Print this page
Sunday, 18 March 2018 00:00

የቡና ዙሪያ ወግ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

  (ሦስት ጎረቤታሞች ቡና ላይ ተገናኝተዋል፡፡)
               
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… አገሩ ሁሉ ጀበና ቡና ሆነና በየመንደራችን ቡና መጠራራት ቀረ እንዴ! ለነገሩ የበፊት አይነት የቡና ስርአት እየቀረ ነው፡፡ በር እየተንኳኳ “እትዬ እከሊት፣ እማዬ ኑ ቡና ጠጡ ብላለች፣” ማለት እየቀረ ነው፡፡ ካለም ያው አቦል ይጠጣና “እስቲ ደጉን ያምጣው፣” ብሎ መለያየት ነው፡፡ ሦስት ጎረቤታሞች ቡና ላይ ተገናኝተዋል፡፡
ሁለት፡— ባለቤትሽ አሁን እንዴት ነው፡ ትንሽ ቀለል አላለውም?
አንድ፡— አይ የእሱን ነገርማ ተዪው፡፡ አሁንማ ግራ ግብት ነው ያለኝ፡፡
ሁለት፡— ሀኪም ሄዶ የለም እንዴ!
አንድ፡— እዛማ ሄደልሽና መድሀኒት ይሰጡታል ስል፣ አቅም ስላነሰህ አትክልት ብላ፣ ሥጋ ብላ፣ ወተት ጠጣ…ብለው  አይልኩት መሰለሽ!
ሦስት፡— ፎቃቆች በያቸው፡፡ እኔ እኮ የምለው ሥጋ ብሉ፣ ወተተ ጠጡ የሚሉን ጠቃሚነቱን እኛስ አጥተነው ነው! በዶሮ ማነቂያ ስናልፍ በአእምሮት እንዴት እንደምንሳቀቅ አላዩ፡፡
ሁለት፡— በሽታ በዛ፡፡ ዘንድሮ ማን ያልታመመ አለ፡፡ በየልብስ ቤቱ የሚቆሙት አሻንጉሊቶች እንኳን ታመዋል፡፡
ሦስት፡— አቤት! አቤት! እንደው ነገር ማሳመር ስትችይበት፡፡
አንድ፡— ምን ታድርግ ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ቱሪናፋ ሆኗል፡፡
ሦስት፡— አንቺ ሴትዮ ይሄን አሽሙርሽን ተይ ብያለሁ፡፡ አገሩ ሁሉ ጆሮ ጠቢ ሆኗል፡፡ በቀደም የቲማቲም ዋጋ ቢያበሳጨኝ “አሁንስ የት አገር እንሂድ!” ያልኩትን ሄደው ሹክ ብለው ይኸው ይገላምጡኝ ጀምረዋል፡፡
ሁለት፡— ስልጣን ፈልጋ ነው ብለው ይሆናል…
አንድ፡— እናንተ ሰዎች ዛሬ ጤናም አልያዛችሁ እንዴ፣ ጦስ እንዳታመጡብን፡፡ ይልቅ ልጅሽ ደህና ነች?
ሁለት፡— ምን ትሆናለች፣ የዘንድሮ ልጆች ምን ይሆናሉ! እኛን ያንገብግቡን እንጂ፡፡
ሦስት፡— ደግሞ ምን ሆንኩ ልትይ ነው! የአንቺ ልጅ እንደሁ እግዚአብሔር የባረካት ጨዋ ነች፡፡
ሁለት፡— አይ ጨዋነት…ጨዋነት ድሮ ቀርቶ፡፡
አንድ፡— አንዴ ድረሻት እፎይ አትዪም!
ሁለት፡— ባል ጓዳሽ ድረስ የሚመጣበት የአንቺ ዘመን መስሎሻል፡፡ ይኸው እንደ እንቁላል የሚንከባከባት አባቷ እንኳን በዛ ሰሞን “ልጄ እድሜ ቆሞ አይጠብቅም፣ እንደው ትዳር ቢጤ ብትይዥ” ሲላት…ብቻ፣ ውይ! ውይ! ውይ! አበስኩ ገበርኩ!
