Sunday, 18 March 2018 00:00

አመፅን ከምንጩ ያደርቃል የተባለው ከምንጩ እንዳያፈልቅ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

 ሀገራችን ኢትዮጵያ ዥንጉርጉር ታሪክ ያላት፤ ታሪኳም በደምና በጦርነት የተለወሰ፤ ሰንደቅዋ በህዝቦቿ አፅም የተውለበለበ፣ ባለ ደማቅ ክብር ሀገር ናት፡፡ ሉዐላዊነቷ በዋዛ፣ ነፃነቷ በዝንጋዔ የተገኘ አይደለም፡፡ እልፍ ጀግኖች መራራ ፅዋን ተጎንጭተውላታል፡፡ በብዙ የጦርነት አውድማ፣ በጦርነት እሳት ተፈትነው ወርቅ ሆነው በመውጣት፣ ክብሯን ጠብቀዋል፡፡ ይሁንና በነዚህ ፍልሚያና ግጥሚያዎች፣ ለውጥና ነውጦች የእልፎች እንባ ፈስሷል፤ የሺህዎች ሥጋ ተቆርሷል፡፡
ነገስታቱም ዙፋናቸው ሥር እሳት ነድዶ፣ አልጋቸው በምጥ ጥርሶች ሥር ገብቶ፣ ያለ እረፍት ባትተው አልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ የራሱን ሽጉጥ ጠጥቶ በክብር ካሸለበው ጀግና ንጉሠ ነገሥት ጀምሮ ሁሉም መሪዎች፣ የነፃነቷን ማማ ከፍ አድርገው፣ ክብሯን በነፍሳቸው ጋርደው ሩጫቸውን ጨርሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱ ነገሥታት ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ የቅርብ ጊዜው ደርግም ሀገሪቱን ከወረራ ለማዳን ሌት ተቀን ተፋልሟል አገር አንድነቷን ጠብቃ የኖረችው እንዲህ ነው፡፡
የዘመኑ መንግስታችን ግን በቅንነት ይሁን በጥመት ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ሀገሪቱን በብሔር እንደ ቆሎ በትኗታል፡፡ የካህን ቢላ እንዳገኘው ዳቦ፤ ቁና ላይ ቆራርሷታል፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ ለብሔሮች እኩልነት ብሎ ያደረገው እንኳ ቢሆን፣ ኢትዮጵያዊ ደርዝ ስላልሰጠው በቀላሉ ተፍረክርኳል፡፡ ልዩነታችንን የተለያዩ ቀለማት እንዳላቸው ዶቃዎች እንኳ ብንቆጠራቸው፣ በአንድ ወጥ ክር ስላላሰራቸው ከውበት ይልቅ ወደ ሞት አቅንተዋል፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ በጉዲፈቻ፣ በዐይን አባት፣ በክርስትና ልጅነት ወዘተ እያለ፣ አሊያም ጥዋ እየጠጣ፣ በዕቁብ እየሰበሰበ፣ በጥምቀትና በእንቁጣጣሽ፤ በችቦና በመስቀል እያባበለ ትስስሩን ለመቀጠል… አንድነቱን ለመጠበቅ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡
እስከዚህ ድረስ በብዙ ዋጋና ትግል የቆመው አንድነት፤ ዛሬም ህልውናውን ከእነአካቴው አላጣም። ግን አዝማሚያው አያምርም፡፡ በፈተና ተከቧል፡፡
በሌላ በኩል ህዝብ አልገዛም ብሎ የመብትና የነፃነት እንዲሁም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የፍትህ ጥያቄ አለኝ ብሎ አመፅ ከጀመረ 3 አመታት ገደማ ተቆጥረዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ቀስ በቀስ እያደገ፣ ለውጥ የሚፈልግበት ነባራዊ ሁኔታ ጡዘት ላይ ደርሶ ሳለ፣ የመንግስት መልስ ግን ዛሬም እንደ ትናንቱ ለጋ ነው። ለጀማሪ አመፅ ይመልስ የነበረውን መልስ ነው ዛሬም እየመለሰ ያለው፡፡ ትናንት ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው ይናገሩ የነበሩ ባለስልጣናት፤ ዛሬም ያንኑ ተመሳሳይና አሰልቺ ፕሮፓጋንዳቸውን ይለፍፋሉ። ያኔ አይናቸውን እያጉረጠረጡ የሚያወሩት፤ ሰዎች ዛሬም በዚያው ቃና ቀጥለዋል፡፡ ስማቸውና ፊታቸው ይቀያየር እንጂ አሁንም የሚያወሩት አንድ ነው፡፡ ችግሩን ከስሩ ለማድረቅ ኃይል መጠቀም! አፍኖ ዝም ማሰኘት! ሰልፍ የወጣ ዜጋ ላይ ጥይት መተኮስ!
