Saturday, 07 April 2018 00:00

ኢህአዴግ አቅቶታል፤ እስቲ እኛ ቤቱን እናጽዳለት!

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(1 Vote)


         “--የኢህአዴግ አመራሮች ‘ፍቅር ያስፈልገናል’ የሚሉትን ጓዶቻቸውን በመከተል፣ኢትዮጵያዊነትን ልባቸው ውስጥ ፈልገው
ለማግኘት መትጋት ይገባቸዋል፤ ሲያገኟትም ጓዶቻቸው እንዳቀፏት አገራቸውን በልባቸው ይቀፏት፤ አገር በልብ ነውና የሚታቀፍ!
ኢትጵያዊነት፥ አንድነትና ፍቅር ሰላምን ያሰፍናል፤ ፈጣሪንም ያስደስታል። አዎን! ፍቅር ያስፈልገናል።--»
 

    (የመጨረሻ ክፍል)
4.1 የአበዳሪ ቅኝ ገዢዎችን
“ልማት” ከማስቀጠል ተነስና አገሬን በል!
ኢህአዴግ ድኽነትን ለማጥፋት የመረጠው መንገድ ፀረ ድኻ ሥርዓት መገንባት መሆኑ አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ፖሊሲው ኢህአዴግ መርጦት ሳይሆን የግዱን የተቀበለው መሆኑ ደግሞ በጣም ያሳዝናል። ከላይ እንደተጠቀሰው፤ የፖሊሲው እውነተኛ ባለቤቶች ፈረንጆች ሲሆኑ ኢህአዴግ እንደ አንድ ሰው ተስማምቶ የቀረበለትን በሚያጸድቀው ፓርላማው፥ እንደ አንድ ሰው በተዋረድ በሚሰራው መዋቅሩ የፈለጉትን ሲፈጽምላቸው ኖሯል። በተለይ በ2012 እ.ኤ.አ የኢትዮጵያን የዕጽዋት ዘር ሐብት እንዳሻቸው ለመመዝበርና ገበሬውንም ለየዕጽዋት ዘርና ማዳበሪያ ደንበኛ ለማድረግ ያስቻሉ ሕጎችን አስረቅቀው አጸድቀዋል። አንድ የገበሬ ወገን ነኝ የሚል ድርጅት፣ የመንግሥት ሥልጣን በያዘበት አገር፣ ይህ ሊደረግ አይገባም ነበር። ሆኗል። አሁን ለውጥ ማምጣት አለብን፤ በማዘዝ ሳይሆን በማሳመን መምራት አለብን የሚለው አዲሱ አመራርና በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ይህን ትልቅ ጥፋት ለማስወገድ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው ሊረዳ ይገባል።
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለበት የወቅቱ ዐቢይ ፈተና፣ ከሁሉ በፊት የአገርን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን አመንጭቶ ለመተግበር የሚችለው የሉዓላዊ አገር መንግሥትነት መለያ ባህሪ የሆነውን የአገር ፖሊሲ አስተዳደር ስልጣን ከአበዳሪ/አጋር ድርጅቶች ትዕዛዞችና ጫናዎች ነጻ አውጥቶ እጅ በማስገባት ነው። የአገርን ዕድገት አቅጣጫ የሚወስኑ ቁልፍ ዕቅዶች በባዕዳን ቁጥጥር፥ ትዕዛዝና ጫና ሥር እስከሆኑ ድረስ ለሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ገንዘብ ልመድብ ቢሉ ቅድሚያ ለብድር ክፍያ በሚል ይከለከላል፤ መንግሥት ሊሠራው የሚገባ ሥራ ሁሉ፤ ‘እዚህ ውስጥማ መንግሥት መግባት የለበትም’ ይባላል፤ ለምሳሌ በትምሕርት ዘርፍ መዋቅር ላስፋ ቢሉ ‘መንግሥትማ ሥራው ደመወዝ መክፈል ብቻ ነው መሆን ያለበት’ ይባላል፤ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ [አሁን ለታ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከውጭ በሚገባ ብረትና አሉሚንየም ላይ 25% ታሪፍ እንደጣሉት] ወደ አገር የሚገባ ሸቀጥ ላይ ገደብ እንዳይጣል፣ ‘የነጻ ገበያ ሥርዓቱን ማወክ’ በሚል ያገር የኢኮኖሚ በር ክፍቱን ያድራል፤ [ሌላው ቤቱ ይቁጠረው] በዚህ መልኩ መንግሥት በገዛ አገሩ የመሪነትን ስም ብቻ ከጠመንጃ ጋር ተሸክሞ ችግራቸውን እያወቀ በመፍትሔ እጦት በሚጮኹት ዜጎቹ ላይ ለመተኮስ ከተገደደ ቢያንስ መሪ አለመሆኑን አይክድም።
በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ያለበት ሁኔታ ከዚህ ምን ያህል እንደሚለይ እሱ ባያጣውም የሕዝብን ችግር እፈታለሁ ብሎ ፎክሮ ሲያበቃ መሬት ላይ ጠብ የሚል ነገር የማይታይበት ምክንያቱ ካለበት የስልጣን ውሱንነት ጋር መያያዙ አይቀርም። ከዚህ አንጻር የችግሩን ምንጭና መፍትሄውን ሌላ ሌላ ቦታ ከማፈላለግ፥ ችግሩን በደፈናውም የአመራር ችግር ነው ብሎ ለማለፍ ከመሞከር፤ የችግሩንም መፍትሔ አንዴ በስልጣን ላይ ያለንን አመለካከት ማስተካከል፣ ሌላ ጊዜ ለውጥ ለማምጣት የቆረጡ ታጋዮችን ማሰባሰብ’ ከማለት ይልቅ ኢህአዴግ ራሱ ችግር ብሎ የለየውን ነገር ለመፍታት ያፈለቀውን ሐሳብ፥ ያመነጨውን መፍትሄ ሕግ አድርጎ ለማውጣትና ገንዘብ መድቦ ለመተግበር ያለው ዐቅም ምን ያህል እንደሆነ መመርመር ነው። የማይችል ከሆነና ችግሩን ችግር አይደለም፥ ወይም መፍትሄውን መፍትሄ አይደለም የሚል ከልካይ ካለበት ባለስልጣኑ ከልካዩ ነው። ከልካይ ከሌለበት ግን መፍትሔ አይቸግርም።
