Sunday, 18 March 2018 00:00

የፍካት ሰርከስ አድማስ ተሻጋሪ ስራዎችና ሃሳቦች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል

   • ከሰባት የአፍሪካ አገራት ከ100 በላይ የሰርከስ ጥበበኞችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
   • ከተለያዩ የዓለም አገራት ከ24 በላይ በጎፈቃደኞች ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡
   • በምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው የሰርከስ ድንኳን ‹‹ድንቅነሽ›› በአዲስ አበባ ተተክሏል፡፡ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ            ሆኖበታል፡፡ ከ800-1000 ታዳሚዎችን ያስተናግዳል፡፡
   • ፍካት ሰርከስ ኪራይ በመክፈል እንደማዕከል የሚጠቀምበትን የፒያሳ ግቢውን ሊያጣ ይችላል፡፡ ግን በሌሎች አማራጮች ስራቸውን     መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በአሮጌ አውቶብሶች፤ በቆመ የአውሮፕላን ካርጎ፤ ወይም ስራ ባቆመው የሜጋ አምፊ ቲያትር ….

    2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል አዲስ አበባ ላይ ጦር ሃይሎች አካባቢ በሚገኘው የመኮንኖች ክበብ በፍካት ሰርከስ አዘጋጅነት  ከ2 ሳምንታት በፊት ተካሂዷል፡፡ ከ11 የአፍሪካ አገራት  ከ100 በላይ የሰርከስ ጥበበኞችና ባለሙያዎች በተሳተፉበት ፌስቲቫል ላይ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው የተባለና በልዩ ዲዛይን የተዘጋጀ የሰርከስ ድንኳን ተተክሎ የተሟላ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ‹‹ድንቅነሽ›› በተባለው የፍካት ሰርከስ ድንኳን፤ ከድንኳን ውጭ ነበረው ልዩ መድረክ በፌስቲቫሉ የማመማ ሰሞን የተካሄዱ መርሃ ግብሮች ከ50 በላይ የሰርከስ ትርኢቶችና ሌሎች አዝናኝ ቀርበዋል  የቀረቡ ሲሆን ከ15ሺ በላይ ታዳሚዎች እንደተከታተላቸውም ተገምቷል፡፡
ፍካት ሰርከስ የመላው አፍሪካን የሰርከስ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ፌስቲቫሉን አዘጋጅቶታል። የአህጉሪቱ ምርጥ የሰርከስ ጥበበኞችና ቡድኖቻቸው ደግሞ የአፍሪካን ኪነጥበባዊ ህብረት በተግባር አረጋግጠዋል፡፡  የባህል ትውውቅና የልምድ ልውውጥ  ከመፍጠራቸውም በላይ በሰርከስ ጥበብ በየአገራቱ ያለውን ደረጃ አስተዋውቀዋል።
የኢትዮጵያና አፍሪካ መመኪያ የሆነው የአድዋ ድል ቀን መታሰቢያ በማድረግ (Adwa Week) ፌስቲቫሉ አዲስ አበባን የአፍሪካ  የሰርከስ ጥበብ መዲና   አድርጓታል፡፡ በመኮንኖች ክበብ በተባለው “ድንቅነሽ” ድንኳን፣ ከውጭ በተዛጀው መድረክ በተከታታይ ለ3 ቀናት ከ50 በላይ የሰርከስ ትርኢቶች ሌሎች አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ በተለያዩ ሙዚቀኞች፣ ዲጄዎች እና ተወዳጅ የሙዚቃ ባንዶች በተሰሩ አፍሪካዊ ሙዚቃዎች የታጀቡ፤ የአህጉሪቱ ባህል፤ ፋሽንና ጣፋጭ ምግቦች የቀረቡባቸው ነበር፡፡  በአጠቃላይ የአፍሪካን ሰፊና ጥልቅ ባህል ማድነቂያ እና ማሳያ መድረክ ነበር ማለት ይቻላል። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ቢሆንም በተለይ ታዳጊ ልጆችና ወጣቶች በሰርከስ ጥበብ የተዝናኑበትና የቦርቁበት ነበር፡፡ በዋዜማው ሰሞን የሰርከስ ጥበብ ልምድ ልውውጦች እና ኮንፍረንሶች በአሊያንስ ኢትዮ ፈራንሴስ አስተባባሪነት ከመካሄዳቸው በተጨማሪም በከተማይቱ ባህላዊና የንግድ ማዕከሎች ላይ ደግሞ የተለያዩ የስርከስ ትርኢቶች ቀርበዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ የመጡት
የሰርከስ ቡድኖች፤ አርቲስቶቻቸውና በጎፈቃደኞች
በ2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ በመምጣት የተሳተፉት በአፍሪካ ደረጃ ምርጦች ተባሉ የሰርከስ ቡድኖች ናቸው፡፡ ኩሎኮሎ ከሞሮኮ፤ ሳራካሲ ትረስት ከኬንያ፤ ዚፕ ዛፕ ከደቡብ አፍሪካ፤ ማርያኔታ ጁጋንቴስ ከሞዛምቢክ እንዲሁም ቲናፋን ከጊኒ፡፡
