Print this page
Tuesday, 20 March 2018 11:33

“ቃል” የሀገር እዳ!

Written by  ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው
Rate this item
(12 votes)

 “መጀመሪያ ቃል ነበር … ቃልም ስጋ ሆነ”  
                           ዮሐ. 1*14
ከሕይወት ዑደት ቅጥ፣
የዘፍጥረት የቃል- ንጥ፣
ሀገር የማቆም፣ ሀገራዊ ቅምጥ…
በፈጣሪኛ ሲሰላ፣ “ሰው” የመሆን ሰዋዊ ምጥ!
“ልሳኑ” ነው መለዮው፣ ከእንሰሳት ሁሉ ተርታ፣
ቋንቋው ነው መለያው፣ ከአውሬ መንጋ እንዲፈታ፤
ዓለምን ሁሉ እንዲገዛ፣ ተፈጥሮን እንዲያስገብር፣
በዓለም ላይ እንዲከብር፣
ከፍጥረታት ሁሉ ልቆ
አእምሮው እጅግ መጥቆ
ታላቅ ፍጡር የመባሉ፣ “ሰው” የመሆኑ
ምስጢር፣
ሌላ አይደለም፣ በልሳኑ ነው፤ ከቋንቋው
በናጠው የቃል ፍጥር፣
ዓለምን ያቆመበት ብልሀት፣ “ቃል”
ማውጣቱ ነው በኅብር፡፡
ፈጣሪውም ዕውቀት ሲቀምር፣ ቃልን በቃሉ ወከለ፣
“መጀመሪያ ቃል ነበር…” አለ፤
ሰውንም በቃሉ ኳለ፡፡
ሰውም በሰውኛ ሲያስብ፣
ዘሩን ከልጓሙ ሲስብ …
የቋንቋ ባለጸግነቱ፣ ልሳኑ ካውሬ እንደለየው፣
ቃል፣ “ሰው” እንደሆነ፣
ቃል፣ “ዕውነት” እንደሆነ፣
ቃል፣ “ሀገር” እንደሆነ፣
ቃል፣ “ዕውቀት” እንደሆነ፣
ቃል፣ “ሕግ” እንደሆነ፣
ቃል፣ “መንግሥት” እንደሆነ፣
ቃል፣ መንግሥተ ሕግ እንደሆነ፣
ቃል፣ ሀገርና ሕዝብ እንደሆነ፣ ማወቅ ስላቃተው፣
ልሳኑን አጣሞ እያዋለው፣ ቃሉን እሽንፍላው ከተተው፡፡
ፈጣሪው በቃል ሲፈጥረው፣ በቋንቋው
ካውሬ ሲለየው፣
አንደበቱን አሰልጥኖ፣ መግባባትን
እያሳየው!
             እሱ ግን …
በቋንቋ ሰየጠነ… ለቋንቋ እየቃተተ፣
ለቋንቋው አውሬ ሆነ፤ በቋንቋው ሞቱን ፈተተ።             
               ***
ለቋንቋ ስንታገል፣ በቋንቋችን አስገደልነው፣
ከቋንቋችን “ቃል” ዘንግተን… ላንግባባ አስቆዘምነው፡፡
               ***
“ጦቢያ” ቃል መሆኗን፣ ቃልም የሀገር እዳ፣
ለብላቴናው ሳንነግረው፣ “የልሳነ ብዝኃን ፍዳ፣”
ዘረኝነት አጀልንበት! የአዕምሮውን ንጹህ ጓዳ፡፡
               ***
የጦቢያን ብላቴና… ከሀገር አብራክ
የፈጠርነው፣
ሁሉን እንዳያውቅ አጥብበን፣ የሕሊናውን
አስኳል ካልቀፈፍነው፣
“የእኔ የአባት ልሳን ይኼ ነው፤ ያ የሰማኸው
የጠላት ነው”
እያልን እያዘመርነው… በመንደር
ካልወሰንነው፣
ሰዋዊነቱን በቁሙ ገፈን፣ እንደ እንግዴ
ልጅ ካልቀበርነው፣
ደም በገበርንበት ሕገዶሴ ውስጥ፣ ጠብ
መጫሪያውን እያሳሰብነው፣
ኅብረ ዝማሬ እንዳያሰማ፣ የወል
ቋንቋዉን እያስቀየርነው፣
ስለ ልዩነት እያራገብን፣ በማንነት ቀውስ
ስናስቆዝመው...
ነፍስ ሲያውቅ ይጠይቀናል፤ ቃል ማውጣቱ
አይቀር? ሰው ነው፡፡
            ***
አዎ! ... ከሀገረ ልሳን “ቃል” ሳንነግረው፣
ቃልን በሕግ ሳናስከብረው፣
ቃልም “ሰው” ነው ሳንለው፣
ሰውም የሀገር ዋልታ መሆኑን …
ሀገርም በቃላችን ያቆምነው!
ቃላችንን ስንገድፍ፣ እንደገደፍነው…
“ቃል” አብለን፣ አንገት እንዳስቀላነው!
አዙሮ ማያችንን
መውጫ መግቢያችንን
ሀገረ-ቃል ተሰብሮብን፣ ወገናችንን እንዳጣነው፣
ወደባችንን እንዳነቀዝነው፣
ቃል ሲጣፋ
ሰው እንዳጠፋ
ቃል ሲቀየር፣ ድንበር እንደቀየረው፣
ቃል በሰው ውስጥ
ሰው በሀገር ውስጥ
ሀገርም በደም፣ እንዳሰመርነው፣
ደማችንን በቃል፣ እንዳቀለምነው፣
ሕገ ቃላችንን በደም ጽፈን፣ በሀገረ
ጅማት እንዳላሰርነው፣
ደምስራችን ሊበጣጠስ ሲል፣ በአንዳርጌ
አንቀጽ እንዳልቋጠርነው!
ለብላቴናው ስላልነገርነው …
“ቃል” የሀገር እዳ ነው!   
          (ሰኔ፣1997ዓ.ም. - ደሴ)

Read 7162 times