Sunday, 18 March 2018 00:00

አበበ ቀስቶ - ከእስር መልስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


    “--ብሔራዊ መግባባት በህገ መንግስቱ በተለይም በአንቀፅ 39 ጉዳይ፣ በሰንደቅ አላማ፣ በሀገር ዳር ድንበር፣ በፌደራል አወቃቀር ጉዳይ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ መንግስትና ህዝብን ያላግባባው አንዱ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነው፡፡ የአርማ ጉዳይ በዋናነት አላግባባም። ለምን በግድ ተቀበሉ ይባላል፡፡ ደርግ እኮ አርማ ያለውን ባንዲራ ይጠቀም የነበረው ለፕሬዚዳንቱ ቢሮዎች ነው።--”
በቅፅል ስሙ አበበ ቀስቶ (ክንፈ ሚካኤል ደበበ) ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፓርቲ ደጋፊነት እስከ ፓርቲ አመራርነት የዘለቀ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ኢዴፓን ከመሰረቱት አንዱ ሲሆን የፓርቲው ዋና ፀሐፊም በመሆን አገልግሏል፡፡ ከፖለቲካ እንቅስቃሴው ጋር በተገናኘ ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል ታስሮ የተፈታው አበበ ቀስቶ፤ በመጨረሻ በ2004 ዓ.ም በሽብር ተከስሶ መጀመሪያ ላይ የ25 ዓመት እስራት የተፈረደበት ሲሆን በይግባኝ ወደ 16 ዓመት ዝቅ ተደርጎለታል፡፡ በቅርቡ በፖለቲካ ውሳኔ ከተፈቱ ፖለቲከኛ እስረኞችም አንዱ በመሆን ከእስር ለመለቀቅ ችሏል፡፡
 እኛ ወደ ፖለቲካ የገባንበት ወቅት ማንንም ኢትዮጵያዊ ለፖለቲካ የሚጋብዝ ነበር የሚለው አበበ ቀስቶ፤ በፖለቲካ ተሳትፎው፣በእስር ቤት ቆይታውና ገጠመኞቹ፣በተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከምና በወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

   የፖለቲካ ህይወት ጅማሮህ ምን ይመስላል?
እኛ ወደ ፖለቲካ የገባንበት ወቅት ማንንም ኢትዮጵያዊ ለፖለቲካ የሚጋብዝ ነበር፡፡ ምክንያቱም የደርግ ስርዓት በኢህአዴግ የተተካበት ጊዜ በመሆኑ፣ የሀገሪቷ ሁኔታም ልክ አሁን እንዳለንበት ቀጣይ እጣ ፈንታዋ አሳሳቢ የነበረበት ወቅት ነው፡፡  በወቅቱ ጉዳዩን በትኩረት የሚያይ ሰው ሁሉ  ወደ ፖለቲካ መግባቱ አይቀርም ነበር፡፡ በእርግጥ ፈርቶ የቀረ ሊኖር ይችላል ነገር ግን የወቅቱ የሀገራችን ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነበር፡፡ በወቅቱ የበኩሌን ድርሻ ማበርከት አለብኝ ብዬ ስላመንኩ በግሌ ነበር ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል ባልሆንም እነሱ የሚጠሯቸውን ሰልፎች በማስተባበር፣ ድጋፍ በማድረግ እንቀሳቀስ ነበር።
በግልህም ለምርጫ ተወዳድረህ ነበር?
