Print this page
Saturday, 14 April 2018 14:10

“ማዕከላዊ” መዘጋቱ ምን አንደምታ አለው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 (“ማዕከላዊ”ን የሚያውቁ ፖለቲከኞች ስጋት አላቸው)

    በሦስት መንግሥታት በዋና የምርመራ ማዕከልነት ያገለገለውና ፒያሳ፣ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ (አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን) አጠገብ የሚገኘው “ማዕከላዊ” ባለፈው ሳምንት አርብ በይፋ መዘጋቱ የተገለጸ ሲሆን እስረኞችም ለጊዜው አጠገቡ ወደሚገኘው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ መዛወራቸው ተነግሯል፡፡ አዲሱ የፌደራል ምርመራ ቢሮም፤ ካዛንቺስ ወደሚገኘው የቀድሞ ዮርዳኖስ ሆቴል ህንፃ  መዛወሩ ተገልጿል፡፡
በደርግ ዘመንም ሆነ በአሁኑ መንግስት በማዕከላዊ የመታሰር ክፉ ዕጣ የደረሳቸውና የተለያዩ የስቃይ ምርመራዎች እንደተፈጸሙባቸው የሚጠቅሱ በአብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑ ግለሰቦች፤ የማዕከሉ መዘጋት ተገቢ ነው ይላሉ - ከመዘግየቱ በቀር፡፡ ይሄ ማለት ከእንግዲህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የስቃይ ምርመራ አይፈጸምም ማለት ላይሆን እንደሚችል ፖለቲከኞቹ  ያሰምሩበታል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ማዕከላዊን በመዝጋት ሙዚዬም ለማድረግ መንግስታቸው መወሰኑን ሲገልጹ፣ በማዕከሉ ሲፈጸሙ የነበሩ ኢ-ሰብአዊ የማሰቃያ መንገዶች ከእንግዲህ ወዲያ እንደማይፈጸሙ ያሉት ነገር እንደሌለ በማስታወስ፣ ይሄም በአዲሱ ቢሮ ተመሳሳይ የስቃይ ምርመራ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ፡፡ ለመሆኑ ስጋታቸው ከምን መነጨ?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በተለያየ ጊዜ በማዕከላዊ ታስረው የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪያንና የህግ ባለሙያዎች በማዕከላዊ መዘጋትና በአዲሱ የምርመራ ቢሮ ዙሪያ ያላቸውን ጥርጣሬ፣ አስተያየትና የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

      
        “መቀየር ያለበት አስተሳሰቡና ድርጊቱ ነው”
           አቶ የሸዋስ አሰፋ (የ”ሰማያዊ” ፓርቲ ሊቀመንበር)