ሆኖም ከልካይ እንዳለበት፥ ከልካዮቹም የገንዘብ ተቋማቱ መሆናቸው ይታወቃል። ቢሆንም ካላቸው የገንዘብ ዓቅም፥ በተለይም በነሱ አመራር በተንቦረቀቀው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን ላይ ካላቸው ቁልፍ ሚና አንጻር የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን ከባዕዳኑ መልሶ መውሰድ ቀላል ሊሆን እንደማይችል የታወቀ በመሆኑ በማስተዋል፥ በጥንቃቄ የሚተገብረውን መላ መምታት ነው። በዚያ ላይ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን እነሱ በቀየሱልን ፖሊሲ አለቅጥ ቢሰፋም ወይ አበዳሪ ወይ አበዳሪ [ተበዳሪ አላልኩም] እያሉ አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን በዕቅድና በትጋት እያፈላለጉ ለጊዜው ከነሱ የሚገኘው ብድር የሚደፍነው ቀዳዳ አያጣም [የድኻ ቀብራራ!]። ታዲያ በዚህ ሂደት ሁሉ ከነዚህ ድርጅቶች ጫና መላቀቅን እንደ ግብ ይዞ የሚሠራ አመራር ያስፈልጋል። እስከዚያውም ድረስ በተቻለ መጠን ተቋማቱ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የአጭርም ሆነ የረዥም ጊዜ ጥቅም ያስገኛሉ ከሚል የዋህ ድምዳሜ መጠንቀቅ ያሻል። እነሱ ኢትዮጵያን ሸቀጣቸውን ለሚያራግፉበት ሰፊ ገበያዋ፥ ለርካሽ ጥሬ ዕቃዋና ‘የሰው ኃይሏ’ ለሚፈልጓት/ላገኟትም አገሮችና ኩባንያዎች ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚያመቻቹ መንገድ ጠራጊዎች ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ ሥራቸው አይደለም። ስለ ኢትዮጵያና ልጆቿ ማሰብ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አመራር ነው። የፖሊሲ አስተዳደሩን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ለመተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር የራሱ ግዴታና ኃላፊነት ነው። እስካሁን ድረስ የቅርብ ጊዜውን የብር የምንዛሪ ዋጋ መቀነስን ጨምሮ በዐበይት የአገር ጉዳዮች ላይ ያለ መረጃ ሲወራ ከሚሰሙት ተነስተው እየወሰኑ፥ ሥራውን በገንዘብ ተቋማቱና አጋር በተባሉ ድርጅቶች እጅ የመተዉን [ወይም እንደተተወ እንዲቀጥል የመፍቀዱን] ጥፋት በማስተዋል ወደፊት በሚደረገው ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግና የቁጥጥር ተቋሞችንም መዘርጋት ለመስራት ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የተቋማቱን እምነቶች የተፈጥሮ ሕግ አስመስሎ ማቅረብ የሚችል ዐቅም ያላቸው እሳት የላሱ ባለሙያዎች እንዳሏቸው ከቶ መዘንጋት አይገባም። ይሁንና አማራጭ የለንም የሚል የቀቢጸ ተስፋ ስሜትና አተያይ የመፍትሔ ምንጮችን በማድረቅ ተወዳዳሪ የሌለው መርዝ በመሆኑ አመራሩ ለጊዜው የሚለውን ባጣበትና በጨነቀው ሰዓትም ጭምር ሊታገለው ይገባል።
አገር ውስጥ የማይገኙና እዚህ ሊመረቱ የማይችሉ አንዳንድ አስፈላጊ ዕቃዎችን መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ምርቶችን መሸጥ ማስፈለጉ ባይካድም እንደ አገር ነጋዴ ለመሆን እንገደዳለን ማለት አይደለም። እንዲያውም ነጋዴ አገር እንድንሆን ግድ የሚል ምንም ምክንያት አለመኖሩን ከቶ መዘንጋት አይገባም። ይህ ማለት ዜጎች በዓለም ገበያ ውስጥ አይሳተፉም፥ ለምሳሌ ኢንተርኔት የሚፈጥረውን ፈርጀ ብዙ ዕድል ተጠቅመው እንደ ሰዉ ሊነግዱ አይችሉም ማለት አይደለም። ይችላሉ። እንዲያውም የፖለቲካ ግብ ሳያስቀምጡ ማደራጀትና ማገዝ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም እንደ አገር በሌለ ምንዛሪ ከዓለም አገራት ሁሉ ሸቀጥ የምናስመጣበት ምክንያት የለም፤ ቢኖርም እነሱን መጥቀም ብቻ ነው። ክፋት ላይኖረው ይችላል። ሆኖም ፍላጎታችን አይደለም። አበዳሪ የተሰኙ ድርጅቶች በሰው ስጥ እንደሚጋብዘው ዶሮ ሆነውብን፤ ጓሯችንም የሞኝ ጓሮ በመሆኑ ነው።  