ከዚያ በፊት በ1984 ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የወረዳ ምርጫ ይካሄድ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔና ጓደኞቼ “እስቲ ኢህአዴግ በምርጫ ያምናል አያምንም፤ በተግባር እናረጋግጥ” ብለን ለምርጫው የሚወዳደሩ እጩዎችን ስንደግፍ ነበር። እንዲመረጡ ለምንፈልጋቸው ተወዳዳሪዎች ፍፁም ድጋፍ ነበር የሰጠነው፡፡ ከዚያ በኋላ በ1986 የህገ መንግስት ረቂቅ ውይይት ጉባኤ በየወረዳው ሲደረግ ወጣቶች ተነጋግረን፣ በሂደቱ ለመሳተፍ ሞክረናል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ በህገ መንግስቱ ረቂቅ ላይ ሰፊ ክርክር አቅርበናል፤ነገር ግን የኛ ክርክር የሚዲያ ሽፋን ያልተሰጠው በመሆኑ ሀሳባችን አልተስተናገደም። በወቅቱ ያ ያቀረብነው የተለየ ሃሳብ ህዝቡ ጋር ደርሶ መወያያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ህገ መንግስቱ የገጠመው የቅቡልነት ፈተና ባልተፈጠረ ነበር፡፡ ምክንያቱም በእውነተኛ ውይይት  የጠራ ህገ መንግስት ሊፀድቅ ይችል ነበር፡፡ ዛሬ እነዚያን መሰል ክርክሮች የሚዲያ ሽፋን አግኝተው ለህዝብ ባለመቅረባቸው ነው፣ ህገ መንግስቱ ኢህአዴግ ብቻውን ያፀደቀው ነው እየተባለ ያለው፡፡
ለህገ መንግስት ጉባኤ ከየወረዳው ሰዎች ሲመረጡም እኛ ወጣቶች ጠንክረን ሰርተን፣ በወረዳችን የምንፈልገውን የግል እጩ አስመርጠን ነበር፤ አቶ ታሪኩ ፅጌ ይባላሉ፡፡ በወቅቱ ይሄን ስናደርግ ብዙ መከራ ተቀብለናል፡፡ በምርጫውም አቶ ታሪኩ በማሸነፋቸው በቀጣይም ህዝቡ ጠንክሮ ከታገለ ኢህአዴግን በሰላማዊ ምርጫ ማሸነፍ ይቻላል የሚል ፍንጭ አገኘን፡፡ እርግጥ ነው እነ ሻለቃ አድማሴ፣ አቶ ዳንኤል በላይነህ፣ እነ ዘለሌ ፀጋ ስላሴም ለህገ መንግስቱ ጉባኤ ከአዲስ አበባ በግል ተወዳድረው የተመረጡ ነበሩ፡፡ የእነዚህ መመረጥ በምርጫ ላይ ተስፋ እንድናደርግ አስችሎን  ነበር፡፡
 በ1987 በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከዚያ በፊት ሌሎችን በማገዝ ላይ የተመሰረተውን ተሳትፎዬን ወደ እጩ ተወዳዳሪነት በማሳደግ፣ እጩ ተወዳዳሪ ሆኜ በግሌ ወደ ምርጫው ገባሁ። በወቅቱ ከባድ ምርጫ ከተካሄደባቸው ወረዳዎች የአዲስ አበባ ወረዳ 24 ተጠቃሽ ነበር፡፡ እኔም እዚሁ ወረዳ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ እዚያው ነው የተወዳደርኩት፡፡ እኔም ጓደኞቼም በወቅቱ ከኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ክርክሮች አድርገን፣ የህዝቡን ቀልብ መሳብ ችለን ነበር፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ አሸንፌለሁ አለ፡፡ የ1987 ምርጫ በዚህ ተደመደመ፡፡
ከዚያ በኋላ የነበረህ ፖለቲካዊ ተሳትፎስ ምን ይመስላል?
