Print this page
Saturday, 14 April 2018 14:32

ይድረስ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር

Written by  ባህሩ ሰጠኝ
Rate this item
(6 votes)


       “--በእውቀት ላይ እውቀት ተጎናጽፈዋል፡፡ በዚያ ላይ የኢህአዴግን ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ያካበቱትን ትምህርትና ልምድ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር ከቀየሩ ኢትዮጵያን ለመቀየር ምን ይሳንዎታል፤ ምንም፡፡ ያስታውሱ፤ ከእርስዎ የሚጠበቀው የላቀ መዋቅራዊ ለውጥ ነው፡፡ በቃ !--”
     
    ኧረ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን አበቃዎት! አቶ ለማ መገርሳንም እንኳን ደ…ስ አለዎት ይበሉልኝ፤ ኳስና ፖለቲካ ካለ ቡድን ስራ ለውጤት ይበቃል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ቅብብሎሽ ያስፈልገዋላ፡፡ አቶ ለማ፤ ያችን ምርጥ ኳስ አመቻችተው ባያቀብሉዎት ኖሮ ይህን ግብ (ጎል) ባላስገቡ ነበር፡፡ አንድ አጥቂ ብቻውን ጎል አያስገባም፤ ምርጥ አቀባይ፣ የክንፍ እና የመሃል ተጫዋች ያስፈልጋል፤ ሞራል የሚለግስ ደጋፊ (ቲፎዞ)ም እንዲሁ፡፡  ስልታዊ ማፈግፈግም እጅግ ያስፈልጋል፡፡ ይገርምዎታል ዶ/ር፤ በህይወቴ ኳስ ማየት አልወድም፤ ግን የእርስዎን ጨዋታ በደረቅ ሌሊት እንቅልፌን ሰውቼ፣ እስከ መጨረሻው ተከታተልኩት። ግን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ያን ያህል ምጡ የጠናበት ምክንያት ምንድነው? [ኢህአዴግ] ሲያምጥ አድሮ፤ ከስንት ምጥ በኋላ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በአብይ ጾም 5ኛ ሳምንት፣ ከሌሊቱ 5፡00 ላይ ዶ/ር አብይን ተገላገለ፡፡ እሰይ!…እ…ል…ል…ል! አለ ህዝቡ፡፡ (በአብይ ጾም ዶ/ር አብይ !) እንኳን ማርያም ማረችህ ኢህአዴግ፡፡ ይች ቀን በታሪክ ልዩ ቦታ አላት። (አንድም እንኳን ተመረጡን ብለን የምናወድስበት አልያም ምነው ባልተመረጡ ብለን የምንቆጭባት ልዩ ቀን)፡፡
ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ (የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር)ም ልዩ ምስጋናዬን ያድርሱልኝማ፡፡ እሳቸው በፈቃዳቸው ስልጣን ባያስረክቡ ኖሮ እኮ ይህን ዕድል በአጭር ጊዜ አያገኙም ነበር፡፡ እኔም ብሆን ይህን ደብዳቤ ባልጻፍኩልዎ ነበር፡፡ አቦ ቤተ መንግስትዎ ይመችዎ፤ ይሙቅዎ፤ አሜን ይበሉማ፡፡ ከእንግዲህ አቶ ኃይለማርያም በህዝብ ትራንስፖርት ተሳፍረው ቢሄዱ ማን ይናገራቸዋል፤ ማንም። በእግራቸውስ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ቢሄዱ ማን ይናገራቸዋል፤ ማንም፡፡ ስንቶቹ መሪዎቻችን ስልጣናቸውን የ…ሙ…ጥ…ኝ ብለው ከወንበራቸው ጋር ተጣብቀው ቢባጁም እሳቸው ግን ስልጣን በሰላማዊ መንገድ ያስረከቡ ፈር ቀዳጅ ምሁር ናቸው፤ ተምሮ ማስተማር ማለት እንዲህ ነው፡፡ ለርስዎም ትልቅ ትምህርትና ተሞክሮ ነው፤ ዘላለም በታሪክ ሲወደሱ ይኖራሉ፡፡ ይህ ድንቅ ተግባራቸው አርቆ አሳቢነታቸውን የሚያሳይ ለመሆኑ ማንም ይስማማበታል፡፡  
