Saturday, 07 April 2018 00:00

ደማሙ ተናጋሪ - ዶ/ር አብይ አህመድ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “ማንነታችን እንዳንለያይ ሆኖ የተሰናሰነ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሃደ ነው”

     የኢትዮጵያ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ንግግር፤ ሁሉን ያስደነቀ በአንጻሩ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉጉትና ተስፋ ሰንቀው በአንክሮ፣ እንዲከታተላቸው ያደረገ ነው፡፡ በበዓለ ሲመታቸው ቀን ያደረጉት ንግግርና የአቀራረብ ሰብዕና፤ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኙት መሪዎች ተርታ ያሰልፋቸዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡ በመጀመሪያ የዳሰሷቸውን ሀሳቦችና ያሄሷቸውን ርዕሰ ጉዳዮች አንድ በእንድ እየነቀሱ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚያስታውሱት፤ ዶ/ር አብይ በጨው የተቀመመ፣ የሰውን ልብ የገዛ፣ የተስፋ ‹‹ገበታ›› ነው በንግግራቸው ያቀረቡት፡፡ የኢትዮጵያ ገበታ ሰፊ ነው እንዳሉት፣ እሳቸው ሰፊውን ገበታ ነው ለኢትዮጵያ እነሆ ያሉት፡፡
የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ንግግር፤ ብዙዎችን የሳበበት ትልቁ ምክንያት የንግግሩ ማጠንጠኛ  የተቋጠረበት የትንታኔ ፍሰት ነው፡፡ የንግግራቸው ጅረት የተቀዳው ከተለያዩ ምልከታዎች በመሆኑ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ የሕዝቡን፣ የፓርቲውንና የጊዜውን እንዲሁም የወጣቱንና የጥቅል ማሕበረሰቡን የፍላጎት አውድ መሰረት አድርጎ የተነሳ በመሆኑም አድናቆት አትርፏል፡፡
 1ኛ. ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናቸው የሚክስ ነው
በንግግራቸው ውስጥ ያቀረቡት የታሪክ ትንታኔያቸው፤ ለኢትዮጵያውያን ካሳ የከፈሉበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክና ማህበራዊ ስሪት ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አቆራኝተው መግለጻቸው፣ አንድ የንግግራቸው ጥንካሬ ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊነትን  ትልቅ ቦታ ሰጥተው፣ ዋጋ የከፈሉ አባቶችን እውቅና መስጠታቸው ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትልቅ ካሣ የከፈሉበት ንግግር ነው፡፡ ከልዩነት አንድነትን አስቀድመው፣ በዚያው ደግሞ አንድነት፤ አንድ ዓይነትነት አይደለም ሲሉ የተደመጡበት ንግግራቸው መሳጭ ነበር፡፡ የሚፈልጉትን ሃሳብ  የገለጹበት ሞገስና  ትህትና፣ ንግግራቸውን አጣፍጦላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ጥምረት ሲገልጡ፤ ‹‹ማንነታችን እንዳንለያይ ሆኖ የተሰናሰነ፣ እንደይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሃደ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን፤ “I have a dream” ዓይነት ንግግር ይመስላል፡፡ መተማን፣ ካራማራን፣ ባድመንና አድዋን ሲያነሱ፤ ሉተር ሚሲሲፒን፣ ጆርጂያን፣ ቴኔሲንና የመሳሰሉትን እየጠቀሱ የተናገሩትን ይመስላል፡፡
2ኛ. አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናቸው
ጥሪ ደማቅ ነበር