በኋላ አማራጭ ኃይሎች የተባለ ስብስብ በሚያዘጋጃቸው ውይይቶች ላይ መሳተፍ ጀመርን። በዚህ ሂደት ስንሳተፍ የነበረን የተወሰንን ወጣቶች “የኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረት” የሚል ስብስብ ለመመስረት ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ይህን ህብረት የፈጠርነው በእነ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራውን የአማራጭ ኃይሎች እንቅስቃሴ፣ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ለማራመድ በማሰብ ነበር፡፡ ይህን ያደረግነውም ከአመራሮቹ ጋር በመነጋገር ነበር። በወቅቱ ለህብረቱ ያረቀቅነውን ደንብም አመራሮቹ አይተውት፣ ይሁንታ ሰጥተውታል፡፡ በኋላ ግን አማራጭ ኃይሎች በአለመግባባቶች ህልውናውን በማጣቱ፣ እኛም እጣ ፈንታችንን ስንተልም፣ ያንን ስብስብ ወደ ፓርቲነት መቀየር የሚለው ሀሳብ በሁለተኛ አማራጭነት የተያዘ ስለነበር፣ ወደ ፓርቲ ቀየርነው። ፓርቲ መሰረትን። በወቅቱ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በሚል በፓርቲ ደረጃ መስርተን መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ እኔም የፓርቲው ዋና ፀሐፊና ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ ኢዴፓን ለመመስረት በተካሄደው ሂደት፣ እኔም ጓደኞቼም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተናል፡፡ በርካታ ወጣቶችም የዚህ ፓርቲ አባል ሆነዋል፡፡ በአጭር ጊዜም ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡
በኋላም በአጭር ጊዜ ለምርጫ ቀርበን፣ በ1992 በአዲስ አበባ ምክር ቤትም በፓርላማም ወንበር ለማግኘት ችለናል፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ የፈቀደላቸው ሰዎች ወንበር ስላገኙ እንጂ እኔም በተወዳደርኩበት ወረዳ ለፓርላማው አሸንፌ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢህአዴግ አመራሮች የነበሩ በኋላ በሙስና ታስረው ቃሊቲ በእስር ቤት ያገኘኋቸው ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ፣ እኔን እንደውም “ወይ እሰሩት ወይ ግደሉት” ተብለው እንደነበር አጫውተውኛል።
በምርጫው ለማሸነፍህ ማረጋገጫ ነበረህ?
በወቅቱ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ የነበረውና አሁን በህይወት የሌለው ግለሰብ ራሱ አሸንፈሃል ብሎኝ እንኳን ደስ ያለህ ተብዬ ነበር፡፡ በኋላ በበላይ አካል ውሳኔ ይመስለኛል ሳጣራ፣ ምርጫ ቦርዱ ም/ል ኃላፊ የነበረውና አሁን በሕይወት የሌለው ግለሰብ አያውቀውም፤ ከአሸናፊዎች ዝርዝር ውስጥ ስሙ የለም ተባለ፡፡ በወቅቱ አሸንፈሃል ፎቶ አምጣ ተብዬ ሁሉ ነበር፡፡ የቀድሞ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ የነበረው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ በመፅሐፉ ለማጋለጥ እንደሞከረው፤ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም በምርጫው አሸንፈው ነበር። ኢህአዴግ ለምን በወቅቱ እኔ ፓርላማ እንዳልገባ እንደፈለገ አላውቅም፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ፣ እኔ በፖለቲካ ውስጥም እንድቀጥል አልፈለገም፡፡
ማሸነፍህን ካረጋገጥክ መብትህን ለማስከበር ምን ያህል ጥረት አድርገህ ነበር?
እኔ፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህ እና አቶ ልደቱ አያሌው ሆነን ቅሬታችንን ለቦርዱ በደብዳቤ አቅርበን ነበር። ይመረመራል አሉን፡፡ በሌላ ቀን ጉዳዬን ለመጠየቅ ወደ ቦርዱ ስሄድ የቦርዱ ዋና ፀሀፊ የነበሩት አቶ አሰፋ ብሩ፤ “አንተ ልጅ ነህ ታድጋለህ፣ እድሜህ ገና ነው ለወደፊት ትወዳደራለህ ምን ያጨቃጭቅሃል” የሚል መልስ ነው የሰጡኝ፡፡ በወቅቱ የኢዴፓ ዋና ፀሐፊ እና የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ ስለነበርኩ ትኩረቴን ፓርቲውን ወደ ማደራጀትና ማጠናከር ነው ያዞርኩት፡፡ በወቅቱ የገባኝ ምርጫ ቦርዱ ምን ያህል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየቀለደ መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ በሄድኩ ቁጥር እኔ በተወዳደርኩበት ወረዳ ያለችው የወረዳው ምርጫ አስተባባሪ፤ውጤቱን ባትቀይረው ኖሮ አልፈህ ነበር እያሉ ይነግሩኝ ነበር። ይሄ ሁሉም የሚያውቀው ነበር፡፡ አንድ የኢህአዴግ አባልም በእስር ቤት አግኝቼው የነገረኝ፣እንደውም እኛ አዝነን ተውንህ እንጂ ወይ እሰሩት አሊያም ግደሉት ነበር የተባልነው ብሎኛል፡፡
የአንተ ተለይቶ መታሰር ወይም መገደል ለምን አስፈለገ?
