Sunday, 01 April 2018 00:00

የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ተግዳሮቶችና ተስፋዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 “በኢህአዴግ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስምሪት ጉዳይ ብቻ ነው”

    የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ፅ/ቤት በድረ ገፁ ላይ “ጠቅላይ ሚኒስትር ኢህአዴግ ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ ”በምርጫ አሸንፎ ይህቺን ሃገር የመምራት ሃላፊነት የተረከበው ኢህአዴግ ነው፡፡ ተወዳድሮ ያሸነፈው የኢህአዴግ ፕሮግራም ነው፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው ኢህአዴግ ነው፡፡ ሰው በሰው ሊተካ ይችላል፡፡ የሚቀጥለው ግን መስመሩና የድርጅቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡ ለውጥ የሚያመጣው ግለሰብ ሣይሆን የጠራውና በተግባር ተፈትኖ ውጤታማነቱ የተረጋገጠው የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመር ብቻ ነው! ለዚህም ነው ለኢህአዴጎች የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ትልቅ  አጀንዳቸው ሊሆን የማይችለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስምሪት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ፕሮግራም፣ ከሁሉም በላይ መስመር፣ ከሁሉም በላይ ውድ ዋጋ የተከፈለበት የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር፡፡ ከኢህአዴግ የተለየ ፕሮግራም የሚፈፅም ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመጣ የሚችለው ከኢህአዴግ ውጪ ብቻ ነው” ብሏል፡፡
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በበኩላቸው፤ የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታትም ሆነ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ኢህአዴግ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣት አለበት፤አለዚያ ግን የጠ/ሚኒስትሩ ለውጥ ምንም ትርጉም አይኖረውም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ኢህአዴግ  ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም የሚተካ አዲስ ጠ/ሚኒስትር እንደሚመርጥ እየተጠበቀ ነው፡፡ አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ እየተናጠች በምትገኝበት ሰዓት በጠ/ሚኒስትርነት ከሚሾሙት መሪ ምን ይጠበቃል? ተግዳሮቶቻቸውና ተስፋቸው ምንድን ናቸው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የፖለቲከኞችን ሃሳብና አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡


             “ጠ/ሚኒስትሩ የህዝቡን ስሜት መከተል ከቻሉ ውጤታማ ይሆናሉ”
               ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት

     የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ አይደለም፡፡ ህዝቡ አቶ ኃይለማርያም ከስልጣን ይውረዱ የሚል ጥያቄ አላንፀባረቀም። ችግሩ ያለው ስርአቱ ላይ ነው፡፡ ስርአቱ አንድን ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን በማውረድ ብቻ ይስተካከላል፣ የህዝቡም ጥያቄ መልስ ያገኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በነዚህ እውነታዎች መሃል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው እሙን ነው፡፡ ለ27 ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ መሠረታዊ  ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በአጭር አመታት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስርአቱ በራሱ ችግር ያለበት በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና ዝቅተኛ ነው፡፡ አሁን አቶ ኃይለማርያም የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል ነው ስልጣን የለቀቁት፡፡ ሌሎችስ ከእሳቸው ጋር የነበሩ አመራሮች የችግሩ አካል አልነበሩም? የመፍትሄው አካልስ መሆን አይገባቸውም ነበር? እሳቸው ስልጣን ሲለቁ አብረው ሊለቁ ይገባ ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ጉዳዩን ሁሉ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አወራርደው፣ “እኛ የችግሩ አካል አይደለንም፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመምራት ዝግጁ ብንሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው እንቅፋት የሆኑብን” አይነት ነው የሚመስለው። ይሄ ደግሞ ለቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትርም ትልቅ ፈተና ነው። የገዥው ፓርቲ የራሱ ድክመት አለ፤ የህዝብ የዲሞክራሲ የፍትህና እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው፣ የቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን በከባድ ፈተናዎች የተሞላ ያደርገዋል፡፡
ህዝቡም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ሊጠብቅ ይችላል፡፡ ለምሣሌ ባለፉት 27 አመታት ለሃገሪቱ ችግሮች ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን ለህግ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ችግር ለ26 ዓመታት እየተንከባለለ እንዲቀጥል ያደረጉ ባለስልጣናት ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መቀጠል የለባቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄን ከግምት ማስገባትና አዲስ ሰዎችን በካቢኔያቸው ማምጣት አለባቸው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁንም በስርአቱ ፖሊሲ አሠራር ውስጥ ነው የሚንቀሣቀሡት፤ ብቻቸውንም አይወስኑም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲታሰቡ የተጠበቀውን ያህል ለውጥ ላይመጣ ይችላል። በዚህ መሃል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያላቸው መልካም አጋጣሚ፣ የህዝቡን ስሜት መከተል ከቻሉ ብቻ የሚሠምር ነው የሚሆነው፡፡ በድርጅታቸው አሠራርና ፖሊሲ ብቻ የሚጠፈነጉ ከሆኑ፣ ምንም የሚፈጥሩት አዲስ ነገር አይኖርም፡፡


