Print this page
Saturday, 14 April 2018 14:48

የቴዎድሮስ ችሎት

Written by  ከመሐመድ ነስሩ /ሶፎኒያስ አዲስ/
Rate this item
(3 votes)

 ዳኞች ከወንበራቸው ተሰይመዋል፡፡
ንጉሱ ከዳኞቹ በስተቀኝ ጃኖአቸውን ደርበው ከእነ ግርማ ሞገሳቸውና ከእነ ሙሉ ክብራቸው ይታያሉ፡፡
ተከሳሽ እጇቹን ጀርባው ላይ አነባብሮ እንዳቀረቀረ. ... ከተከሳሽ ቦታ ላይ ቆሟል፡፡
የሟች ቤተሰቦች በደላቸውን በዝርዝር ገለጹ፡፡ ልጃቸውን እንደወጣ ያስቀረባቸው ክፉ ሰው ላይ ብይን እንዲያስተላልፉ ዳኞቹን ከተማፀኑ በኋላ፤ የመናገር ዕድል ለተከሳሽ ተሰጠ፡፡    
“በርግጥ ነፍስ ማጥፋት ፅድቅ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ከምወደው የእናቴ ሌማት የምጎርሰው እንጀራና  ከማድጋዋ የምጠጣው የዶሮ ዐይን የመሰለው ጠላ. . ደም ደም እያለኝ ሰላም አጥቼያለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ከሟች ይልቅ የሚጎዳው ገዳይ ነው፡፡ የሰው ደም ያፈሰሰ ሰው ቆሞ ስለሔደ ብቻ ዘመድ አዝማድ ሞቷል ብሎ የማይቀብረው ሬሳ ነው፡፡ በየመአልቱና በየሌቱ ነው ራሱን የሚገድል! ያፈሰሰው ደም ፈረሰኛ ወንዝ ሆኖ ቀኖቹን ይዞበት ይሔዳል፡፡ ያ ሰው በእጄ ካለፈ ወዲህ ቁጭ ያልኩ እንደሁ የምቀመጥበት በርጩማ ይኮሰኩሰኛል፡፡ የሔድኩ እንደሁ የምረግጠው መሬት  ይጎረብጠኛል፡፡ የተኛሁ እንደሁ ጎኔን ያሳረፍኩበት መደብ ቃሬዛ ይሆንብኛል፡፡ የበላሁ እንደሁ ምግብ ያቅረኛል፡፡ የጠጣሁ እንደሁ ውሃው ያንቀኛል…..››
“ነገር መዘባዘቡን ተወውና ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ“ አሉ መኸል  ላይ የተሰየሙት ዳኛ፡፡
“ጥፋትህን ታምናለህ? ወይስ ትከላከላለህ?››
 “ጥፋቴ ምን ላይ እንደሆነ አልገባኝም ጌቶች!›› አለ ተከሳሽ፤ ግራ መጋባትና ልምምጥ እየተዳሩበት ያለ አልጋ የመሰለ ፊቱን ግራ ቀኝ እያመላለሰ፡፡ “የፈጸምኩት ወንጀል ሳይሆን ትዕዛዝ ነው፡፡” የሟች ቤተሰቦች  ጉርምርምታ አሰሙ፡፡ ዳኞቹ፤ “በምን ማለት ነው ?”› ስልት ተያዩ ፡፡
“ከተራራ የገዘፉ፣ከአልማዝ የተወደዱ፣ከሰማይ የከበዱ፣ ከንጉሶች ሁሉ የላቁት ታላቁ ንጉሳችን፤ በዚህ በኩል አንድም ሰው እንዳታሳልፍ በሚል በጥብቅ አስጠንቅቀውኝ በዘብነት ወደ ስፍራው . . . ላኩኝ። ብርሀንማው ልባቸው ንስሩ ዐይናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እየመጣብን ያለውን አደጋ ገልጦ አሳይቷቸው እንደሆነ ከልቤ በማመን ትዕዛዙን ተቀብዬ ወደ ስራዬ ስገሰግስ ግልጋሎቴ ለሀገሬ ነውና ፤ ታዛዥነቴም ለንጉሴ ነውና ደስ ብሎኝ በተሰጠኝ ግዳጅ ላይ ተሰማርቼ ሳለሁ፣ አንድ ቀን አንድ ከውካዋ ሰው በዛ ሊያልፍ መጣ፡፡ እንደማይቻል ነገርኩት፡፡ የንጉሴን ጥብቅ ትዕዛዝ የምዘነጋ ብኩን /ከንቱ/ ሰው አይደለሁምና አልፈቅድልህም አልኩት፡፡ እሱም እኔም የተላኩት ከንጉሳችን ነው፡፡ አጣዳፊ መልዕክት ልከውኛልና ግዜዬን አታባክንብኝ” ብሎ ጥሶኝ አለፈ፡፡
“ምርጫ አልነበረኝም፡፡ የታላቁ ንጉስ ትዕዛዝ ከሚጣስ የአንድ ሰው ህይወት ይበጠሰ ብዬ በጥይት ቀለብኩት! ታዲያ ምን አጠፋሁ ጌቶች?! ነፍሴ በሰው ነፍስ የምትኮንነኝ አንሶ ሌላ ቅጣት ሊበየንብኝ ይገባልን?! ጥፋቴ ምኑ ላይ ነው? እኔ ጥፋተኛ አይደለሁም፤ ሆኖም ፍርድ አዋቂው ችሎት አጥፍተሀል ካለኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?!››
“አጥፍተኻል !”  አሉ ከግራ በኩል የተቀመጡት ዳኛ፤ “የንጉሳችንን ትዕዛዝ ለመጠበቅ የነበረህ ተነሳሽነት ማለፊያ ነው፡፡ ነገር ግን ከመግደል የተሻለ አማራጮች ነበሩህ፡፡ የተጣለብህን ኃላፊነት በማስረዳትና በማሳመን ማገድ ትችል ነበር፡፡ ይሄ አንደበተ ርቱዕ ያለመሆንህን ይመሰክራልና  ቅኔ በሚዘረፍበት ምድር እየኖሩ አንደበተ ስስ መሆን ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡
“እውነቱን ከንጉሱ ዘንድ ማጣራት ትችል ነበር። አሊያም ሌላ ሰው ለመፍትሄ እንዲያግዝህ ምክር መጠየቅ ነበረብህ፡፡ በዚህች ሊቃውንት እንደ አሸን በሚፈሉባት ምድር  አማካሪ አጣሁ ማለት የማይቻል ነው፡፡ ይቺ ሀገርኮ የተከበሩትን ንጉስ ያፈራችልን ሀገር ነች፡፡ እንዴት የሚያማክር ጠቢብ ይጠፋባታል። ሌሎችም ብዙ አማራጮች እያሉህ አንተ ግን በማን አለብኝነት ተነሳስተህ የሰው ሰው ደመ-ከልብ አድርገኻል፡፡”
ከንጉሱ ለጥቀው የተቀመጡት ዳኛ ለጠቁ፤
“ጥፋተኛው እኔ ነኝ!”
“በጣም አዝኜያለሁ፡፡ ሰው መግደልህ ጥፋት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እኔን ያሳዘነኝ ጥፋትህን ለማድበስበስ የተከተልከው ጠመዝማዛ መንገድ ነው። ንግግርህን ሳስተውል የተገነዘብኩት የሚያስደነግጥ ነገር ነው። የተገነዘብኩትን ባልናገር እወዳለሁ፡፡ ቢሆንም መናገር አለብኝ፡፡ ታላቁ የሀገራችን አድባር ንጉሳችን ሲወቀሱ ሰምቶ ዝም ማለት በራሱ ወንጀል ነው። እኔ ደግሞ የወንጀለኛ ነፍስ የለኝም፡፡ በሌላ መልኩ መከላከል እየቻልክ የንጉሳችንን ስም ደጋግሞ ማንሳት ለምን አስፈለገህ?! . . . .እኔ ያንተን ብልግና ደግሞ እንዲያብራራ በማድረግ አንደበቴን አላባልገውም፡፡ ግን እንዴት ብትዳፈር ነው ንጉሳችንን ነፍስ ገዳይ ልትል የቃጣህ በል?!”
