Tuesday, 20 March 2018 11:30

የበቀል ጥም

Written by  ደራሲ፡- ጌ ደ ሞፓሳ ተርጓሚ፡- ሀ.ገ
Rate this item
(4 votes)

 የሟቹ ፓውሎ ሳቬሪኒ ሚስት በቦኒፋቺዮ ከተማ ዳርቻ በአንዲት ጠባብ ጎጆ ውስጥ ከአንድ  ልጇ ጋር ትኖር ነበር፡፡ ከተማዋ ባፈነገጡ የከተማዋ ክፍሎች መሀል የተቆረቆረች፣ ከባሕሩ በላይ በተንጠላጠሉ ኮረብታዎችም ሳይቀር የተገነቡ ቤቶች ያሏትና ከባሕር ወሽመጡ ወዲያ ደግሞ የደቡባዊ ሰርዲንያን ጫፍ የሚያዋስን የአሸዋ ቁልል የሚገኝባት ናት። ከዚያ ሥር በተቃራኒ አቅጣጫ ደግሞ ሊከባት ምንም ያልቀረው ገደሉ ላይ የተደረተ እንደ ወደብ የሚያገለግልና ትናንሽ የጣልያን እና ሰርዲንያ የዓሳ ማጥመጃ ጀልባዎች የሚመላለሱበትና በገደላማውና ጠመዝማዛው መንገድ በኩል አልፈው ጫፍ እስከሚገኙ የመጨረሻ ቤቶች ዘንድ ለመድረስ የሚጠቀሙበት መተላለፊያ አለ፡፡ በየሁለት ሳምንቱ ወደ አጃክሲዮ የሚሄዱና በእንፋሎት የሚሰሩ ፉጨታም ጀልባዎች ይመላለሱበታል፡፡
ነጩ ተራራ ላይ የተከማቹት ቤቶች ተራራውን ይበልጥ የነጣ አስመስለውታል፡፡ ቤቶቹ፤ ከአምባው ጋር የተጣበቁ፣ ጀልባዎች ብዙም የማይታዩበት፣ አደገኛውን መተላለፊያ ለመመልከት የሚያስችሉና ጥቅጥቅ ብለው ሲታዩ ትልቅና ሰፊ ዛፍ ላይ የተከማቹ የወፍ ጎጆዎች ይመስላሉ፡፡ ያለማቋረጥ የሚነፍሰው ነፋስም በጠባቦቹ ወሽመጦች መሐል እየተጥመለመለ በመምጣት አስፈሪውን ዳርቻ ረባዳና ከጥቅም ውጪ አድርጎታል፡፡  የተወሰነ ደብዛዛ የአረፋ ጎርፍ ከአለቱ ጋር ተጣብቆ ሲታይ ሌላው ደግሞ ከውሃው ብቅ ጥልቅ ሲል ባሕር ላይ እየተንሳፈፈ የሚዋልል  ነጭ ቁርጥራጭ ጨርቅ ይመስላል፡፡
ዋናው ገደል ላይ የተተከለው የጋለሞታዋ ሳቪሬኒ ቤትም በሦስቱ መስኮቶቹ አማካኝነት ጭር ያለውንና የሀዘን ድባብ ያንዣበበበትን አካባቢ ለማየት ያስችላል፡፡ ባልቴቷ አንቷን ከሚባል ልጇና ሰሚላንቴ ከምትባል  ትልቅ፣ ፀጉራምና በጎችን ለመጠበቅ ከሰለጠነች ውሻ ጋር ትኖር ነበር፡፡ ወጣቱ ልጇ ወደ አደን ሲሄድ ውሻዋን ይዟት ይሄድ ነበር፡፡
አንድ ማታ ታዲያ የማይረባ ፀብ ውስጥ የገባው አንቷን ሳቬሪኒ፣ ኒኮላስ ራቮላቲ በሚባል ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ በጩቤ ተወግቶ ተገደለ፡፡ ገዳዩ በዚያን ምሽት ወደ ሳርዲንያ ሸሽቶ አመለጠ። አሮጊቷ የልጇን ሬሳ ጎረቤቶቿ ሲያመጡላት አንዲት የዕንባ ዘለላ እንኳን አላነባችም፡፡ ምንም ሳትንቀሳቀስና አንዲት ቃል ትንፍሽ ሳትል ለረዥም ሰዓት ስታየው ቆየች፡፡ ከዚያ የተጨማደደውን የእጇን መዳፍ ወደ ሬሳው ሰደደችውና ለደረሰበት ሁሉ እንደምትበቀልለት ቃል ገባችለት፡፡
