Saturday, 14 April 2018 14:47

ጲላጦስ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  (የፍርደ ገምድሎች እንጦሮጦስ!)
        ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ? አላቸው። (ዮሐ. 18፡29)
        በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። (ሉቃስ 23፡4)

    (ካለፈው የቀጠለ)
3 - ዥዋዥዌ
በእርግጥም ጲላጦስ አለቅጥ እንዲንገጫገጭ ሆኖ ነበር...
  . . . አስቀድሞ ፤ (ዮሐ. 18፡31-32) . . . እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት አላቸው። አይሁድም ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም አሉት፤ ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። (ወንጀለኞችን በስቅላት ቅጣት መግደል ሮማዊያኑ ወደ ቅድስቲቱ ምድር ያመጡት አዲስ ባህል በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር - የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 82 - ስቅለት - ነገር ግን እስራኤላውያን ሰውን በስቅላት አይገድሉም ነበር፤ ዘዳ 21፡21-23/ኢያሱ 10፡26)
በኋላም፤ ጲላጦስ ‹‹የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?›› ብሎ አማራጭ ሲያቀርብም፤ እግረ መንገድ አሁንም ከኢየሱስ ያጣውን ምላሽ ለማሟላትና ያንኑ ሮማዊያኑን የሚያባትታቸውን የንጉሥነቱን ጉዳይ ከሕዝቡም እያውጣጣ (investigate እያደረገ) ነበር፡፡ በተለይም በዮሐንስ ወንጌል እንደምናነበው፤ ጲላጦስ የኢየሱስን ፖለቲካዊ ‹አዝማሚያ› ለማወቅ አስልቶ ነበር ይላሉ፤ የታሪክ ተመራማሪያኑ፡፡ Pilate carefully questioned the prisoner about His political roll.
እውነትም ከዚያ ሁሉ ጥያቄና መልስ በኋላ አሁንም ለኢየሱስ ያንኑ ጥያቄ ደግሞ ያቀርብለታል . . .
ጲላጦስም፡- እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ  ስለ እውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ጲላጦስ፡- እውነት ምንድር ነው? አለው። (ምናልባት የጲላጦስ እውነት ንጉሡን ከማገልገል ያለፈ ስላልነበረ ይሆንን?) ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም። ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን? አላቸው። ሁሉም ደግመው በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ። (ዮሐ. 18፡37-40) እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ፣ ሚስቱ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። (ማቴ.27፡13-19) (ጲላጦስ ግን የሚስቱን ምክር አልሰማም፡፡ ሆኖም ግን አሁንም በኢየሱስ ላይ ለመፍረድ ዝግጁ አይደለምና ደግሞ ይጠይቃል) በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። (ግን ይህን ራሱ የሚያውቀውንም ውስጡን አልሰማም)... በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። (ሉቃስ 23፡4) ገዢውም፤ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ (ማቴ. 27፡23)
(እስከ መጨረሻው ቅጽበት ኢየሱስን ሊፈታው መፈለጉን እናስተውላለን፤ግና እርሱ ራሱ የወደደውንም አላደረገም፡፡ ወደ መጨረሻም ከከሳሾቹ ድምጽ ውስጥ ያስተጋባው አንዳች አስገምጋሚ ምላሽ ሳያናውጠው አልቀረም፡፡)
...ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት። ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ፤ ተመልሶም ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም። ስለዚህ ጲላጦስ አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን  . . . (ዮሐ. 19፡7-12)
(ፍፁም ባልጠበቀው መንገድ በስጋት የሚንጥና የሞት ፍርድ ውሳኔውን ከማሳለፍ ወዴትም ውልፍት ማለት የማያስችለው ወጥመድ ፊቱ ተደቀነበት! . . .)
...ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ።
