Saturday, 14 April 2018 14:49

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

     “ለነፃነቱ የማይጨነቅ እንዳለ አይቆጠርም”
        ምክንያታዊ ለመሆን ስንት ዘመን መኖር ይጠበቅብናል? … “እንኳን ስለ ዘመን ለማውራት የሚቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘ ማን ያውቃል?” ልትለኝ ትችላለህ፡፡ እሱን ባውቅማ ጨካኝ፣ አታላይ፣ ጉበኛ፣ አስመሳይ፣ ዘረኛ፣ አልሆንም ነበር፡፡
ወዳጄ፡- ነፍስ፣ ውበት፣ ፍቅር፣ አዕምሮ፣ ፅድቅ፣ ኩነኔ፣ የጊዜ ፍልስፍና፣ የቁጥር ምስጢር፣ የህዋስ ተዓምር፣ የጥበብ ምትሃት፣ የተስፋና የምኞት፣ የመውደድና የመጥላት ምክንያት ምን ይመስልሃል? … ለመልሱ አትጨነቅ፣ ድሮ መልሰህልኛል፡፡ ‹እንዴት?› ብትል ነፃ አይደለህማ!! … “ለነፃነቱ የማይጨነቅ ደግሞ እንዳለ አይቆጠርም” ይባላል፡፡
“ነፃነትን የሚያክል ምንም የለም፡፡ ያለ ነፃነት ማንነት አይታሰብም፡፡ ስህተቶቻችንን አርመን፣ ህመማችንን አክመን ወደ እውነት የምንደርሰው በነፃነት ስንወያይ ነው፡፡” (Freedom is the supreme good, without it personality is impossible … only by free dicussion can we pick our way through erors and prejuducers to that total perspective which is truth.) በማለት የሚመክረን ዊል ዱራንት ነው፡፡ ነፃነት ከሌለ ፈጠራ፣ ነፃነት ከሌለ ዕድገት፣ ነፃነት ከሌለ አንተ፣ ነፃነት ከሌለ አገር የለም የሚል ይመስላል፡፡
ብዙ ሰዎች ነፃነት ማለት የፈለጉትን የመሆን ወይም የማድረግ መብት ይመስላቸዋል፡፡ ልክ ናቸው። አይደሉምም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው መጮህ ቢፈልግ መብቱ ነው፣ አይከለከልም፡፡ ነገር ግን ሲኒማ ቤት፣ ቴአትር ቤት፣ ትራንስፖርት ላይና የመሳሰሉት ቦታዎች ውስጥ “እሳት!” ወይም “ቦንብ!” እያለ ቢጮህ ወይም ከፍተኛ ድምፅ በማውጣት የሌሎችን ስራ ወይም ኑሮ በማወክ ‹መብቴ ነው›፣ ‹ነፃነቴ› ነው ማለት አይችልም። ነፃነት ኃላፊነት አለበት፡፡ መጮህ መብቱ ነው፤ ቦታን መምረጥ ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ ሰውየው የሚኖረው ለንደን ቢሆን፣ ሃይድ ፓርክ ኮርነር ሄዶ፣ እንደ ፈለገው ማቅራራት ይችላል፡፡ … ያውም ጥበቃ እየተደረገለት። ይኸ የሚያሳየው ደግሞ ፍፁም ነፃነት (absolute freedom) ብሎ ነገር ያለመኖሩን ነው፡፡
ሊቃውንት ነፃነትን በሁለት ይከፍሉታል፡- አንደኛው ከማትፈልገው ነገር ለመላቀቅ ወይም ነፃ ለመውጣት (Freedom from) የምታደርገው ትግል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የምትፈልገውን ለማድረግ ወይም ለማግኘት (Freedom to do something) የምታደርገው ትግል ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁለት መንታ አስተሳሰቦች “ነጋቲቭ ፍሪደም” (Negative freedom) እና “ፖዘቲቭ ፍሪደም” (Positive freedom) በመባል ይገለፃሉ፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዊድሮው ዊልሰን ስለ “ነጋቲቭ” ፍሪደም ሲናገሩ፤ “ነፃነት ማለት የመንግሥትን ስልጣን መገደብና ማናቸውንም ጭቆና አለመቀበል ነው” ይላሉ፡፡ የማህበራዊ ስምምነት ውል “Social contract” የተሰኘው የፍልስፍና መጽሃፍ ደራሲ ዢን ዣኩዊስ ሩሶ፤ ደግሞ “ነጋቲቭ ፍሪደምን” ሲያብራራ … “ማንም ሆነ ማን ማህበራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ህጎችን የመቀበል ነፃነት ሊኖረው ይገደዳል” ብሏል፡፡