… ጠቅላይ ሚኒስትሩ … የኮማንድ ፖስቱ ፀሐፊ … የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ … ሁሉም ቋንቋቸው አንድ ነው፡፡ ዛቻና ማስፈራሪያ!! ግን ተሸውደዋል፡፡ ኃይልና ጉልበት የሚያስቆመው ጥያቄ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ህዝብ ለምን ህይወቱን ይገብራል! ደረቱን ለምን ለጥይት ይሰጣል? ለምን ሞትን ይደፍራል? ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ደግሞስ ስንት ዓመት ይዘለቃል? … የመግደልስ የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነው? በህዝብ ልብ ውስጥ የሚጋገረው ቁርሾ ፍፃሜው ምን ይሆናል? ይህንን ማሰብ የማይችል የመንግስት ባለስልጣን፤ ሥራውን በሚገባ የሚያውቅ ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ ይሄን ለማሰብ ጠቢብነት አያሻም”፤ ሥልጣንን ተሻግሮ እንደ ሰው ብቻ ማሰብ በቂ ነው፡፡
ወደድንም ጠላንም የዛሬ 3 ዓመት ግድም የተጀመረው የህዝብ አመፅና ተቃውሞ፤ እየባሰበት የቀጠለው በዋነኝነት በግድያ መዘዝና ጦስ ሳቢያ ነው፡፡ ወንድሙን፣ አባቱን፣ እናቱን፣ አጎቱን፣ ወዳጅ ዘመዱን በሞት ያጣ ሰው … ሌላ ጥያቄና ጉዳይ ባይኖረው እንኳን አርፎ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ቂምና ቁርሾ በልቡ ይቋጥራል፡፡ የጥላቻ ግንብ በውስጡ አቁሟል፡፡ እናም ለህዝብ ተቃውሞና አመፅ መፍትሄው የመንግሥት የሃይል እርምጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ለጥያቄው መልሱም ግድያና ጥይት አይሆንም፡፡ ለመንግስትም ለህዝብም ለአገርም አይበጅም፡፡ ለአሁንም ለነገም አይጠቅምም፡፡ ጠቅሞም አያውቅም!
ሲጀመር ኢህአዴግ ዛሬም ከአምስቱ የስነ - አመራር ደረጃዎች የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያ ረድፍ ደግሞ Positional የሚባለው ነው፡፡ “የወንበር አቅም” እንበለው ይሆን? … የዚህ ዓይነቱ አመራር ደግሞ ህዝብ የማሳመን አካሄድን አይከተልም። የሚያምነውና ዓይኑን የሚጥለው በገዛ ስልጣኑ ላይ ብቻ ነው - “ወዶ ሳይሆን በግዱ ይታዘዛታል።” ብሎ ያምናል፡፡ “Only influence comes with the title” የሚባለው ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ይህ የአመራር ደረጃ የሚመጣው በዕውቀትና ክህሎት ሳይሆን በሹመት ነው፡፡ “This level gained by appointment (All other levels are gained by ability)” ይላሉ - ምሁራኑ፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለድርጅታችን ታማኝ ከሆነ ከደገፈ ሊስትሮም ቢሆን ችግር የለውም እንዳሉት ነው፡፡ አቅም ያለው ሰው ሳይሆን፣ ተገዢ ሰው ይፈልጋል፡፡ የኢህአዴግ ዓይነተኛ መገለጫም ይኼ ነው፡፡
ሌሎቹ አራት ደረጃዎች ግን ህዝብን የሚያሳትፉ፣ በፈቃደኝነት ህዝብን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ Permission ሰዎች ያለምንም ግዳጅ መሪያቸውን በመከተል እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌሎቹም ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ይቀጥላሉ፡፡
