበት፤ ጽዋው ሞልታ ተረፈችና፡ ጥብቅ ምርመራ ይደረግበት ዘንድ ወደ ሮም ሄዶ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ጢባርዮስ ቄሳር ፊት ቀርቦ እጅ እንዲነሳና ስለ ሳምራዊያን የጅምላ ግድያ ጉዳይ እንዲናዘዝ (‹‹እንዳቦካሻት ጋግሪያት››) ሲል የአሦር ሀገረ ገዢ አፋጠጠው፡፡ (ታዲያ ምን ችግር አለው፡ ጲላጦስኮ ለቄሳሩ እጅግ ታማኝ አገልጋዩና ታዛዥ ባለውለታው ነው፡፡)
‹‹አወይ ክብረት ዓለም
አዬ ክብረት ዓለም፤
የጀመረሽ እንጂ
የጨረሰሽ የለም!››    
           (የሕዝብ ግጥም፡፡)
ከጲላጦስ ጋር ወደ ሮማ ከመጓዛችን በፊት ፤ ላፍታ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ እንመለስ . . .
መልካም ትንሣኤ፡፡
ስቅለት - በሰአሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

Read 1177 times