የሞሮኮው ኩሎኮሎ በሞሮካዊ ባህል የታጀበ  ልዩ የሰርከስ ዳንስና ቲያትር አቅርቧል፡፡ በ8 የሰርከስ ጥበበኞች ከተመሰረተ ገና 5 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ከፈረንሳይ ከፍተኛ የሰርከስ ተቋማት እና ታዋቂ የሰርከስ ቡድኖች ጋር የሚሰራና ድጋፍ የሚያገኝ ነው፡፡ የሞሮኮ  የሰርከስ ጥበበኞች በአውሮፓ በሚካሄዱ የተለያዩ ዝግጅቶች በየጊዜው የሚጋበዙ እና የሚፈለጉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
 ሳርካሲ ትረስት ከኬንያ የመጣ የሰርከስ   ቡድን ሲሆን በአፍሪካ የሰርከስ ጥበብን ለማስፋፋት እና ለማሳደግ ይንቀሳቀሳል፡፡ የሰርከስ ጥበብን በአካዳሚ ደረጃ ለማስፋፋት ያነገበውን ራዕይ በፌስቲቫሉ ያስተዋወቀው ልዩ የአክሮባት ትርኢቶቹን በማሳየት ነው፡፡
 በምዕራብ አፍሪካ የመጀመርያው ነው የተባለ የሰርከስ  ጥበብ ማሰልጠኛ አካዳሚን ለማስተዋወቅ በፌስቲቫሉ ትርኢታቸውን ያቀረቡት ደግሞ ቲናፋን ከጊኒ ናቸው፡፡
ከደቡብ አፍሪካ የመጣው ዚፕዛፕ የሰርከስ ቡድን ደግሞ በፌስቲቫሉ ላይ ከተሳተፉት ከፍተኛ ልምድ በማስመዝገብ ቀዳሚው ነው፡፡ በልዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ የሰርከስ ጥበብ ትርኢቶቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ባህላዊ ዳንስ በማዋሃድ አሳይተዋል፡፡ በአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ከፍተኛ እድገት ካሳዩ አገራት በምትጠቀሰው ደቡብ አፍሪካ በታዳጊዎች ላይ በማተኮር የሚሰራው ዚፕዛፕ የሰርከስ ቡድን ከ26 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ነው፡፡
በፌስቲቫሉ አስገራሚ ትርኢት ያቀረቡት ደግሞ  ማርያኔታ ጁጋንቴስ ከሞዛምቢክ ናቸው፡፡ አዝናኝና አስቂኝ ባህላዊ የዳንስ ውዝዋዜዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በግዙፍ አሻንጉሊቶች በሚያቀርባቸው ትርኢቶች የሚለይ ነው፡፡ አሻንጉሊቶችን በሚያመርት ኩባንያ ስር የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን አከጊኒ እና ከፈረንሳይ የሰርከስ ጥበበኞችና ቡድኖቻቸው ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
‹የአፍሪካ የሰርከስ ቡድኖች፣ ጥበበኞችና ባለሙያዎቻቸው በተለይ በአውሮፓ በተደጋጋሚ ትርዒቶችን ያቀርባሉ፡፡ ፍካት ሰርከስ ኢትዮጵያን በመወከል ለሚሰራባቸው መድረኮች ከእነዚህ ቢድኖች ጋር ይገናኛል፡፡ የሰርከስ ጥበብ ሊያድግ የሚችለው ግን በአፍሪካ ማዕከል አድርጎ አፍሪካ ላይ በሚካሄድ ፌስቲቫል ብቻ ነው› በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረው የፍካት ሰርከስ ፕሬዚዳንትና መስራች ደረጀ ዳኘ ነው፡፡
በሌላ በኩል በ2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫልን የተሳካ ያደረገው የበጎ ፍቃደኞች ተሳትፎ ነው፡፡ ከ11 የተለያዩ አገራት 24 የመዝናኛው ኢንዱስትሪ፤ የሰርከስ ጥበብ ባለሙያዎች   በበጎ ፈቃደኝነት ድጋፍ ሰጭ ሆነው መስራታቸው የተገኘውን ዓለም አቀፍ ትኩረት ያመለክታል፡፡ የፍካት ሰርከስ ፕሬዝዳንት ደረጀ ዳኜ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው  በጎ ፍቃደኞቹ በድንኳን ተከላ፤ በመድረክ ግንባታ፤ በብርሃንና የድምፅ ግብዓቶች ዝግጅት፤ በፕሮሞሽንና በተለያዩ የቴክኒክ ስራዎች እንደባለቤት የሚመሰገን አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡
ፍካት ሰርከስ የአፍሪካ ሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫልን በየዓመቱ ለኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ፍላጎት ቢኖረውም የስፖንሰር ሺፕ ድጋፍ ካልተጠናከረ ፈታኝ እየሆነብን ነው የሚለው ደረጀ “ከውጭ የመጡ የሰርከስ ቡድኖችና አባላቶቻቸውን በፌስቲቫሉ ለማሳተፍ እስከ 8 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያዎቹ  የሰርከስ ቡድኖች በፌስቲቫሉ ላይ እና ያሉበት ደረጃ….
