Tuesday, 20 March 2018 11:37

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

“የራስህን ዕውነት ምረጥ”
                

    አንድ የፈረጠመ ጉልበተኛና አንድ ተራ ሰው አርበ ሰፊ በሆነ ወንዝ ላይ በተዘረጋ ቀጭን የገመድ ድልድይ ላይ ተገናኙ፡፡ ድልድይዋ ሁለት ሰዎችን በአንድ ጊዜ ለማስተላለፍ አትበቃም። … ጉልበተኛው ከተነሳበት ቦታ ብዙ ባይርቅም፣ ሰውየው ግን ረዥሙን መንገድ ጨርሶ ሊሻገር የቀረበ ነበር፡፡ …
“ጤና ይስጥልኝ” … አለ ሰውየው፤ … ከላይ እስከ ታች ለሚገላምጠው ጉልበተኛ፡፡
“ወዴት እየሄድክ ነው?” … ሲል ጠየቀ፤ … ጉልቤው … ሰላምታውን ችላ ብሎ፡፡
“እዛ ማዶ እሳት ተነስቷል፣ እሱን ለማጥፋት እየተቻኮልኩ ነው” … አለ ሰውየው .. በጁ እያመለከተ፡፡
“የኛ እሳት አደጋ ተከላካይ … በል ወደኋላ ተመለስ … ልሂድበት፡፡”
“እኔ‘ኮ ደርሻለሁ … እርሶ ወደ ኋላ ቢመለሱ ምናለበት?”
ይህን ሲሰማ የበሸቀው ጉልበተኛ፤ “ወደ ወንዙ ሳትወረወር … ወደ መጣህበት ቀኝ ኋላ ዙር” በማለት ሰውየውን አዘዘው፡፡ ሰውየው ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ተመለሰ፡፡ አጅሬው እየተከተለው መንገዳቸውን እንደጀመሩ ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ ድልድዩን በጣጠሳት። ሁለቱም ወንዙ ውስጥ ወደቁ፡፡ ሰውየው እየዋኘ ሲያቋርጥ አጅሬው ግን አቃተው፡፡ … እየተንደፋደፈ ሊሰምጥ ሆነ፡፡ ይህን የተመለከተው ሰውየውም ወደ ኋላ ተመልሶ ጉልበተኛውን መጎተት ጀመረ፡፡ ወደ መዳረሻው ሲቃረቡ እሳቱ እየተባባሰ ነበርና ሰውየው በፍጥነት ዋኝቶ በመሻገር ወደ እሳቱ ገሰገሰ፡፡ ….
*       *      *
ወዳጄ፡- አንዳንድ ጊዜ በአራት አቅጣጫዎች ልትጎተት፣ በአስራ አራት ገመዶች ልትወጠር፣ በብዙ መንገዶች ልትታለል፣ በብዙ ሁኔታዎች ልትገደድ፣ በብዙ ምክንያቶች ልትዋሽ፣ ፈርተህ ልታጎነብስ፣ ከመንገድህም ልትደናቀፍ ትችላለህ። አንድ ነገር ግን ልብ በል፡- እንኳን ያለ ፈቃድህ፣ በፈቃድህም ቢሆን አንተን ሊሆን የሚችል ማንም የለም፡፡ እኔ “የኔ” ነኝ፣ ራሴ ለ “ራሴ” ነው፣ መንፈሴ የነፍሴ የምትል ከሆነ፣ የተሰራ ማንነትን የማትቀበል ከሆንክ፣ ህሊናህን የምታከብር ነፃ ሰው ነህ!!