ከዚህ አንጻር የኢህአዴግ አመራር ባጠቃላይ፥ በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር “የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ማስቀጠል” ወዘተ ማለቱን ትቶ በቆራጥነት እስካሁን ሲተገበሩ ከነበሩት “የኢህአዴግ” ከተሰኙ ምዕራባውያን ፖሊሲዎች ራሱን ማራቅና በኢትዮጵያዊ ወገንተኝነቱ ልክ፣ ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን፥ በረዥም ጊዜም ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የሚታደጉ አማራጮችን ለመቀየስ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘውን የኢትዮጵያውያን ኃይል ማስተባበር ያስፈልጋል፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አመራር የሚቀርቡለትን ሀሳቦች ሁሉ «ለሕዝቤ ምን ይፈይድለታል? ምንስ ጉዳት ያመጣበታል? ምንስ አማራጮች አሉት?» የሚሉትን ጥያቄዎች በተለያዩና ተቃራኒ አመለካከት ባላቸው አማካሪዎች ጭምር እየታገዘ ለመምረጥና ለመተግበር አብዝቶ ማሰብና መጠንቀቅ ግድ ይለዋል።
የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል ይገባል የሚለው ወገንም ለአገር የሚያስበውን ቀና ነገር የፖሊሲ አስተዳደሩን ስልጣን የያዙት የገንዘብ ተቋሞች ለአገሩ ከሚያስቡትና አስበውም ከሚፈጽሙት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከሚያራምደው የልማት ማስቀጠል ዓላማ ለያይቶ መመልከት ያስፈልገዋል። ደግሞም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ለመተንተን ሲነሳ ኢህአዴግ ያልነገረንና የህዝቡን ችግር ለመፍታት እንዳይችል ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት የአገራችንን ፖሊሲዎች ይዘትና አፈጻጸም የመወሰን ስልጣኑ በአበዳሪ የገንዘብ ተቋሞች ቁጥጥር ሥር የሚገኝ የመሆኑን እውነት ማስተዋል ማየት እንደሚያስፈልገው አያጣውም።
የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን ከባዕዳን አለቆቹ ተረክቦ እጁ ሳያስገባ ኢህአዴግ መቼም ቢሆን ምንም ዓይነት የህዝብ ጥያቄ ሊመልስ አይችልም፤ ጊዜ በገፋ ቁጥር ደግሞ ብድሩና ጥገኝነቱ ይጨምራል። በዚያው ልክ የገንዘብ ተቋማቱ ጫናና ትዕዛዝ ያይላል። ዛሬ የማያዙባቸው ዘርፎች ካሉ [ምናልባት የባንክና የቴሌኮም] አድብተው ጊዜ እየተጠባበቁ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ኢህአዴግሳ? ምን እያሰላ ነው? ዕድገቱን ለማስቀጠል? አለቆቹ በሳቅ እንዳይሞቱበት ይጠንቀቅ! ባዕዳኑ የሚቀይሱት መንገድም የህዝባችንን ችግር የሚፈታ ሳይሆን የየህዝባቸውንና የየወገናቸውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የሚቀመር በመሆኑ ያልፈጠረበትን፥ ደንታ የማይሰጠውን የኢትዮጵያውያንን ችግር እንዲፈታ፥ ፍላጎታቸውንም እንዲያሟላ አይጠበቅበትም። የሚያሳዝነው ገዢዎቻችን አስጨንቀው የጫኑብን ጠማማ ፖሊሲዎች ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ፣ «ችግሩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው» እያሉ መሪዎቹ ላይ መደፍደፋቸው ሳያንስ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር የሚበጁ ማሻሻያ ካላቀረብን ማለት የታወቁበት ሙያ መሆኑ ነው። በዚያ ላይ የኢህአዴጎች ኑዛዜ ሲጨመር፣ የሚያቀርቡላችሁን የማሻሻያ ዓይነት እያሰቡ፣ አቤት የሚስቁት ሳቅ! ስለሆነም የአበዳሪ ቅኝ ገዢዎችን “ልማት” ከማስቀጠል ተነስና አገሬን በል!

