Print this page
Saturday, 07 April 2018 00:00

የፖለቲካ አፈ ከራዲዮን

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

አውደ ዓመት ነው፡፡ ጽሑፌ የተዋዛ እና ከትንሳዔ ጋር የተያያዘ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ ስለዚህ ንጽጽሩ ፀያፍ ካልሆነ (Blasphemy)፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሐገራችን ፖለቲካ በሰሙነ ህማማት መቆየቱን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ከህማማት በኋላ ትንሳዔ ነው፡፡ መጪው ጊዜ ለሐገራችን ፖለቲካ ትንሳዔ መሆኑን በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፤ የትንሳዔ ወጋጋን መኖሩን፤ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ወዲህ ህዝቡ ከሚሰጠው አስተያየት ለመረዳት ይቻላል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት የሐገሪቱ የፖለቲካ ሰማይ በጥቁር ደመና ተጋርዶ፣ በጭጋግ ተሸፍኖ እና ጭፍና ለብሶ ነበር የቆየው፡፡ በቅርቡ በታወጀው ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ›› የተነሳ ትንሽ መረጋጋት ካሳዬ በኋላ፤ አሁን ከአዲሰ ጠ/ሚ መመረጥ በኋላ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ሁኔታ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ሁኔታው እንዲህ ይቀጥላል? ወደፊት ይታያል፡፡
እኔ፤ የሁከት ደመናው በድንገት እልም ብሎ፤ በህዝቡ ልብ የተስፋ ፀሐይ ወጥቶ መመልከቴ ግራ ቢያጋባኝም፤ እናቴ ግን ‹‹የእግዚአብሔር ምህረት›› ብላ ደምድማለች። ‹‹አሁንም ወደ እርሱ ማንጋጠጥ ነው›› ትላለች፡፡ እኔ ‹‹ፈጣሪንም አምናለሁ፤ ግመሌንም አስራለሁ›› ባይ ነኝ። በምክንያት ገመድ ግመሌን ካላሰርኩ በቀር ዕረፍት አይሰማኝም፡፡ ግን ገመድ አጣሁ፡፡
አንድ ነገር በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› አግኝቷል፡፡ ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› የትንሳዔ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ ተደርጎ የሚቀርብ ወፍ ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ሦስት መዐልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር ቆይቶ ለመነሳቱ ምሳሌ የሚደረግ ወፍ ነው፡፡ ይህን ወፍ የሐገራችን የሐይማኖት ሊቃውንት (በግዕዝ) ‹‹አፈ ከራዲዮን›› ይሉታል፡፡ ‹‹የከራዲዮን ወፍ›› ማለታቸው ነው፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚሉት፤ ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› በቤተ መንግስት የሚኖር ወፍ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ኦፈ ከራዲዮን››ን የቤተ መንግስት ሐኪም ይሉታል፡፡ ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› መልኩ ጸአዳ (ነጭ) ነው፡፡ ሰው በታመመ ጊዜ፤ ከህመምተኛው ሰው አጠገብ ሲያስቀምጡት፤ ሰውዬው የማይድን ከሆነ ፊቱን ያዞራል፡፡ የሚድን ከሆነ ግን የህመምተኛውን በሽታ ይወስድለታል፡፡ በዚያ ጊዜ ጸአዳ መልኩ ተቀይሮ ጥቁር ይሆናል፡፡ እናም ፀአዳ ላባው እንዝዝ ጥቁር እንደሆነ ወደ ተራራ ይበርራል፡፡ ከዚያም ወደ ባህር ጥልቅ ወርዶ ለሦስት ቀናት ይቆያል፡፡ በሦስተኛው ቀን፤ ከባህር ሲወጣ፤ የቀደመ መልኩን ይዞ ወደ ቤተ መንግስት ይመለሳል፡፡ ይህን ብዙ የማላውቀውን የነገረ - ሐይማኖት ሐቲት፤ ከነ ሙሉ ክብሩ እና ምስጢሩ ከዚህ ትቼ፤ እኔ ወደ ፖለቲካ አስተያየቴ አልፋለሁ፡፡ 