 ይህ ፍልስፍናቸው የሚቀዳው ምናልባትም ስለ ኢትዮጵያ ካላቸው እውቀት፣ የስራ ልምድ እንዲሁም ወጣትነታቸው ካቀበላቸው ስንቅ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ ቁስል እንዳለብን ተገንዝበው የቁስል መፈወሻ ቃል ማቀበላቸው ያስደንቃል፡፡ ተቃዋሚ የሚለውን ተፎካካሪ፣ “ህገ መንግስቱን ለመናድ” የሚል ቅጥያ ስም የወጣላቸውን፣ ለሃገራችን በጎ ርዕይ ያላቸው ወንድሞቻችን፣ ጽንፈኛ ዲያስፖራ የሚለውን፣ ኢትዮጵያን በውስጣቸው ይዘው የሚዞሩ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ሲሉ ቁስሉን ሽረውታል፡፡ በተዘዋዋሪ ነፍጥ አንስተው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ሲዋደቁ የኖሩትን አርበኞች እውቅና መስጠታቸው ያስደንቃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ፤ ከኢህአዴግም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በላይ መሆኗንም ተናግረዋል - ‹‹ኢትዮጵያ ከፖለቲካ አመለካከት በላይ ነች›› በማለት። ይህ ምን ማለት ነው? “ኦህዴድ ወይም የፖለቲካ መስመሩ ከኢትዮጵያ አይበልጥብኝም” እንደ ማለት  ነው፡፡ ይህ ነው አዲሱ መንገዳችን የሚሉም ይመስላል፡፡ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እውነትና “የኔ ብቻነት” የተላቀቁ መሆናቸውን ንግግራቸው ይጠቁማል፡፡ ድርጅቱንም ወደዚህ ጠርዝ ፈቀቅ ያደርጉታል ብሎ መገመት ይቻላል።
3ኛ. ዴሞክራሲንና ፍትህን ከነጻነት
ጋር አንስተው ያሄሱበት ንግግር ይለያል
በንግግራቸው ውስጥ የዴሞክራሲን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነቱን ፈትሸዋል፡፡ አገሪቱ በተስፋና በስጋት ውስጥ ናት ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ምክንያቱን ሲዘረዝሩ፤ የዴሞክራሲ እጥረት ነው ብለዋል፡፡ ግለሰቦች ነጻነታቸው ተገድቧል ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በአጭሩ የዲሞክራሲ ሥርዓቱን የተቸ የሰላ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ነጻነት የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ የመንግስት ሥጦታ አይደለም ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ በዚህም ከቡድን  ነጻነት ይልቅ ለግለሰብ ነጻነት ቅድሚያ (ትኩረት) መስጠታቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ይህም ኢህአዴግን ወደ አዲስ መንገድ  ይመሩታል የሚል ሃሳብ ያጭራል፡፡አዲሱ ጠ/ሚኒስትር፣ ማልኮም ኤክስ እንዳለው፤ “we haven’t benefited from America’s democracy, we suffered from America’s hypocrisy” (ከአሜሪካ ዴሞራሲ እየተጠቀምን ሳይሆን በግብዝነቱ እየተሰቃየን ነው) የሚለውን ዓይነት ሃሳብ ማንጸባረቃቸው ያስደምማል፡፡
4ኛ. የተዘነጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በተገቢ ሁኔታ ያስታወሰ ንግግር
የተዘነጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን ለተጠቃሚነታቸው መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ የወጣቱን ክፍል ሃሳብ፣ጥያቄና ትግል እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ተግባር ሲጨመርበት ደግሞ የግሩም ግሩም ይሆናል፡፡ ሌላው ያነሱት የሴቶችን ትግል አስፈላጊነት ነው፡፡ የሴቶች ትግል በትክክል ሊወከል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አብይ በንግግራቸው መደምደሚያ ላይ የእናታቸውን፣ የሚስታቸውንና የሌሎች እናቶችን ሚና በሚገባ ማንሳታቸው፣ ቁርጠኛ የሴቶች መብት ተሟጋች ያደርጋቸዋል፡፡ ምናልባትም የእናታቸውን ውለታ እያዩ አድገው፣ የኢትዮጵያውያንን እናቶች ጭቆና አስተውለውና የወለዷቸው ሦስት ሴት ልጆች ዕጣ ፈንታን