በ2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል  ላይ ከኢትዮጵያ 6 የሰርከስ ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የፌስቲቫሉ መስራችና አዘጋጅ ፍካት ሰርከስን ጨምሮ ሰርከስ አርባ ምንጭ፤ ሰርከስ ባህርዳር፤ ሰርከስ ደብረብርሃን፤ ሰርከስ ሃዋሳና ሰርከስ ድሬዳዋ ናቸው። የተለያዩ ከተሞችን የወከሉት የሰርከስ ቡድኖቹ ለፌስቲቫሉ በቂ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀሳቸው ይደነቃል፡፡
በየሰርከስ ቡድኖቹ ልዩ የሰርከስ ትርኢቶችን በማቅረብ፤ የአክሮባት ብቃታቸውን በማሳየት፤  ሌሎች ልዩ ተሰጥኦዎቾቻውን በማስተዋወቅ  ታዳጊና ወጣት የሰርከስ ጥበበኞች በብዛት ተሳትፈዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ ማደግ ተስፋ የሚፈጥር አቅም መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ በፌስቲቫሉ እንደመርሃ ግብራቸው በቡድን ሆነው ባቀረቧቸው   ትርኢቶቻቸው በባህላዊ አልባሳት እና ውዝዋዜዎች ማሸብረቃቸውም ይበረታታል፡፡
የኢትዮጵያ የሰርከስ ቡድኖች  ትርኢቶቻቸውን በተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች አጃቢነት ማቅረባቸውም መጠናከር ያበት አቅጣጫ ነው፡፡ ፍካት ሰርከስ ለወደፊቱ ፍላጎቱ ካላቸው ምርጥ የሙዚቃ ባለሙያዎችና ከሌሎች የሙዚቃ ተቋማት ጋር በአጋርነት ለመስራት እንደሚፈልግም ደረጀ ደኘ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡
አህጉራዊው የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል  በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደነበሩት ሲገልፅም፤  በተለይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ለማሳደግ የምትጫወተውን ግንባር ቀደም ሚና እንደሚያሳድግ በአገር ውስጥ ያሉ የሰርከስ ጥበበኞች የሰርከስ ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት እድል እንደሚፈጥር እና ከአፍሪካውያንና ከዓለም አቀፍ የሰርከስ ቡድኖች እና አዘጋጆች ጋር እንደሚያቀራርባቸው አመልክቷል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ትርኢት ሲያቀርቡ ከተመለከትኳቸው ቡድኖች አንዱ ሰርከስ ደብረ ብርሃን ነበር፡፡ ከዚሁ ቡድን አባላት ጋር ባደረግነው ውይይት እንደተገነዘብኩት ከአፍሪካ አገራት ጋር ሰፊ ልምድ በሚቀስሙበት ፌስቲቫል መስራታቸው በከፍተኛ ደረጃ አበረታቷቸዋል፡፡ የሰርከስ ጥበብ ለአንድነት፣ ለሰላም፣ ለባህል ብዝሀነት እና የዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር የሚኖረውን አስተዋፅኦ  ከማስተዋላቸውም በላይ፤ በሰርከስ ጥበብ የሚገኙበትን ደረጃ የገመገሙበት አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል፡፡
ሌላው መበረታት ያለበት ደግሞ ለየቡድኖቹ የሰርከስ ትርኢቶችን በማጀብ ባህላዊ የሙዚቃ ባንድ የነበረው ተሳትፎ ነበር፡፡ የሙዚቃ ቡድኑ በክራርና በቤዝ ክራር፤ በማሲንቆና በከበሮ መሳርያ ተጨዋቾች በሰርከስ ትርኢቶቹ ላይ እያንዳንዱ የትርኢት ቅፅበቶች እና የሰርከስ ጥበበኞች የአካል እንቅስቃሴና አኳኋን በመጣጣም ልዩ ድባብ ለመፍጠር ተጨንቀው፤ የተመልካችን ስሜት በመግዛት ሊሰሩ ሞክረዋል፡፡
የሰርከስ ቡድኖቹ ኢትዮጵያዊ የሆነ ባህላዊ እሴት ላይ በማተኮር  ለመስራት እንደሚጥሩ በየትርኢቶች ላይ ማስተዋል ተችሏል፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችን በመወከል በፌስቲቫሉ መሳተፋቸውና ድምቀት መፍጠራቸውን የሚያደንቀው የፍካት ሰርከስ ፕሬዝዳንት ደረጀ ዳኘ፤ የሰርከስ ጥበብ በኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ሲንቀሳቀስ ቢቆይም  በከፍተኛ የእድገት ደረጃ ለመስራት ብዙ መሰናክሎች የሰርከስ ቡድኖቹ እንደሚገጥማቸው ይናገራል፡፡ በማዕከል እጦት፤ በገቢ ምንጭ ማነስ እና በአባላቶቻቸው መቀነስ ወደኋላ ሲጎተቱ እና ሲፈርሱ  ቆይተዋል፡፡ ከተሞቻቸውን በመወከል በእንቅስቃሴው መቆየታቸው የሰርከስ ጥበብና ባህሉን ከባሰ ውድቀት ያተረፉበት ነው ብሏል፡፡  
