Sunday, 18 March 2018 00:00

ሁነኛ መፍትሄ ያልተሰጠው ቁ.1 ችግር - የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ!! መፍትሄ ጠፍቶ ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(6 votes)

  • ለዚህ ኋላቀር የዘረኝነት በሽታ መድሃኒት አልተገኘለትም? “በጅምላ የመቧደን ጭፍንነት”ን የሚያስወግድ መድሃኒት የለም?
     • መድሃኒትማ አለው። “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚል ስልጡን አስተሳሰብ ነው ፍቱን መድሃኒቱ
        - (Individualism)።
     • በዘር የመቧደንና የመደራጀት የፖለቲካ ጭፍንነትስ? መድሃኒት አለው? የብሔር ብሔር ፖለቲካስ መፍትሄ አለው?
     • መፍትሄማ አለው - “የግል ነፃነት፣ የግል ንብረትና የግል ማንነት ይከበር” የሚል ትክክለኛና ስልጡን ፖለቲካ ነው        መፍትሄው።
   
    ድሮ ድሮ፣… የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ለማለዘብ፣… “ዲሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት”፣… “አብዮታዊ ዲሞክራሲ”፣… “ልማታዊ መንግስት”፣… የሚሉ ቅፅሎችንና ሐረጎችን አዘውትረው ይጠቀሙ ነበር። ዘር ዘተግን፣ “የጥፋት ጎዳናን ማለዘብ” ማለት፣ ከጥፋት ጎዳና መውጣት ማለት አይደለም። ለዚህም ነው፤ ዛሬ ዛሬ፣… ሌጣ ዘረኝነት እየገነነ፣… ማጣፍያ እንደታጣለት ሰደድ እሳት፣ መከላከያም ሆነ ማምለጫ እንዳልተገኘለት ወረርሽኝ እየመሰለን፣… አይናችን እያየ፣ አስቀያሚውና አስፈሪው የጥፋት አፋፍ ላይ የደረስነው። የተቃውሞ ፓለቲካው አዝማሚያና ቅስቀሳም፣ ከዚህ የራቀ እንዳልሆነ ሳንረሳ ማለት ነው።
ታዲያ፣… እልፍ ምሁራንና አዋቂዎች፣ የዘረኝነት በሽታን ለማስቆም፣ ቀን ከሌት በትጋት ሲጥሩ ማየት አልነበረብን? አስፈሪና አሳዛኝ ነው፤ የተወሰኑ ሰዎች ከሚያደርጉት ሙከራ በስተቀር፣ ከቁጥር የሚገባ፣ ብዙም ጥረት አይታይም።… “ኧረ ይሄ ነገር አያዋጣም! አያዛልቅም! መዘዙ ክፉ ነው” ብሎ እውነተኛና ሁነኛ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብና የሚያስረዳ፣ በተግባርም በቅንነት የሚሰራና በፅናት የሚጥር ፖለቲከኛና ምሁር በብዛት አጋጥሟችኋል? የብሔር ብሔረሰብና የዘረኝነት ፖለቲካ፣ እጅግ አሳሳቢ ቁጥር 1 ችግር የመሆኑ ያህል፣ የመፍትሄ ጥረት ግን፣ ገና ጎልቶ አይታይም።
የዘረኝነት በሽታ፣… ቀስ በቀስ ሲባባስና ሲጦዝ፣… ከተወሰነ ደረጃ በኋላ፣… ማምለጫ ወደሌለው የእልቂት ወረርሽኝ እንደሚሸጋገር፣ መውጪያ ወደሌለው የጥፋት እንጦሮጦስ እንደሚሰምጥ፣… ፓርቲዎች፣ ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን… ጠፍቷቸው ነው? አገሪቱ ገደል አፋፍ መድረሷን ሳያውቁ ቀርተው ነው? በዘረኝነት በሽታ ምክንያት፣ አገር ተተራምሶ እንክትክቱ እንደሚወጣ፣… ሚሊዮኖችም የእልቂት፣ የስቃይና የስደት ሰለባ እንደሚሆኑ… መገንዘብ አቅቷቸው ነው? እንዴት ሊሆን ይችላል?!