ማንም አጠገብዋ እንዲሆን አልፈለገችም። ከውሻዋ ጋር በመሆን ቤቷን ዘግታ ከሬሳው አጠገብ ተቀመጠች፡፡ ውሻዋ ከአልጋው እግር አጠገብ ሆና፣ ጭንቅላቷን ወደ አሳዳጊዋ ቀና አድርጋና ጭራዋን ሁለቱ እግሮቿ መሀል ቆልፋ ያለማቋረጥ ትጮኻለች። እንደ እናትየዋ ሁሉ እሷም ሳትንቀሳቀስ አንድ ቦታ ቆማለች፡፡ አሁን እናትየዋ የልጇን ሬሳ ተደግፋ ዓይኖቿን ተክላ እየተመለከተችው ድምፅ ሳታሰማ ማንባት ጀመረች፡፡
ከሸካራ ጨርቅ የተሠራ ጃኬት ለብሶ፣ ደረቱ ተቦድሶ በጀርባው የተንጋለለው ወጣቱ ልጅ፤ ዓይኖቹን ከድኖ የተኛ ይመስላል፡፡ ሆኖም መላ ሰውነቱ በደም ተጨማልቋል፡፡ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ለመስጠት ተብሎ የተቦጫጨቀው ሸሚዙና ጃኬቱ እንዲሁም ፊቱና እጆቹ በደም ተለውሰዋል፡፡
አሮጊቷ እናት ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ለልጇ (ሬሳ) ቃል ትገባ ጀመር፡፡ ውሻዋም በፀጥታ ተውጣ፣ ዓይኗን እያቁለጨለጨች የምታዳምጥ መሰለች፡፡  
“በፍፁም እንዳትፈራ ልጄ፡፡ ውዱ ልጄ፤ እበቀልልኻለሁ፡፡ አንተ እረፍ፤ ተኛ፡፡ እኔ እበቀልልኻለሁ፡፡ ሰምተኸኛል አይደል? የእናትህ ቃል ነው፡፡ እናትህ ሁሌ ቃልዋን ታከብራለች፡፡ ቃልዋን አጥፋ እንደማታውቅ አንተም ታውቃለህ።”
በመጨረሻም በዝግታ ጎንበስ አለችና ቀዝቃዛ ከንፈሮቿን ከበድን ፊቱ ጋር አጣበቀቻቸው። ይኼን ጊዜ ሰሚላንቴም ረዥም፣ወጥ፣ አስፈሪና ኃይለኛ ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡ ባልቴቷና ውሻዋ እስከ ንጋት ድረስ እዚያው ቆዩ፡፡ አንቷን ሳቬሪኒ በሚቀጥለው ቀን ተቀበረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ስሙ በቦኒፋችዮ ከተማ ይረሳ ጀመር፡፡
ሟቹ ወጣት በከተማዋ ምንም የቅርብ ዘመድ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ደሙን የሚመልስለት ማንም አልነበረውም፡፡ አሮጊቷ እናቱ ብቻ ስለተፈጸመበት አሰቃቂ ግድያ ጉዳይ ስታብሰለስል  ሰነበተች፡፡