4.2 ኢህአዴግ የመለወጥ ዕድል አግኝቷል፤ የመለወጥ ግዴታም አለበት
ከግዴታው ብንጀምር አሁን ያለንበት አጠቃላይ ሁኔታዎች ኢህአዴግ በመረጣቸው ውሳኔዎች አማካይነት የተፈጠሩ ናቸው። ውሳኔዎቹ በማድረግም ባለማድረግም የሚገለጹ ነበሩ። የባዕዳንን የፖሊሲ ጫና መቋቋም ነበረበት፤ አጥፊ ውሳኔዎችን በግድ መተግበር አልነበረበትም። አሁን ያበላሸውን ለማስተካከል መጣጣር አለበት፤ ኢህአዴግ አገራችንን ከቅኝ ገዢዎች መዳፍ ውስጥ እንዳስገባት ራሱ ፈልቅቆ ለማውጣት መታገል ይኖርበታል። የተፈጠረለት እድል አዲሱ አመራር ያመጣው አዲስ አገራዊ መንፈስ ነው። ይህን ተገንዝቦ፥ በመካከሉ ነፋስ እንዳይገባ አድርጎ፣ አንድ ላይ ቆርጦ ከተነሳ ብዙ ላይቸግረው ይችላል። ለዚህም በጥንቃቄ የታቀደ የእምቢታና የድርድር አቅጣጫ መቀየስ መቻል አለበት። ኢህአዴግ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ አዲሱ አመራር ይዞት የመጣውን የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መንፈስ ቢከተል፣ ራሱን ከተዘፈቀበት የርዕዮተ ዓለም ቀውስ እንዲያወጣና እስከ ዛሬ አልያዝልህ ብሎት የኖረውን አገራዊ ዓላማ እንዲጨብጥ ያስችለዋል።
ከሁሉ አስቀድሞ እናስቀጥለዋለን የሚለውን ውርስ/ውጥን ምንነት፥ የተባለውን ‘የሕዳሴ ጉዞ’ የሚመሩት ፖሊሲዎች ምንነትና የፖሊሲዎቹን እውነተኛ ባለቤት በሚገባ ተገንዝቦ፥ አንጋች ከማሰማራትና የሕዝብ ገንዘብ ከመዝረፍ የተሻለ ሥራ ሊያሰራ የሚችል ዕቅድ ነድፎ በመተግበር የሚገለጽ፥ የማስተዳደር ሥራ የሚያሰራ ስልጣን በማን እጅ ተይዞ እንደሚገኝ ተረድቶ፣ መልሶ እጅ ማስገባት መቻል አለበት። ኢህአዴግ ሕዝብን የሚጠቅም ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል ስልጣን በእጁ መኖሩን ሳያረጋግጥ፥ ይልቁንም ሌሎች የጫኑበትን ተቀብሎ እያስፈጸመ መቼም ሕዝባዊ ሊሆን አይችልም። በፈረንጆች አድናቆትና በዜና አውታሮቻቸው ልፈፋ ላይ የተንጠላጠለ ሆያ ሆዬውንና የተያዘው መንገድ፣ እውነተኛ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት የመሪ ሥራ ለማከናወን ቁልፍ ነው። እውቀት ያስፈልጋል። ሆኖም ሁል-አውቃ መኮን የለበትም። ጥርት ያለ ዓላማ ተይዞ፥ የአገር ጥቅም የሚገኝ የሚታጣበት መንገዱን ለይቶ፥ ወዳጅ ጠላቱንም ጠንቅቆ አውቆ፥ አስፈላጊውንም ሙያ ሁሉ ጠንቅቆ ታጥቆ የተነሳ በማንም ማስፈራሪያም ሆነ ሽንገላ ከመንገዱ አይወጣም። ከባዕዳን ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ሁሉ መብቱንና ጥቅሙን ስለሚያውቅ፥ ማንም — ኃያልም ይሁን ደካማ — አገርህን ላስተዳድርልህ ለማለት እንዲደፍር አይፈቅድም። ሲደራደርም ሰጥቶ የሚቀበለውን ስለሚያውቅ የሚያዋጣው ስምምነት ካልሆነ በቀር ማንም ምንን ቢል በጅ አይልም። ደግሞም እውቀትና ሙያውን የታጠቀ በመሆኑ በቀላሉ አይረታም።