ምናልባት በሚደረጉ ክርክሮች ላይ ጠንካራ ሙግት ስለማቀርብ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ በምከራከር ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜናውም አይሰራም። የሌሎች ወረዳዎች ክርክር ሰፊ የአየር ጊዜ ተሰጥቶት ሲቀርብ፣ የኛ የወረዳ 24 ግን አይቀርብም ነበር፡፡ በኋላ የገባኝ በቃ፣ ኢህአዴግ እኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንድቀጥል እንደማይፈልግ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በ2004 ዓ.ም ሰልፉን አስመልክቶ በሰሜን ሆቴል ለሁሉም ሚዲያዎች የሰጠነው መግለጫ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሳይዘገብ ቀርቷል፡፡
ከፖለቲካ ተሳትፎህ ጋር በተገናኘ  ምን ያህል ጊዜ ነው የታሰርከው?
ለ9 ጊዜያት ያህል ታስሬያለሁ፡፡ አንዳንዶቹ የታሰርባቸው ምክንያቶች ዛሬ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስባቸው፣ ያስቁኛል ያስገርሙኛል፡፡ በ1990 ዓ.ም የታሰርኩበት ምክንያት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጋር በተያያዘ የወረዳ 24 ህዝብ ተሰብስቦ፣ በጦርነቱ ጉዳይ ይወያይ ሲባል፣ እኔ አቶ መለስ ዜናዊ በያዙት አቋም አልስማማም ነበርና፣ ህዝብ በተሰበሰበበት አዳራሽ በአቶ መለስ አቋም እንደማልስማማ ገልጬ፣ከስልጣን ይልቀቁ የሚል ጥያቄ ነበር ያቀረብኩት፡፡ በዚህ ንግግር ያልተደሰቱ የፀጥታ ኃይሎች፣ በነጋታው ጠዋት መጥተው ከቤቴ ወስደው አሰሩኝ፣ ለምን እንደዚያ አልክ አሉኝ፤ እኔም ይሄን ማለት መብቴ ነው፣ አሁን አገሪቷ ከገባችበት ችግር አንፃር አቶ መለስ ለማስተዳደር አይመጥኗትም፤ ይሄ አቋሜ ነው አልኳቸው፡፡ በኋላ በ1 ሺህ ብር ዋስ ለቀውኛል፡፡
ሌላው በጣም የሚያሳዝነኝ የእስር አጋጣሚዬ፣ የፕ/ር አስራት ወልደየስ ህይወታቸው ያለፈ ጊዜ የተፈፀመብኝ እስር ነው፡፡ አስክሬናቸውን ከቦሌ ተቀብለን ፕሮግራሙን የምንመራው እኛ ነበርን፡፡ አስክሬኑን ከቦሌ አጅበን እየዘመርን፣ ልክ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ስንደርስ፣ ፖሊሶች ከመኪና ወርደው ተኩስ ከፈቱብን፡፡ እኛ በወቅቱ አጅበን የምንሄደው አስክሬን ነው፡፡ ሃዘን ላይ ነን፣ ሌላ ምንም ወንጀል አልፈፀምንም፡፡ በወቅቱ ህዝቡን በተኩስ ከበተኑ በኋላ ከቦታው ያልሄዱትን ያስሩ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ከአስክሬን መኪናው ጋር ወደ ፕ/ር አስራት ቤት ሄደን አስክሬኑን አሳርፈን ስንወጣ፣ ጥበበ ከሚባል ልጅ ጋር ተይዘን ታሰርን፡፡ ያ የእስር አጋጣሚ ሳስበው ሁሌ ልቤን ይነካኛል፡፡ አስክሬን እንኳ ማጀብ ነውር የነበረበት ስርአት እንደተገነባ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ ከታሰርኩበት አጋጣሚ አሳዛኝነት በመለስ ደግሞ የተፈታሁበት መንገድ አስቂኝ ነበረ። በወቅቱ በ1987 ምርጫ የእጩ ተወዳዳሪነት መታወቂያ በኪሴ ነበር፡፡ መታወቂያ ሲጠይቁኝ እሱን ሰጠኋቸው፡፡ በመታወቂያው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት … የሚል ሃረግ ነበረች፤በዚያም የምክር ቤቱ አባል መሰልኩት መሰለኝ መርማሪው ስልክ ደወለና፣ “በቃ ተለቀሃል” አሉኝ፡፡