ሦስት፡— አፍ አውጥታ አባቷን እምቢ አለቻቸው!
ሁለት፡— እንደሱማ ቢሆን ደግ ነበር፣ ብቻ ቤቱን አመሰችው ነው የምላችሁ፡፡ እንዴት ብላችሁ አግቢ ትሉኛላችሁ! እኔ ልጅ መሰልኳችሁ! እያለች እንዴት እንዳርገፈገፋት!…. አባቷ ደንግጦ “በቃ ትቸዋለሁ፣ እንዲሁ ለጨዋታ ነው፣” ቢላት ልትሰማ ነው!…
አንድ፡— ምናልባት አጉል ጓደኛ ገጥሟት እንዳይሆን…
ሁለት፡— ጥጋብ ነው እባክሽ…ደግነቱ ታላቋን በጊዜ መዳራችን፡፡
ሦስት፡— እኔ የምለው፣ እሷ ልጅ ባለቤቷ ነጋዴ ነው?
ሁለት፡— ኸረ እሱ የመንግሥት ሠራተኛ ነው።
ሦስት፡— እኔ እኮ የፋብሪካ ባለቤት ምናምን መስሎኝ ነበር፡፡
ሁለት፡— እና ለሀብታም መዳር ነበረባችሁ ማለት ነው?
አንድ፡— ታዲያስ! ጓደኞቿን አታዪያቸውም… የሆቴል ባለቤት፣ የህንጻ ባለቤት አይደለም እንዴ ያገቡት! ምን በወጣት፣ በድህነቷ ላይ ሌላ ድህነት!
ሁለት፡— እናንተ ገና ጉድ ታመጣላችሁ፡፡ እኔንም ባልሽን ፍቺና እህል ነጋዴ አግቢ ሳትሉኝ አትቀሩም፡፡
አንድ፡— ተገኝቶ ነው!
ሁለት፡— ጉድ ፈላ…ቡና ልንጠጣ ነው የመጣነው፣ ባሎቻችንን ልንፈታ! ወይ ልጅቷን ለእናንተ እሰጣችሁና ትድሯታላችሁ፡፡
ሦስት፡— ግዴለሽም እንደዛማ አትማረሪ፣ ዘመኑን ማየት ነው፡፡ እነሱ እኮ እንደ እኛ አይደሉም። ይልቅ ተበሳጭታ አጉል ነገር እንዳታደርግ እናንተም ረጋ በሉ።
ሁለት፡— የራሷ ጉዳይ…እኔ እኮ ጠባዩዋ እንደተለወጠ ያወቅሁት ‘እማዬ’ ማለቷን ትታ ‘ማም፣’ ‘ማሚ፣’ ማለት ስትጀምር ነው፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ ‘ማም፣’ ‘ማሚ፣’ ምናምን የድመት ወይ የውሻ መጠሪያ ነው፡፡
ሦስት፡— አንቺ እንግሊዝኛ ስለማይገባሽ ነው፡፡
አንድ፡— አንቺ አውቀሽ ሞተሻል፡፡ ይልቅ ሳልነግራችሁ… በቀደም ነው፣ የዘመድ ስብሰባ ላይ ያቺ ገጠር ያለችው እህቴን አገኘኋት፡፡
ሦስት፡— እሷ እህትሽ አለች እንዴ? ካየኋት ስንት ጊዜ…
አንድ፡— እኔም ካገኘኋት አራት፣ አምስት ዓመት ባይሆነኝ ነው!
ሁለት፡— አይ ጊዜ! እንዲህ እንደው ነፋስ እንደበተነው ጤፍ ተበታትነን እንቅር!
አንድ፡— ነፋስ የበተነው ጤፍ የት እንዳለ ንገሪኝና ሰፌዴን ይዤ ሄጄ አፍሳለሁ፡፡
ሦስት፡— አንቺ!… አበስኩ ገበርኩ በይ፣ ይሄንን ትመኛለሽ!