“መ . . .መቼ . . . . .?” ተከሳሽ ሊያስተባብል ሲሞክር “አልተፈቀደልህም!” ብለው አስቆሙት፤ የመሀል ዳኛው፡፡ እሱን አስቆሙትና እሳቸው መናገር ጀመሩ፤ “እንግዲህ የተባለው ተብሏል፡፡ እኔም የተባለው ላይ ልጨምር ካልኩ ነገሩ ላይ የማቱሳላን ዕድሜ ያህል እዚሁ ማሳለፋችን በመሆኑ  ... ወደ ብይኑ ብንሄድ መልካም ነው፡፡”
ከግራና ቀኛቸው ወደ ተቀመጡት አጋሮቻቸው ተመለከቱ፡፡ በምክክር ጥቂት ደቂቃዎችን ካሳለፉ በኋላ
“እህ . . .እህህ . . . . .” የመሀል ዳኛው ጉሯሯቸውን አፀዱ፤ “እሺ! . . . ያስተላለፍነውን ውሳኔ እንደሚከተለው እገልፃለሁ . . .”›
ጆሮዎች ቁመት ጨመሩ . . . ልቦች ምታቸው በእጥፍ ጨመረ፡፡
 “ችሎቱ የከሳሽም የተከሳሽንም ሀሳብ አድምጦ፣ ጉዳዩን ከግራም ከቀኝም ተመልክቶ የሚከተለውን ብይን አስተላልፏል
1ኛ) ተከሳሽ የሰው ነፍስ ማጥፋቱ አግባብ ባለመሆኑና ያቀረበው መከላከያም ተልካሻ በመሆኑ    ጥፋተኝነቱ ተሰምሮበታል፡፡
2ኛ) ተከሳሽ ራሱን ከቅጣት ለማዳን ሲል ያቀረበው መከራከሪያ ውስጥ የተሸሸገ የንጉሳችንን ሞገስ የሚገፍ፣ ልዕልናቸውን የሚያንኳስስ፣ የስድብና የውንጀላ ዳርዳርታ እንደነበረበት ታምኖበታል፡፡
በነዚህ ሁለት ትላልቅ ምክንያቶች የተነሳ የሞት ፍርድ ተፈፃሚ እንዲሆንበት ወስነናል!”
ዕልልታ!
በስተቀኝ የተቀመጡት ዳኛ፤ንጉሱን በኩራት አዩ - ሙገሳን በሚማፀን  ዐይን፡፡
‹‹የለም . . . .የለም!!››  አሉ ንጉሱ፡፡
ከዙፋናቸው ላይም ተነሱ፤ ወርደው በተከሳሽ ቦታ ላይ ቆሙ፡፡
“ሁለት የሚቃረኑ ትዕዛዞች በመስጠት ሳላውቅ ለሟች ነፍስ መጥፋት ሰበብ የሆንኩት እኔ ነኝ፤ ለዚህም ተጠያቂ እንደሆንኩ ልቦናዬ አምኗል፡፡›› እጃቸውን ወደ ኋላ እንዳጣመሩ፣ ከአንገታቸው በአክብሮት ጎንበስ አሉ. . .