ባተሌ ሆነው በስራ ሳይጠመዱብኝ ዛሬ የልብ የልባችንን እናወጋለን፡፡ መቼም ከፊት ለፊትዎት ብዙ ፈተና መጋፈጥ እንዳለብዎት ለእርስዎ መናገር፣ ለቀባሪ እንደ ማርዳት ይቆጠርብኛል። ሰው ቢፈልግም ባይፈልግም መፈተኑ አይቀርም አይደል ያሉት እርስዎ። መቼም ስንት ደም የፈሰሰበት ውጤት መሆኑን ለአፍታም የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ እዚህ ላይ “እንዴት ይረሳል” የሚለውን ሙዚቃ ልጋብዘዎትማ። ኧረ አይረሳም። ጉልቻ ቢለወዋጥ ወጥ አያጥፍጥም እንዳይሆንብዎ እንደ ብረት ጠንክረው መስራት ይጠበቅብዎታል። ከበሮ በሰው ላይ ታምር ሲይዟት ታደናግር እንዳይሆንብዎት ሌትም ቀንም ጥረት አይለየዎት - ያው ገብተውበታላ፡፡ ልዩ የኮምፒውተር እውቀት፣ የፖለቲካ ብቃት፣ የውትድርና ጥበብ ሲደማመር እጅግ ምሉዕ ያድረግዎታል፡፡ በእውቀት ላይ እውቀት ተጎናጽፈዋል፡፡ ታዲያ ምን ይጎድልዎታል? ምንም፡፡ በዚያ ላይ የኢሀአዴግን ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ያካበቱትን ትምህርትና ልምድ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር ከቀየሩ ኢትዮጵያን ለመቀየር ምን ይሳንዎታል፤ ምንም፡፡ ያስታውሱ፤ ከእርስዎ የሚጠበቀው የላቀ መዋቅራዊ ለውጥ ነው፡፡ በቃ!
የሚዲያ ነጻነት እንደሚሰጡም ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡  በአንደበትዎ ሚዲያ ሃሳብ የሚፈስበት…ሀሳብ የማይገደብበት አውድ ሆኖ ማገልገል እንዳለበት ጠቁመውናላ፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ቀድሞ መረጃ እንደሚደርሰው እንደ እርስዎ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ለሰራ ሰው የሚሰወር አይመስለኝም። ህዝብ መረጃዎችን ማነፍነፍ ለምዷል፡፡ ህዝብን መሸወድ አይቻልም፡፡ መንግስትንና ህዝብን ካለያዩት መካከል አንዱ የሚዲያዎች ዘገባ ነው። በቴሌቪዥን መስኮታቸው ብቅ ይሉና አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (አሸባሪዎች) በፈጠሩት ግርግር የንጹህ ወገኖቻችን ደም ፈሰሰ፤ እዚህ ቦታ ላይ ህይወት ጠፋ የሚል ድፍን ያለ መረጃ ይናገራሉ። ዩኒቨርሲቲ እያለን የጆርናሊዝም አስተማሪያችን ባስተማሩን መሰረት፤ ማን፣ መቼ፣ የት፣ ስንት፣ እንዴት፣ምን… ምናምን የሚሉ “WH” ለሚባሉ ጥያቄዎች ምላሽ ካልሰጠ አንድ መረጃ (ዜና) ምሉዕ አይደለም፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞ ሲቀጣጠል ኢንተርኔት ወይም ሞባይል ዳታ አልያም የሚዲያ አውታር መዝጋት አማራጭ አይደለም፡፡ በጅምላ ማሰርም እስር ቤት ከማጣበብ ውጭ ለውጥ አያመጣም፡፡ በየጊዜው ኮማንድ ፖስት ማወጅም ቢሆን አማራጭ አይሆንም። ዘጠኝ ቦላሌ…..ምን አያድንም፡፡ ብቸኛው አማራጭ ችግሮች ስር ሳይሰዱ መፍትሄ መስጠት ነው - ሳይቃጠል በቅጠል፡፡ ይኼ ነው ፍቱን መድሃኒቱ። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እርስዎን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃዎት ሚዲያ (Facebook) አይደለም እንዴ?  አደራ የበሉበትን ሞሰብ እንዳይረግጡ፡፡ ኧረ ማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክ) ለዘላለም ይኑር!