ከጥዋት እስከ ማታ ከወሽመጡ ወዲያ ማዶ በሚገኝ ኮረብታ ላይ የምትገኘውን ትንሽ ነጭ ነቁጥ ስትመለከት ትውላለች፡፡ ነቁጧ ሎንጎሳርዶ የምትባል ትንሽ የሰርዲንያ ቀበሌ ስትሆን የኮርሲካ ወንጀለኞች አምልጠው የሚሸሸጉባት ቦታ ናት፡፡ ቀበሌዋ ከትውልድ ቦታቸው ያመለጡ ሽፍቶችና ወደየቤቶቻቸው ለመመለስ አመቺ ጊዜ የሚጠብቁ ሰዎች አስጠልላለች፡፡ አሮጊቷ፤ የልጇ ገዳይ የሆነው ኒኮላስ ራቮላቲም እዛችው ቀበሌ ውስጥ ጥገኝነት እንደጠየቀ አውቃለች፡፡
ቀኑን ሙሉ መስኮቱ አጠገብ ብቻዋን ቁጭ ብላ የልጇን ደም የምትመልስበትን መንገድ ስታሰላስል ትውላለች፡፡ እንደዚህ ምንም አቅም የሌላትና ለመሞት አንድ ሐሙስ የቀራት ባልቴት ሆና ሳለ  ያለ ሌላ ሰው እርዳታ የተመኘችውን ታደርግ ዘንድ እንዴት ይቻላታል? ግን ደግሞ ለልጇ ቃል ገብታለታለች፡፡ ቃልዋን ማጠፍ አትችልም፡፡ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍም አትችልም፡፡ ታዲያ ምን ይሻላታል? ሌሊት እንቅልፍ ነሳት፡፡ እረፍትና ሰላም አጣች፡፡  ያለማቋረጥ መብሰክሰኩን ተያያዘችው፡፡
ውሻዋ አሮጊቷ ሥር ታሸልባለች፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጭንቅላቷን ቀና ታደርግና ትጮኻለች፡፡ ጌታዋ ከሞተ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ ዓይነቱን የተለየ ጩኸት ማዘውተር ይዛለች፡፡ እየጠራችው ያለች ትመስላለች፡፡ ሀዘኑ ያልወጣለት የአውሬ ነፍሷ፣ በጌታው ናፍቆት የተጎዳና ምስሉን ከጭንቅላቷ ለማውጣት የተቸገረች ትመስላለች። አንድ ሌሊት ሰሚላንቴ እንደ ልማዷ መጮኽ ስትጀምር እናትየዋ አንድ ጨካኝ፣ በበቀል የተበረዘ ኃይለኛ ሀሳብ ተከሰተላት፡፡ እስከ ጥዋት ድረስ ስለ ጉዳዩ ስታሰላስል አደረች፡፡ ጎህ ሊቀድ ሲል  ወደ ቤተ ክርስትያን አቀናች፡፡ በሩ ሥር ተደፍታ ፀለየች። ፈጣሪዋ እንዲረዳት፣ የደከመው ጉልበቷን እንዲያበረታላትና የልጇን ደም ለመበቀል የሚያስፈልጋትን ጥንካሬ እንዲቸራት ለመነችው፡፡ ከዚያ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
መኖርያ ግቢዋ ውስጥ ውሃ ለማቆር የሚያገለግል አንድ የእንጨት በርሜል ነበር፡፡ በርሜሉን ገልብጣ ውሃውን ደፋችውና ድንጋይና እንጨት በመጠቀም መሬቱ ላይ አደላድላ ተከለችው፡፡ ከዚያም ውሻዋን በርሜሉ ላይ አሰረቻትና ወደ ቤቷ ገባች፡፡