ይህንን የኛው አክሊሉ ሀብተወልድ በጊዜው አድርጎታል፤ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመቀላቀል ዓላማውን ይዞ ዓለምን ዞሮ ድጋፍ በማሰባሰብ ያሰበውን ፈጽሟል። ዛሬ ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ልትሆን የምትችል አገር ኢራን ናት። የኒኩሊየር ኃይል የማመንጨት ዓላማዋን ይዛ የጀመረችውን ጥረት ወደ ጦር መሣሪያ እንዳትለውጠው ስጋት የተሰማቸው ኃያላን አገሮች ከኢራን ጋር ንግግር ጀመሩ። የኒኩሊየር ፕሮግራሙ የእውነት ለሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚውል መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ለመቅረጽ አሜሪካ፥ እንግሊዝ፥፥ ፈረንሳይ፥ ሩሲያ፥ ቻይናና ጀርመን አንድ ላይ ሆነው ድርድር ገጠሟት። እስራኤል በበኩልዋ፤ ድርድሩ እንዲከሽፍ ለማድረግ ትጣጣር ነበር። ሆኖም የኢራን ዲፕሎማቶች ድርድሩን በተደራዳሪ ወገኖችና ለድርድር በቀረበው ጉዳይ ብቻ እንዲወሰንና ወሰኑን ሳያልፍ እንዲዘልቅ በማድረግ ከውስጥና ከውጭ በሚሰነዘር ጫና ሳይረበሹ፣ ትኩረታቸውንም ከተነሱበት ያገራቸው ዓላማ ለአፍታም ሳይነቅሉ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ ችለዋል። ዕውቀቱ፥ ዝግጅቱ ነበራቸው። የሚፈልጉትን ያውቁ ነበር። የሚሆናቸውን ባዕዳን እንዲወስኑላቸው አልፈቀዱም። ይልቁንም በዚህ ዓለም ለመኖር የማንንም ፈቃድ መጠየቅ ወይም የማንንም ይሁንታ ማግኘት እንደማያሻቸው ነጋሪ የሚፈልጉ አልነበሩም። አይደሉምም። ከምዕራባውያን ሸር ለማምለጥ የሚፈልግ ሁሉ በኒኩሊየር ድርድሩና በዚያ ዙርያ የኢራንን አካሄድ ልብ ሊለው ይገባል። የኢራን ስኬት ጥቅሙን ለማስከበር ለሚፈልግ አገር ሁሉ ልምድ ከወኔ የሚያሰንቅ ሲሆን የስኬቱን ታላቅነት ማስታወስም በቂ ጥንቃቄና ዝግጅት ለማድረግ ወሳኝ ነው። [እኛ ዘንድ ያገር ሚስጥር የሚባል ነገር መኖሩ ተረሳ ይሆን? የባቄላ ወፍጮ ሁላ! የኛማ ፓርላማ ፈረንጆች፤ ርዳታ/ብድር የተባለ የመግቢያ ዋጋ ከፍለው ገብተው ይመለከቱታል። ምንኛ ይስቁ!]
ስለሆነም ቅድሚያ የራሳችሁ የሆነ አገርና አገራዊ/ሕዝባዊ ፖሊሲ/ዕቅድ እንደሌላችሁ ማመን፥ ከዚያም መቅረጽ ይቻላችሁ እንደሆነ፥ እንቅረጽ ስትሉ አለቆቻችሁ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠንቅቆ በማወቅ መከላከያ ማበጀት ያስፈልጋል። ኢህአዴግ አንዳች  ዐቢይ አገራዊ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ከሥራ ፈትነት ብቻ ሊመጣ በሚችል መጠራጠር/አለመተማመን ተበጣብጦ አይበጠብጠንም ነበር። በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ሊከናወን የሚችልና የሚገባው አያሌ ሥራ ባለበት ባሁኑ ወቅት ግንኙነታችን ሻከረ ብሎ ተሸብሮ ማሸበር ሳያንስ ሥራ ሁሉ ተትቶ ስብሰባ ከተገባ በኋላ ደግሞ ሕዝብን ዘርፈናል፤ ሆኖም ላለመዝረፍ ተስማምተናል፤ ሕዝብ ከሕዝብ አጋጭተናል፤ ላለማጋጨት ተስማምተናል፤ ጭራሽ ድርጅታችን ስህተቱን ማመኑ ትልቁ ጸጋው ነው. . . ቀልድ ነው ሥራ ነው?