“የሚገባኝን ቅጣት እንዲወሰንብኝ ችሎቱን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡››
እኒያ ቁጡና ጀግናው ንጉስ፤ ተከሳሽ ቦታ ቢቆሙ ድንጋጤና ሽብር ዳኞቹ ፊት ላይ ሽቅብ ቁልቁል አሉ፡፡
ዳኞቹ ደፍረው ለመበየን በመቸገራቸው የሚያስመልጣቸውን መንገድ ፍለጋ ዳከሩ፡፡
“ንጉስ ሆይ !›› አሉ በግራ የተቀመጡት ዳኛ፤ “ጥፋተኛ ነኝ ብለው ማሰብዎ ገርሞኛል፤ በእርግጥ ምን ያህል አስተዋይ እንደሆኑ ከስቶልኛል፡፡ እርስዎን የሚያህል ታላቅ ንጉሥ ከዙፋኑ ወርዶ ተከሳሽ ቦታ መቆም መቻሉ ትልቅ መምህርነትዎን ያሳያል፡፡ ሆኖም ስጋት አለኝ፡፡ ይሄ የተቀደሰ፤ የተባረከ ድርጊት . . . የትኛውም መናጢ ነገ ተነስቶ ሰው እያገደለ፤ በርስዎ እንዲያላክክ በር የሚከፍት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን አሁንም ተጠያቂው ይሄ ሰው ነው ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ሰው አታሳልፍ እንጂ ሰው ግደል አላሉትም፡፡ እሱ ግን ሩህሩህነትዎን በመገንዘብ መግደል አሰኝቶት ስለ ነበር በጥጋብ ተነሳስቶ ገደለና ጣቱን ወደ እርስዎ ጠነቆለ፡፡ ከዚህም በላይ ጃንሆይ! መግደሉ እንኳን ይሁን ብንል መግደል ያለበት እንዲህ አልነበረም፡፡
“የእርስዎ ትዕዛዝ ሰው እንዳያልፍ ነው፡፡ እሱ ግን ሰውዬው ካለፈ በኋላ ነው የገደለው፡፡ ሆነ ብሎ ትዕዛዝዎን ከጣሰ በኋላ የመግደል አምሮቱን ተወጣ፡፡ እርስዎን በማጭበርበርም ይኼ ወንበዴ፤  አባታችንን ያለቦታዎ አስቆመዎት፡፡”
ቀኝ ዳኛው ተቀበሉ፡፡
“ንጉሳችን በደመ ነፍስ እንደማይወስኑ የታወቀ ነው፡፡ የእኛ ንጉስ ከዓለም ነገስታት ሁሉ የላቁ ታላቁ ንጉስ ናቸው፡፡ ከፈጣሪ ጋር ተጎራብተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ያንን ትዕዛዝ የሰጡት ፈጣሪ አንዳች ነገር ሹክ ቢላቸው ነው፡፡ ያ ሰው መሞት ነበረበት፤ ይኼ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው፡፡ የሱን ስልጣን አንገዳደረውም። ይህ እንዲሆን ነብይ ቢሻ ንጉሣችን ልቀው ተገኙ። ፈርኦንን ለማንገታገት ሙሴን የላከ እግዜር ፍቃዱን እንዲያስፈፅሙ አባታችንን መረጠ፡፡ ይሄ ደግሞ ብፁእነት ነው፡፡ ንጉሥ ሆይ ታዲያ ስለ ምን አጠፋሁ ይላሉ? እንደኔ እንደኔ ይህ እግዜርን መቃወም ነው፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ያደረጉትን ትክክለኛ ነገር እንደ ክፉ ሥራ አይቁጠሩት!”