ኤግዚስተንሺያሊስቶች (existentialists) … እያንዳንዱ ሰው የነፍስ ወከፍ ጦርነቱን አሸንፎ ‹ሰው መሆን› መቻል አለበት የሚሉት ያለ ምክንያት እንዳይመስልህ፡፡ … ወደድክም ጠላህም መጨረሻህ እዛ ጋ እየጠበቀህ ነው፡፡ አንተ ወደሱ እየሄድክ ብትሆንም እሱም ወዳንተ ሊመጣ ይችላል፡፡ ራስህን ሳትኖር ከተገናኛችሁ ሞት ፊቱን ይነሳሃል፣ ምራቁን ይተፋብሃል። … እየጎተተ፣ እያንገላታ፣ እየተገፈተረ ይወስድሃል። የራስህ ጌታ ከሆንክ ብቸኛ እንኳ ብትሆን ሞትህ ውስጥ ብቸኝነት የለም፡፡ ሞት ያከብርሃል፣ ጎንበስ ብሎ እጅ ይነሳሃል፣ በአክብሮት ይሸኝሃል፣ አትደናበርም። … አለበለዚያ ህይወት እንደ ወራጅ ውሃ ብቅ ጥልቅ እያረገችህ፣ በመኖርና ባለመኖር መሃከል እያላተመችህ፣ ትንፋሽ የሰጠችህ እየመሰለች፣ ቀስ በቀስ ትንፋሽህን ትነጥቃለች፡፡
የነፍስ ወከፍ ጦርነቱ እያንዳንዱ ሰው ከሚፈልገውና ከማይፈልገው፣ ማድረግ ከሚገባውና ከማይገባው፣ በዕድልና ዕጣ ፈንታ ከማመንና ካለማመን፣ በራስ ጊዜ ውስጥ ከመቆለፍና ካለመቆለፍ፣ ከማህበራዊ ባህሪ ውጭ በራስ ቅኝት ከመቃናትና ካለመቃናት፣ የራስ ነፃነት እንዲጠበቅ የሌላውን ከማክበርና ካለማክበር፣ ለረገጥከው መሬት ኃላፊነት ከመውሰድና ካለመውሰድ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡
የኤግዚስተንሺያሊዝም ንቅናቄ በአጠቃላይ መሰረት ያደረገው፡- ነፃ ፈቃድ (free will)፣ ሰብዓዊነት (humanism)፣ ጊዜና ወቅት (time)፣ ነፃነትና ኃላፊነት (freedom and responsibility)፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መኖርን ማስቀደም (existence preceds essenic) በሚሉ እሳቤዎች ሲሆን በነዚህ የብርሃን ግድግዳዎች ታጥራ በተከረከመች ዕውነት ላይ ‹ሰው መሆን›ን መገንባት ነው፡፡
‹Either/or› በሚለው መፅሐፉና በሌሎች ድርሰቶቹ ‹የራስህን ዕውነት ምረጥ› የሚለን ሶረን ኪርግጋርድ (1813-1855) በኮፐንሃገን የኖረ፣ የኤግዚስተንሺያሊዝም አባት የሚባል ሊቅ ነበር። ከሱ በኋላ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ጊዜ የኖሩት (contemporaries) ገብርኤልክ ማርሴል፣ ማርቲን ሄዲገር፣ ካርል ጃስፐርና ሌሎች ሊቃውንት የፍልስፍናውን ፅንሰ ሃሳብ በተለያየ መንገድ በመጽሃፋቸው አብራርተዋል፡፡
ፍልስፍናው እንደ ንቅናቄ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ማዕከሉ ፈረንሳይ ውስጥ ነበር። የንቅናቄው ፊት አውራሪ የግራ ዘመም ፖለቲካ ደጋፊ የነበረ፣ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ፈላስፋ የሚባለው ዠንፖል ሳርትር ነው፡፡ ሳርትር በፃፋቸው መጽሐፍትና ድራማዎች የንቅናቄውን መንፈስ በሚገባ አሳይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1943 ባሳተመው ‹Being and Nothingness› በተሰኘው መጽሃፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ቢሆንም “አልፈልግም” በማለት ሳይቀበል ቀርቷል፡፡