እንደ መንግስት መብትን አውቆ ለመጠየቅና ለመደራደር አቅም መገንባት ያስፈልጋል። በመቀጠል የአገራችንን የፖሊሲ አስተዳደር ሥራውን የተቆጣጠሩት፥ ‘አማካሪ’ ድርጅቶች ድኻ የሚሏትን ሀብታም አገር ለመዝረፍ የተሰማሩ ጩልሌዎች መሆናቸውን ሳይረሱ ማንነታቸውን ለራሳቸው ማስታወሱ ለጉራቸው መድኃኒት ሲሆን፤ በአገራችን ጉዳይ ዋናዎቹ ባለ ጉዳዮቹ ባለ አገሮቹና ባለመብቶቹ እኛው መሆናችንን እና በገዛ አገራችን ላይ የሚያራምዱት ፖሊሲ እንኳን ስህተት ሆኖ ትክክልም ቢሆን የመቀበል ግዴታ የሌለብን መሆኑን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው። በዚህ ጊዜ እነሱም በበኩላቸው፣ የብሔር ልዩነትን እያነሱ አንድነት የላችሁም ለማለት መከጀላቸው፥ ከመካከላችንም አንዱን አይዞህ እያሉ ሌላውን እያጣጣሉ ሊያጋጩን መቃጣታቸው አይቀር ይሆናል። ለዚህ መፍትሄው ከነሱ ጋር ክርክር መግጠም ሳይሆን የእውነት አንድ ሆኖ መገኘት ቢሆንም አፍ ለማስያዝ የሚሰነዘር ደህና ነገር ቢገኝም አይከፋም። ከዚህ ጎን ለጎን ግን የነሱን የድጋፍ ቃል ሰምቶ የገዛ ወገኑ ላይ የሚነሳ እንዳይኖር በጥንቃቄ መጠበቅ ግድ ነው።
በሌላ በኩል፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአገር ወዳድነታቸውና ለሕዝብ ባላቸው ተቆርቋሪነት ምክንያት የገንዘብ ተቋሞቹ በፍቅር ዓይን ሊመለከቷቸው እንደማይችሉና ይልቁንም ድጋፋቸውንም ሊነፍጓቸው እንደሚችሉ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም። በመሆኑም ከነሱ ጋር በሚደረግ ግንኙነት ሁሉ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ፥ ከነሱ በኩል መረጃ መጣ ሲባልም በተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ መመዘን ያስፈልጋል። በተጨማሪ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ላይ ሙሉ መብት ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አሃዳዊ አደረጃጀት በተዘረጋው አገር አቀፍ መዋቅር አማካይነት የፈለጉትን ትዕዛዝ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመፈጸም የሚያስችላቸው በመሆኑ አሁን ያለውን አሐዳዊ አደረጃጀት ከነዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነቱ እንዳለ እንዲቆይ ሊፈልጉ እንደሚችሉ አለመዘንጋት ነው። ሆኖም ክልላዊ ስልጣን ተጠቅሞ በክልል የሚተገበሩትን ሥራዎች በተመረጡ ባለሙያዎች ድጋፍ በቂ ግንዛቤ እየወሰዱ በትንሽ በትንሹ ለማስተካከል መሥራትና በሂደቱም የፖሊሲዎቹን ይዘት በተግባር መዝኖ ለመለወጥ መሥራት ግድ ነው። በሌላ በኩል፤የገንዘብ ድርጅቶቹ ዐቅም ከውጭ ምንዛሪና ከብድር ፍላጎታችን ጋር የተያያዘ መሆኑን በማስታወስ የነሱን ጊዜያዊ አድራጊ ፈጣሪነት ለመመከት የሚያስችል አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ለማዘጋጀት መጣጣርና ይህንንም በጥብቅ ምስጢር ይዞ ማራመድ ግድ ነው።
ማሳረጊያ፦ የአንድ
ተራ ዜጋ ቁጭት-ቀመስ ምክሮች
የገዢው ፓርቲ የበላዮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንን በፍጥነት የሚጨምሩ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሲመክሩና ሲያስገድዱን ቆይተዋል። አገር ውስጥ የሚፈለጉ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎቻችንን እንድንሸጥ ፥ ገበያችንን ክፍት እንድናደርግና ሸቀጣቸውን በገፍ እንድንገዛ ግድ ሲሉን ኖረዋል። ያኔም ሆነ አሁን ብድር ስንጠይቅ የሚያዙንን እንድንቀበል ማስጨነቃቸው አልቀረም። ወደፊትም ልብ ገዝተን፥ የአገር ወዳድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን ዐቅም አሰባስበን መላ ካልመታን በቀር አይለቁንም። ከውጭ የማናስመጣው የዕቃ ዓይነትና ከማናስመጣበት አገር የለም። አንዳንዱ ዕቃ እዚህ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን በተለይ የውጩን ዕቃ ለመተካት ተብሎ በብድር ጭምር በተገነቡት አዳዲስ ፋብሪካዎች የሚመረት ሆኖ ሳለ ያው ዕቃ ከውጭ እንዲገባ ይደረጋል። ለምሳሌ በአገራችን አራት ክልሎች የተገነቡት የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ማዳበርያ እያለ፣ ከውጭ በዶላር ገዝተን እያስመጣን ነው፤ምክንያቱም ያገር ውስጡን እንከን አናጣበትም።