ፍርሀት እንደ ቤቱ ካደረበት ልብ ከፍ ብሎ የሚገኘው የመሀል ዳኛው አፍ በቃላት ተሞላ፡፡ ቃላቱ እንደ ጉንዳን ቅፍለት ከአፋቸው ወደ ጆሮዎች ደፍ በሰልፍ ይጓዝ  ጀመረ፡፡
“እንግዲህ ንጉሥ ሆይ፤ ፍርድ ስጡኝ እያሉን ነው፤ እንደ ሚታወቀው ፍጡር ፈጣሪው ላይ ሊፈርድ አይቻለውም፤ ከባዶ ቦሀቃ ሊጥ መች ይዛቃል?! ከአበባ ማር ይሰራል እንጂ ከማር አበባ መች ይበጃል?! እኛ የእርስዎ ማር ነን፡፡ እርስዎ የኛ አበባ ነዎት፡፡ ውሃ ከከፍታ ወደ ዝቅታ ይንደቀደቃል ፤ይጋልባል እንጂ ከታች ወደ ላይ አይፈስም፡፡ እንኳን መፍሰስ ሽቅብ ማየት አይኖርበትም፤ ይሄ ከሆነ ተፈጥሮን ይቃረናል፡፡
“በእውነቱ እርስዎ እዛ ጋ ቆመው እኔ እዚህ በመቀመጤ የጥፋተኝነትና የወንጀለኝነት ስሜት እያወከኝ ነው፡፡ ቢሆንም እርስዎ ብለዋልና ቃልዎን በማክበር እኔ መቆም በነበረብኝ ቦታ ላይ እርስዎ መቀመጥ በነበረብዎት ቦታ፣ እኔ ተቀምጬ በመናገር ላይ ነኝ፡፡ አሁንም ከተፈጠረው ሁኔታ የምንገነዘበውም፣ ይሄ ነፍሰ ገዳይ ሶስተኛ ጥፋት ማጥፋቱን ነው፡፡ ሰው ገደለ፡፡ ታላቁን ንጉስ ወረፈ፡፡ ይኸው አድባራችንን የማይመጥናቸው ቦታ ላይ እንዲገኙ ሰበብ ሆነ፡፡ እንግዲያው ከዚህ የላቀ ወንጀለኛ ከየት ሊገኝ ይችላል። ንጉሳችን የሚቃረን ትዕዛዞችን ቢሰጡም፣ ሁለቱንም ትዕዛዝ ያስተላለፉት ለሀገራችን እድገትና ለህዝባችን ጥቅም ሲሉ መሆኑ የታመነ ነው፡፡  ታዲያ ሀገራቸውን ለማስጠበቅና ህዝባቸውን ለመጥቀም በሰሩት ስራ እንደ ጥፋተኛ ሆነው እንዴት ይቆጠራሉ?
“ታላቁ ንጉሥ፤ እንደ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ሊቀበሉ ቆመዋል፡፡ ለዚያውም ኢየሱስ ተይዞ ነው፤ እሳቸው ግን በፍቃዳቻው የሰው ሀጢያት ሊቀቡ፣ ሌላው ላጠፋው ሊቀጡለት ይጠብቃሉ፡፡ የፈጣሪ ልብ ምን ያህል ተደስቶ ይሆን ?! ንጉሥ ሆይ፤ አረ እንዴት ያሉ ቅዱስ ነዎት?!! በእውነት አቻ አይገኝልዎትም፡፡  . . .እ . . .ለማንኛውም ፍርዱን ተነጋግረን እንሰጣለን፡፡”
ዳኞቹ ዳግም ተንሾካሾኩ፡፡
ከቆይታ በኋላ ‹‹ይህ ጥፋተኛ ሰው፤ ለሶስተኛው ጥፋቱ ንጉሳችን እግር ላይ ወድቆ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሞራል ካሣም እንዲከፍልና ከዛን በኋላ በሞት እንዲቀጣ ይሁን! በማለት ወስኗል፡፡” አሉ የመሀል ዳኛው፤ በኩራት፡፡ ንጉሡን እያዩም፤ “ወደ ዙፋንዎ ይመለሱ ንጉሥ ሆይ !” ሲሉ ተማፀኑ፡፡