ሰሚላንቴ ዐይኖቿን ከወዲያ ማዶ ወደሚገኘው ዳርቻ አሻግራ ሩቅ ትመለከታለች፤ ዐይኖቿን አሞጭሙጫ ታያለች፡፡ ውሻዋ ቀንና ማታ ስትጮህ ውላ አደረች፡፡ ሲነጋ አሮጊቷ ትንሽ ውሃ ብቻ በጎድጓዳ ሳህን አቀረበችላት፡፡ ሌላ ምንም አልሰጠቻትም፡፡ ዳቦም ሾርባም- ምንም፡፡
ሌላ አንድ ቀን አለፈ፡፡ ሰሚላንቴ ደክሟት አንቀላፋች፡፡ በሚቀጥለው ቀን ግን ዐይኖቿን እያጉረጠረጠች፣ ፀጉሯ ቆሞ የታሰረችበትን ሰንሰለት በኃይል ስትስበው ዋለች፡፡ አሮጊቷም ምንም የሚበላ ነገር ሳትሰጣት ዋለች፡፡ አውሬዋም በቁጣ እየተንቀጠቀጠች በኃይል መጮኽዋን ቀጠለች፡፡ ሌላ ሌሊት አለፈ፡፡
ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲመስል ባልቴቷ ጎረቤቶቿ ዘንድ ሄዳ ሰንበሌጥ እንዲሰጡዋት ጠየቀቻቸው። ከዚያም ባልዋ ሲለብሳቸው የነበሩ ቡትቶዎችን አወጣችና ሰንበሌጡን ጠቅጥቃበት የሰው ሰውነት እንዲመስል አደረገችው፡፡ ሰሚላንቴ ከታሰረችበት በርሜል አጠገብ በሰው ቁመት ልክ እንጨት ተከለችና የቆመ ሰው እንዲመስል ጨርቁን አለበሰችው፡፡ ቀጥላ ጨርቆቹን በመጠቀም ጭንቅላቱ ላይ ራስ ነገር ሰራች፡፡
ውሻዋ ይሄን ከሰንበሌጥ የተሰራ አሻንጉሊት በግርምት ትመለከተው ገባች፡፡ ምንም ቢርባትም አሁን ፀጥ ብላለች፡፡ አሮጊቷ  ወደ ሱቅ ሄዳ ጠቆር ያለ ቋሌማ ይዛ ተመለሰች፡፡ ቤት ስትደርስ ውሻዋ ከታሰረችበት በርሜል አጠገብ እሳት ለኩሳ ቋሌማውን ታበስለው ጀመረች፡፡ ሰሚላንቴም በንዴት ወዲያ ወዲህ እየዘለለች፣ ለኻጭዋን እያዝረከረከች፣ ዐይኖቿን ምግቡ ላይ ተክላ፣ ከምግቡ የሚመነጨውን ጠረን ወደ ሆዷ ትምገው ያዘች፡፡ አሮጊቷም የሚጨሰውን ቋሌማ የአሻንጉሊቱ አንገት ላይ እንደ ከረቫት በሲባጎ ጥብቅ አድርጋ አሰረችው።  አስራም እንደ ጨረሰች ውሻዋን ፈታቻት፡፡
ውሻዋ በአንድ ዝላይ ወደ አሻንጉሊቱ ጉሮሮ ወጣችና በእግሮቿ ጥፍር የአሻንጉሊቱን ትከሻ ትቦጫጭቀው ገባች፡፡ ትንሽ የምግብ ቁራጭ ይዛም ትወድቅና እንደገና ተመልሳ ትዘላለች፡፡ ክራንቻዋን ሲባጎው ላይ ትሰነቅረዋለች፡፡ የተወሰነ የምግብ ቅንጣቢ ይዛ ትወድቃለች፡፡ እንደገና ትዘላለች። የአሻንጉሊቱን ፊት በጥርሶቿ ቦጫጨቀችው። አንገቱን በሞላ ተረተረችው፡፡ አሮጊቷ ፀጥ ብላ በአንክሮ ትመለከታለች፡፡ ትንሽ ቆይታ አውሬዋን እንደገና አሰረቻትና ለሁለት ተጨማሪ ቀናት ያለ ምግብ በማቆየት፣ ይህንን እንግዳ ድርጊት እንድታከናውን አደረገች፡፡
