Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 April 2012 14:08

የጊቤ ግድብን የተቃወመች ተሸለመች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ተብሎ የሚገነባውን የግልገል ጊቤ 3 ግድብ ለማስቆም ዘመቻ የምታካሂድ ኬንያዊት የአካባቢ ጥበቃ ተሸላሚ ሆነች። የ30 አመቷ አይካል አንጀሊ የግድቡን ግንባታ ለማስቆም የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ያቋቋመችው ከሶስት አመት በፊት ሲሆን፤ በተመሳሳይ አለማቀፍ ቡድኖች ድጋፍ አማካኝነት ለግድቡ ግንባታ ታስቦ የነበረ የብድር ገንዘብ እንዲቆም ማድረግ ችላለች። ግድቡን የሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፤ የድህነት ጠበቆች ናቸው በማለት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ተቃውሞውን አውግዘዋል።በኦሞ ወንዝ ላይ የሚገነባው የሃይል ማመንጫ ከጊቤ1 እና ከጊቤ2 ቀጥሎ እየተገነባ የሚገኘው ሶስተኛው የሃይል ማመንጫ፤ በግዙፍነቱ ከአለም በአራተኛ ደረጃነት የሚጠቀስ ይሆናል በማለት “የል ኢንቫሮመንት” የተሰኘ ተቋም ተቃውሞውን የገለፀ ሲሆን፤ አይካል አንጀሊ የአመቱ ተሸላሚ መሆኗን ደግፏል።

ጎልድማን ኢንቫሮመንት አዋርድ የተሰኘው ሽልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ሽልማት እንደሆነ ተቋሙ ጠቅሶ፤ የዘንድሮዋ ተሸላሚ ግዙፉን ግድብ ለመታገል በፅናት የቆመች ነች ሲል አድንቋታል። 1800 ሜጋ ዋት በማመንጨት፣ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የኤሌክትሪክ ሃይል በእጥፍ ያሳድጋል ተብሎ የሚጠበቀው ጊቤ 3፤  የኦሞ ወንዝ የውሃ ፍሰትን በማዛባት የአካባቢውን ነዋሪዎች ይጎዳል ስትል አንጀሊ ትቃወማለች። በጊቤ 3 ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ሩብ ያህሉ ለኬንያ በሽያጭ እንደሚተላለፍ ሁለቱ አገራት ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በርካታ የኬንያ ዜጎች በኤሌክትሪክ እጥረትና በመብራት መቋረጥ በመማረር የግድብ ግንባታውን ይደግፉ እንደነበር አንጀሊ ገልፃለች። የመንግስት ባለስልጣናትም ግድቡን ይደግፉ የነበረ ቢሆንም፤ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ባካሄዱት ዘመቻ በርካታ ሚኒስትሮችና ብዙ ዜጎች ሃሳባቸውን በመቀየር ተቃውሞ እያሰሙ ናቸው ብላለች - አንጀሊ። በኢትዮጵያ ሙርሲ እና ሃመር የመሳሰሉ ማህበረሰቦች እንዲሁም በኬንያ ዳሰነች እና ቱርካና የተባሉ ማህበረሰቦች በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሃይቅ ዙሪያ እንደሚኖሩ የምትናገረው አንጀሊ፤ በአርቢነት የሚተዳደሩት ማህበረሰቦች በግድቡ ምክንያት የአኗኗር ዘይቤያቸው መቀየር የለበትም በማለት ተከራክራለች። “ልማት” ማለት የአኗኗር ዘይቤን መቀየር እንዳልሆነ አምናለሁ ያለችው አንጀሊ፤ ለምሳሌ በመኪና መጠቀም የማይፈልግ ሰው፣ “ልማት” አላገኘም ማለት አይደለም ብላለች። መኪና ባለመጠቀም፤ መንፈሳዊና መሰረታዊ ፍላጎቶቼን ብቻ በማሟላት ተስማሚ የአኗኗር ዘይቤ መምረጥ ይቻላል በማለት የምትናገረው አንጀሊ፤ የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሃይቅ ዙሪያ የሚገኙ ማህበረሰቦች በቀድሞው የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዳይቀጥሉ የጊቤ 3 ግድብ ከፍተኛ አደጋ ሆኖባቸዋል ብላለች። አንጀሊ ላለፉት ሶስት አመታት ባደረገችው አለማቀፍ ዘመቻ፤ በተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች እገዛ አማካኝነት የግድቡን ግንባታ ለማጓተት እንደቻለች “የል ኢንቫሮመንት” ገልጿል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ለግድቡ ግንባታ ማጠናቀቂያ ብድር ለመስጠት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም፤ ከአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች በደረሰበት ተፅእኖ አማካኝነት ብድሩን ከመስጠት አፈግፍጓል። ከፍተኛ ብድር በመስጠት የሚታወቀው የአለም ባንክም ለግድብ ግንባታ ብድር መስጠት ካቆመ ቆይቷል። ከስድስት አመት በፊት የተጀመረው የግድብ ግንባታ፤ በሚቀጥለው አመት ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ገና ለበርካታ አመታት እንደሚዘገይ ይገመታል - እስካሁን የግድቡ 50 በመቶ ነው የተገነባው። የግድቡን ግንባታ የሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፤ የአካባቢው ህዝብ ከኋላቀር አኗኗር እንዳይወጣ የሚፈልጉ ናቸው በማለት ያወገዙት ጠ/ሚ መለስ፤ ገና ጊቤ4 እና ጊቤ5 ግድቦችም ይገነባሉ ብለዋል። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖቹ የድህነት ጠበቆች ናቸው በማለትም ተናግረዋል።

 

 

 

Read 15556 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 14:13