   ማዕከላዊ ስሙ ገነነ እንጂ በሀገሪቱ ብዙ የምርመራ ማሰቃያ ቦታዎች አሉ፡፡ ከማዕከላዊ በፊት አይናችንን ተሸፍነን የምንወሰድባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ፡፡ ይሄን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ለመፈፀም ገፊ ምክንያት የሚሆነው ደግሞ የሽብር እንቅስቃሴ፣ህገ መንግስት ለመናድ፣ ስርአት በኃይል ለመለወጥ የሚሉ የክስ መነሻዎች ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ሃሳቦች ነው በመጀመሪያ ማስተካከል የሚገባው እንጂ አንድ በጃንሆይ ዘመን የተሰራን ቤት ዘግቶ አዲስ ቤት መክፈት ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡
ለኔ አዲስ የምርመራ ቢሮ ማለት የቦታ ለውጥ እንጂ ለድርጊት ለውጥ ማስተማመኛ ሊሆነኝ አይችልም፡፡ ዋናው አያያዙ ነው መቀየር ያለበት። ለምሳሌ እኔ ስታሰር ወደ 17 የሚጠጉ ፖሊሶች ናቸው መጥተው የያዙኝ፡፡ የፍ/ቤት ወረቀት እንኳ አሳዩኝ ስላቸው፣ “አሸባሪ” ብለው ስለደመደሙ ማዋከብ ውስጥ ነው የገቡት፡፡ ስለዚህ ለውጡ መጀመር ያለበት ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ነው እንጂ ያረጀ ቤትን በመዝጋት አይደለም፡፡
አዲሱ የምርመራ ማዕከል ለወደፊት ምን ሊመስል ይችላል ከተባለ፣ማየት ያለብን ቤቱን፣ ሰዎቹንና ህጎችን ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ህጎቹን ብንመለከት የፀረ ሽብር ህጉ አለ፡፡ በዚህ ህግ የተጠረጠረ ወንጀለኛ፣ አሸባሪ ተደርጎ ነው የሚደመደመው፤የተጠርጣሪነት መብት እንኳ የለውም፡፡ ይሄ መቀየር አለበት፡፡ ሰዎቹን ስንመለከት እንግዲህ ብዙ በማዕከሉ የታሰሩ ግለሰቦች እንደሚናገሩት፤ጥፍር መንቀል፣ ሽንት መጠጣት፣ በቀዝቃዛ ነገር ተመትቶ ራስን መሳት-- የመሳሰሉ ማሰቃየቶች ተፈጽሞባቸዋል፡፡ እኛም የደረሰብን ነገር ነው፡፡ ይህን ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎች፤ ወደ አዲሱ ቢሮ ከመጡ ለውጥ የለውም፤ያው ነው፡፡ ቢሮው ተቀየረ እንጂ ሰዎቹ አልተቀየሩም፡፡ እነሱ እስካሉ ድረስ ምንም ነገር አይለወጥም፡፡
ያለ ህግ ሰዎችን መያዝ፣ በምርመራ ወቅት ማሰቃየትን ክልክል የሚያደርግ፣ ድርጊቱንም የፈፀሙ መርማሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ እስካልወጣ ድረስ ለውጥ አይመጣም። ማዕከላዊ ምሳሌ እንጂ ብቸኛው ማሰቃያ ማዕከል አልነበረም፡፡ ዋናው የፍትህ ተቋማትን ነፃ ማድረግ ነው እንጂ ህንፃ መቀየር አይደለም። ህንፃው መቀየሩ ምናልባት በቤቱ የአሰራር ባህሪ የተነሳ የሚደርሰውን ስቃይ ሊቀንሰው ይችላል። ለምሳሌ እኔ ስታሰር የነበርኩበት ቤት ቀዝቃዛ ነበር፣ ውሃ ያመነጫል፡፡ በቅዝቃዜው ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ  የግራ እግሬን ያመኛል፡፡ ምናልባት አዲሱ የምርመራ  ቢሮ እንዲህ ያሉ ሆነ ብለው ለማሰቃየት የሚሰሩ ቤቶች ከሌሉበት መልካም ነው፤ እንደሌሉት ግን አሁንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ መሰረታዊ ለውጥ የሚባለው አስተሳሰብ፣ አሰራሮች፣ ህጎችና የተቋማት ነፃነት ሲስተካከሉ ብቻ ነው፡፡

------------

        “ሰብአዊ መብት በመፈክርና በስብሰባ አይከበርም  
               አበበ ቀስቶ (ክንፈሚካኤል ደበበ) (ፖለቲከኛ)