የሰርከስ ቡድኖቹ በቴክኒክ፤ በልዩ ተሰጥኦዎች እና ችሎታዎች፤ በአቀራረብ እና በሙያው ትጋት ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የሚስተካከሉ ቢሆንም በሚያቀርቧቸው ትርኢቶች አዳዲስ ፈጠራዎችን ለመስራት መትጋት እንዳለባቸው፤ ከምዕራባያን የሰርከስ ባህል ብዙ ከሚኮርጁ ይልቅ በራሳቸው ፈጠራ ኢትዮጵያዊ የሰርከስ ባህልን በሚያሳድጉበት አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል በማለትም ደረጀ ምክሩን ይሰጣል፡፡
ከተሞችን የወከሉ የሰርከስ ቡድኖች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ለማጠናከር በየራሳቸው የልምምድ እና የስልጠና ማዕከል መስራታቸው፤ የገቢ ምንጮቻቸውን የሚያሰፉባቸው ዝግጅቶች በየጊዜው መኖራቸው፤  የሚወክሏቸው ከተሞች የበጀት ትኩረት እና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አያይዞ ተናግሯል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ የሰርከስ ድንኳን ‹‹ድንቅነሽ›› መተከልና አንድምታው
2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫልን  ልዩ ካደረጉት ሁኔታዎች ዋንኛው በመኮንኖች ክበብ ሜዳ ላይ የተለያዩ የሰርከስ ትርኢቶችን ለማቅረብ የሚያመች  ግዙፍ ድንኳን መተከሉ ነው፡፡ ‹‹ድንቅነሽ›› በሚል የተሰየመው ይህ ድንኳን በምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የፍካት ሰርከስ ፕሬዝዳንት ደረጀ ዳኘ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ድንኳኑን ገዝቶ ፤ አጓጉዞ አዲስ አበባ በማድረስ ለመትከል እስከ 2 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት መደረጉን ይህ ደግሞ ያልተጠበቀ ወጭ እንደሆነባቸው ጥሪታቸውን እንዳሟጠጠው አልሸሸገም፡፡
‹‹ድንኳኑ ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት የወሰነው የህልውና ጉዳይ ሆኖብን ነው፡፡ የፍካት፤ የኢትዮጵያና የአፍሪካ የሰርከስ ህልውና በሚያሳስበን ደረጃ ላይ የምንገኘው፤ በዚህ ኃላፊነታችንም ‹ድንቅነሽ› ድንኳንን ንብረታችን አድርገነዋል፡፡›› ብሏል ደረጀ፡፡
በነገራችን ላይ ፍካት ሰርከስ እንደማዕከል የሚገለገልበት ግቢ በፒያሳ አካባቢ የሚገኝ ነው። እስከ 25 ሺህ ብር በወር የኪራይ ሂሳብ በመክፈል የሚጠቀመው ነው፡፡ የግቢው ባለቤት ቦታውን መሸጥ እንደሚፈልግ በመግለፅ  በቅርቡ እንደሚያሰናብታቸው አስታውቋቸዋል፡፡  
ደረጀ እንደሚለው ፍካት ሰርከስ እና አጋሮቹ አሁን እንደማዕከል፤ ቢሮ፤ እና የልምምድ ስፍራ የሚገለገሉበትን ግቢና መሬቱን የመግዛት አቅም የላቸውም፤ ስለዚህም አማራጭ መፍትሄ ማፈላለግ ነበረባቸው፡፡ በየቦታ ተዟዙረው የሚሰሩበት፤ በቀላሉ ማጓጓዝ የሚችሉትና እና የሰርከስ ባህላቸውን የሚያጠናክር ድንኳን ለመግዛት የወሰኑት እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመቀጠል ነው፡፡
ስለሆነም ፍካት ሰርከስ ቡድን ድንኳኑን ለመግዛት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በመዘዋወር ካቀረባቸው ትርኢቶች ከሰበሰበው ገቢ እና ከሰርከስ እንቅስቃሴው ደጋፊዎች መዋጮ ሊያሰባስብ ሞክሯል፡፡