በርግጥም ያኔ፤ ጲላጦስ ክፉኛ ክው ያለ እናም በቃ በእጅጉ የተንገጫገጨ አሳዛኝ ሰው የሆነ ይመስላል፡፡ በደካማ ጎኑ ነበር የመጡበት፡፡ አዎን! ማንም ቢሆን በዚህ መሰል ሁኔታ ውስጥ ራሱን ቢያገኘው፤በዚያች ወሳኝ ፍትሀዊ የፍርድ ውሳኔ የማሳለፊያ ቁርጥ ጊዜ ላይ በፍርድ ወንበሩ ቢቀመጥ ላፍታም ቢሆን  ይዋልላል፡፡ ግን ደግሞ ሁለት አማራጭ ይኖረዋል፤ ወይ ከአለት የጸና የልዕለ ሰብዕና ካባ የሚያጎናጽፈውን እውነት ጠብቆ ለእውነቱና ለራሱ ህሊና ታማኝ መሆን ይችላል ወይም ደግሞ ህሊናውን እየቧጠጠ ለሚያደማ ሀሰት ተገዝቶ፣ የአዕምሮ እረፍቱን አሟጥጦ ደፍቶ፣ ሰላምና ክብሩን አጥቶ፣ እስከ ዘላለሙ ንፁህ ሰብእናውን አጉድፎ ከራሱ ከማንነቱና ከመላው ሕዋ ጋርም ተቆራርጦ ያርፈዋል። ውሳኔው ቀላል አይደለም፡፡ እናስ እሺ ጲላጦስ ምን ሊል ይችላል... ‹‹አሁን ባይኔ መጣሽ!››  እንዴ! ለምን ምንም ነገር ጥንቅር ብሎ አይቀርም፤የንጉሡን ወዳጅነት አጥቶ ከመኖር፡፡ ህእ!›› (‹‹የምኖረው ለማን ሆነና!›› አይነት፡፡)
...በዚህ አተያይ/ መላምት ዙሪያ ያጠነጠኑት የታሪክ ተመራማሪዎቹም ይህን አሻሚ የኢየሱስ ከሳሾች አቀራረብ፤ የጲላጦስን የዳኝነት አቋም እሁለት ቦታ የከፈለ (explicit threat against Pilate) ፈተና ነበር ይሉታል ፡፡
ጲላጦስ፤ በኢየሱስ ላይ ባሳለፈው ፍርዱም ለንጉሡ ስሞታ ቀርቦበት እንደለመደው ከምርመራ ጥያቄ ቢያመልጥም፤ በኋለኞቹ ተደጋጋሚ ስህተቶቹ ምክንያት ግን ወደ ሮማ መጠራቱ አልቀረለትም፡፡
4 - የፍርድ ጥፍር
‹‹ህማማት ነውና የይሁዳን ታሪክ ልንገርህ...›› ይለናል፤ የኔታ ስብሀት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በ567 ድርሰቱ ውስጥ አምስት ልጆቹንና ስድስተኛ ሚስቱን በረሀብ ሞት ተነጥቆ፣ 7ኛ አንድ እሱ ብቻውን ቀርቶ እብደት ባናወዘውና ታማኙን የእርሻ በሬውን አርዶ በመብላቱ ራሱን በአስቆሮቱ ይሁዳ በመሰለው ገጸ ባሕርይው አንደበት፡፡... ‹‹ ይሁዳ ከዳተኛ ነው ይላሉ፣ የኔን ታሪክ ያልሰሙ፡፡ ይሁዳ እንኳ ተጸጸተ፤ ተሰቀለ፤ ራሱን ገደለ፤ እኔ ግን! እኔ ግን! ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ!
ይህ ድምጽ በሀገረ ገዢው፣ በተንገጫገጨው ዳኛ ልቦናም ውስጥ ያለማቋረጥ መጎሰሙ አይጠረጠርም፡፡
ጲላጦስ፤ ከቄሣሩ ጋር ሲገናኝ የቀረቡበትን ስሞታዎች ሁሉ በወዳጅነት መንፈስ ሊያስተባብል ይቻለዋልና እምብዛም አያሳስበውም፤ ምናልባትም በታማኝነትና ፍጹም ታዛዥነት ለአስር ዓመታት በጽናት ላበረከተው አገልግሎቱ ከንጉሡ ዘንድ ውዳሴና ሹመትም ሳይጠብቅ አይቀርም፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ጲላጦስ ሀገሩ ሲደርስ፤ እንዲያ አቅሉን እስኪስት ጠብ እርግፍ ያለለት ጌታው ጢባርዮስ ቄሣር ሞቶ ነበር። ይህም ብቻ አይደል፤ ጲላጦስ ገፍቶት/ ሰቅሎት የመጣው ክርስትናም ትንሣኤ አድርጎ በራሱም ምድር ዙሪያ ቀድሞት መድረሱንና ዘሩ ማጎንቆል መጀመሩን በገነገነ ጊዜ፤ (በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። ሐዋ.3፡13) በምርመራው ፍጻሜ በVienna-on-Rhone  በግዞት ሳለ ፤ ሁለመናውን እንደ ረመጥ እየፈጀ እሚያብከነክነው በኢየሱስ ላይ ያሳለፈው ፍርድ ሌት ተቀን እረፍት ስለነሳው፤  ጲላጦስም የከሀዲውን የይሁዳን ጽዋ ጨለጣት፡፡ ... ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥...ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። (ማቴ. 27:3/5) ጲላጦስም እንዲሁ ‹‹የቤተ መንግሥት ክብሩን ጥሎ›› ራሱን ገደለ፡፡
ከቶ አይቀርም ሞቱ
ምንም ቢታክቱ
ምን ቢሰነብቱ፡፡
 (የሕዝብ ግጥም - በገና፡፡)
5 - ባርነት ወ ነጻነት
‹‹ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።›› እንዲል መጽሐፍ፤ አልፋና ኦሜጋ ኗሪው ህያው ቃል፣ ስለ ፍጥረት ባርነት እና ስለ እግዚአብሔር ነጻነት፣ ክብር፣ተስፋ፣ ምህረት፣ ሕግ እና ፍርድ ...ያበረከተልንን የሕይወት ስንቅ አስታውሰን እናሳርግ ...ሰዎች ነንና ከኃጢዐት ፈተና ባናመልጥም፣ እንደ ስራችን ሳይሆን እንደ ፀጋና ቸርነቱ ማስተዋሉን ቢያድለን እንማርበት ዘንድ፤ ከልብ እውነቱ የተፋታ፣ ለሌሎች በባርነት ተኮድኩዶ፣ ላላመነበት እውነት አጎብድዶ ራሱን የካደ ሰው ያመሻሽ እድሜ ዘመን እርቃኑን ሲቀር ምን እንደሚመስል የምስኪኑ ፈራጅ አሳዛኝ ገድል ጥሩ ማሳያ ነውና ከጲላጦስ ከንቱ ፀፀት ያትርፈን፡፡ ሁሉ ከንቱ ከንቱ፡፡ እነሆ . . . (ሮሜ  8:20-21) ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው። (ገላትያ 5፡1) በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። (የያዕቆብ መልእክት 2፡12-13) በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል።
አሜን ፡፡
መልካም ዳግማይ ትንሣኤ!!

Read 930 times