ተገንዝበው ትኩረት የሰጡት ጉዳይ ስለሚመስለኝ፣ ከንግግራቸው ትልቁን ቦታ የሚይዝ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ “Which side of America are you living in” እንደተባለው፤ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የአኗኗር ሁናቴ አጢነው፣ በዚህ አቅጣጫ ለውጥ ለማምጣት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ ድሃ አደጉን አይተውታል፡፡ የእናቶችን፣ የባልቴቶችንና ሕጻናትን ሁኔታ ያውቁታል፡፡
4ኛ. የማህበራዊ ፈውስ (ሶሻል ቴራፒ) ፈጣን መርሃቸው ይመስላል
የንግግራቸው አንኳር ማጠንጠኛው፤ ማሕበራዊ ፈውስ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን የተሳሳተና የተንጋደደ አስተሳሰብ በተመለከተ እርምት ሰጥተዋል፡፡ ጨለምተኛነትንና ጠባብነትን እንዲሁም የታጋይ ግብዝነትን ተችተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት አገር ናት ሲል ደምድሞ የተነሳውን ድርጅታቸውንም ቢሆን  ሞግተውታል፡፡ በመጀመሪያ ለሰብአዊ መብት ሲሟገቱ፣ ህይወታቸውን ለተነጠቁ  ግለሰቦች ይቅርታን ጠይቀዋል፡፡ ይህ ትልቅነት ነው። ፈውስ ያመጣል፡፡ ይህን በማለታቸው ጠ/ሚኒስትሩ ከድርጀታቸው ያፈነገጡ የሚመስላቸው አይጠፉም። ግን አፈንግጠው አይደለም፡፡ ብዙዎቹም የድርጅቱ አባላትም ይህን ይጋሯቸዋል፡፡
የሙሰኞችን የበረታ እጅ አንስተው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንደሌለ አስምረውበታል፡፡ አንዱ ዘርፎ አንዱ ሰርቶ የሚኖርባት አገር ማየት አንፈልግም ብለዋል። ‹‹የልዩ ተጠቃሚ ነን” ኃይሎችንና ወደፊት አዳዲስ ጎሳን ወይም ሌላ የጥገኝነት መስመር ዘርግተው፣ ለዘረፋ የተዘጋጁ ተስፈኞችን፤ ድርጅታቸውንና ሰፊውን ሕዝባቸውን ይዘው እንደሚታገሏቸው መግለጻቸው ያስደንቃል። የማሕበራዊ ማለትም የፖለቲካ ተጽዕኖ፣ የኢኮኖሚ ብዝበዛና በአዲስ መልክ የተገለጸውን ዘረፋና ማሕበራዊ ውርደት (ሶሻል ዲግሬዲሽን) አውግዘዋል፡፡ ወደፊት እንደማይከሰትም ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሰርቆ አደሮች››፣ በሰርቶ አደሮች ይሸነፋሉ ማለታቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ዕድገት አላሳየችም የሚሉትንም ጨለማ አንጋሾች በሥነ አመክንዮ ሞግተዋል፡፡በአንጻሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ተስፋ እንዲሞሉ፣ ”ኢትዮጵያ ማሕጸነ ለምለም ናት” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ተስፋ ነው፡፡ የትምህርት ጥራቱን አንስተው ሲናገሩም፤ “ጥራት የለም” ከሚሉ ብዙ ተችዎች ጋር አቀራርቧቸዋል። ይህም ማህበረሰቡን  የማድመጥ ችሎታቸውን ያሳያል። ጠ/ሚኒስትሩ ለትምህርት የሰጡት ቦታ ትልቅ ነው፡፡ ትምህርት ለነጻነት ያለውን አስተዋጽኦ ታላቁ የጥቁሮች ታጋይ ፍሬደሪክ ዳግላስ አጽኖት እንደሰጠው መሆኑ ነው፡፡
ይቅርታንና ፍቅርን ማንሳታቸው አንዱ የማህበራዊ ፈውስ ፈላጊነታቸውን ማሳያ ነው፡፡ አንዳንዶች ብሔራዊ እርቅ ሲሉት ሌሎች ብሔራዊ መግባባት ይሉታል። እሳቸው ግን ሦስተኛውን መንገድ መርጠዋል፡፡ ይቅርታ እና ፍቅር፡፡ ይቅርታ ሲሉ፤ በዳይና ተበዳይ አለ ማለታቸው ነው፡፡ ፍቅርን ሲያነሱ፤ ጠብ ወይም ቁርሾ አለ ማለታቸው በመሆኑ የቃላት ንትርኩን ትተው፣ የይቅርታ እና የፍቅር አስፈላጊነትን  ነው ያነሱት፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ጠ/ሚኒስትሩ ተግባሩ ላይ ነው ትኩረት ያደረጉ የሚመስሉት፡፡ ለፍቅር ያላቸው ሃሳብ፣ ከደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡”እምዬ ምኒልክ” እንዲሉ፣ “እምዬ ፍቅር” እንላቸው ይሆናል፤ማን ያውቃል!?