በወህኒ ቤት ታጉረው የሚማቅቁ ዜጎችስ ፍትህ ያገኛሉ ወይስ እንደታጎሩ፣ የቀን ጨለማ እንደዋጣቸው ይቀጥላሉ? ለነገሩ እነ [ቂሊንጦ] ባዶ ይቀራሉ ሃ…ሃ…ሃ (ወንጀለኛ አይታሰር እያልኩ እንዳይመስልዎ)፡፡ ቂልንጦ ባዶ እንዳይሆን መፍትሄውን ልጠቁምዎት፤ የህዝብ ንብረት ሲዘርፉ፣ በግፍ እየጨፈጨፉ የህዝብ ደም ሲያፈሱ የቆዩ ባንዳዎች፤ ቂሊንጦ ይግቡና እስኪ ስቃዩን በማንኪያ ይቅመሱት (ነገር ግን ብልታቸው ላይ ሀይላንድ በማሰር፣ የዘር ፍሬያቸውን በማምከን ልጅ እንዳይፈጥሩ ይደረጉ ብዬ አልመክርም፤ እርስዎም አያደርጉትም)፡፡
በአንድ ወቅት ለምልመው የጠፋ ጋዜጦችስ እንደገና ያለመልማሉ ወይስ እንደደረቁ ይቀራሉ? እኔ እርስዎን ጋሻ መከታ አድርጌ የመጻፍ ነጻነቴን ይኸው ዛሬ በይፋ አውጃለሁ፡፡ አዋጄን ያጽድቁልኝማ። ታፍነው የኖሩት ህዝቦችና ጋዜጦች የተቆረጠው ተስፋቸው በአንድ ቀን አቆጥቁጦ ይኸው መተንፈስ  ጀመሩ፡፡ ይኸው እኔም ተነፈስኩ እ…ሰ…ይ! ወጣልኝ።
ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የመሰብሰብ መብት ጉዳይስ? እስካሁን ባለው ሁኔታ ያልተከለከሉ ሰልፎች (ታክሲ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ዳቦና ባንክ ቤት) ናቸው። ከዚያ ውጭ ጎዳና ወይም አደባባይ ወጥቶ መሰለፍ ምላሹ አፈ ሙዝ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ባዶ እጁን ወደ ጎዳና በወጣ ህዝብ ላይ መንግስት እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ ነዎታ፤ የጦር አዛዥ እርስዎ ነዎታ፡፡ የርስዎን ይሁንታ ካላገኘ አንድም ወታደር በህዝብ ላይ አንዲት ጥይት ጢው የሚያደርግ አይመስለኝም፡፡
ሌላው ጉዳይ በተለመደው አግባብ ከቁጥር ላይ ቁጥር እየከመርን ትራንስፎርሜሽኑ ያመጣው፤ አድገናል ተመንድገናል፤ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት እያልን ነው የምንቀጥለው ወይስ ድሃ መሆናችንን አምነን፣ ከተረጂነት የሚያወጣ ስልት ይቀይሳሉ? እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ [ታይቶ የማይታወቅ] የሚባለው የአቶ ኃይለማርያም በፈቃደኝነት ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው መልቀቅና የእርስዎ መመረጥ ነው፡፡ (ፍጹም ለውጥ የለም እያልኩ አይደለም)፡፡
ምሁራን ምን አሉ፤ ተቃዋሚዎችስ ምን አሉ….ለማለት ተዘጋጅተዋል? ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የሚቀጥሉ ከሆነ ለሹመትዎ የነበረው ዳንኪራ ወደ ተቃውሞ ጩኸት እንደሚቀየር አይጠራጠሩ፡፡ አስተዳደራዊ ችግሮች አሉ ይስተካከሉልን የሚሉ ዜጎችን ትምህክተኛ፣ ጠባብ፣ የአመለካከት ችግር፣ የልማት አደናቃፊ…..የሚሉ ተቀጽላ ስሞችን መለጠፍና ማሸማቀቅ ከእንግዲህ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ችግር በተፈጠረ ቁጥር በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው “አንዳንድ የውጭ ሃይሎች፤ አንዳንድ አሸባሪዎች፣ አንዳንድ ጽንፈኞች….. የፈጠሩት” ምናምን የሚሉ ማስተባበያዎችን ከእርስዎ አልጠብቅም፤ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነዋ። (አሸባሪ የለም እያልኩ አለመሆኔ ይሰመርልኝማ)። ይልቁንም ችግሩ የመንግስት መሆኑን አምነው ካስተካከሉ፣ የህዝቡ ሁለተኛ አምላክ ነዎት፡፡