----                “በልዩነታችን ላይ ሳይሆን በአንድነታችን ላይ ማተኮር አለባቸው”
                  አቶ ተመስገን ዘውዴ (የቀድሞ ፓርላማ አባል)

   አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በልዩነታችን ላይ ሳይሆን በአንድነታችን ላይ እንዲያተኩሩ ያስፈልጋል፡፡ ታሪካችንን መርምረው አንድ ያደረጉንን ነገሮች ይዘው፣ ወደፊት የሚያስቀጥሉን ከሆነ የሚያስኬድ ይሆናል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ የህዝብን ልዩነት እንደ ትልቅ ነገር አስምረው፣ በትናንሽ ልዩነቶቻችን በተለይ በቋንቋ፣ በሃይማኖት የሚከፋፍሉን ከሆነ፣ አሁን ያለው ትውልድ ይሄን አስተሳሰብ የሚሸከም ባለመሆኑ አይቀበላቸውም፡፡
በሰብአዊና ዲሞክራሲ መብቶች መረጋገጥ፣ በህግ የበላይነት መከበር ከልባቸው የሚያምኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ እሴቶች ሳይሸራርፉ የሚተገብሩ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት የማያገኙበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ባለፉት 27 አመታት ገዥው ፓርቲ የመንግስት ተቋማትን የራሱ ተላላኪ አድርጎ የማየት ሁኔታ  ነበር፤ ይሄን አስተሣሠብ በመተው የመንግስት ተቋማት የፓርቲ ሳይሆኑ ቋሚ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረቶች በመሆናቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያገለግሉ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፡፡
ስለ ነፃ ገበያ ስርዓት በቂ ግንዛቤ ያላቸው፤ መንግስትና ገዥው ፓርቲ፤ ከነፃ ገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸው መሰብሰብ እንዳለበት የሚያምኑና በርትተው የሚሠሩ ከሆነ፣ ለወደፊት ያላቸው ጊዜ ብሩህ ነው የሚሆነው፡፡ ነፃ ገበያ ውስጥ በመግባት ሂደቱን የሚያኮላሹ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ህዝብም ተቀባይነት የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡
ሌላው ላነሣው የምፈልገው፤ ህገ መንግስቱን የሚያከብሩና የሚያስከብሩ፣ በህግ አውጪው፣ በፍትህ አካላቱና በስራ አስፈፃሚው መካከል ያለውን የስራ ክፍፍል ማክበር ከቻሉ፣ የሰመረ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡


----


               “ጠ/ሚኒስትሩ ሃገርና ህዝብን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል”
                  አቶ አስራት ጣሴ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    የህዝቡ ጥያቄ ጥገናዊ ለውጥ ሣይሆን አጠቃላይ የስርአት ለውጥ ነው፡፡ ህዝቡ በገፍ የተገደለው ለአካል ጉድለት የተዳረገው፣ የተፈናቀሉት፣ የተሰደዱት፣ በብዙ ሺዎች በእስር ቤት የሚማቅቁት--- ለጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ሳይሆን ለስርአት ለውጥ ነው፡፡ ጥያቄው የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ ነው፡፡ ጥያቄው፤ እኔ መመራት ያለብኝ በነፃና ተአማኒነት ባለው ምርጫ በመረጥኳቸው ተወካዮቼ ነው የሚል ነው። ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መለወጥ ለህዝቡ ጥያቄ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙ ምናልባት ትርጉም የሚኖረው፣ የሚሾመው ሰው፤ የስርአት ለውጥ አዋላጅ ለመሆን የሚሞክር ሃዋርያ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለዚህ የተዘጋጀ ከሆነ ብቻ ነው ውጤት የሚኖረው፡፡ አሊያ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ነው የሚሆነው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ ውጪ በነበረው ልቀጥል ካለ ህዝባዊ ተቃውሞው ማቆሚያ አይኖረውም፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራሱን ከህዝቡ ጥያቄ ጋር ያቆራኘ መሆን አለበት፡፡ ህዝብና ህዝብን ለማቀራረብ፣ የፍቅርና የአንድነት መሠረት የጣለ ሰው መሆን አለበት፡፡ የሠናፍጭ ቅንጣት ታህልም ቢሆን የህዝብን አክብሮት ያገኘ ሰው ሊሆን ይገባል፡፡ በተቃራኒው የህዝብን መሠረታዊ ችግር፡- የመልካም አስተዳደር፣ ሙስና ---የኢኮኖሚ ጥያቄ አድርጎ አሣንሶ የሚያይ ከሆነ፣ የህዝብን አመፅና ትግል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይሆናል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመሪያ ፈተናው የሚሆነው፣ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 74 የሠፈሩትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን እና ሃላፊነት ሳይሸራረፍ በእጁ የማስገባት ጉዳይ ነው። ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚገጥሙትን ችግሮችም በይፋ ለህዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከማንኛውም ወገን የሚመጣውን ማስፈራራት መጋፈጥ፣ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ከሆነም መክፈል ይጠበቅበታል እንጂ እንደ ከዚህ በፊቱ ከመጋረጃ ጀርባ ባሉ ሌሎች ሃይሎች እጁን እየተጠመዘዘ መስራት የለበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ በሪሞት ኮንትሮል የሚሽከረከር አሻንጉሊት አይደለሁም ማለት አለበት፡፡ ሃገርና ህዝብን ማስቀደም አለበት፡፡ ለዚህ ሲል ሁሉን አቀፍ መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ መሆን አለበት፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ተቃዋሚዎችን፣ ታዋቂ ምሁራንን፣ የሃገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ያካተተ የሠላምና የእርቅ ጉባኤ መጥራት አለበት፡፡ ከዚህ ጉባኤ ከሚያገኘው ግብአት በመነሳት ወደ ባለአደራ መንግስት በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን በማድረግ ፋንታ ኢትዮጵያ የሶሪያ፣ የሊቢያ እጣ ይደርሳታል እያሉ ማስፈራራቱ ዋጋ የለውም፡፡ ህዝብን በማስፈራራት ብቻ ሃገራዊ ባለቤትነቱን ዘላለም ነጥቆ መኖር አይቻልም፡፡