እኛ ግን ፈርዶብን ሁሌም ጉልበት … ሁሌም ኃይል … ሁሌም ግዳጅ ነው የሚገጥመን፡፡ … ደርግ በግዳጅ፣ ኢህአዴግም በግዳጅ! ደርግ ግንባሩም ደረቅ፣ አፉም ደረቅ፡፡ ኢህአዴግ ግንባራቸው እሾህ፣ ምላሳቸው ጮማ፡፡ “ዴሞክራሲ” በምትለው ቅቤ የራሰች ናት፡፡ ፊት ለፊት ዲሞክራሲ እያሉ ከጀርባ ወህኒ ቤት የሚያዘጋጁ፡፡ ስለ ዲሞክራሲ ተማሩ ተመራመሩ ካሉ በኋላ፣ ተማሪዎች በተማሩት መሰረት አደባባይ ወጥተው መብታቸውን ሲጠይቁ፣ መልሱን ጥይት ያደርጉታል፡፡ የሃይል እርምጃ፡፡ እንዴት ለአንድ ትውልድ ጥያቄዎች ሁሉ መልሱ አረር ብቻ ይሆናል? ከዚህ ፈጣን መልስ ጀርባስ ስለሚመጣው ዕዳና የደም ዋጋ አይታሰብም? … መዘዙ ማለቂያ የለውም፡፡ የጠብመንጃና የኃይል እርምጃ! እነ ሶርያም … እነ የመንም … እነ ኢራቅም … እነ ሊቢያም … የምድር ሲኦል የሆኑት በፈጣሪ ቁጣ አይደለም፡፡ በሰው ልጅ ሥራ ነው፡፡ በሰው ልጅ የጥቅምና የሥልጣን ስግብግብነት፡፡ በሰው ልጅ ክፋት፡፡ እኛም ቆም ብለን ካላሰብን እዚያ ለመድረስ ሩቅ አይደለንም፡፡ ጥቅምም ሥልጣንም ክብርም አገር ስትኖር ነው፡፡ ይሄን ሃቅ ነው የዘነጋነው፡፡ በተለይ ደግሞ መንግስት!፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፣ መንግስታት ከዚህ ቀደም ነበሩ፣ አሁን የሉም፡፡ ሁሉም በየተራው አልፏል፡፡ ይኼኛውም መንግስት ያልፋል፡፡ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ አሳሳቢው፤ አገርና ህዝብ ይቀጥላሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች በተማሪነት ዘመናቸው ተቃውሞና ነውጥ ሲቀሰቅሱ ጃንሆይ እንዴት ነው ያስተገዷቸው? እስቲ መለስ ብለው ያስታውሱት፡፡ ፊውዳል እያሉ የሚያብጠለጥሊት የንጉሱ አገዛዝ መቼም በጥይት አልተኮሰባቸውም፡፡ ዛሬስ?
መንግስት ለእያንዳንዱ ችግር መልስ ከመስጠት ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየሸበበ፣ የሚሰራው ተመሳሳይ ሥራ፣ ነገ የባሰ አፀፋ ከማምጣት ውጭ መፍትሄ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው፡፡ ለዛሬና ለአሁኑ ትውልድ፣ ለዛሬ ሰላሳ ዓመቱ ትውልድ የሚሰጥ መልስ ለመስጠት መሞከር የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከሃያ ሰባት ዓመታት ጀምሮ በተፈናጠጠበት ሥልጣን ላይ ተቀምጦ፣ ያለ አዲስ ሃሳብ፣ አዳዲስ ስብሰባዎች ቢያደርግ ውሃ የሚያነሳ መፍትሄ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ይልቅስ በሰከነ መንፈስ፣ ሁኔታዎችን እያጤኑ፣ በየደረጃው እያደገ፣ ለመጣው ጥያቄ የለውጥ እርምጃ መውሰድን ሳይፈሩ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መድፈር ተገቢ ነው፡፡
ከዚያ ውጭ ያንኑ የተለመደ ጩኸት በየመገናኛ ብዙኃኑ ማስተጋባት መፍትሄ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ፓርቲው በተለያዩ ጊዜያት “በሰበስኩ” እያለ ያቀረበው ኑዛዜ ውጤት፣ በአዳዲስ ሃሳቦችና በለውጥ ርምጃዎች የታጀበ ሊሆን ይገባው ነበር፤ ግን አልተደረገም፡፡ አፈ ጉባኤውንና ሚኒስትሩን፣ “ለቀናል” ወጥተናል እያስባሉ አኩኩሉ ማጫወቱ ከትዝብት ውጭ የሚያመጣው ትርፍ ያለ አይመስለኝም፡፡ የህዝቡን ጥያቄ “ዕድገት የፈጠረው ነው” በሚል ሹፈት የመሰለ ምላሽ መገላገል አይቻልም፡፡