ስልጣናቸውን የትርኪምርኪ ፖለቲካ ፍጆታ የሚያደርጉትን መንገዱ በእሾህ ሊታጠርባቸው፣ በብረት ሊዘጋባቸው ይገባል፡፡ የፍትህ እጦት አንገላቷቸው ስንቶቹ ደም እያነቡ ይኖራሉ መሰልዎት። እንባቸውን እንደሚጠርጉላቸው እምነት አለኝ። ብዙዎች ትንሽ ሽራፊ ስልጣን ሲያገኙ በአቋራጭ ለመክበር ነው የሚሯሯጡት፡፡ ህግን ከለላ አድርገው ሲዘርፉ የነበሩ ባንዳዎችንስ እንዲሁ ዝም ብለው ነው የሚያልፏቸው ወይስ ይቆነጥጧቸዋል? ኧረ ይቆንጥጧቸውማ፡፡ ምን ይህ ብቻ ንጹሃን ዜጎችን በግፍ ሲጨፈጭፉ የቆዩ አረመኔዎችስ በዋዛ ሊታለፉ ነው እንዴ? ይኼ በፍጹም አይታለፍም፡፡ ታዲያ በየጊዜው እንደ ጅረት የሚፈሰው የሰው ደም ያቆማል ወይስ ይቀጥላል? የተዘረፈውስ ንብረት ይመለሳል? እዚህ ላይ የእርስዎ ቁርጠኛ አቋም ይፈለጋል - አባቴ ይሙት፡፡
በስሙ ሲነገድበት የቆየው የትግራይ ህዝብ  ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል? የአንዳንድ ባለስልጣናት ዘመድ አዝማድ (ሁነኛ) የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች እንጂ በገጠር እየኳተነ የሚኖረው የትግራይ ህዝብ ምን ጥቅም አገኘ? ምንም፡፡ ስሙ እንጂ የተረፈው እስካሁን ከእጅ ወደ አፍ አልወጣም። መቼም ከኑግ ጋር ያለህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ መሆን የለበትም። ይህንንም ተቀምጠውም ተኝተውም ያስቡበት። ምናልባት ደሙ አልፈሰሰ ይሆናል፣ ምናልባት ከመኖሪያ ቦታው አልተፈናቀለ ይሆናል፣ ምናልባት ወህኒ ቤት ገብቶ አልማቀቀ ይሆናል እንጂ ከሌላው ብሄር በተለየ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ አልሆነም። እስካሁን በንብ ምልክት የቆየው ድርጅታችን፤ ምናልባት አልነደፈው ይሆናል እንጂ ለድሀው የትግራይ ህዝብ ማር አላቀመሰውም፤ ሰንኮፉ ነው የተረፈው፡፡ 27 ዓመት የበግ ለምድ ለብሰው ሌላውን እየተናደፉ (እያናደፉ) ማሩን በገበቴ እያቦኩ የዛቁት በስልጣን ኮርቻ የተፈናጠጡ ባንዳዎችና ጥቂት ግብረ አበሮቻቸው ናቸው፡፡
ከኤርትራ ህዝብ ጋርስ ቢሆን ተራርቀን ልንቀር ነው እንዴ? ወንድሞቻችን ናቸው እኮ፡፡ ያው እርስዎ በገቡት ቃል መሰረት፤ “ዲፕሎማሲ” በሚሏት መርህ እልባት ፈልገው፣ ከወንድሞቻችን ጋር እንደሚያገናኙን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በባዕድ አገር በስደት ዓለም (በጥገኝነት) የሚኖሩ ወገኖቻችንን ወደ እናት ሀገራቸው ከመመለስ አኳያስ ምን አስበዋል? ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ወይስ እንደወጡ ይቀራሉ?