የዘመናዊ ሰርከስ ቀደምት መድረክ ሆኖ የሚጠቀሰው ይህ ልዩ ድንኳን  የጥንካሬ፤ የእድገት እና የብልፅግና ምልክት እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ ፍካት ሰርከስ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እና በአገሪቱ የተለያዩ  ክልሎች ለሚያቀርባቸው ትርኢቶች  ይህ ድንኳን በቀላሉ እያጓጓዘ መስራት ስለሚችል ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ድንኳኑ ዓለም አቀፍ የሰርከስ ቡድኖች ለሚያቀርቧቸው ልዩ ትርኢቶች በቂ መድረክ ሊገነባበት የሚችል  ሲሆን በአንድ ዝግጅት ከ800 እስከ 1000 ታዳጊዎችን የሚያስተናግድ ነው፡፡ 2ኛ የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌሰቲቫልን ባስተናገደው ድንኳን ታዳሚዎችን በወንበር ለማስቀመጥ ተሞክሮ ከ600ሺ ብር በላይ በመጠየቁ አልተቻለም ያለው ደረጀ፤ በሳር የተሞሉ ማዳበሪያዎችን ለመቀመጫ በመደርደር ትርኢቶችን ለማቅረብ ችለናል ሲል ተናግሯል፡፡
ደረጀ ለስፖርት አድማስ ‹‹ድንኳኑ አሁን ካለንበት የፒያሳ ግቢ ድንገት ውጡ ብንባል በአማራጭነት ልንጠቀምበት  እንችላለን፡፡ በየቦታው ተንቀሳቅሰን በመስራት  የቡድናችንን ህልውና ያተረፍንበት እቅድ ነው የሆነልን፡፡ ስለዚህም አሁን ባለንበት ሁኔታ ከመንግስት መሬት ይሰጠን አንልም፡፡ የሰርከስ ትርኢቶችን ለመስራት የሚያመቹ  ስፍራዎች፤ እንደመናፈሻ፤ ገላጣ ሜዳ እና ሌሎች አመቺ ቦታዎች ላይ  በጊዜያዊ ፍቃድ እየተጠቀምን መስራት እንፈልጋለን›› ሲል ተናግሯል፡፡
ለወደፊቱም በድንኳኑ በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር በትልልቅ ከተሞች ትርዒቶችን የማቅረብ እቅድ አለን ከዚያም ባሻገር በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተዘዋውረን መስራት እንፈልጋለን የሚለው የፍካት ሰርከስ ፕሬዝዳንት ደረጀ ኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ በሚቀትሉት 5 ዓመታት በወጥነት ዕድገት በማሳየት ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝናኛ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” ብሏል፡፡ ከግዙፍ የመንግስት ተቋማት በአጋርነት ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን ሁኔታዎችንም ለስፖርት አድማስ ጠቃቅሷል፡፡ ለምሳሌ የጠቀሳቸው የከተማ አውቶብስ አገልግሎት የሚሰጠውን መንግስታዊ ተቋምና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ናቸው፡፡ ይህን እቅዱን ለስፖርት አድማስ ሲገልፅም  ‹‹ አንበሳ አውቶብስ በጊቢው ያቆማቸው  አሮጌ አውቶብሶች ይኖሩታል። በኢትዮጵያ አየር መንገድም  አገልግሎት መስጠት የማይችሉ  ካርጎዎች እና አውሮፕላኖች ሊኖሩ ይችላሉ። አንበሳ አውቶብስ ከአሮጌዎቹ አራቱን ቢሰጠን ወይም አየር መንገድ የቆመ ካጎ አውሮፕላንን እንድንሰራበት ቢፈቅድልን ምን አለበት? በድንኳናችን ተዟዙረን በምናቀርባቸው ትርኢቶች አሮጌዎቹን ባሶች ወይም የአውሮፕላኑን ካርጎ በመጠቀም ማረፊያ አልጋዎችን እየዘረጋን፤ የቢሮ ስራዎችን የምናከናውንባቸውን ስፍራዎች እየፈጠርን  ልንሰራባቸው እንችላለን። ይህ አይነቱን ፍቃድ እና ድጋፍ ካገኘን ደግሞ እኛም በሰርከስ ቡድናችን የተለያዩ ልዩ ትርኢቶች እያዘጋጀን ሳምንታዊ አገልግሎት ለተቋማቱ ሰራተኞች በመስጠት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ነን፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
የ2ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል ነፀብራቆች
የአፍሪካን አንድነት፤ ባህል፤ ህብረ ብሄራዊነትና ኪነጥበብ እመርታ በሚያጎለብቱ እቅዶች በተዘጋጀው ፌስቲቫሉ፤ ፍካት ሰርከስ በነበረው ሚና አገሪቱን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን በምንመራበት የሰርከስ ጥበብ የእድገት ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ተረድተናል ይላል ደረጀ ዳኘ፡፡