በሐገሪቱ ያንዣበበውን ጥቁር ደመና የገፈፈው ወይም የኢህአዴግን ህመም የወሰደለት ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይባላል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› አግኝቶ ነፍስ ዘራ፡፡ ይህም ሁኔታ በትንሳዔ እንድናምን የሚያደርግ ነው፡፡
እዚህ ላይ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ የጋዜጣውን አንባቢዎች፤ እንኳን ለበዓለ ትንሳዔው አደረሳችሁ፡፡
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ድብዳቤ›› ሲል የሰየመው አንድ ግጥም አለው፡፡ ግጥሙ ስለ ትንሳዔ ይናገራል፡፡ ግጥሙ የተጻፈው ደበበ በዕድገት በህብረት ዘመቻ ወሎ ክፍለ ሐገር በሄደ ጊዜ፤ በወቅቱ የነበረውን አስከፊ የረሃብ ሁኔታ ተመልክቶ፤ የተሰማውን ስሜት ለመግለጽ በማሰብ፣ የጻፈው ተራኪ ግጥም ነው፡፡
ገጣሚው ‹‹ጋሼ›› ብሎ ከሚጠራው አንድ ሰው ጋር የሚነጋገርበት ግጥም ነው፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው ለጋሼ ሆኖ ሳለ፤ ርዕሱ ግን ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› ይላል። ስለዚህ ደበበ ‹‹ጋሼ›› የሚለው ራሱን ይመስላል፡፡ ደበበ በዚህ አቀራረብ ምን ዓይነት ግጥማዊ ሐቅ ማንሳት እንደፈለገ ለማተት አልፈልግም፡፡ አሁን የእኔ ትኩረት ኪናዊ ትርጉም ማደን አይደለም፡፡ አሁን እኔ የምፈለገው፤ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤
ጋሼ፤
ያብቡ ይሆን አበቦቹ፤
ይተሙ ይሆን ንቦቹ፤
በትንሳዔ እንድናምን፤ በሚል ከሚሄደው ግጥሙ ‹‹በትንሳዔ እንድናምን›› ከምትለው ስንኝ ጋር መዛመድ እፈልጋለሁ፡፡ ገጣሚው የድርቁን ሁኔታ ተመልክቶ ‹‹እኔ በትንሳዔ የማምነው፤ ከዚህ አካባቢ ህልው ሳቅ የሚስቅ ሰው በተመለከትኩ ጊዜ ነው›› የሚል ሙግት ያለው ነበረው፡፡ ደበበ ‹‹በዚህች ምድር ዳግም አበቦች ሲያብቡ፤ ንቦች ሲተምሙ ማየት ካልቻልኩ›› በትንሳዔ አላምንም የሚል ኪናዊ ሙግት አንስቶ ነበር። እኔም ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢህአዴግን የገጠመውን ፖለቲካዊ ቀውስ በመመልከት የራሴ ሙግት ነበረኝ። ሆኖም በአዲሱ ጠ/ሚ መመረጥ ሳቢያ በሐገራችን ፖለቲካ ገጽታ ላይ የተፈጠረውን ለውጥና በህዝቡ ዘንድ የፈጠረውን ስሜት ማየት በትንሳዔ እንድናምን የሚያስገድድ ክስተት ነው፡፡
በዚህ የትርጉም ገበታ የፖለቲካው ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› አቶ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ አሁን በፖለቲካው ሜዳ አበቦቹ ዳግም አብበው ይታያሉ፡፡ ንቦቹም ዳግም ለመብረር ክንፋቸውን ያፍታታሉ፡፡ የደበበን አላውቅም። እኔ ግን በትንሳዔ አምኛለሁ፡፡ ሐገሪቱ ከዚህ በኋላ ወዴት እንደምትሄድ ባላውቅም፤ የሐገሪቱን የፖለቲካ ሰማይ ጋርዶት የነበረው ጥቁር ደመና ለጊዜው ገለል ብሎ ይታያል፡፡ ይህም ትምህርተ-ትንሳዔ ይሆናል፡፡   
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አቢይ አህመድ በፓርላማ  ተገኝተው የብዙዎችን ቀልብ መግዛት የቻለና የእንባ ነቅዕ የከፈተ ንግግር አድርገዋል፡፡ ንግግራቸው የሐገራችን ፖለቲካ ከአንድ ምዕራፍ መድረሱን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወዴት እንደምንሄድ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ሆኖም ለሦስት ዓመታት የሚሰራውን አሳጥቶት የከረመው የሐገራችን ፖለቲካ፤ ከዚህ እልባት የደረሰው፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የግል ውሳኔ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሐገራችን ፖለቲካ በአንድ አቅጣጫ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ፖለቲካችን የሚከተለው ጎዳና ጥሩም