    ዋናው ቁም ነገር አሰራርን ማስተካከል እንጂ ማዕከል የመዝጋትና ሌላ አዲስ ማዕከል የመክፈት ጉዳይ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ምርመራውን የሚያካሂዱ ግለሰቦች ወትሮ በለመዱት አሰራር መቀጠል እንዳይችሉ ማድረግ ነው፡፡ ዋናው ለውጥ አስተሳሰብ እንጂ ህንፃ አይደለም መሆን ያለበት፡፡ አስተሳሰቡ ሳይቀየር ቤቱ ቢቀየር ጥቅም የለውም፡፡ ኋላ ቀር የሆነው የምርመራ ባህልና፣ የእስረኞች አያያዝ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስር ነቀል ለውጥ አድርጎ መቀየር ነው ውጤት የሚያመጣው፡፡
ለኔ አሁንም ፕሮፓጋንዳው ነው የገነነው እንጂ ማዕከላዊ ተዘግቷል የሚያስብል አይደለም። ዮርዳኖስ ሆቴል ላይ የተሰራው ቢሮ እንጂ ማቆያ ማዕከል ያለው አይመስለኝም፡፡ ማቆያው አሁንም እዚያው ማዕከላዊ አጠገብ ያለው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ማዕከላዊ ተዘግቷል ሲባል፣”ቤቱ ነው የፈረሰው ወይስ አስተሳሰቡ?” የሚለውን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ለዚህች ሃገር የፍትህ ስርአት ግንባታ ጠቃሚው፣ ህንፃ መዝጋት ሳይሆን አስተሳሰቡንና አሰራሩን መቀየር መቻል ነው፡፡
አሰራሩ መቀየር አለበት ሲባል ለምሳሌ፡-ማስረጃ የሚሰበሰበው ሰውየው ከታሰረ በኋላ እየተደበደበ ነው፡፡ አንድ ሰው ሲታሰር ማስረጃ ተሰብስቦበት አይደለም፡፡ ከታሰረ በኋላ ነው “እንዲህ ታደርጋለህ አይደል?” እየተባለ የሚደበደበው፡፡ አንድ ተጠርጣሪ መያዝ ያለበት በቂ ማስረጃ ከተያዘ በኋላ ነው፡፡ እየተደበደበ እንዲያምን ማድረግ ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡ ይሄ አሰራር ነው ጨርሶ መቀየር የሚገባው፡፡ መርማሪዎቹም ስልጠና ማግኘትና አስተሳሰባቸው መለወጥ አለበት፡፡
እስከ ዛሬ እየደበደበ ኢ-ሰብአዊ ምርመራ ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰ ሰው ሰምተን አናውቅም። ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰብአዊ መብት በመፈክርና በስብሰባ አይከበርም፡፡ መሬት ወርዶ በሚሰራ ህግ ነው ሰብአዊ መብት የሚከበረው፡፡

---------------

            “ማዕከላዊ፤ የጭቆና ሐውልት በመሆኑ መዘጋቱ ያስደስተኛል”
              በፍቃዱ ኃይሉ (ጦማሪና ጋዜጠኛ)  

   ማዕከላዊ መዘጋቱ ያስደስተኛል፡፡ ምክንያቱም ለስቃይ ምርመራ ትዕምርት (Symbol) የሆነ ቦታ ነው፡፡ ለሦስት ስርዓተ መንግሥታት የጭቆና እምብርት ሆኖ አገልግሏል፡፡ እዚያ ውስጥ ነው የፖለቲካ ሰዎች ከፍተኛ የስቃይ ጊዜ የሚያሳልፉት፣ ክሳቸውም የሚቀመመው እዚያ ቦታ ላይ ነው። ብዙ በደል ነው በቦታው የሚደርሰው፡፡ ከዚህ አንፃር መጥፎ ትዕምርት ነው ሆኖ የቆየውና፣ይህ ትዕምርት ነው አብሮ የሚዘጋው፡፡
ከዚያ በመለስ ግን ማዕከላዊ ስሙ ገነነ እንጂ ከባባድ ማሰቃየቶች የሚፈፀሙት ከዚያ ውጪ ባሉ ቦታዎች ነው፡፡ ብልት ላይ ውሃ የተሞላ ላስቲክ ማንጠልጠል፣ ጥፍር መንቀል የመሳሰሉት ነገሮች የሚፈፀሙት ሌላ ቦታ ነው፡፡ እኔ ራሴ ቃለ ምልልስ ያደረግሁላቸው ሰዎች፤ አይናቸውን ተሸፍነው የሚገቡባቸው ያልታወቁ ቦታዎች እንዳለ ነግረውኛል። እኔ ማዕከላዊ ታስሬ ስገባ ያገኘኋቸው ታሳሪዎችም ይሄን አረጋግጠውልኛል፡፡ ለምሳሌ ከኛ ጋር እኩል የተያዘ አንድ ታሳሪ፤ ከ17 ቀን በኋላ ነው ወደ ማዕከላዊ መጥቶ የተቀላቀለን፡፡ ልጁ ሲነግረን ከአዳማ ታስሮ ሲመጣ አይኑን ተሸፍኖ የማያውቀው ቦታ ነው የገባው። ግቢውን አያይም፣ የት እንዳለም አያውቅም ነበር፡፡ ሌሎችም ይህ ድርጊት የተፈፀመባቸው አሉ፡፡ ስለዚህ ትልልቅ ማሰቃየቶች የሚፈፀሙት ከማዕከላዊ ውጪ ባሉ ቦታዎች ነው፡፡ ማሰቃየት በማዕከላዊ መዘጋት ብቻ ይቆማል የሚል ግምት የለኝም፡፡
አዲስ የምርመራ ቢሮ ሲሆን ምናልባት ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን ከምናያቸው ነገሮች አንፃር አስተሳሰቡ አልተቀየረም፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ማዕከላዊ እንደሚዘጋ ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው፤ “ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን” ነው ያሉት እንጂ “እኛም ተጠቅመንበታል” አላሉም፡፡ ችግሩ መኖሩን አለማመን ደግሞ ለመፍትሔ አለመዘጋጀትን ነው የሚያመለክተው፡፡ ማዕከላዊ በዘመነ ኢህአዴግ ማሰቃየት ሲፈፀምበት እንደቆየ ቢያምኑ ነበር አዲሱ ማዕከል ላይ ተስፋ ማድረግ ይቻል የነበረው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ባልተለወጡበትና አስተሳሰብ ባልተለወጠበት ሁኔታ አዲስ ነገር መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በይፋ የማይታወቁ ማቆያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መዘጋት አለባቸው፡፡ በየፖሊስ ጣቢያ ባሉት ማዕከላት ደግሞ ምርመራ ሲካሄድ፣ግለሰቡ በጉልበት እንዲያምን ነው የሚደረገው፡፡ ይሄን አሰራር ማስቀረት የሚቻለው ፖሊሱን በማሰልጠን ወይም ፖሊሱን ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ በማዘጋጀት ነው፡፡ ሌላው መፍትሄ ደግሞ በየጣቢያው ቢያንስ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ኮሚሽን ቢሮዎችን መክፈት ነው። እነዚህ ቢሮዎች በቀጥታ ታሳሪዎችን የሚያነጋግሩ ሆነው ከተዘጋጁ ለውጥና መሻሻል ሊመጣ ይችላል፡፡ ማረሚያ ቤቶችም ውስጥ በተመሳሳይ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ቢሮዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡

------------
               “ዋናው የሥቃይ ምርመራን ማስቆም ነው”
                 ዳንኤል ሺበሺ (ፖለቲከኛና ጦማሪ)


    ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እንደሚባለው ሁሉ የቀድሞ ማዕከላዊን ዘግቶ ሌላ ማዕከላዊ ነው የተከፈተው፡፡ ይሄ አልጋ መቀያየር ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ በሀገሪቱ ማዕከላዊን የሚያስንቁ ብዙ ማጎሪያና ማሰቃያ ቤቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ማዕከላዊ ተዘጋ ተብሎ እስረኞች የተዘዋወሩት እዚያው አጠገቡ ወደሚገኘው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡ አሁንም የስቃይ ምርመራ እዚያም የማይፈፀምበት አሳማኝ መመሪያ ሲተላለፍና ወደ ተግባር ሲወርድ አላየንም፡፡ ዋናው ጉዳይ ደግሞ ህንፃ መቀያየር ሳይሆን የስቃይ ምርመራን ማስቆም ነው፡፡ በሰው ልጅ ሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው ሙሉ ለሙሉ መቅረት ያለበት፡፡
ኢህአዴግ አለ፤ መርማሪዎቹም አሉ፤ አስተሳሰቡም አለ፤ ፍ/ቤቱ  አለ፤ መዋቅሩም እንዳለ ነው ያለው፡፡ ታዲያ ከአዲሱ የምርመራ ቢሮ፣ ምን የተሻለ ነገር ይጠበቃል? ለኔ ያው ነው፤ አዲስ ነገር ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ እኔ ለምሳሌ ቦሌ ፖሊስ ጣቢያ ታስሬያለሁ፤ ማዕከላዊ ታስሬያለሁ፤ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሬያለሁ፤ ክፍለ ሃገር ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሬያለሁ፡፡ ማዕከላዊ የሚፈፀመው የምርመራ ስልት በሙሉ በእነዚህ ቦታዎች ሲፈፀም አይቻለሁ፤ ደርሶብኛልም፡፡ ታዲያ የማዕከላዊ መዘጋት ምን ለውጥ ያመጣል? ትልቁ ጥያቄ፤እንደ ሀገር የስቃይ ምርመራ ቆሟል ወይ ነው፡፡ ለውጥ መጥቷል ሊባል የሚችለው ይህ እውን ሲሆን ነው፡፡
ትልቁ ቁም ነገር ህንፃውን መቀየር ሳይሆን ድርጊቱን ማስቆም ነው፡፡ ውጤት የሚመጣው ሰዎቹን መቀየርና ሰብአዊነት በሚሰማቸው መተካት እንዲሁም አስተሳሰቡን በሌላ በጎ አስተሳሰብ መለወጥ ሲቻል ነው፡፡
እላይ ያለው የመንግስት አስተዳደር ሰብአዊ መብትን ማክበርና ለሰብአዊ መብት መከበር በቆራጥነት መቆም ሲጀምር ነው ህግ በሀገሪቱ ላይ ሰርቶ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ በተለይ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከተሾሙ ወዲህ ብዙ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በኔ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን አገር፤የህግ አገር ማድረግ  ሲችሉ ነው የለውጥ ጭላንጭል ልናይ የምንችለው፡፡ ለኔ አንድ ሰው ዋጋ አለው፡፡ ማንዴላ አንድ ሰው ነው፤ ከኤኤንሲ ፓርቲ ተሻግሮ ብዙ ቁም ነገር ሰርቷል፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አብይም የዚህ አይነት ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቃል፡፡ በተለይ የሰብአዊ ክብርና መብት አያያዝ ላይ ለውጦች በስፋት  መምጣት አለባቸው፡፡  