“የለ . .. . . . . የለ !” አሉ ንጉሱ፤ በሚያስገመግም ድምፃቸው፡፡
“እናንተ የተናገራችሁት ሁሉ ስህተት ነው፤ እኔ ጥፋተኝነቴን አውቃለሁ፤ ስለዚህም ለሟቹ ቤተሰቦች... የካሣ ገንዘብ እሰጣለሁ፡፡” አሉ፡፡
ገንዘቡም ተሰጠ፡፡ ተከሳሹም በነፃ ተለቀቀ፡፡ ንጉሡ ወደ ዙፋናቸው ተመለሱ፡፡ ኮስታራው ፊታቸው ቁጣ አንቦለቦለ፡፡ በንዴት እየተንቀጠቀጡ ለዳኞቹ እንዲህ አሉ፤ “እናንተ ፍርደ ገምድሎች፤ ዙፋኔን እንዴት አላገጣችሁበት?! እንዴት ያላችሁ ጭካኔ የተዘራበት ማሳ ናችሁ?! እንደ ምን ያላችሁ የውሸት ጎተራ ናችሁ?! እንዴት የምትደንቁ ማስመሰል የሚርመሰመስበት ጎዳና ናችሁ?! አየኋችሁ፡፡ ሰማኋችሁ፡፡ ለመወደስ ስትጥሩም ለሌላው ሰው ነፍስ የማይገዳችሁ መሆናችሁ ፍንትው ብሎ ታየ፡፡ አታውቁም?! የድሀውን እንባ ጠባቂ እንጂ የደሀን ነፍስ ነጣቂ አይደለም የቴዎድሮስ ችሎት! ለበላው ላክለት እንጂ ጥፍሩን ልነቅልበት አይደለም ዙፋን የያዝኩት፡፡ የተራበውን ላጎርስ እንጂ ርሀብ ላጠና አይደለም ዘውድ የጫንኩት፡፡ የተበደለ ሊክስ --- የበደለ ሊገስፅ እንጂ በደል ሊያራባ ስቃይ ሊቀፈቅፍ አልቆመም የቴዎድሮስ መንበር፡፡”
ዓይናቸውን አጉረጥርጠው እያፈራረቁ ወደ ዳኞቹ ተመለከቱ፡፡
“ከንቱዎች ናችሁ! በሌላው ነፍስ የምትሸቅጡ አድርባዮች! አታውቁም ?! የኔ ልብ ያለ ቦታው ልደር የሚለውን የማያውል ቆራጥ መሆኑን አታውቁም?! እኔ ላይ መበየን ስለፈራችሁ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጋችሁ፣ ነገር አሰማምራችሁ ከወንጀል ነፃ አደረጋችሁኝ፡፡ ምስኪኑ ሰው ላይ ደግሞ የጥፋት ጉድጓድ እየማሳችሁ የወንጀል አለት ጫናችሁበት፡፡ በኔ የተነሳ በሰራው ሀጢያት፤ በህይወት የተቀጣውን ሰው ዳግም ልትቀጡት ቋመጣችሁ፡፡ እኔ እሾማችኃለሁ፤ እሸልማችኃለሁ፤ እሱ ግን ምንም የሌለው ምንም የማያደርግላችሁ ሰው ነው፡፡ እንዲህ ነው ያሰባችሁት። ስሙኝ . . . . ይሰጠኛል ለሚለው እጅ፤ ከምንጭ ምንጭ መርጦ ንፁህ ውሃ የሚቀዳ፣ችግር በያዘው እጅ ላይ ደግሞ ሽንቱን የሚሸና፣ እበትም የሚለቀልቅ ሰው የሚሸልም አይደለም የኔ መንግሥት !”
ዳኞቹ በያሉበት ኩምሽሽ አሉ፡፡
“በሉ ወርዳችሁ ተከሳሽ ቦታ ላይ ቁሙ!” አሉ ንጉሡ “ለጥፋታችሁ የሚገባችሁን ፍርዴን ተቀበሉ!”
ሦስቱም ዳኞች ከወንበራቸው ወርደው ተከሳሽ ቦታ ላይ ቆሙ፡፡              
በድንጋጤም እርስ በርስ ተያዩ፡፡

Read 3793 times