5ኛ. ተስፈኛነትና እራስን ማግኘትን
ያንጸባረቀ ንግግር   
ድርጅታቸውን ኢህአዴግን እንደሚወዱት ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ባይሆን ኖሮ ይህን ያህል ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ አይቆዩም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለድርጅቱ ያላቸው ፍቅር፤ በድርጀቱ አስተሳሰብ  ሙሉ በሙሉ የሟሙ አላደረጋቸውም፡፡ ማልኮም ኤክስ፤ ‹‹እኔ አሁንም የእስልምና እምነት ተከታይ ነኝ፤ ከዚሁ ጋር የጥቁሮች ብሔርተኛ መሪ ነኝ፡፡ የኔ ሐይማኖታዊ ፍልስፍና እስልምና ነው፡፡ ለነብዩ መሐመድ ትልቅ ቦታ አለኝ፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍልስፍናዬ፣ የጥቁር ብሔርተኝነት ነው፡፡›› እንዳለው ነው፡፡ ዶ/ር አብይ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማሕበራዊ ፍልስፍናቸው፤የኢህአዴግ ዓይነት ቢሆንም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፍልስፍና ሌላ የሃይማኖት ፍልስፍናቸው በግልጽ ነጥሮ የወጣበት ንግግር ነው ያቀረቡት፡፡
ለዚህ አንዱ ምስክር፤ እኔ ብቻ ወይም ለእኔ ብቻ ወይም ፓን ሰልፊዝም አያስፈልግም ብለዋል፡፡ ቃል በቃል ለማስቀመጥ፤ ‹‹የኔ ሃሳብ ብቻ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ›› ማለትን ተችተዋል፡፡ የሪፐብሊካኑ እጩ ተወዳዳሪ ዶ/ር ካርሰን፤ የሪፐብሊካንን እና የዴሞክራትን “የኔ ይሻል፣ የኔ ይሻል” ደረቅ ሙግትን ሲተቹ፤  “My way or the Highway” ማለት አያስፈልግም እንዳሉት ማለት ነው፡፡ የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ፍልስፍና፤ መደማመጥ፤ መመካከር ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ”ይህ ወይም ያኛው ፖሊሲ ወይም አዋጅ የሚለወጠው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው” የሚለውን ግትር አቋም አሂሴው ነው ያለፉት - በንግግራቸው፡፡
ሌላው  የፈጣሪን ስም  ማንሳታቸው ካለፉት ሁለት ጠ/ሚኒስትሮች ይለያቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፈሪሃ እግዚአብሔርን አስተሳሰብና የማሕበረሰቡ የሞራል መሪ ምስረታ ላይ ገንቢ ሚና ይኖረዋል፡፡ “ለምመራው ሕዝብ ስል የማምንበትን እምነት አልናገርም” ሲሉን እንደነበሩት መሪዎች፤ አብይ (ዶ/ር) ድብቅ አልሆኑም። የአዲሱ ትውልድ ትሩፋት ይህ ነው፡፡ ግልጽነት!!! የተግባር ፈፋውን ይሻገሩት ይሆን? እግዚአብሔር ይርዳቸው፤ ሰውም ይስጣቸው፡፡ የኦሮሞው ታሪክ ፀሃፊ ዓፅመ ጊዮርጊስ፤ “አቤቱ እባክህ ጌታዬ፤ ምኒልክን ከክፉ …ጠብቃቸው” እንዳለው፤ እኔም “አቤቱ  ጌታዬ፤ እባክህ አዲሱን ጠ/ሚኒስትር ከእንቅፋቶች ሁሉ ጠብቃቸው፣ መከናወንንም እንደ ታላላቆቹ መሪዎቻችን ስጣቸው፣ የታላላቆቹን መሪዎች ድካምንስ አርቅላቸው። ኢትዮጵያውያን እፎይ ብለው ይኖሩ ዘንድ!!” እላለሁ፡፡

Read 1444 times