ሌላው ይቅርና፣ እዚሁ አገራችን ውስጥ፣ ባለፉት 24 ወራት የተከሰቱ አሳዛኝ ጥፋቶችና ጉዳቶች ትንሽ ናቸው እንዴ? አይደሉም። ከሌሎች አገራት የትርምስና የእልቂት አጀማመር ጋር፣ የአገራችን ሁኔታ እንደሚመሳሰል ማስተዋል አይከብድም። “በጊዜ፣ ስህተቶችን፣ ጥፋቶችንና ክፋቶችን ካላረምን፣ ገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃውሞ ፖለቲካው፣… ከዘረኝነት ቅስቀሳና ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ካልተላቀቁ፣… የአገራችን መጨረሻ እጅግ አስከፊ ይሆናል” ብለው አይሰጉም? የዘመናችን ትርምስ፣ ከነሰበቡና ከነመዘዙ ምን እንደሚመስል፣ በየእለቱ፣… እንደ ሶሪያ እና እንደ የመን በመሳሰሉ አገራት እየታየ!
የስካር ቤት ብሽሽቅ፣ ጠልፎ የመጣል ሽኩቻ፣ የማዋረድ ውርርድ ውስጥ የተዘፈቁና የተጠመዱ፣ ወይም ይህንን የጥፋት ጎዳና ለመከላከል ጥረት የማያደርጉ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ፓርቲዎች፣ ተቀናቃኞች፣ ፀሃፊዎች፣ የፌስቡክ አላፊ አግዳሚዎች ጨምር፣… በአንዳች ምክንያት አይናቸው ካልተጋረደ በቀር፣… አገራችን ወደነሶሪያና የመን አይነት ጥፋት እያመራች እንደሆነ ማወቅ አይሳናቸውም። ለዚያውም፣… የኢትዮጵያ የጥፋት ጎዳና፣ በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን አይጠየቅም።
የ25 ሚሊዮን ዜጎች አገር የነበረችው ሶሪያ፣… ቀስ በቀስ እየተቃወሰች ስትናጥ ብትቆይም፣ ከዳር ዳር ወደ ለየለት ጥፋትና ትርምስ ለመሸጋገር፣ ከጥቂት ወራት በላይ አልፈጀባትም። በአራት ዓመታት ውስጥ፣… ሩብ ሚሊዮን ሰዎች በጦርነት በትርምስ ሞተዋል። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች አካላቸውን አጥተዋል። ሚሊዮኖች ተርበዋል። ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በየአቅጣጫው አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል - (ከአገሪቱ ህዝብ ሩብ ያህሉ… ማለት ነው)። ሌሎች 7 ሚሊዮን ዜጎች ከአገር መውጣት ባይችሉም፣ ከየአካባቢያቸው ሸሽተዋል፤ ተፈናቅለዋል።
በሌላ አነጋገር፣ ከአገሪቱ ህዝብ ግማሽ ያህሉ፣ ከአገር ውጭ ለመሰደድ ወይም ከየአካባቢው ለመሸሽ ተገዷል። ግማሽ ያህል! አገራችን ውስጥ፣ እንዲህ አይነት ጥፋት፣ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። አዎ ሲያስቡት ይዘገንናል።
ይህንን ዘግናኝ የጥፋት ጎዳና ማየትና ማሰብ የሚችል ሰው፣… እንዴት እንዴት በክፋት ቢሳከር ይሆን… ወደ ጥፋት የመንደርደር እሽቅድምድምና ውድድር ውስጥ ለመግባትና ለማባባስ የሚሻማው? ይህንን የክፋት ስካር፣ በዝምታ የሚታዘብ አብዛኛው ሰው፣… በስጋትና በጭንቀት፣… የብሽሽቅ፣ የሽኩቻና የውርርድ ሩጫው እንዲረግብ እየተመኘ፣… የጥፋት ተሳታፊና አባባሽ ላለመሆን መቆጠቡ ጥሩ ነው። መልካም የጨዋነትና የህግ አክባሪነት ባህርይ ነው።
ነገር ግን በዝምታ የታጀበ ጨዋነትና ህግ አክባሪነት… ብቻውን በቂ አይደለም። የክፋት ስካር እንዳይፈጠር ለመከላከል ለመግታትና ለማስተካከል ብቁ መሆንም ያስፈልጋል። የአቅሙና የብቃቱ ያህል መጣርም ይኖርበታል። እንዴት?

ለዘመናት የዘለቀ፣… አገራትን ያካለለ በሽታ!!