እንደ ማር ከሚጥመው ንግግርዎ ጋር ግርማ ሞገስዎም ማራኪ ነው፡፡ እንደ እርስዎ ሁሉን የተቸረው እስካሁን አላየሁም፤ በእውነት ታድለዋል። በርግጥ የፖለቲካ ሜዳ ባያገኝ ይሆናል እንጂ ሌላ ብዙ “አብይ” ይኖራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን እኮ እንደ እርስዎ ያለ  በየፈርጁ ብዙ የተማረና የተመራመረ የሰው ሀብት አለን፤ ግን አልተጠቀምንበትም፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን በአንድነታችን ላይ ብዙ መርዝ ተረጭቶብናል፡፡ መርዝ አምካኝ ያስፈልገናል። ታሪክን ወደሚመቻቸው መንገድ እየቆለመሙ፣ ወደ ትውልድ የረጩት የተዛባና የተበረዘ ማንነት መድሃኒት ያስፈልገዋል። ታዲያ ኢትዮጵያን ዳር እስከ ዳር ወደ አንድ ለመመለስ ዝግጁ ነዎት? የቁርጥ ቀን ጓድዎትና የአንድነት አቀንቃኙ አቶ ለማ መገርሳ አንድነትን ሲሰብኩ፤ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” እንዳሉት፣ የአንድነት ሱሳችንን ያስታግሱልንማ። ዘረኝነትን አከርካሪውን ይስበሩትማ፡፡ እርስዎ እንዳሉት፤ አንዳችን ለአንዳችን የምናስደነግጥ ሳይሆን ጋሻ መከታ መሆን አለብን። በመሆኑም የደፈረሰውን ሰላማችን እንዲጠራ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባርዎት ይመስለኛል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሚያስፈልገው የሰላም ፌስቲቫል ሳይሆን [ብሄራዊ እርቅ ነው]፤ አዎ ብሄራዊ እርቅ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ይህን ደብዳቤ ሳሰናዳ ድንገት አይቶኝ፣ ቃሊቲ መግባት ፈለክ ወይ አለኝሳ፤ እኔ ደግሞ በእርሳቸው ዘመን አይደረግም  ብዬ ተወራርጃለሁ። አደራ ውርርዴን ከንቱ እንዳያስቀሩብኝ፡፡
በአባይ ጉዳይስ ከግብጽ ጋር ጠንከር ያለ “ዲፕሎማሲ” አያስፈልግም ይላሉ? አንዳንድ ሰዎች ግብጽ እየዛተች ነው ይላሉ፡፡ አላወቀችንም ማለት ነዋ! ለምን ጣሊያንን አትጠይቃትም፤ ወይ ድፍረት! ለካ አያውቁንም አለ - ያ ዘፋኝ። አይ የኔ ነገር እንደተራ ነገር እረስቻት፤ ኧረ ሞት ይርሳኝ። ያዋጇስ ጉዳይ፣ ለ6 ወር ትቀጥላለች ወይስ ያሳጥሯታል? ለነገሩ ህዝቡ ራሱ አዋጁን አንስቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ለምን? እርስዎ ከተመረጡ በኋላ ሀገሪቱ ፍጹም መረጋጋት ላይ ናት፡፡ (ህዝቡ እርስዎ ላይ ብርቱ ተስፋ ስለጣለ ነዋ)፡፡  
ደግሞ ከፊት ለፊትዎ ምርጫ 2012 ተደቅኖብዎታል፡፡ እንዴት ሊያደርጉ አሰቡ? በተለመደው የምርጫ ስርዓት ነው የሚያስፈጽሙት ወይስ ማሻሻያ ያድርጉበታል? በእውነት ይኼ ትልቅ የቤት ስራ ነው፡፡ የምክር ቤት ተወካዮችስ እንዴት? ለምን? እያሉ ሞጋች ይሆናሉ ወይስ ተቃውሞ ሲባል “እጅ አይታየኝም” እየተባለ ነው የሚቀጥለው። በሙሉ ድምጽ ድጋፍ ማስወሰን ምን ጠቀመ? 27 ዓመት ሙሉ ሲጠራቀም የቆየው “አ…ሜ…ን” ባይነት ውጤቱ እነሆ ህዝባዊ አመጽ አፈነዳ። የዓለማችን ገዳይ በሽታ ሁሉን ነገር በጅምላ “አ…ሜ…ን” ብሎ መቀበል ነው። ህገ መንግስታችን ላይ እንደተቀመጠው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ3 ነገሮች (ለህዝብ፣ ለህገ መንግስቱ እና ለህሊናቸው) ተገዥ ናቸው ይላል። ከሁሉም በፊት ለህሊናቸው የሚገዙ አባላት ናቸው የሚያስፈልጉን፤ ለህሊናቸው ካልተገዙ ለህዝቡም ሆነ ለህገ መንግስቱ ሊገዙ አይችሉማ፡፡ ተቃዋሚ ሃይሎችን በተመለከተ እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን ወንድም እንደሚያዩአቸው ቃል ገብተውልናል፤ እንዴት ደስ ይላል፡፡
ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመጡ ስንት የቤት ስራ እንዳለብዎት ጠንቅቀው ያውቁታል። የመንግስት ሰራተኛው ቤት ያምጡ፤ ደመወዝ ያሻሽሉልን (መሰረታዊ ፍላጎቶቼን) ያሟሉልኝ….ምናምን እያለ መወትዎቱ አይቀርም፡፡ ነጋዴውስ ቢሆን ህገ ወጥ ንግድን ያስወግዱልን፣ ግብራችንም እንዳይጫንብን ማለቱ ይቀራል? ስራ አጡ ደግሞ የምተዳደርበት ስራ ይፈልጉልኝ ማለቱ አያጠራጥርም፡፡ ያው እርስዎ እንዳሉት፤ በወጣትነት ዘመን ለጫት የምንሰጠውን ጊዜ ለመጽሀፍ ካልሰጠን  መስመራችን ሳተ ማለት ነው። ወጣቱ ጫቱን ትቶ በስራና በንባብ ሱስ እንዲጠመድ ለማድረግ ምን አሰቡ? ይኼ ለሱስ የተገዛ ወጣት እንዴት እንደሚገዛልዎት እንጃ፡፡ ከባድ ፈተና ነው፤ሌትም ቀንም ያስቡበት፡፡