በዓመት 16 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዕቃ ተበድረን የምንገዛ ደህና የፈረንጅ ሸቀጥ ማራገፊያ  መሆናችን ታውቋል፤ ሃብታችንን የማናውቅ መሆናችንንም ሁሉም አውቆታል፤ የገዛ ዜጎቻችንን ጉልበት አሳልፈን ለበዝባዥ እንደምንሰጥ ታውቋል። ጭራሽ የዓለም አቀፉ የሰራተኛ ድርጅት ኃላፊዎች እዚህ ድረስ መጥተው፤ “ኢንቨስተሩ ዜጎቻችንን ሲቀጥር የሚከፍለው ደመወዝ ለኑሮ የሚበቃ መሆኑን ማረጋገጥ አለባችሁ” እስኪሉን ድረስ የዜጎቻችንን ጉዳይ ረስተነዋል። ግዴለም። ልዩ የፖሊሲ ትኩረትና የሚፈልጉት ከውጭ የምናስመጣቸው ዕቃዎች የሚፈጥሩብን ተጨማሪ ፍላጎት የሚመለከት ነው። ተገንብተው ለማያልቁት ግድቦች የሚፈለገውን ትተን፣ በተለይ እንዳሸን ለፈሉት ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልገን ላምባና መለዋወጫ ዕቃ ነው። እስከ 1996/7 ዓ.ም ከ230-280 ሺህ የነበረው አጠቃላይ የኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ዛሬ 850 ሺህ ደርሷል። በአስራ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ520 ሺ መኪኖች በላይ አስገብተናል። ሀብት መሆኑ እውነት ቢሆንም ይሄ ሁሉ እንግዲህ ነዳጅ ሳይጠጣ፥ ጎማ ሳይጫማ፥ የተጎዳ አካሉ ሳይለወጥለት አይነቃነቅም። አሁንም እየገዛን ነው፤ ያው በብድር። እንግዲህ በምስራቁ ያገራችን ክፍል አለ የሚባለው ነዳጅ የእውነት ካለ፣ ለዛሬ ካልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው? ደህና ወዳጅና ሸሪክ ፈልጎ ለማውጣት መጣጣር ግድ ነው። ከዚያ ጎን ለጎን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች እንዲገቡ ማበረታታት፥ መኪና እንገጣጥም የሚሉት ያገር ውስጥ ድርጅቶችም እዚያ ላይ እንዲሰማሩ መጠቆምና ማገዝ፥ እዚህ መጥተው መገጣጠም የሚፈልጉ ትላልቅ ኩባንያዎች የሚፈልጉትን አጥንቶ ማሟላት፥ በመስኩ የሚሰማሩ ልጆችን አሰልጥኖ ማዘጋጀት፥ ለዚህም ልዩ የቴክኖሎጂ ትምሕርት ቤቶችን መክፈት [ጌቶች ከፈቀዱ፤ ደግሞ ለመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ፈረንጁን ጥሩት አሉ!] ከዚያም ጎን ለጎን በላምባ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር መቻሉ የታወቀ ስለሆነ የኛ ሰዎች እዚያ ላይ እንዲሰማሩ ማበረታታት ያስፈልጋል።
አሁን ይህን ሁሉ ያተትኩበትን ምክንያት ላስቀምጥ። በዚሁ በውጭ ምንዛሪ ችግራችን ምክንያት መንግሥት በቅርቡ ብሔራዊ የትንባሆ ሞኖፖል ድርጅት ውስጥ የነበረውን ድርሻ ሙሉ በሙሉ ለጃፓኖች ለመሸጥ መገደዱን ሰምተናል። ሌላም እኛ ሳንሰማው የሸጠውና የፈቀደው ሳይኖር አይቀርም። አበዳሪዎቻችን ግን አሁንም ሌላ አምጡ ማለታቸው፥ ያገርና የሕዝብ ንብረት ስጡን ማለታቸው አይቀርም። ጨካኞች ናቸው፤ ግሪክን ደሴቶቿን ለመሸጥ እስክትገደድ አድርሰዋታል። ያገር ጥቅም የሚጎዱ ጥያቄዎቻቸውን አንቀበልም ማለትና የሚመጣውንም ጫና ለመቋቋም የሚቻለው መንግሥት ሕዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ ሲችል ብቻ ነው። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ እነዚያው ምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች በፍርደ ገምድልነት የጣሉብንን የጦር መሣርያ ማዕቀብና በወቅቱ ያጋጠመንን የእህል እጥረት ተቋቁመን ለማለፍ የቻልነው ከእግዚአብሔር ጋር በኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት ስሜት በተፈጠረው ኢትዮጵያዊ አቅም ነበር። ስለሆነም አንድነትንና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ለማጠናከር፥ እውነተኛ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርም የምር መስራት ያስፈልጋል።