እንደኔ እንደኔ መንግስት ያስተዳድራል፣ የተወሰነ ዘመን ይኖራል፡፡ ህዝብ ግን ቀድሞ ነበረ፤ ዛሬም አለ፡፡ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ስለዚህ ለመንግስት የሥልጣን ዕድሜ ተብሎ በደም የተዋሀደውና ላንድ ባንዲራ በየቦታው የሞተው ህዝብ ለመከፋፈልና ለመነጣጠል አደጋ መጋለጥ የለበትም፡፡
(“አዲስ ስርዓት ገንብተናል” በሚል ሰበብ የበታተናችሁት ህዝብ ተበትኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ አድርጉ! …)
ወቀሳዬን ረዘም ላድርገው! … ህዝብም በመንግሥት ጥላቻና ሴራ ሌላው ወገኑ ላይ ያለውን ጥላቻና ቂም ቢያስወግድ መልካም ነው፡፡ ፓርቲና ህዝብን፣ መንግሥትና የፖለቲካ አመለካከትን በብልሃት ለመለየት ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ይትጋ! እኛን የፈጠረንና የመሰረተን የኢህአዴግ መንግስት አይደለም፡፡ የረዢም ዓመታት መሰረት ያለንና የተሳሰርን ህዝቦች ነን፡፡ ስለዚህ ከመበታተን ይልቅ አንድ መሆናችን ክብራችንና ሀብታችን ነው፡፡ አክሱም የኔ ነው፤ ላሊበላ የኔ ነው፡፡ ፋሲል ግንብ የኔ ነው፡፡ ከማለት ይልቅ “ሶስቱም የኛ ናቸው” ማለት የተሻለ ብልህነት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም አሁን ካለው ሁኔታ ወጣ ብለን፣ ራቅ ብለን እናስብ! … ሁሉም ነገር ያልፋልና!
ታላላቅ ሀገራት፣ ብዙ ጨለማ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬ ዓለምን በስንዴ ርዳታ የምታጥለቀልቀው ካናዳ፤ ትናንት ዳቦ አጥታ ነበር፡፡ ዛሬ እኛን ከሚረዱን ሀገራት አንድዋ የነበረችው አየርላንድ፣ በረሀብ ብዙ ዜጎቿን አጥታለች፡፡ ብዙ ስደተኞችን ከአፈርዋ ነቅላለች፡፡ ይሁን እንጂ ከስደተኞቹ ጆን ኤፍ ኬኔዲን የመሰሉ ክዋክብት አፍርታለች፡፡
የኛም መከራ ያልፋል፣ የኛም ችግር ያልፋል። ስለዚህ አርቀን ብናስብና ከእልህ ይልቅ ወደ ማስተዋልና ወደ ቀና መፍትሄ ብንመለስ፣ ሀገራችን ታላቅ ሆና ትቀጥላለች፡፡ በግሌ የአቶ ለማ መገርሳን ሀሳብ የመደገፌ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ አንድነት … ፍቅርና ይቅርታ! ሀገር ያለማል … ቂምና ጥላቻ ሀገር ያፈርሳል፡፡
ጥሎብን የኛ ነገር እንደ ገጣሚ  አሌክስ አብርሃም ግጥም እየሆነ ተቸግረናል፡፡
ድሮስ በምድራችን መስመር መች ቸገረ፣
አስማሪስ መች ጠፋ?
የፊተኛው ሲያሰምር ኋለኛው ሲያጠፋ፣
መስመሩ ሲታለፍ “መስመር ምን ነበረ” … ብለው የሚክዱ
መስመር ገንቡ ብለው መስመር የሚንዱ፣
ሲያሻቸው መስመሩን የሚያወላግዱ፣
ከጀመዓው መሐል ይህን የጠየቁ፣
“መስመር አለፋችሁ” ተብለው አለቁ!
ሰሞኑን ደግሞ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ብቅ እያሉ አዲስ ዛቻ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ የፓርቲው አመራሮች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እየመጡ ያስፈራሩን ነበር - ያለ ሃጢያታችን!! በትዕግስት … አጎንብሰን እናልፋቸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተረጋግቶ የሚያረጋጋ ይመጣል ብለን ስንጠብቅ ሌላ አዲስ የሚያስፈራራ ፊት ብቅ አለ፡፡  እመኑኝ ይህ ግን መፍትሄ አይሆንም! … ከምንጩ ያደርቃል አላችሁ እንጂ አመፅን ከምንጩ ያፈልቃል!ሰ

Read 7370 times