ሆነ መጥፎ፤ አቶ ኃይለ ማርያም ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ታላቅ ሰብእና ያላቸው መሆኑን ለሐገራቸውና ለዓለም ህዝብ የሚያመልክት ትልቅ ውሳኔ አድርገዋል። ከዚህ በኋላ የሚመጣው ነገር ምንም ይሁን ምንም አቶ ኃይለ ማርያም፤ ሐገራቸውን የሚወድዱ፣ ቅን እና አስተዋይ መሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግስት እና ድርጅታቸው ኢህአዴግ በታላቅ አክብሮት ሊያንቆጠቁጣቸውና ሊሸልማቸው የሚገቡ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በሥልጣን ላይ ሆነው ከሰሩት ሥራ በበለጠ፤ ሥልጣናቸውን በመልቀቅ የሰሩት ሥራ የሚበልጥ ሆኖ ታየኝ፡፡ አሁን በህዝብ ዘንድ የምናየው ስሜት ይህን ያረጋግጣል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም በጡረታ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ይልቅስ ሐገራዊ ኃላፊነት ሊሸከሙ በሚችሉበት ጥሩ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው። ለዝንባሌአቸው በተስማማ የሥራ ዘርፍ ቢመደቡ ለሐገራቸው ትልቅ ሥራ ለመሥራት የሚችሉ ናቸው፡፡ በአጭሩ አቶ ኃይለ ማርያም ትልቅ ሰው ናቸው፡፡
ሆኖም የአቶ ኃይለ ማርያም ትልቅ ሰብእና ከድርጅታቸው ኢህአዴግ ሁኔታ ጋር ተናብቦ መታየት ይኖርበታል፡፡ የኢህአዴግ ዕጣ ፋንታ ምንም ይሁን ምንም፤ በቀድሞ ጥንካሬው ላይ ይገኝ -አይገኝ፤ መሬት አርድ - አንቀጥቅጥ የሆነ እና ለሦስት ዓመታት የዘለቀን የፖለቲካ ቀውስ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በፀጥታ ኃይሉ ድጋፍ ተሻግሮም ቢሆን፤ አስቸጋሪውን የውስጥ ማዕበል ጥርሱን ነክሶ ተቋቁሞ፤ የስልጣን ሽግግር በማድረግ ከዚህ ነጥብ መድረሱ፤ ኢህአዴግ መሠረት ያለው የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ያመለክታል፡፡
በዚህ ረገድ የሚያገኘው አድናቆት በምንም ዓይነት ማስተባበያ ሊሻር የማይችል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኛ ያመጣነው ለውጥ ይላሉ፡፡ በርግጥ እነሱ በሰሩት ሥራ ኢህአዴግ መንገዳገዱ፤ የእነሱን ጥንካሬ ያመለክታል። በዚያው ልክ፤ ኢህአዴግ አፈር ልሶ ዳግም መነሳቱ የኢህአዴግን ጥንካሬ የሚያመለክት መሰለኝ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ አርጅቷል፡፡ ታዲያ በትንሳዔ እንድናም ራሱን ይቀይር ይሆን?
ኢህአዴግን የገጠመው ሁከት ለሦስት ዓመት የዘለቀ፤ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጊዜ የወሰደ፤ እንዲሁም ሰፊ የሐገሪቱን ግዛት ያካተተ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ሦስቱን ዓመታት እየተናጠ ቆይቷል፡፡ በአንድ ሳምንት እና በአንድ ወር ሁከት ከተናዱ ስርዓቶች ጋር ሲተያይ የኢህአዴግ መንግስት ጠንካራ ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ነው፡፡ አሁን ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ባይመለስም ትንፋሽ የዘራ ይመስላል፡፡ ሦስት ዓመት ታምሞ የቆየው ኢህአዴግ፤ በአቶ ኃይለ ማርያም የመልቀቅ ውሳኔ መልሶ አንሰራራ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ‹‹ኦፈ ከራዲዮን›› ሆነው ድርጅቱን ከህመሙ አነሱት፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ‹‹ኢትዮጵያ በልጆችዋ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር›› እንዳሉት፤ እኔም ‹‹አንቀጽ 29 በባለስልጣናት ታፍራና ተከብራ ለዘላም ትኑር›› እያልኩ፤ እንዳሻኝ እናገራለሁ፡፡ እኔ በእውነት አንቀጽ 29ን እወዳታለሁ፡፡ ህገ መንግስቱ በዚህ አንቀጽ፤ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል(29/1)፤ ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው (29/2)፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል (29/4)›› እያለ ለእኔም ሆነ ለአዲስ አድማስ መብት ይሰጠናል፡፡