ሳርትር ሲነሳ በጊዜው ብዙ መጽሐፍትንና ቴአትሮችን የደረሰችው፣ በተለይ ደግሞ ለሴታዊነት (Feminism) ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋለች የምትባለው ስምኦን ዳቩዋም የሳርትርን ያህል ዝነኛ የነበረችና ለንቅናቄውም አካል፣ ለህይወቱም ደባል ነበረች፡፡
ሌላኛው የንቅናቄው መሪ ታላቁ ፀሐፊና ጋዜጠኛ አልበርት ካሙስ ነበው፡፡ አልበርት ካሙ “ዘ ሚት ኦቭ ሲሲፐስ (The Myth of Syssiphus)” የተባለውን፣ የሰው ልጆችን ዘለዓለማዊ ፍዳ በአማልክት ቅጣት አስመስሎ ያቀረበበትን መጽሐፍ ጨምሮ ብዙ አስገራሚ ድርሰቶችን ያበረከተ ፀሐፊ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1957 የኖቤል ሽልማት ተቀብሏል፡፡
ወደ ተረታችን ስንመለስ፤ ሰውየው ወዲያ ወዲህ ተሯሩጦ እሳቱን እንደ ምንም አጠፋ፡፡ ገና እፎይ ከማለቱም፡- “ቅድም ዝም ያልኩህ ሁለታችንም እንዳንጠፋ ነው” የሚል ድምፅ ከበስተኋላው ተሰማ፡፡ … ዞር ሲል አፄ በጉልበቱ እየተንደረደረ መጥቶ ሰፈረበት፡፡ በሁኔታው ግራ እየተጋባ … “ምነው … ምን ነካህ?” እያለ ቢጮህም፣ አጅሬው አልሰማውም፡፡ ትንፋሽ ለማሳጣት፣ አንገቱን ለመጠምዘዝ ሲታገል፣ ከየተደበቁበት ጎሬ የወጡ የሚመስሉ ብዙ ሰዎች ተንጋግተው እየተረባረቡ በዱላ አራወጡት፡፡ አጅሬው ሰውየውን ለቆ ወደ ወንዙ መሸሽ ጀመረ፡፡ እንደማይለቁት በማወቁም ወደ ወንዙ ዘለለ። ወንዙን በዋና ማቋረጥ ከባድ ስለሆነበት ቀስ በቀስ እየተደፈቀ፣ ብቅ ጥልቅ እያለ፣ ወደ ውስጥ ተንከባለለ። ጉልበተኛው መንገድ ከጀመረበት ተመልሶ ዓይናቸው ስር ፍርድ ሲቀበል በማየታቸው፤ … “ተፈጥሮ ፍትህ ሰጠችን” ብለው አጨበጨቡ፤ ምስኪኖቹ፡፡
“እንዴት?” ቢላቸው ሰውየው …
“እኛን አባሮ፣ ንብረታችንን አቃጥሎ የሄደው እሱ ነው” አሉ … አንድ ላይ!!
ወዳጄ፡- ኤግዚስተንሺያሊስቶች … እያንዳንዱ ሰው የግል ጦርነት አለበት ሲሉ … ሰው በገዛ ሃሳቡ ከራሱም ከሌላውም ጋር እንደተወዛገበ መኖሩን ለመግለፅ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ሁለት የአስተሳሰብ ፅንፍ (opposite extremes) ላይ የቆሙ ነበሩ፡፡ አንደኛው ‹ሰው ለመሆን› የሚታገል፣ አንደኛው ‹ሰው መሆን›ን የሚገድል!!
“በራስ ላይ የሚቀዳጁት ድል .. የፀጋዎችን ፀጋ መታደል ነው፡፡” (The virtue of all achievement is victrory over oneself) ይላል፡፡ ትስማማለህ ወዳጄ?
በነገራችን ላይ ኤግዚስተንሺያሊስት ማለት “ወጣ ያለ፣ ከመንጋው ርቆ በራሱ የቆመ› እንደ ማለት ነው፡፡
ሠላም!!  

Read 1269 times