አፍሪካ እንደ አውሮፓ የትልልቅ የሰርከስ ቡድኖች መናሐርያ ልትሆን እንደምትችል በማመን  መስራታችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ልዩ ክብርና አድናቆት እያተረፍንበት ነውም ሲል ይናገራል፡፡ ለፌስቲቫሉ ስኬታማነት የአውሮፓ ኮሚሽን በኢትዮጵያና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዋንኛዎቹ አጋሮች በመሆን መስራታቸው፤ በተለይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በቅርብ ዓመታት የሰርከስ ጥበብ በካሪኩለም ተቀርፆ ትምህርት የሚሰጥበት ሙያ እንዲሆን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን ማስታወቁም ሌላው ውጤት ነው፡፡
ፍካት ሰርከስ 2ኛውን የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫልን ያዘጋጀው በመላው አህጉሪቱ ለሰርከስ ጥበብ ያለውን ትኩረት ለማሳደግ፤ በታዳጊዎችና ወጣቶች ተወዳጅ እንዲሆንና በየማህበረሰባቸው እንዲያዘወትሩ ለማነሳሳት፤ በአፍሪካ በሰርከስ ዙርያ የሚሰሩ ቡድኖችን ለማቀራረብ፤ ልምድ ለማለዋወጥ እና በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል እንዲሁም በአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ የገበያ ሁኔታን ለማሟሟቅ ነው፡፡
የሰርከስ ጥበብ ባለፉት 10 ዓመታት በተለይ በአፍሪካ አህጉር  በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ነው የሚለው ደረጀ፤ ወጣት የአፍሪካ የሰርከስ ጥበበኞች በየአገራቸው ያለውን የበለፀገ ኪነጥበባዊ እና ባህላዊ ቅርስ ከዘመነኛ የሰርከስ እድገት ደረጃ ጋር በትይዩ ለማንቀሳቀስ በየአቅጣጫ የሚያደርጉትን ጥረት በፌስቲቫሉ ላይ ማንፀባረቃቸው የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡ የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል ወደፊትም በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያሳየ እንደሚቀጥል ከብዙዎቹ የሰርከስ ጥበበኞች ጋር ባደረግኳቸው ውይይቶች ከሰማኋቸው አስተያየቶች ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
በተለይ ፍካት የሰርከስ ቡድን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ወሳኝ እየሆኑ መምጣታቸውን የአፍሪካ ምርጥ የሰርከስ ቡድኖች እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሰርከስ ተቋማት አዲስ አበባን የአፍሪካ የሰርከስ መዲና ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ በመግለፃቸው የሚረጋገጥ ነው፡፡
ፍካት ሰርከስ በ2ኛ የአፍሪካ የስነጥበብ ፌስቲቫል ያገኘውን ልምድ በመጠቀም በቀጣይ መስራት የሚፈልገው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ትርኢቶችን ማቅረብ ነው የሚለው ደረጀ፤ ለ3ኛው የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል ስኬታማነት የሚያግዝ በተለይ የአፍሪካን አገራት በአገር አቋራጭ ጉዞ የሚያካልል የሰርከስ ዝግጅቶችን ለመስራት እቅድ መኖሩን አስታውቋል፡፡
ስለ ፍካት ሰርከስ
ፍካት ሰርከስ በሰርከስ ጥበበኞቹ ደረጀ ዳኘ፤ ሳምሶን ወንድወሰን እና ሰለሞን ባልቻ የተመሰረተ ቡድን ነው፡፡ የፍካት ሰርከስ ፕሬዝዳንት የሆነው ደረጀ ዳኜ በሰርከስ ጥበብ እና ሙያ ሲንቀሳቀስ ከ16 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ለ3 ጊዜያት በጅምናቲክ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ደረጀ በአክሮባቲክስ እና በባርኔጣ ቅልብልቦሽ አጨዋወቱ፤ በሰርከስ ትርኢቶች ድርሰት እና አዘጋጅነቱ በአገር ውስጥ፤ በአፍሪካ በዓለም ዙርያ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ባለሙያ ነው፡፡ የአፍሪካን የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ደረጀ ከጣሊያናዊቷ ባለቤቱ ጆርጅያ ጊዊንታ ሰርቷል፡፡ በፒያሳ ልዩ የስልጠና፤ የልምምድ እና የቢሮ ማዕከል ተከራይቶ የሚንቀሰቀሰው  ፍካት ሰርከስ 30 ቋሚ የሰርከስ ጥበበኞችን በአባልነት እና በባለቤትነት ያቀፈ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ከ100 በላይ የሰርከስ ጥበበኞች እና አሰልጣኞችን በስሩ አሳድጓል፡፡  በተለያዩ የሰርከስ እንቅስቃሴዎች በየዓመቱ ከ450 በላይ ታዳጊዎች እና ወጣቶችን እያሳተፈ ሲሆን በአፍሪካ እና በአውሮፓ አገራት ተዟዙረው በመስራት ከፍተኛ ልምድ ካላቸው አባላት ጋር ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