ወዳጄ፡- ነፃነት ማለት በእጅጉ ጥልቅ፣ ረቂቅ፣ ተዛማጅ፣ ተለዋዋጭና አንፃራዊ፣ በጊዜና በሁኔታዎች የሚቀያየር፣ በተለያየ ስርዓት ውስጥ በግልና በጋራ አተረጓጎም የሚለያይ፣ በጊዜና በዕውቀት፣ በቦታና አጋጣሚ፣ በውጫዊ፣ በውስጣዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች የሚወሰን፣ በሂደት ወይም በድንገት የሚወለድ፣ የሚያድግና የሚሞት፣ እንደገናም የሚነሳ ግላዊና ማህበራዊ ስሜት ነው ይባላል፡፡
የአንድ ሰው ነፃነት ከአፈጣጠሩ ይጀምራል ብለው የሚያስቡ ጠቢባን አያሌ ናቸው፡፡ … ሰውየው ተረግዞ የተወለደበት ሁኔታ፣ ቤተሰቡ፣ ያደገበት ማህበረሰብ፣ የአእምሮው ብስለትና የመረዳት ፀጋው (Knowledge and wisdom)፣ ፍላጎቱና ምኞቱ፣ እምነቱና ሃይማኖቱ፣ የሚተነፍሰው የኢኮኖሚና ፖለቲካ አየር እንዲሁም አለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ተደማምረው የነፃነቱን መስመር ያደምቃሉ፤ ትናንት ነገና ዛሬ አንድ ላይ ተፈጭተው፣ በዚች በጁ በጨበጣት ቅድስት ምትሃታዊ ደስታ ከፈጠሩለት፣ የነፍሱ መድን ከሆኑለት …“ እሱ ነፃነት አለው!!” ይላሉ፡፡
በባሪያ አሳዳሪው ስርዓት አንዳንዱ ‹ሰው› አንዳንዱ ደግሞ ሸቀጥ ነበር፡፡ ሰው ሰውን ይሸጣል፣ ይለውጣል፣ በስጦታ ይሰጠዋል፣ ቋንጃውን ቆርጦ ያሽመደምደዋል፣ ይገርፈዋል፣ ከፈለገም ይገድለዋል፡፡ … ንብረቱ ነዋ! …. በጭሰኛው ስርዓትም አንዱ ያርሳል፣ ያመርታል፣ ከብት ያግዳል፣ ይገብራል፣ ባለርስቱ ተንደላቆ ይኖራል፡፡
በእነዚህ ሥርዓቶች ነፃነት ትርጉም የሚኖረው ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ነው፡ በካፒታሊስት ስርዓት የነፃነት ትርጉም በስራ ሰዓት ቅነሳ፣ በደሞዝ ጭማሪ፣ በእረፍት ጊዜና በወሊድ ፍቃድ ይቀየራል፡፡
ዲሞክራሲን አቆይተን ሌሎች የአገዛዝ ስርዓቶችን ማለትም - ፕሉቶክራሲ (Pulto cracy)፣ ሜሪቶክራሲ (Merito cracy)፣ ቴዮ ክራሲ (Theio cracy)፣ አሪስቶ ክራሲ፣ (aristo cracy) ሞናርኪ (monarchy) እና ኦሊጋርኪን (Oligarchy) ስንመለከት፣ በያንዳንዳቸው ውስጥ ያለው የነፃነት ትርጓሜና ቃና በግልም ሆነ በጋራ የተለያየ ነው፡፡
ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ስንመጣ፤ አነሰም በዛ ሰዎች ተፈጥሯዊ፣ ግለሰባዊ፣ ማህበራዊና ምክንያታዊ ነፃነታቸው የሚከበርበት ስርዓት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ጥያቄው፡- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አለ ወይ?፣ ለዜጎች ነፃነት የሚሰጥ ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከቀለም ልዩነት የፀዳ፣ ፍትሃዊነት ያለው፣ አድሎ የሌለበት፣ ዕኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል፣ ዕኩል የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ ዕኩል የመደራጀትና የመፎካከር ስልጣን፣ በሀገሪቱ ሃብት (የመሬት፣ የመንግሥት ቤት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን) ዕኩል የመጠቀም፣ ከቦታ ቦታ እንደ ልብ የመዘዋወርና በመረጡት አካባቢ የመኖር፣ በተለያየ መንገድ ሃሳብን የመግፅና የመሳሰሉት ሰብዓዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶች የተከበሩበት ስርዓት አለ ወይ? ነው መልሱን ላንተ እተወዋለሁ፡፡
የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከሌለ ነፃነትን እንደ ሰው፣ ነፃነትን እንደ ዜጋ፣ ነፃነትን እንደ መብት ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ “ሞቱን ንፈገው፣ ህይወትም አትቸረው” እንደ ተባለው ከሞቱት በላይ፣ ካሉት በታች ሆኖ መንከላወስ ላብዛኛው ህዝብ የምርጫ ወይም የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የያንዳንዱ ሰው በባርነት ወይም በነፃነት የመምረጥ ግላዊ ውሳኔ ይመስለኛል፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ የአውሮፓና የሩቅ ምስራቅ ሃገሮች፤ የነፃነትን ትርጉም ከተረዱ ቆይተዋል። ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መቻቻል የሚባሉ ቃላቶች ያላቸውን ውድ ዋጋ በሚገባ አውቀውታል። አንዳንዶች ደግሞ እነዚህን ውድ ቃላቶች ከጧት እስከ ማታ ቢደጋግሟቸውም ከቃላት ያለፈ ትርጉም ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግሥታቸው እንደ ቃላቶቹ ወረቀትና ቀለም ከመሆን አልፈው፣ ከባለስልጣናቱ መሳቢያ ወጥተው፣ ፀሐይ ሊሞቃቸው ባለመቻሉ ነው፡፡ … እንኳንስ በስራ ሊተረጎሙ!!
ወዳጄ፡- ህገ መንግሥት በተግባር ስራ ላይ እስካልዋለ ድረስ በባዶ ሜዳ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መቻቻል የምንላቸው ነገሮች ዘፈን በሌለበት እስክስታ እንደ መውረድ አይመስልህም? … “መጀመሪያ መቀመጫዬን!!” አለች አሉ ዝንጀሮ፡፡ መጀመሪያ ህዝቦች ከተተበተቡበት የስለላ ድር ተፈትተው በነፃነት መኖር፣ በህግና በስርዓት መተዳደር መቻል አለባቸው። የህግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል፡፡ ያኔ …
ገጣሚው፡- “ሰው ነፃ ይሁን በቃ
ሥርዓት በምትኩ ታስሮ
ላያንሰራራ ይወቃ!
መኖር ልኩ ይታወቅ
ነፃነት ባገር እንዲደምቅ!”
ማለቱ እውነቱን ነው፡፡ በነፃነት ቀልድ የለም! … ታላቁ ፓትሪክ ሄንሪ “Give me liberty or give me death” (ነፃነት ወይም ሞት!!) እንዳለው፡፡
በነገራችን ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ HR128 በማፅደቅ ‹ነፃነታችንን› ገፈፈው የተባለው እውነት ነው? ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ እኛም ግን (እንደ መንግሥትና ገዢ ፓርቲ ማለቴ ነው!) ህገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር፣ የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ ማሻሻል፣ ለዜጎች ህይወት ዋጋና ቅድምያ መስጠት፣ ነፃነትንና ፍትህን ማስፈን፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን መመስረት (ከልብ ነው ታዲያ)፣ ለተለዩ ሃሳቦች ጆሮና መድረክ መስጠት፣ ችግሮችና አለመግባባቶችን በውይይትና በንግግር መፍታት ወዘተ … በአጠቃላይ የሥልጣኔ ጉዞን ደፍረን መጀመር አለብን፡፡ ያኔ የእነ HR128 ጉዳይ አያሳስበንም። የዲሞክራሲም የስንዴም እጥረት ያለባት አገር ይዘን ግን “እንዴት ሲሆን ተነካን? በውስጥ ጉዳያችን ማን ያገባዋል? ሉአላዊነታችን ተደፈረ?” ወዘተ ብንል ብዙም አያዋጣም፡፡ ነፃነት ሙሉ የሚሆነው ራሳችንን ስንችል ነው በሁሉ ነገር!!
ሠላም!!
(*ግጥሟ ‹ችሎቱ› በሚል ርዕስ ጥር 4 ቀን
  1994 ለንባብ ከበቃው “አዲስ አድማስ”
  የተቀነጨበች ስትሆን የፀሐፊው ናት፡፡)  

Read 828 times