ይህን ህገ መንግስታችንን በእጅጉ እያመሰገንኩ፤ ይህን መብት ከሚሸራርፍ ባለ ስልጣን እንዲጠብቀኝ አምላኬን እየተማጸንኩ፤ የሐሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ለውጥ ሊገታ አይገባውም የሚለውን ህገ መንግስታችንን እየታመንኩ (29/6)፤ ፖለቲካዊ አስተያየቴን አቀርባለሁ፡፡
ህገ መንግስታችን፤ የወጣቶችን ደህንነት የሚጎዳ፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም የሚነካ፣ ሰብአዊ ክብርን የሚያሳንስ ወይም ጦርነትን የሚቀሰቅስ የአደባባይ መግለጫ እንዳልሰጥ ከመከልከል በቀር ሌላ ገደብ የለብህም ብሎኛል፡፡ ስለዚህ እናገራለሁ፡፡ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 29 እወደዋለሁ የምለው ለዚህ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ ለሁላችንም መብት ሰጥቶናል፡፡ እንዳሻን መናገር እንችላለን፡፡ የህዝብ አስተያየት ወሳኝ ነው፡፡ የፖለቲካ ምሁራን የህዝብን አስተያየት በመተንተን ከኛ ይበልጣሉ እንጂ በመናገር መብት አጠቃቀም ከኛ አይበልጡም፡፡ ፖለቲካ የሁላችንም ነው፡፡ በፖለቲካ ረገድ የእኔ አስተያየት ከፖለቲካ ፕሮፌሰሩ እኩል ዋጋ አለው። የሚሰማኝ ሰው ላግኝ እንጂ በመናገር መብት ረገድ የፖለቲካ ፕሮፌሰሩና እኔ እኩል ነን፡፡
ፕሮፌሰሩ ‹‹ከነ ሙሉ ክብሩ፣ ጥቅሙና ግዴታው›› ተብሎ የተሰጣቸው አካዳሚያዊ መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ይህ የሚሰራው በትምህርት ተቋማት እንጂ በቀበሌ ስብሰባና በፕሬስ መድረክ አይደለም፡፡ በፕሬስ ጉባዔ እኩያ ነን፡፡ እርሳቸው የተሻለ ዕውቀት አላቸው፤ አስተያየታቸው ይጠቅመኛል ብዬ ቅድሚያ ልሰጣቸው እችላለሁ፡፡
ሆኖም ፖለቲካ ሙያ ብቻ አይደለም፤ ህይወትም ነው። እንደምታውቁት፤ በህግና በህክምና ዘርፎች፤ ከተቋማት ተመርቀው ከወጡ ሰዎች የተሻለ ዕውቀት ያለው ሆኖ ቢገኝም አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ በታሪክ፣ በሥነ ጽሑፍ ወዘተ መስክ እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡ በነዚህ ዘርፎች የፈቀደ ሁሉ፤ ሳያንኳኳ ሊገባ ይችላል፡፡ የማን አስተያየት ከማን ይበልጣል፡፡ ሁሉም አስተያየት እንጂ የእውነት ሞኖፖል ሊኖረው አይችልም፡፡ ‹‹ዘፈተወ ይስተይ›› ብሎ መናገር ብቻ ነው፡፡
አንድ የቆሎ ተማሪ፤ አንዲት ሴት ከመንገድ ሲሸኑ አይቶ፤ በነገር ሊወጋቸው፤ ‹‹ነቅዐ ፈልፈለ ማየ ህይወት›› አላቸው - በግዕዝ፡፡ ‹‹የሕይወት ውሃ መነጨ›› ማለቱ ነው። እርሳቸውም ባለቅኔ ኖረው፤ ‹‹ዘፈተወ ይስተይ›› ሲሉ መለሱለት፡፡ ‹‹የፈለገ ይጠጣ›› ሲሉ ነው፡፡ ‹‹ይህ አለማፈር ነው›› የሚል ሰው ይኖራል፡፡ ግን የሐሳብ ሽንት በአደባባይ መሽናት ይቻላል፡፡ ዕድሜ ለህገ መንግስቱ፤ በሐሳብ አደባባይ ‹‹መሽናት ክልክል ነው›› ብሎ መጻፍ ወይም በፖሊስ ማስፈራራት አይቻልም፡፡ ሐሳቡን የማይወደው ሰው አፍንጫውን ይዞ ማለፍ እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ‹‹ይህን አካባቢ አበላሹት›› እያሉ ማማረርም ይቻላል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲሁ ነው፡፡ ሁሉም ያለውን ገበያ ይዞ ሊወጣ ይችላል፡፡ ተፈላጊነቱን ገበያው ይነግረዋል፡፡ እንደ ቆሎ ተማሪው የሚለክፍ ሲመጣ፤ ‹‹ዘፈተወ ይስተይ›› ብሎ መመለስ ነው፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል!! እመኛለሁ!!

Read 2083 times Last modified on Saturday, 14 April 2018 15:43