Saturday, 14 April 2018 14:58

የኪነ ጥበብ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፎረም በደባርቅ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


    የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደባርቅ ከተማ የኪነ ጥበብ፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፎረም እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡ ከፎረሙ ጎን ለጎን ዘንድሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲም እንደሚመረቅ የዝግጅቱ አስተባባሪ ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ በተደረገው ድልድል የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደባርቅ፤ የአገራችን አስደናቂ ተራሮች ስነ ምህዳር መገኛ፣ የጥንታዊና ታሪካዊ መስህቦች ምድር ስትሆን፣ በዩኔስኮ የተመዘገበው ብቸኛው ፓርካችንን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ መስህቦች ይገኙባታል። ፎረሙም ይህን ተፈጥሮ ይበልጥ ለማስተዋወቅና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ለመፍጠር መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
ከሚያዚያ 13-15 ቀን 2010 ዓ.ም በሶስቱ ቀናት ትልቅ የኪነ ጥበብ ትርኢት፣ በአስቸጋሪው የሊማሊሞ መንገድ ላይ ሩጫ እንዲሁም በዞኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎችና ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን ታዋቂ የሙዚቃና የቴአትር አርቲስቶች የአካባቢው ተወላጅ ኢንቨስተሮች፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በፎረሙ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰሜን ጎንደርን ለማልማት በጋራ እንሩጥ” በሚል መርህ በሚዘጋጀው በዚህ ፎረም የሰሜን ጎንደር ዞን የአስተዳደር ህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2406 times