-----             “ጠ/ሚኒስትሩ የህዝቡን አንድነት ማጠናከር አለባቸው”
                 አቶ አሰፋ ሃ/ወልድ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፓርቲ ጫና ተላቆ በራሱ ቆሞ፣ በልበሙሉነት በመስራት ቅራኔዎችን መለየትና ያለ ይሉኝታ ለውጥ ማምጣት መቻል አለበት፡፡ የህዝብን ስሜት እያደመጠ ከህገ መንግስቱ ጋር ያልተቃረኑ መፍትሄዎችን መስጠት ይገባዋል፡፡ ከአሁን ቀደም የነበሩ ስህተቶችን ለይቶ ማረምና  ማስተካከል  አለበት፡፡
ሦስቱ የመንግስት አካላት በእኩልነት እየተንቀሳቀሱ ህዝብን እንዲያገለግሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉ በላይ በልዩ ልዩ ሁኔታ የዳበሩ የሙስና አሰራሮችን ማረም ከቻለ ተቀባይነት ያስገኝለታል፡፡ የአመራር እና የአሠራር ንቅዘትን ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ አሁን ያሉትን የኢህአዴግ ፖሊሲዎች፣ ርዕዮተ አለሙን ጭምር ለህዝብ ተስማሚ በሆኑ ፖሊሲዎች መቀየር መቻል አለበት።
ሌላው በህዝባችን መካከል ያለውን አንድነት ማጠናከር በተለይም በብሄር መስመር የተከፋፈለውን የህዝብ አመለካከት አርሞ ህብረ-ብሄራዊ ስሜት በማስፈን፣ የጠባብነት አመለካከትን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የተስፋፋውንም የጠባብነት አመለካከትና አደረጃጀት መለወጥና ህብረ-ብሄራዊ አመለካከትን እንዲሰፍን ማድረግ አለበት፡፡
ፌደራሊዝሙን እንደ ናይጄሪያ ከልሶ ማስተካከል አለበት፡፡ ናይጀሪያውያን ልክ እንደኛ ነበር ፌደራሊዝማቸው፡፡ በኋላ ግን ከባድ ጦርነትና ግጭት ነው ያስከተለባቸው፡፡ ሶስት ክልል የነበረውን ከፋፍለው 39 ካደረጉ በኋላ አንፃራዊ ሠላም አግኝተዋል፡፡
በአጠቃላይ ህዝብ ያልተቀበለውን አሠራር በሙሉ ህዝብ ሊቀበለው በሚችለው መለወጥ አለበት፡፡ ህገ መንግስት መሻሻል ካለበትም አሻሽሎ፣ አርኪ የስራ ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እስካሁን የነበረውን ፖሊሲ ሳይለውጥ፣ እንደነበረው እቀጥላለሁ ካለ ግን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ለዚህ ሁሉ ስራ እንዲረዳው ያለ ፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ብስለት ያላቸውን ሃገራዊ ምሁራን አሰባስቦ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ምሁራን ውግንናቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ይሄን አሠራር ይከተላሉ፡፡ የፓርቲ መስመር ብቻውን አይሠራም፡፡ ምሁራንን መጠቀም መቻል አለበት፡፡ ይሄን ካደረገ ለውጥ ማምጣት በጣም ቀላል ነው፡፡

Read 1088 times