ዛሬ በኢህአዴግ አመራር ውስጥ የተነሳው የኢትዮጵያዊነትና የፍቅር አጀንዳ ቢተገበር፣ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር፣ ከውጭም ከውስጥም በማስተባበር አንድ ላይ እንዲቆሙ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያን በማለታችን ምዕራባውያኑ የገዢዎቻችን አለቆች ያስለመዱንን ብድር ቢከለክሉን፥ የቀራችሁ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከአንድ ወር ተኩል በላይ አያቆይም ቢሉን፥ በድንቁርና የጀመርነውን የስንዴ ሸመታ ለመገብየትም ምጽዋቱን ቢከለክሉን፤ ባጠቃላይ ከኤርትራ ጋር ጦርነት በገጠምን ጊዜ እንዳደረጉት አንቀው ሊያሽመደምዱን ቢፈልጉ፣ ሕዝብና መንግሥት አንድ ከሆነ ሁሉንም ለመሸከም የሚያስችል አቅሙና መላው አይጠፋም። ያኔ መንግሥትን ለመርዳት በአንድነት መንፈስ የተረባረቡት ውጭ ኗሪ ኢትዮጵያዊያንን ዐቅም ኢህአዴግ ያውቀዋል፤ ከጎኑ ቢቆሙ አይጠላም፤ ታዲያ ስለ አንድነት፥ ስለ ኢትዮጵያ የሚያሰሙትን ጩኸት መስማትና በጎ ምላሽ ለመስጠትም የእውነት መትጋት ግድ ይላል።
ከዚህ ጎን ለጎን ቃል በተገባው መሠረት፤ ጥፋትን በሥራ ለመካስ መጣጣር ግድ ነው። ከግምገማው በኋላ በተሰጠው መግለጫ፤ ለተሠራው ጥፋት ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው፣ አመራሩ ህዝቡን በሥራ ለመካስ እንደሚሰራ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። የእውነት ሕዝብን ለመካስ ፍላጎቱና ማስተዋሉ፥ ወኔውም ካላቸው ፀረ ድኻውን ፖሊሲ ለማሻሻል መታገል ነው። በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቂት እርምጃዎችን ባስቸኳይ መውሰድ አይከፋም። አንደኛ ሞልቶ በተረፈ መሬትና ውሃ፣ ለአገር የሚበቃ እህል አገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርብበት መንገድ በመቀየስ፣ ህዝቡ በልቶ ተመስገን እንዲል አድርጉ፤የከተሜውን የቤትና የትራንስፖርት ችግር ባስቸኳይ መፍታት፤ሰው መቸም ቢሆን ባለው አቅም መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይታወቃል። በተለይ በአዲስ አበባ ያለውን የቤት ችግር ብታውቁትም በተቻለ ፍጥነት ለመገንባት ከመድከም ሰበብ ፍለጋ መባከናችሁ ሳያንስ የኪራዩን ሁኔታ ተመልክታችሁ እንደ መሪ መፍትሔ እንደ ማበጀት ትታችሁታል። ‘ይጠላናል’ የምትሉትን ከተሜ፣በዚህ ሲያማርር ይበለው እያላችሁ ችግሩን በደላላ ላይ ታላክካላችሁ። [ውይ ሞት ይርሳኝ፤ ከልካዮቹን የገንዘብ ተቋሞች እርስት!] በገበያዋ ነጻነት ዓለም ያወቃት ዱባይ እንኳ በኪራይ ላይ በዓመት ከ15% በላይ መጨመር አይቻልም ስትል ደንግጋለች፤ እናንተ ግን አከራይ የተመነውን ዋጋ አንሷል ትላላችሁ [ሕዝባዊነት!]
የታክሲው ችግር ባይገባችሁም አላጣችሁትም። ከዚያ መከረኛ ምርጫ 97 በኋላ የጠመዳችኋቸውን ባለ ታክሲዎች ለመቆጣጠርና ለመበቀል የጀመራችሁት የታፔላ ምደባ፣ በየወሩ ከታፔላ መቀየሪያ የሚሰበሰበው ብር ጣማችሁ መሰል ቀጥላችሁበታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ተሳፋሪ የሚጠብቅ ታክሲና ታክሲ የሚጠብቅ ሰው በአንድ ጎዳና ላይ ማዶ ለማዶ ቆሞ ሲተያይላችሁ ይውላል። ይኸውም መፍትሔው የግድ የመኪኖች ቁጥር መጨመር ብቻ አለመሆኑን ለመጠቆም ነው። [በርግጥ ስንጠብቅ ውለን ታክሲ ስናገኝ፣ ሎተሪ የደረሰን ያህል እየፈገግን የሄድንበት ጊዜ መኖሩ አይካድም።]
አዎን! ፍቅር ያስፈልገናል!
ኢትዮጵያውያን በፈጣሪያቸው ኃይልና ቸርነት የበጥባጭ ገዢዎችን ግፍ ለመሸከም ያስቻላቸው እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለውን የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ አክብረው በመኖራቸው ነው። ፍቅራቸውና እምነታቸውም የውስጥና የውጭ ጠላትን ድል የሚነሱበት ትጥቃቸው ሆኖ ኖሯል። በኢህአዴግ ቤት የተነሳው ‘ፍቅር ያስፈልገናል’ የሚለው ሐሳብ፣ በህዝቡና በፖለቲከኞች መካከል ጠንካራ ድልድይ ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ የሐሳቡን ፋይዳ በጥንቃቄ ማጤን ያስፈልጋል። የኢህአዴግ አመራሮች ‘ፍቅር ያስፈልገናል’ የሚሉትን ጓዶቻቸውን በመከተል፣ኢትዮጵያዊነትን ልባቸው ውስጥ ፈልገው ለማግኘት መትጋት ይገባቸዋል፤ ሲያገኟትም ጓዶቻቸው እንዳቀፏት አገራቸውን በልባቸው ይቀፏት፤ አገር በልብ ነውና የሚታቀፍ! ኢትጵያዊነት፥ አንድነትና ፍቅር ሰላምን ያሰፍናል፤ ፈጣሪንም ያስደስታል። አዎን! ፍቅር ያስፈልገናል።

Read 1567 times