ለሦስት ወራት ያህል ይሄንን ለምግብ የሚደረገውን ግብግብ እንድትለምድ አሠለጠነቻት፡፡ አሁን ውሻዋን ማሰር አቁማለች። በእጇ ወደ አሻንጉሊቱ ስትጠቁማት፣ ውሻዋ ዘላ ትከመርበታለች፡፡ አሻንጉሊቱን እንዴት መቦጫጨቅና አፏ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ሳታስቀር መሰልቀጥ እንዳለባት ሳይቀር አስተማረቻት፡፡ እንደ ሽልማት ትንሽ ቋሌማ እየሰጠቻት፡፡
ውሻዋ አሻንጉሊቱን ስታየው በቁጣ ትንቀጠቀጣለች፡፡ ከዚያ ቀና ብላ ወደ እመቤቷ ትመለከታለች፡፡ አሮጊቷ ደግሞ ጣቷን አንስታ “ያዢው!” ትላታለች፤ በኃይለኛ ስሜት፡፡
ባልቴቷ ትክክለኛውና አመቺው ጊዜ እንደደረሰ ስትገነዘብ፣ ንስሀ ለማድረስ ወደ ቤተ ክርስትያን አመራች፡፡ አንድ የሰንበት ዕለት በወኔና በሃሴት ተሞልታ ቅዱስ ቁርባን ወሰደች፡፡ ከዚያም የወንድ ልብስ ተከናንባና አዛውንት መስላ እሷንና ውሻዋን ከባህር ወሽመጡ ማዶ ወደሚገኘው ቦታ እንዲወስዳት ከአንድ ሰርዲንያዊ ዓሳ አጥማጅ ጋር ተስማማች፡፡
ቦርሳዋ ውስጥ አንድ ትልቅ ቋሌማ ይዛለች። ሰሚላንቴ ለሁለት ቀናት ያህል ምንም አልቀመሰችም፡፡ አሮጊቷ የምግቡን ጠረን ውሻዋ እያሸተተች እንድትቆይና የመብላት አምሮቷ እንዲግል ስታስጎመጃት ቆየች፤ በመጨረሻ ሎንጎቫርዶ ላይ ደረሱ፡፡ የኮርሲካዋ ባልቴት እያነከሰች ወደ አንድ ዳቦ ጋጋሪ ቤት አመራችና ኒኮላስ ራቮላቲ የት እንደሚገኝ ጠየቀች፡፡ ሰውየው የድሮ ሥራው የነበረውን የአናፂነት ሥራ መሥራቱን ቀጥሎበታል፡፡ ከመጋዘኑ ጀርባ ሆኖ ነበር ሥራውን የሚያከናውነው፡፡
አሮጊቷ በሩን ከፍታ ተጣራች፡፡
“ሀሎ ኒኮላስ!”
እሱም ዞር ብሎ አያቸው፡፡ ከዚያ ውሻዋን ለቀቀቻትና፤ “ሂጂ ያዢው! ብዪው!” ብላ ጮኸች፡፡
እብዷ አውሬ ወደ ጉሮሮው ተወረወረች፡፡ ሰውየው እጆቹን እያወራጨ ውሻዋን ለመከላከል ሲታገል መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ለተወሰኑ ሴኮንዶች መሬቱን በእግሮቹ እየደበደበ ተንፈራገጠ፡፡ ከዚያ ፀጥ አለ፡፡ ሰሚላንቴም ጥርሶቿን ጉሮሮው ላይ ሰክታ ትቦጫጭቀው ቀጠለች፡፡ በመጨረሻም የበሮቻቸው ደጃፍ ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሁለቱ ጎረቤቶቹ፣ አንድ ለማኝ ከአንድ ጥቁርና ቀጭን ውሻ ጋር ከሟቹ ቤት ሲወጣና ጌታው ለውሻው የሆነ የሚበላ ነገር ሲሰጠው እንዳዩ ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡
አመሻሹ ላይ አሮጊቷ ቤቷ ደረሰች፡፡ የዚያን ዕለት ሌሊት ጧ ብላ ተኛች፡፡


Read 2613 times