Saturday, 14 April 2018 14:59

“የተበላሹና በህገወጥ መንገድ የተመረቱ ምግቦች ገበያውን አጥለቅልቀውታል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  - ባለፉት 6 ወ ራት ብቻ 13 የምግብ ማምረቻ ፋብሪካዎች ታግደዋል
         - ከ10 ሺ ቶን በላይ ምግብ ለህብረተሰቡ እንዳይሰራጭ ተደርጓል
            
   የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና በተለያዩ መንገዶች የተበላሹ ምግቦች ከተማዋን እንዳጥለቀለቋትና ህብረተሰቡ ለምግብነት የሚውሉ ነገሮችን ሲገዛ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠቆመ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ለሚዲያ ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ላይ እንደተገለፀው፤በከተማዋ ህገወጥና ለምግብነት መዋል የማይገባቸው የተበላሹ ምግቦች በስፋት ተሰራጭተዋል። ባለስልጣን መ/ቤቱ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰቡና ለምግብነት ይውላሉ ተብለው ለገበያ የቀረቡ ምግቦች ላይ ምርመራ አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት፤የተለያዩ ዘይቶች፣ ዱቄት፣ የህፃናት ምግብ፣ ጁሶች፣ ኦቾሎኒ፣ ጨውና ሌሎችም የምግብ አይነቶች በከፍተኛ መጠን ለብልሽት የተዳረጉና ለጤና እጅግ አደገኛ መሆናቸውን በምርመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ምግቦቹ፤ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው፣ ለጤና አደገኛ የሆኑ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀሉባቸው እና ምንነታቸው ያልታወቀ በሚል በባለስልጣኑ ባለሙያዎች የተረጋገጡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
እነዚህን ምግቦችና መጠጦች ለህብረተሰቡ ያቀረቡ አስራ ሦስት የምግብ አምራች ፋብሪካዎች የታገዱ ሲሆን አስሩ ደግሞ መታሸጋቸው ተገልጿል። በዚህ ድርጊት ውስጥ ሲሳተፉ ለነበሩ ሌሎች ዘጠኝ ፋብሪካዎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ታውቋል፡፡
በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 10.164.8 ቶን ምግብ (ስኳር፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብስኩት፣ ጁስ፣ ወተትና የምግብ ጥሬ ዕቃዎች) የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ፣ በህገወጥ መንገድ የተመረቱና ለጤና አደገኛ ሆነው የተገኙ --- እንዲወገዱ መደረጋቸው ተገልጿል። ከምግብ ግብአቶችና የታሸጉ ምግቦች በተጨማሪ በርካታ መድሃኒቶችም በህገወጥ መንገድ ገብተው ለገበያ የቀረቡና የተበላሹ ሆነው በመገኘታቸው፣ ጥቅም እንዳይውሉና በአግባቡ እንዲወገዱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣የምግብ አስመጪዎች ላኪዎችና አከፋፋዮች ኢንስፔክሽን ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ፍቅሬ እንደተናገሩት፤ከበዓል ጋር በተያያዘ በርካታ ለጤና አደገኛ የሆኑ ምግቦች፣ የምግብ ግብአቶችና የታሸጉ ምግቦች ለገበያ ይቀርባሉ። ታላቅ ቅናሽ አድርገናል በሚል የማጭበርበሪያ መንገድም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና የተበላሹ ምግቦች በገበያ ላይ ይውላሉ፤ስለዚህ ህብረተሰቡ እነዚህን ለጤና አደገኛ የሆኑ ምግቦችና መጠጦች ከመግዛትና ከመጠቀም እንዲቆጠብና እንደዚህ አይነት ነገሮች ለገበያ ቀርበው በሚመለከት ጊዜም በነፃ የስልክ መስመር 8482 ለባለስልጣን መ/ቤቱ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በበዓል ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ቅቤና ዘይት ባሉ ነገሮች ላይ የተለየ ጥንቃቄና ፍተሻ ማድረግ እንደሚገባም አቶ ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡
በታዳጊ አገሮች 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ከ5 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ህፃናት፣ በየዓመቱ ከምግብ ወለድ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን በአገራችን ደግሞ ህብረተሰቡን ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል 92% ያህሉ የሚከሰቱት ከምግብ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

Read 3943 times