አንድ፡— መሶቤን ብታዪ አብረን እንፈስ ነበር የምትዪኝ፡፡ አሁንማ ጤፏ ከመጥፋቷ የተነሳ በእግራም ሳሀን አብሲት ልጥል ምንም አልቀረኝ
ሦስት፡— ይልቅ ስለ እህትሽ ጀምረሽ ነበር…
አንድ፡— እንደው ተጠመጠምኩባትና “እህት ዓለም ደህና ነሽ!” እያልኩ ስንሳሳም፣ ወጣቶቹ ሁሉ አያፈጡብኝም!
ሁለት፡— ምን አደረግሽ ብለው?…
አንድ፡— እህት ዓለም ማለት ምን እንደሆነ ግራ ገብቷቸው ነዋ፡፡ በኋላ እኮ አንደኛዋ “ምንሽ ነች?” ብላ ጠየቀችኝ፡፡
ሦስት፡— አንቺም አጠፋሽ…ሰልጥኚ እንጂ!
ሁለት፡— ጎሽ ሴትዮዋ ዛሬ ጉድ አመጣች፣ ታዲያ ምን ትበላት…ታላቅ እህቷ አይደለች እንዴ!
ሦስት፡— ሲሱ ነው የሚባለው፡፡
አንድ፡— ጉድ! ጉድ! ጉድ! አንቺ ደግሞ ይሄን ሰማሽ?
ሦስት፡— ነገርኩሽ፣ መሰልጠን ነው…
ሁለት፡— መሰለጠን ስትይ ያ የባሌ ወንድም ልጅ…ያ እንኳን ጠጉሩን እንዲህ አንደ መጥረቢያ ያሾለው…
አንድ፡— እሱ ልጅ እኮ አንዳንዴ አንተ ልበለው፣ አንቺ ግራ ይገባኛል፡፡ እንዴ ወንድ ልጅ ምንድነው እንዲህ መቅለቅለስ!
ሦስት፡— እሱ ምን አደረገ ልትዪን ነበር…
ሁለት፡— በቀደም ቤት መጥቶ ነበር፣ ሱሪው ወርዶ፣ ወርዶ ጭኑ ጋ ሊደርስ ምንም አልቀረው፡፡
አንድ፡— ምን ይገርማል፣ ዘንድሮ ሦስት ጸጉር ያወጣው ሁሉ ሱሪውን ዝቅ ያደርግ የለ እንዴ!
ሁለት፡— ቆይ አስጨርሺኝ… እቃ ይወድቅበትና ለማንሳት ጎንበስ ሲል…ኸረ እንደው ምን አይነት ዘመን ነው የመጣብን!
አንድ፡— እኮ ምን ሆነ?
ሁለት፡— እንደው ምን ልበላችሁ፣ ልክ እንደዚህ ጀበና መቀመጫው እርቃኑን ቁልጭ አይልላችሁም!
አንድ፡— እንግዲህ ይታይልኝ ካለ ምን ይደረጋል…
ሁለት፡— በአራስነቱ እኮ እናቱ ሰው እንዳያይባት በስንት ጨርቅ ስትጠቀልለው ነበር። አሁን በትልቅነቱ …የአትክልት ተራን ሀብ፣ ሀብ አስመሰለውና አረፈው፡፡
ሦስት፡— ተዉት እባካችሁ፣ ልጆቻችንን አሳለፈን ከሰጠን በኋላ እንዲህ ሆኑ፣ እንዲህ አልሆኑ ማለት ዋጋ የለውም፡፡ 
አንድ፡— ኸረ እባክሽ ቡናው ገነፈለ!
ለመገንፈል የሚበቃ ቡና ከተገኘም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ቡናውን በግራምና በኪሎ መመዘናችን ቀርቶ ፍሬውን አንድ፣ ሁለት ብሎ የሚያስቆጥር ዘመን እንዳያመጣብን… በቡናው ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 9307 times