Tuesday, 20 March 2018 11:39

180 - ዕጣ ፈንታችንን የሚወስን ቁጥር

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ትዝ ይለኛል የዛሬ አስራ አራት አመት ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር አብረን ለመኖር ስወስን አንድ የቅርብ ወዳጄን ላገባ ነው ብዬ አማከርኩት፡፡ “እሱም ትዳር ጥሩ ነው፤ አግባ ግን ሪሞት ኮንትሮልህን አሳልፈህ እንዳትሰጥ” አለኝ፡፡ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ወራት ሪሞት ኮንትሮሉን ላለመስጠት ብዙ ታገልኩ። ግን አልቻልኩም ፍቅር አሸነፈኝ፡፡ እናም ሪሞት ኮንትሮሉን አሳልፌ ሰጠሁ፡፡
ይህን በማድረጌ ግን ሦስት በዚህ ዓለም ላይ ካሉ ጥሩ ነገሮች ሁሉ አብልጬ እምወዳቸው ውብ ልጆች አተረፍኩ፡፡
ታዲያ ሁሌ የቴሌቪዥኔን ሪሞት ኮንትሮል ባየሁ ቁጥር፣ ያ ወዳጄ ትዝ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አስባለሁ፤ አሁን እሳት ቢነሳ እማድነው ሪሞት ኮንትሮሉን ነው ወይስ ቴሌቪዥኑን? የሚቀለው ሪሞት ኮንትሮሉን ብድግ አድርጎ መሮጥ ነው፤ ግን ቴሌቪዥኑ ከሌለ ሪሞት ኮንትሮሉ ብቻውን ምን ይሰራል? ቢከብድም ቴሌቪዥኑን ማዳን ግን  ይጠቅማል፤ ምክንያቱም ቴሌቪዥኑ ከዳነ በኋላ ሪሞት ኮንትሮሉ በቀላሉ ስለሚገኝ፤ ባይገኝም  ቴሌቪዥኑ ምቾት ይቀንሳል እንጂ ያለ ሪሞት ኮንትሮል ማሳየት ስለሚችል! አሁን ሀገራችንን  እንደ ቴሌቪዥን፣ ስልጣንን ደግሞ እንደ ሪሞት ኮንትሮል እንይ፡፡
እሳት ሀገራችን ላይ ተነስቷል፡፡ እምናተርፈው ሪሞቱን ነው ወይስ ቴሌቪዥኑን? 180 አሁን ይህ ቁጥር ለሐገራችን ብዛትን መግለጫ ተራ ቁጥር አይደለም፡፡ ይህ ቁጥር ቀጣዩን የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ የሚወስን ቁጥር ነው፡፡ እናንተ አንድ መቶ ሰማንያ ሰዎች!! ምናልባትም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራችሁ እጃችሁ ላይ ወድቃለች፡፡
ይህ ወቅት እንደ ሌላው ጊዜ እጅ አውጥታችሁና አጨብጭባችሁ የምትለዩት ወቅት አይደለም!! ይህ ወቅት እድሜ ልካችሁን በፀፀት ወይም በእርካታ የሚከተላችሁ ታሪካዊ ወቅት ነው!! እናም ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ስትመርጡልን.........ስለ ብሄር ሳታስቡ.......በተፅእኖ ሳትረቱ.........ስለ ምቾታችሁ ሳትጨነቁ.......በሆዳችሁም በልባችሁም ሳይሆን በጭንቅላታችሁ ብቻ አስባችሁ........... ለወከላችሁ ብሔር ብቻ ሳይሆን ሳይፈልጉ እጃችሁ ስር ለወደቁ መላ ኢትዮጵያውያን ጭምር ተጨንቃችሁ፣ ይህቺን አገር ከገባችበት አዘቅት የሚያወጣት፤ ኢትዮጵያውያንን  ከዞረብን የዘረኝነት አባዜ የሚያላቅቀን፤ እያደር በጥልቀት ከምንሰምጥበት ያስተሣሠብ ድህነት የሚያድነን፤ ከዘወትር ተመፅዋችነት የምንገላገልበትን አቅጣጫ የሚያሣየን፤ መሪ ምረጡልን!ሪሞት ኮንትሮሉን ሳይሆን ቴሌቪዥኑን አድኑልን፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ፡፡
(ከቴዎድሮስ ተሾመ ፌስቡክ)

Read 3060 times