የሰርከስ ጥበብን  በህፃናት ማሳደጊያ ማዕከሎች፤ በግል ትምህርት ቤቶች እና በተለያዩ ዝግጅቶች በማስተዋወቅም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው፡፡  
ፍካት ሰርከስ ከ2 ዓመት በፊት የመጀመርያውን የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል በዩኔስኮ ድጋፍ ማካሄዱም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ከ107 በላይ የሰርከስ አርቲስቶች ያቀረቧቸውን ትርኢቶች ከ12ሺ በላይ ታዳሚዎች እንደተከታተሉት ተወስቷል፡፡ በ2015 እኤአ ላይ የመጀመርያ የአፍሪካ የሰርከስ ጥበብ ፌስቲቫል እንደ ፕሮጀክት ተቀርፆ በዩኔስኮ ድጋፍ ሲካሄድ በአፍሪካ የሰርከስ እንቅስቃሴ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ስድስት ቡድኖች  ተሳትፈዋል። ከኢትዮጵያ፤ ከቡርኪናፋሶ፤ ከኬንያ፤ ከማዳጋስካር፤ ከሴኔጋል እና ከደቡብ አፍሪካ ከ50 በላይ የሰርከስ አርቲስቶች ትርኢቶቻቸውን ማቅረብ ችለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሰርከስ ደብረብርሃና ፍካት ሰርከስ፤ ሰርከስ ዛምቢያና ማቲው ቴምፖ ከዛምቢያ፤ አክሽንአርቴግሩፕ ከደቡብ አፍሪካ፤ ላ ኤላ ዴስ ፖሴብልስ ከማዳጋስካ፤ ሬድ ቶማቶ ከግብፅ እንዲሁም ሳርካሲ ከኬንያ ነበሩ፡፡ በአውሮፓ ግዙፉ በሆነው የሮተተም ሬጌ ፌስቲቫል በ3 የተለያዩ ጊዜያት ትርኢቶችን ማቅረቡም ያለውን ከፍተኛ ደረጃ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የፍካት ሰርከስ አባላት የተቋሙም ባለቤት ናቸው የሚለው ደረጀ በጥበቡ ፕሮፌሽናል ደረጃ ያላቸው፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ትርኢቶቻቸውን አቅርበው ወደ አገራቸው የሚመለሱ በመሆናቸው፤ በሰርከስ ልምዶቻቸው ወቅታዊ እና ዘመነኛ ትርኢቶችን በመፍጠር መራመዳቸው ልዩ ያደረጋችዋል ብሎ ይመሰክርላቸዋል። የፍካት ሰርከስ ንብረቶች በጋራ ሆነው እንደቤተሰብ ተሰባስበው የሚሰሩት የሰርከስ ጥበበኞች እና ሌሎች አባላቶች ናቸው የሚለው ደረጀ፤ ከዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ከህፃናት ማሳደጊያ ተቋማት፤ ከጎዳና ህይወት፤ ከትምህርት ቤት፤ ከጅምናቲክ ስፖርት እና ቡድኖች እንዲሁም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አባላቱ መሰባሰባቸውን ይገልፃል፡፡
የፍካት ሰርከስ አባላት አስደናቂና ልዩ ተግባር ግን ለፅኑ ህመምተኞች ስቃይ የማረሳሻ ጨዋታዎችን በበጎ ፍቃደኝነት መስራታቸው ነው፡፡ ደረጀ ዳኜ ስለዚሁ የፍካት ሰርከስ መገለጫ ለስፖርት አድማስ በዝርዝር ሲናገር ‹‹በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰባተኛ ፎቅ ላይ ለሚገኙ ህፃናት፤ ቤተሰብና ዶክተሮች ነው ልዩ ድጋፍ የምንሰጠው፡፡ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በፈረቃ በምንሰራው  ይህ ተግባር ላይ 13 የፍካት ሰርከስ አባላት ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ በተለያየ መንገድ ፅኑ ህመምተኞችን በማፅናናት፤ በማበረታታት፤ ከዶክተሮች ውጭ የሆኑ ስሜቶቻቸውን በማነቃቃት፤ ስቃያቸውን እንዲችሉ፤ እንዲዝናኑ በማስታመም እንሰራለን፡፡ በመጀመርያ ፍካት ሰርከስ ይህን ሳምንታዊ አገልግሎት ማከናወን ሲጀምር በሙሉ በጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡ ያለፉትን 9 ዓመታት ደግሞ  እንደፕሮጀክት ተቀርፆ አስፈላጊውን ድጋፍ በማግኘት በአስተማሚነት የምንሳተፈው የሰርከስ ጥበበኞች ወርሃዊ ክፍያ እያገኘን ስንሰራ ቆይተናል›› ብሏል፡፡ ይሁንና ለዚሁ የፍካት ሰርከስ እንቅስቃሴ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ፕሮጀክቱ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጠየቁ ናቸው፡፡ እንደ ደረጀ እምነት የፍካት ሰርከስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሚፈፅሙት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቂ ድጋፍ በማግኘት በመላው ኢትዮጵያ ማስፋፋት ይፈልጋሉ፡፡
ስለ ሰርከስ
ዘመናዊ የሰርከስ ጥበብ በዓለማችን 250 ዓመታትን ያስቆጠረና ኪነጥበባዊ፤ ባህላዊና ስፖርታዊ ብቃቶች ተዋህደው በአስደናቂ ትርኢቶች የሚዘጋጅ የመዝናኛ ባህል ነው፡፡ ባለብዙ የመዝናኛ ዘርፍ በሆነው ሰርከስ ላይ የሰርከስ አርቲስቶች አሻንጉሊት አጫዋች፤ አክሮባቲስቶች፤ ዳሰኞች፤ የሚዛን እንቅስቃሴ ባለችሎታዎች፤ አስገራሚ ተሰጥኦ እና ችሎታዎች፤ የቅብብሎሽ ተጨዋቾች፤ የማይም ቲያትር ተዋናዮች፤ ኮሜዲያኖች፤ በልዩ ስልጠና ትርኢት የሚያሳዩ እንስሳትን አልማጆች እየሆኑ ብዙ ባለሙያዎች ይሰሩበታል፡፡ ዘመነኛ የሰርከስ ትርኢት በ1768 እኤአ ላይ ፈረንሳዊ ፈረስ ጋላቢ በሚያሳየው የግልቢያ ትርኢት እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ይጠቀሳሉ፡፡ የድሮዎቹ የሰርከስ ትርኢቶች በገላጣ ሜዳ ላይ የተጀመሩ ከዚያም በኋላ የተለያዩ የሰርከስ ቡድኖች በእንጨት በሚገነቧቸው አዳራሾቻቸው ይሰሩ ነበር፡፡ በዛሬ ጊዜ ሰርከሶች በልዩ የሰርከስ ድንኳኖች፤ በቲያትር ቤቶች፤ በሁለገብ የመናፈሻ እና መዝናኛ ስፍራዎች እና በጎዳናዎች እየቀረቡ ናቸው። ዘመነኛ የሰርከስ ትርኢቶች በተለይ ከ1974 ወዲህ በፈረንሳይ ሞናኮ ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰርከስ ፌስቲቫል ወዲህ መስፋፋት ጀምረዋል፡፡ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት በእንግሊዝ፤ በጣሊያን፤ ፈረንሳይ እንዲሁም በአሜሪካ በዘመነኛ የሰርከስ ጥበብ ከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኙ የሰርከስ ቡድኖች መናሐርያነታቸው የሚታወቁ አገራት ናቸው፡፡  
ሰርከስ ስፖርት፤ ሙዚቃ፤ ባህልና ሌሎች ዘርፎች የተጣመሩበት ኪነጥበብ ነው፡፡ 21ኛው ክፍለዘመን ላይ በዓለም ዙርያ የሰርከስ ጥበበኞች በፕሮፌሽናል ሙያተኛነት እየታዩ ናቸው፡፡ በታዋቂ እና ስኬታማ የሰርከስ ቡድኖች ውስጥ የሚሰሩ ፕሮፌሽናል የሰርከስ ጥበበኞች በዓመት እስከ 300 መድረኮችን እንደሚሰሩ የሚያመለክቱ መረጃዎች ታዋቂዎቹ ዶላር በዓመት ከ40 እስከ 70ሺ ዶላር በአማካይ እንደሚያገኙ ይጠቁማሉ። ከፍተኛ ልምድ፤ የትምህርት ደረጃ፤ ልዩ ተሰጥኦ እና ብቃት ያላቸው የሰርከስ ጥበበኞች ደግሞ በዓመት እስከ 600ሺ ዶላር እንደሚያገኙ ይነገራል፡፡
በዓለማችን ከ300 በላይ ታዋቂ የሰርከስ ቡድኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ባለው ከፍተኛ የትርኢት አቀራረብ ደረጃ፤ ትርፋማነት፤ እና እድገት  የሚጠቀሰው የካናዳው ‹‹ሰርኪዮ ዴ ሶሊል›› ነው፡፡ ከተመሰረተ ገና 16ኛ ዓመቱን የያዘው ሰርኪዮ ዴ ሶሊል በመላው ዓለም በርካታ ትርኢቶችን የሚያቀርብ ሲሆን ከ5ሺ በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድርና ከ2000 በላይ የሰርከስ ጥበበኞችን የሚያሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የኦሎምፒክ መክፈቻ የሚሆኑ ትርኢቶችን በማቅረብም ከፍተኛ ዝና እና ክብር የተጎናፀፈው ይህ ቡድን ከ25 የተለያዩ አገራት የሰርከስ ጥበበኞች እና አክሮባቲስቶች ከማቀፉም በላይ ከቡድኑ አባላት 40 በመቶ ያህሉ የቀድሞ አትሌቶች ናቸው፡፡


Read 4953 times