በጅምላ የመቧደንና የመደራጀት ጭፍንነት፣… ኋላቀር የዘረኝነት አስተሳሰብ፣… የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣… “የኋላቀርነቱና የጭፍንነቱ ግዙፍነት” ያህል፣ እጅግ አጥፊ ነው።  
በእርግጥም፣ የሰው ልጅን ለእልቂት ከሚዳርጉ፣ “ሦስት ኋላቀር፣ አጥፊና ክፉ አስተሳሰቦች” መካከል አንዱ፣… በጅምላ የመቧደን ጭፍንነት (collectivism)… እንደሆነ ተጠቅሷል - በAyn Rand ፈላስፍና። በዘር በጎሳ፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በዘልማድ፣ በመንደር፣ በሰፈር… በእምነት በሃይማኖትም ሳይቀር እያመካኙ በጭፍን የመቧደንና የመደራጀት በሽታ፣… ብዙ አገራትን ለትርምስ የዳረገ በሽታ ነው። በየዘመኑ፣ የብዙ ሚሊዮኖች ሕይወት ጠፍቷል፤ የብዙ ሚሊዮኖች ኑሮ ተናግቶ፣ ለስደት፣ ለረሃብና ለስቃይ እሮሮ ተዳርገዋል።
በጅምላ የመቧደን ጭፍንነት… የዘረኝነት በሽታ፣…  በዘመን በጊዜ ሳይወሰን፣ በአካባቢ በድንበር ሳይታጠር፣ ከጥንቱ ፋታ የለሽ እልቂት ጀምሮ፣ ሚሊዮኖች የሞቱበት የናዚና የኮሙኒስት ጥፋትን ጨምሮ፣ ዛሬም በየአገሩ፣ ከሶማሊያና ከየመን፣ እስከ ሊቢያና ሶሪያ፣… ለትርምስ እየዳረገ የሚገኝ ኋላቀር በሽታ ነው።    
እና፣… ለዚህ ኋላቀር አስተሳሰብ፣ ለዚህ የዘረኝነት በሽታ መድሃኒት አልተገኘለትም? “በጅምላ የመቧደን ጭፍንነት”ን የሚያስወግድ መድሃኒት የለም?
መድሃኒትማ አለው። “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚል ስልጡን አስተሳሰብ ነው ፍቱን መድሃኒቱ - (ማለትም Individualism)። ይሄ፣ እውነታን የመገንዘብ ጉዳይ ነው። ሌላ አይደለም። እውኑን ሰው አስተውለንና ተገንዝበን፣… እውነተኛ እውቀትንና ትክክለኛ አስተሳሰብን የመጨበጥ ጉዳይ ነው። ማለትም… “የሰው አእምሮ የግል ነው፣ የሰው አካል የግል ነው፣ የሰው ማንነት የግል ነው” የሚል ስልጡን ሃሳብና አስተሳሰብ።

የሰው አእምሮ፣ አካልና ማንነት፣… የግል ነው!!
የሰው አእምሮ ማለት፣ የግል አእምሮ ማለት ነው። ጋን የሚክል የጋራ አእምሮ የለም። የጋራ የእውቀት ጎተራ የለም።
እውነተኛ አልያም ሃሰተኛ መረጃ፣ ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ ሃሳብ፣ ጠቃሚ ወይም ጎጂ አስተሳሰብ… በዘር የሚወረስና የሚተላለፍ አይደልም - በብሔር ብሔረሰብ፣ በመንደርና በሰፈር፣ በጋርዬሽና በጅምላም አይደለም። እያንዳንዱ ሰው፣ የግል አእምሮውን መጠቀም አለበት - እውነትን ከሃሰት ለመለየት፣ ግንዛቤ ለመጨበጥ፣ ለማወቅ ከፈለገ። ለምን?
አእምሮ የግል ስለሆነ ነው። ይህንን እውነት መገንዘብ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው Individualism። በዚህ ትክክለኛ አስተሳሰብም ነው እያንዳንዱ ሰው፣ የግል አእምሮውን በመጠቀም፣… መረጃንና ሃሳብን መለዋወጥ፣ መወያየትና መማማር የሚችለው።
የሰው አካልም፣ የግል አካል ነው። ጤንነት ማለት “በጋራ እግር መሮጥ” ማለት አይደለም። “የብሄር ብሔረሰብ የጋራ እግርና ሩጫ” ሊኖር ይቅርና፣ የአባትና የልጅም እንኳ የየግላቸው ነው። ፍጥነትና ሬከርድ ማለት፣… የጋራ ፍጥነትና የጋራ ሬከርድ አይደለም። እጁን አጣጥፎ፣ “ያንተ ሩጫና ሬከርድ፣ የጋራችን ነው። ያንተ ጥረት፣ የጋራ ጥረታችን ነው። ያንተ ምርት፣ የጋራ ምርታችን ነው” እያለ የስካር ሃሳቦችን የሚያራግብና የሚሰብክ የጅምላ አስተሳሰብ መብዛቱ ነው ችግሩ። ግን፣… ይሄም መፍትሄ አለው። በእውን የምናያቸው ሰዎች የጋራ እግር እንደሌላቸው ግልፅ ነዋ! ይህንን እውነት መያዝ፣ ይህንን እውነት አለመካድ ነው መፍትሄው።
