Saturday, 14 April 2018 14:25

“አምጣ!” እና “አምጪ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ዶሮ ሰርቆ ሊናዘዝ አንድ ቄስ ዘንድ ይሄዳል፡፡
ተናዛዥ፡— ከአንድ ግቢ የሆነች ዶሮ ሰርቄያለሁ፡፡
ቄስ፡— ይሄ ትልቅ ስሀተት ነው፡፡
ተናዛዥ፡— እርሶ ዶሮዋን ይቀበሉኛል?
ቄስ፡— በምንም አይነት አልቀበልህም፡፡ ይልቅ ለሰረቅኸው ሰው መልስለት፡፡
ተናዛዥ፡— ግን ለእሱ ዶሮህን ውሰድ ብለው አልቀበልም አለኝ፡፡
ቄስ፡— እንግዲያው ለራስህ አድርገው፡፡
ተናዛዥ፡— አመሰግናለሁ አባቴ፡፡
(ቄሱ ማታ ቤት ሲመለሱ ለካስ የተሰረቀው የራሳቸው ዶሮ ነበር፡፡)
የራስ ያልሆነ ነገር መፈለግና በሆነ መንገድ ለመውሰድ መሞከር እንደ ታሪክ የሚወራ ሳይሆን የእለት ከእለት ድርጊት እየሆነ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ ‘ሊናዘዝ’ ሳይሆን እንደተለመደው አቤቱታውን ለማቅረብ የአንድዬን በር ያንኳኳል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይኸው ደግሞ መጥቼ በርህን አንኳኳሁ……
አንድዬ፡— አንተ ማነህ?
ምስኪን ሀባሻ፡— እኔ ነኛ አንድዬ፣
አንድዬ፡— ዝም ብለህ እኔ ነኛ ብትል በምን ላውቅህ ነው… እከሌ ነኝ አትለኝም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ ተው አንድዬ፤ እኔ ግራ ገብቶኝ እንድታጽናናኝ አንተ ዘንድ ብመጣ፣ ሞራሌን እንዲህ ቀሺም ቡድን መከራዋን ያበላት ኳስ አታድርገኝ!
አንድዬ፡— ከዚህ ሁሉ ማንነትህን መግለጹ አይሻልም …
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ… ወዳጅህ ምስኪን ሀበሻ ነኛ! የአንተን ስም በቀን ሠላሳና አርባ ጊዜ ካላነሳሁ እንቅልፍ የማልተኛ ምስኪን ሀበሻ ነኝ! በአንተ ስም…
አንድዬ፡— በቃ፣ ይበቃል… አወቅሁህ
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ… ይህን ያህል ረስተኸኛል?
አንድዬ፡— አዎ፣ ያን ያህል እየረሳኋችሁ ነው… ደግሞም አውቄ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በእውነቱ ይሄንን ከአንተ አልጠብቅም ነበር፡፡ አንተን  በምንፈልግበት በወሳኝ ሰዓት እንዲህ ከአእምሮህ አውጥተህ ትወረውረናለህ ብዬ አላስብም ነበር፡፡
አንድዬ፡— እውነት!…ለምን?
ምስኪን ሀበሻ፡— ለምን አንድዬ! ለምን ነው ያልከኝ?
አንድዬ፡— አዎ ለምን ነው ያልኩህ። እናንተ ምንድናችሁና ነው ከሀሳቤ አውጥቼ የማልወረውራችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ፍጡሮችህ ነና! የምትወደን ፍጡሮችህ ነና!…
አንድዬ፡— እርግጠኛ ለመሆን እሱን እንደገና እየመረምረኩ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን?
አንድዬ፡— የእኔ ፍጡር መሆናችሁን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ ተው! ኸረ ተው በዚህ የከፋ ኑሮ፣ በዚህ የተወሳሰበ ዘመን፣ በዚህ ግራ የገባው ጊዜ እንደማጽናናት ተስፋ አታስቆርጠን አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— ለምን ተስፋ ትቆርጣላችሁ… አሁን እኮ ለእናንተ እንደ ፈጣሪ አላስፈልጋችሁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን እያልከኝ ነው!…ምን ያህል ብንበድልህ ነው ይሄን ያህል ያመረርከው?
አንድዬ፡— አላመረርኩም…እናንተ ግን ክዳችሁኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛ! እኛ አንተን ክደን የት ልንገባ!
አንድዬ፡— ተው እንጂ፣ አፍ አውጥታችሁ አትበሉት እንጂ ክዳችሁኛል…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተ ላልከው የእኔ ልብ በፍርሀት ልትሰነጠቅ ነው፡፡ አንተን ክደን ሌላ አምላክ ልንፈጥር!