-----------

           “መቀየር ያለባቸው የሥቃይ ምርመራ የሚፈፅሙት ናቸው”
             አቶ ወንድሙ ኢብሣ (የህግ ባለሙያ)

     በዓለም ላይ አስቸጋሪ እስር ቤት የሚባለው ጓንታናሞ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ማዕከላዊ፡፡ እኔም በደርግ የመጨረሻ ዘመናት ታስሬበታለሁ። ግፍንም ቀምሼበታለሁ፡፡ ስቃዩ የሚፈፀመው በቤቱ በራሱ ሳይሆን በመርማሪዎች ነው። እነዚህ መርማሪዎች “ከቤ” ነው የሚባሉት። አንድ ተጠርጣሪ ቃሉን መስጠት ያለበት በራሱ ፍቃደኝት እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 27 ያስቀምጣል፡፡ ቃሉን ለመስጠት ካልፈለገም ዝም ማለት መብቱ ነው ይላል፤ ህጉ፡፡ ነገር ግን መርማሪዎቹ በድብደባና በተለያዩ ማሰቃያዎች፣ደም አስተፍተው ነው የሚመረምሩት፡፡ እኔ ላለፉት አስርት ዓመታት ከያዝኳቸው 600 ያህል የሽብር ተከሳሽ ደንበኞቼ አብዛኛዎቹ የነገሩኝና ለፍ/ቤትም ያስረዱት ጉዳይ ነው፡፡
ተጠርጣሪዎች በየችሎቱ “ደማችን እየፈሰሰ ነው የተመረመርነው፤ብልታችን ተኮላሽቷል” እያሉ ነው ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩት። ስለዚህ ታሳሪዎች ስቃይ የሚደርስባቸው በመርማሪዎቹ እንጂ በህንፃው ብቻ አይደለም። ስለዚህ የስቃይ ምርመራ ፈፃሚዎች ናቸው ከስራው መገለል ያለባቸው፡፡ በምትካቸው ሰብአዊነትን መሰረት አድርገው በመስቀለኛ ጥያቄዎች ብቻ የሚመረምሩ፣ የበሰሉ ሙያተኞች መስራት አለባቸው፡፡ በቴክኒካዊ ምርመራ እንጂ በዱላ የሚያሳምኑ መርማሪዎች ከስራው ገለል መደረግ ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ መርማሪዎች ታዘው ለፈፀሙት ድርጊት መንግስት ህዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ማዕከላዊ ተዘጋ ማለት የምንችለው ቢሮው ወደ ካዛንቺስ ስለዞረ ሳይሆን “ከቤዎች” ስራቸውን ሲያቆሙ ብቻ ነው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚህ ረገድ ለውጥ ያመጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ከአነጋገራቸው እንደተረዳሁት ሰብአዊነት አላቸው። ኢትዮጵያን ፈጣሪ አስታውሷታል የሚል እምነት ያለኝ፡፡ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው ያላቸው ስልጣንና ኃላፊነት በይፋ በአዋጅ ተነጣጥሎ መቅረብ አለበት፡፡ ይሄ ሲሆን ነው የምንፈልገው የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት የሚመጣው፡፡

Read 3097 times