“የግል አካል እንጂ የጋራ አካል የለም። እሱኛው ሰውዬ፣ በራሱ የግል እግር ይራመድ፣ በራሱ ብርታት ይስራ፣ በራሱ ዓላማ ያምርት”፤… “አንተም በራስህ የግል እግር ተራመድ፣ በራስህ ብርታት ስራ፣ በራስህ ዓላማ አምርት”… ብሎ እንደመናገር ነው። ይህንን እውነት በመገንዘብና… በዚህ እውነት ላይ በመመሰረትም ነው፣… ምርት መለዋወጥና መገበያየት፣ የስራ እድልና የንግድ ውል መፈራረም፣ በሽርክና ቢዝነስ ማቋቋምና መተባበር፣ መረዳዳትም የሚቻለው።
በሰው አእምሮና አካል ከሚከሰቱና ከሚከናወኑ የዛሬ ሃሳቦችና ድርጊቶች በተጨማሪ፣… በሂደት የሚታነፁ የእውቀትና የሙያ ሃብቶች፣ የአእምሮና የአካል ብቃቶች፣ እንዲሁም ባሕርይ፣ ሰብእናና የእኔነት መንፈስ ሁሉ… የግል ማንነቶች ናቸው። ይህንን እውነት የሚክድ ቀሽም ሰው፣ በዘር እንድትቧደንለት ምን ብሎ ይሰብክሃል? “በግል ብቃትህ መኩራት የለብህም” ብሎ ይሰብክሃል። “ያንተ ማንነት የጋራ ማንነታችን ነው። ያንተ ብቃት የጋራ ብቃታችን ነው። የጋራ ኩራታችን ነው” ይልሃል - ቅንጣት ብቃት የሌለው ክብረቢሱ ፍጡር። ይህም ብቻ አይደለም። በዘር እንድትቧደንለት የሚመኘው፣… የግል መናኛነቱንና ወራዳነቱን፣ አንተ በጋራ እንድትሸከምለትም ጭምር ይፈልጋል። ያንተን የብቃት ሽልማትና ክብር ለመጋራት፣ የራሱን የጥፋትና ውርደት ለማጋራት ይመቸዋል - ኋላቀር ዘረኝነትና በጅምላ የመቧደን ጭፍንነት (collectivism)።
የዚህ በሽታ ፍቱን መድሃኒትም ተመሳሳይ ነው - “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚል እውነተኛ፣ ትክክለኛና ስልጡን አስተሳሰብ (Individualism) ነው ሁነኛው መፍትሄ።
ይህንን ግልፅ እውነታ፣ በየሄድንበት በሁሉም ቦታ፣ እለት ተእለት ሁልጊዜ የምናየው እውነታ አይደለምን? ለዚያውም የኑሮ አለኝታና የሕይወት ዋስትና ነው እንጂ! ርቆ የመራቀቅ ጉዳይ አይደለም።በቃ፣ “የሰው ማንነት ማለት፣ የግል ማንነት ነው”።
ብቃትህን አስመስክረህ በሕክምና ዶክተርነት ስትመረቅ፣… ዘመድ አዝማድ፣ ዘር ማንዘር፣ ሰፈርና መንደር ሁሉ፣… “በጋራ ብቃት”፣ “በጋራ የሕክምና ዶክተር” ይሆናል? አይሆንም!! ይህንን አስተሳሰብ በቅንነት የመያዝና በፅናት የመተግበር፣… በማንኛውም ሰበብ እንዳይሸረሸር የመከላከል ጥንካሬ ነው - ስልጣኔ። “የጋራ የብቃት ጎተራ” የለም። በዘርና በሰፈርም አይወረስም። የሰው ብቃት፣ የግል ብቃት ነው። ይህን እውነታ በመገንዘብ ነው - መደናነቅ፣ መዋደድ፣ መከባበር የሚቻቻለው። “እያንዳንዱን ሰው፣ በግል ድርጊቱ፣ በግል ብቃቱና በግል ባሕርይው መመዘን!”… የቅንነት፣ የፍቅርና የፍትህ ሚዛን ይህ ነው። ቅንጣትም ትሁን ትልቅ፣ ሕይወትን የምናጣጥመው፣… ይህችን እውነት ተገንዝበን በተገበርናት መጠን ነው።

እያንዳንዱን ሰውን በስልጡን የስነምግባርና የሕግ ሚዛን
ድንቅ ብቃቱን ያስመሰከረ ሰው፣ በትልቅ አድናቆት፣ በከፍተኛ ክብር፣ በውድ ሽልማት ሲንበሸበሽ ማየት ያስደስታል። ግን፣ የብቃት ባለቤት ከሆነው ጀግና ይልቅ፣… አራት አምስት የዘር ሐረግ እየተቆጠረ፣ በአያት በቅድመ አያት እየተመዘዘ፣… ከብቃት አጠገብ ያልደረሱ ዘመድ አዝማዶች፣ ለሽልማትና ለሙገሳ ቢመረጡስ?
ሰውን በማሰቃየት እርካታ የሚያገኝ የሚመስለው አንድ መናኛ የክፋት ሱሰኛ፣ ትናንት ወይም ከ40 ዓመት በፊት በፈፀመው ወንጀልስ፣ ማን ይኮነናል? በጅምላ ዘመድ አዝማድ ሁሉ? ቅጣትስ ማን ላይ? በጅምላ የሰፈር የመንደር ሰው ሁሉ ላይ? ሰውን በጅምላ ሳይሆን በግል ባሕርይውና በግል ድርጊቱ ልንመዝነውና ልንዳኘው አይገባም? ይገባል እንጂ።
“የሰው ማንነት የግል ማንነት ነው” የሚለውን እውነት በመገንዘብ ላይ የተመሰረተ፣ የስነምግባር ሚዛንና የሕግ ዳኝነት ሊኖረን አይገባም? ይገባል እንጂ።
ስልጡን የሕግ ሚዛን?
“በሃሰት አትመስክር፣ የሰውን ንብረት አትንካ - አትስረቅ፣ የሰውን አካልና ሕይወት አትድፈር - አትግደል”… ይሄ፣… እያንዳንዱን ሰው በግል ተግባሩ የምንዳኝበት ፍትሃዊ የሕግ ሚዛን ነው። እንዲህ አይነት የፍትሃዊ ሕግ፣…
አንደኛ ነገር፣… “ለዚህ ዘር ወይም ለዚያ ሰፈር”፣… “ለዚህኛው ብሔረሰብ ለዚያኛው ቋንቋ” ተብሎ የሚፈረጅ አይደለም - ለማንኛውም ሰው፣ ለእያንዳንዱ ሰው በግል የምንመዝንበት የዳኝነት ሚዛን ነው - ፍትሐዊ ሕግ።
ሁለተኛ ነገር፣… ብሔር ብሔረሰብን፣ ቋንቋን፣ ሰፈርና መንደርን በጋርዬሽና በጅምላ ለመክሰስ የሚቃጣ አይደለም። እያንዳንዱን ሰው በግል ተግባሩና ባሕርይው የሚዳኝ ነው - ፍትሃዊ የሕግ ሚዛን።
ፍትሃዊ የስነምግባር ሚዛንስ?
“በሃሰት አትመስክር” ከሚለው መርህ በተጨማሪ፣.. በአጠቃላይ “ከሃሰትና ከዋሾነት መራቅ ያስፈልጋል” የሚል መርህን ይጨምራል - የስነምግባር ሚዛን።
“የሰው ንብረትን መስረቅና ማጥፋት ወንጀል ነው” ከሚለው መርህ በተጨማሪ፤ “የሰውን ቤትና ንብረት ለመውረስ መመኘትም ሆነ መመቅኘትም ክፋት ነው” ብሎ ያስተምራል - የስነምግባር ሚዛን።
“የሰውን አካልና ሕልውና መዳፈር ከባድ ወንጀል ነው” ከሚለው የሕግ ሚዛን በተጨማሪ፤… “የሰው ሕይወት ክቡርነትን ማጣጣልና ማናናቅ አይገባም። ሰውን በቅንነትና በሃቅ መመዘን አለብህ። ሰዎችን እንደራስህ ውደድ የሚለው አባባልም ከዚህ ጋር ቢተሰሳር ትክክለኛ ሃሳብን ያስተላልፋል። ሰዎችን እንደራስህ፣… ማለትም ራስህንም ጭምር፣… እያንዳንዱን ሰው፣ በግል ባሕርይውና በግል ድርጊቱ መመዘን ያስፈልጋል” ብሎ ያስተምራል ፍትሃዊ የስነምግባር ሚዛን።
በአጭሩ፣ “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚል እውነተኛና ስልጡን አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው፣… እውነተኛና ቀና፣ ትክክለኛና ጠቃሚ፣ ስልጡንና ፍትሃዊ የስነምግባር ሚዛን፣ እንዲሁም የሕግ ዳኝነት መያዝ የሚቻለው። ይሄም ነው፣ የዘረኝነት በሽታንና መዘዙን የሚያስወግድ ፍቱን መድሃኒት፣ ሁነኛ መፍትሄ።

Read 3269 times