ከአንደበትዎ ሳይሰሰት የሚፈልቀው ቃል ማር ማር ይላል፡፡ በምሳሌ ቅመም ተከሽኖ ከአንደበትዎ የሚዘንበው ልዩ ትንታኔ እንዴት ይጥማል መሰልዎት። አፌን ከፍቼ አዳምጠዋለሁ ግን አልጠግበውም፡፡ አደራ ይህ ማር አንደበትዎ ወደ ሬት እንዳይቀየርብዎት፣ ወገብዎትን አስረው ሰርተው ያሰሩ፡፡ አለበለዚያ ያው…..፡፡ እርስዎ እኮ ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያመጡ ነው የሚጠበቁት፤ ካልሆነ ግን አንድም አቶ ኃይለማሪም ባሳዩት መንገድ አልያም በሙጋቤ መንገድ ስልጣንዎትን እንደሚለቁ እሙን ነው። ይጠራጠራሉ እንዴ? አይ አይጠራጠሩ፤ ካልሰሩ ወንበሩም ያስፈነጥርዎታል (አንድ ሰው ሰልችቶታላ)፡፡
“ከላይ ስትሆኑ ከላይ ባለው መነጸር ብቻ አትመልከቱ”፤ “ላይ ሆኖ የሚቀር የለም፤ መ…ፈ…ጥ…ፈ…ጥ ስለሚመጣ” የሚለው ንግግርዎ ይጣፍጣል። ይኼ እኮ ነው ትልቁ ነቀርሳ። እኔ ከደላኝ ሌላው የሚቸግረው አይመስለኝማ፡፡ “ሁሉም ከፍታ መነሻው ዝቅታ ነው፤ ሁሉም ከፍታ መጨረሻው ዝቅታ ነው”፤ “ተንጠልጥሎ የሚቀር የለም”፡፡ ምን ዓይነት ውብ አገላለጽ ነው፡፡ ይህን የሚያስብ ጭንቅላት ጠፍቶ እኮ ነው፣ ያ ሁሉ ትርምስ የተፈጠረው፡፡ እንደ ምንም አንዴ ወደ ስልጣን ከተንጠለጠለ ወደ ላይ እንጂ ወደ ታች አያይም። እሱ በምርጥ ቪላ ቤት የተንደላቀቀ ኑሮ ስለሚኖር ብቻ የቤት ችግር ያለ አይመስለውም። በህዝብ ገንዘብ በተገዛለት [የክት የዘወትር መኪና] ስለሚንሸራሸር የትራንስፖርት ችግር ለሱ አይገባውም። ርሃብ ነጭ ነው ቀይ ማለት ይጀምራል። የፈለገውን መርጦ ይመገባል፣ መርጦ ይጠጣል፤መርጦ ይለብሳል። ጦም አዳሪ ያለ አይመስለውም፤ እሱ ምን አለበት። እርስዎ እንዳሉት፤ የችግሩን ምንጭ ወደ ታች ማየት ያልቻለ ወደ የትም አይሸጋገርም፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ እንደራሴዎቻችን ፊት ቆመው፣ ቃል ኪዳን ከገቡ በኋላ ባደረጉት የኢትዮጵያን አንድነት የሚሰብክ ልዩ ንግግርዎ፣ ዓለም ዳር እስከ ዳር  ተደመመ፤  ስንቱ ኢትዮጵያዊ ተንሰቅስቆ አለቀሰ መሰለዎት፤ የኢትዮጵያዊነት ወኔው አገርሽቶበት፤ የኢትዮጵያዊነት ወኔው ነሽጦት ስንቱ በስሜት ሰከረ መሰለዎት። በትረ ስልጣንዎትን ከአቶ ኃይለ ማርያም በሰላም ሲቀበሉ መላው ዓለም እያጨበጨበላት ኢትዮጵያ ዳንኪራ መታች፤ ይገባታል፡፡ ማህጸኗም ትልቅ ኩራት ተሰማው። እነሆ በአፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ምርጫ ስርዓት አዲስ አበባ ላይ ዕውን ሆነ፡፡ ቃል ጉልበት አለው - ይተክላል ይነቅላል፤ ትውልድ ይፈጥራል፤ ትውልድ ይነቅላል…ኢትዮጵያ የምትሰራውና የምትፈርሰው በቃል ነው፤ ይህ የእርስዎ ትንታኔ ነው፡፡ ህዝቡ የተገባለት ቃል ሲፈርስበት አይወድም፤ ያንገሸግሸዋል፡፡ ነጩን ነጭ ጥቁሩን ጥቁር እንዲባልለት ይፈልጋል። የሚቻለውን ይደረግልሃል፣ የማይቻለውን አይደረግልህም ከተባለ  ህዝብ ምንም አይልም እኮ፡፡ አበው ሲተርቱ፤ አትቁም ያሉት ለማኝ ከሰጡት ይቆጠራል ይላሉ። በዚህ ጊዜ መንገድ ይሰራልሃል፤ ፋብሪካ ይተከልልሃል ብሎ ቃል ገብቶ “ላሽ” የሚልበትን አይወድም፡፡ ጀምሮ መጥፋትን እንደ ማረጋጊያ መጠቀም ትልቁ በሽታችን ነው። ጀምሮ ከመጥፋት ይሰውርዎትማ። “የኛ ሀገር ከእናት  አባት የወረስነው ሳይሆን ከልጆቻችን የተዋስነው ነው”። ይኼ ወርቃማ ንግግርዎ ምን ያህል ለቀጣዩ ትውልድ ማሰብ እንዳለብን ያሳያል። በተጨማሪም “እወቀት ለሰው ልጅ የተሰጠ ውድ ስጦታ ነው” ብለውናል። እርስዎም የተሰጠዎትን ስጦታ (እውቀት) ድህነትንና ዘረኝነትን ለመደምሰስ ይጠቀሙበትማ፡፡ ዘረኝነትን በደማሚት ያፍርሱትና እንደ ድሯችን አንድ እንሁን፡፡ ኧረ ዘረኝነት ይውደም!  
የኢህአዴግን ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቀው ማወቅዎን፤ እጅግ የተማሩና የተመራመሩ መሆንዎን ሳስብ ዴሞክራሲን ያለማምዱናል፤ አንጸባራቂ ለውጥ ያመጡልናል ብዬ አስባላሁ። ከአንዳንድ ነባር “ጓዶች”ዎ የሚገጥምዎትን ግፊት ሳስብ ደግሞ በእጅጉ እጠራጠራለሁ፡፡ ካልታዘልኩ አላምንም አለች ሙሽራ፡፡ በሙስና የጨቀዩ አንዳንድ ነባር ጓዶችዎትን በአዲስ መተካት (ካቢኔዎትን እንደገና ማዋቀር) ከባዱ ፈተናዎት ይመስለኛል፤ ያን ካላደረጉ ደግሞ ለውጥ የማምጣትዎ ጉዳይ በጥያቄ ምልክት ወስጥ ነው፡፡ አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ  አይሆንማ፡፡ የጋራ ርብርብ ይጠይቃላ፡፡ አንድ እንጨት ብቻውን ይነዳልን? በአንድ እጅስ  ማጨብጨብ ይቻላልን? አ…ይ…ቻ…ል…ም፡፡
ክፉኛ ወግ አበዛሁብዎት መሰለኝ፤ ወግ ቢበዛ በአህያ አይጫንም ይላል የአገሬ ሰው። ልሰናበትዎት ነው፡፡ በደረቁ አልለይዎትም፤ “ፈረሱም ይኸው ሜዳውም ይኸው” የሚለውን ሙዚቃ ይጋበዙልኝማ። እርስዎም ወጉ ደርሰዎት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ያብቃዎ፡፡ ኢትዮጵያም እንኳን በዶክተር ለመመራት አበቃሽ! መልካም የስልጣን ዘመን ይሁንልዎ! ወደፊትም “ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር” በሚል ደብዳቤ የልብ የልባችንን እናወጋለን፡፡ ቀጥልበት ይበሉኝማ፡፡
ሰላም አይለየን!!

Read 4909 times