አንድዬ፡— አሁን ዋናው አምላካችሁ ገንዘብ ሆኗል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ቆይ ልጨርስ…ፈጣሪያችሁ ገንዘብ ሆኗል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— ተው እንጂ ምስኪኑ፣ ሁልህም የምትሰግደው ለገንዘብ አይደለም እንዴ! የምታደገድጉት ለባለገንዘብ አይደለም እንዴ…ገንዘብ እስካገኛችሁ ድረስ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማትሉ አይደላችሁም እንዴ! በል ይህንን ካደኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያ ገንዘብ የማይወድ አለ እንዴ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— ላይኖር ይችላል፣ የእናንተ ግን እኮ መውደድ ሳይሆን ማምለክ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አሁን ኑሮ እንዲህ በከበደበት ዘመን ገንዘብ ብናሳድድ ምን ይገርማል! የምግብ ፍጆታ በየሳምንቱ ሳይሆን በየቀኑ በሚባልበት ሁኔታ ዋጋ ይጨምራል…ዛሬ በሠላሳ ብር የተገዛ እቃ ከነገ ወዲያ ሀምሳ ብር ይሆናል፡፡ ዛሬ…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ…ይሄ በመጣህ ቁጥር የምትጨቀጭቀኝን፣ይሄ ተወደደ፣ ያ ጣራ ነካ የምትለውን ነገር ተወኝ፡፡ እኔ ያልኩት ስለተራባችሁ፣ ስለታረዛችሁ ብቻ ሳይሆን ሞልቶ ተርፏችሁም በቃኝ አታውቁም፡፡ ጭራሽ ሌላውን ነጠቃ ትገባላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያ እንደዛ የሚያደርጉት ጥቂቶች ናቸዋ…
አንድዬ፡— አይ፣ ጥቂት!… በየቦታው ምንም የሌላቸውን “አምጣ፣ አምጪ” ስትሉ አይደለም እንዴ የምትውሉት! መታያ ካልተሰጣችሁ፣ ትንሽ ገንዘብ ጣል ካልተደረገላችሁ ሥራችሁን እንኳን መሥራት ያቆማችሁበት ጊዜ አይደለም እንዴ! እውነቱን ንገረኝ ካልክ የምታደርጉት ግራ ስለገባችሁ ነው እንጂ ለመተንፈስም ሰውን ክፈል ትሉት ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔ’ኮ መካዴ ሳይሆን እንዲህ የሚያደርጉት…
አንድዬ፡— አንተ እንዲህ አድርገህ አታውቅም?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አንድዬ! የሰው ገንዘብ መውሰድ?
አንድዬ፡— አዎ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንኳን ልወስድ ሌሎች ለሚሠሩትም ስቅጥጥ ይለኛል፡፡
አንድዬ፡— እንደው ምንም ወስደህ አታውቅም?
ምስኪን ሀበሻ፡— በእርግጥ አልፎ፣ አልፎ በሥራዬ ተደስተው ሲሰጡኝ እቀበላለሁ..
አንድዬ፡— እምቢ ግን አትልም…
ምስኪን ሀበሻ፡— ለምን ብዬ አንድዬ፣ ለምን ብዬ እምቢ እላለሁ?
አንድዬ፡— የአንተ ገንዘብ አይደለማ…ለምትሠራው ሥራ ደሞዝ ይከፈልህ የለም እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡— በእርግጥ ይከፈለኛል…ግን አኮ ስጡኝ ሳልላቸው ነው የሚሰጡኝ!
አንድዬ፡— የሚሰጡህ እኮ ምናልባት ሌላ ቀን ሲመለሱ ጉዳያቸውን እንዳትጎትትባቸው ሊሆን ይችላል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንደዬ…
አንድዬ፡— ስማኝ… የአንተ ምናልባት አሁን ይህን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ይለምድብህና ወደፊት ሰው የማይሰጥህ ከሆነ ራስህ አምጡ ማለት ትጀመራለህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— በጭራሽ! አንድዬ፣ በጭራሽ…መቼም ቢሆን እንዲህ አላደርግም፡፡
አንድዬ፡— ብቻ …ሰው የራሱን ያልሆነ ገንዘብና ንብረት በጉልበትም ይሁን በማታለል ለማግኘት የሚሄድበት ርቀት እኔንም ቢሆን እያስደነገጠኝ ነው…እንደውም ያስፈራል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንዲህ ሲከፋኝ፣ እንዲህ ሆድ ሲብሰኝ፣ እንዲህ ነገር ሁሉ ግራ ሲገባኝ አንተ ያላጽናናኸኝ፣ አለሁልህ ያላልከኝ ማን ሊለኝ ነው?
አንድዬ፡— የእኔን ማጽናናት ከፈለጋችሁ ይሄ የላይ፣ ላይ ድራማችሁን ተዉና እስቲ መጀመሪያ እናንተው “አምጣ”…“አምጪ” መባባሉን ተዉና ከልባችሁ ‘አንተ ትብስ/ አንቺ’ ተባባሉ፡፡ ከዛ በኋላ ኑና በጎደለ ሙላልን በሉኝ፡፡ እናንተ ሌላውን መክተቻ ጉድጓድ እየቆፈራችሁ፣ እናንተ ካብ ለካብ እየተያያችሁ እኔን አትጨቅጭቁኝ፡፡
እግረ መንገድ…ሰውየው ጓደኛውን “ሬድዮ የተጀመረው በገነት ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፤ ይሄንን ታምናለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ሬድዮ የተጀመረው ገነት ነው ብሎ የነገረህ ሰው፤ከአዳም ጎን አንድ የጎድን አጥንት ተወስዶ የመጀመሪያው ድምጽ ማጉያ የተሠራበትን ጊዜ እያስታወሰ ነው” ብሎት አረፈ አሉ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Read 2799 times