ሌላው በ1994 የታሰርኩበት አጋጣሚ እንዲሁ አስገራሚ ነበር፡፡ በወቅቱ “አሰብ የኢትዮጵያ ናት” በሚል እንቅስቃሴ ፊርማ አሰባስብ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ሚያዝያ 5 ቀን 1994 አቶ ስዩም መስፍን ባድመ ለኛ ተፈርዷል ከማለታቸው በፊት ሚያዝያ 4 ቀን ነው እኔና ጓደኞቼ ከየቤታችን የታሰርነው። እንደውም አንደኛው ጓደኛችን ወንድሙ ሞቶ ለቅሶ ላይ ነበር፡፡ ጋቢ ለብሶ እያለቀሰ እያለ ነው ከወንድሙ ለቅሶ ላይ ይዘው ያሰሩት፡፡ የታሰርነው ሜክሲኮ የሚገኘው ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ መርማሪ ተብሎ የጠየቀኝ ፖሊስ፤ “አሰብ የኢትዮጵያ ናት ብለህ የምትለው የኢትዮጵያ መሆኗን ማን ነው የነገረህ?” ነበር ያለኝ፡፡ ይሄ ለኔ የቀልድ አይነት ጥያቄ ነበር፡፡ የመጀመሪያው አያቴ ነገሩኝ፣ አሰብ ብቻ ሳይሆን ኤርትራም፣ ቀይ ባህርም የኢትዮጵያ አካል ናቸው ብዬ አምናለሁ አልኩት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ት/ቤት አስተማሪዬ አስተምረውኛል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሳነብ፣ የኛ መሆኗን አረጋግጫለሁ አልኩት። በንዴት የወረቀት መብሻ ወርውሮ ግንባሬን መታኝ፣ ከመቀመጫው ተነስቶም በሽጉጥ ሰደፍ መታኝ፡፡ በወቅቱ እጆቼን ወደ ኋላ በሰንሰለት ታስሬ ነበር፡፡ እየመታኝ ሳለ ሌላ ባለስልጣን ገባ፤ ምንድን ነው የተፈጠረው ሲለኝ፣ የተነጋገርነውን አስረዳሁት፡፡ አሰብ የኢትዮጵያ መሆኗን ማን ነገረህ አለኝ … እኔም አያቴ ነገረኝ፣ ት/ቤትም ተምሬያለሁ፣ መፅሐፍም ሳነብ አውቄያለሁ አልኩት፡፡ “እንደዚህ አስረኸው እንደዚያ ካለህ ፍታው” አለው፡፡ ወዲያው ካቴናውን ከእጄ ፈታ፡፡ ከዚያም “ነገ የአልጀርሱ ስምምነት ውጤት ለህዝቡ ይነገራል፤ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ አሰብ የኢትዮጵያ ናት ብሎ ተቃውሞ የሚያሰማ ከሆነ ለሚደርሰው ሁሉ ኃላፊነት እወስዳለሁ ብለህ ፈርመህ መውጣት ትችላለህ” አሉኝ፡፡ እኔም “ይሄ ለኔ በጣም ቀላል ነበር፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ከተቃወመና ክብሩን ሃገሩን ለማስመለስ ከተንቀሳቀሰ ግዴለም እኔ ተጠያቂ እሆናለሁ፤ ኃላፊነቱንም እወስዳለሁ” ብያቸው በደስታ ነው የፈረምኩላቸው። ይሄ ሂደት ያስገርመኛል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ በርካታ የታሰርኩባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡
በመጨረሻ የታሰርክበት ሁኔታ እና የእስር ቤት ቆይታህ ምን ይመስላል?
የተያዝኩት ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባልያዙ ሰዎች ነው የተያዝኩት። ሰዎቹ የፖሊስ ልብስ አልለበሱም፤የፖሊስ መኪና አልያዙም፡፡ መታወቂያቸውን እንኳ አላሳዩኝም። እንደያዙኝ ልብሴን ከላዬ አውልቀው ነው ያራገፉት። ከዚያ መኪና ውስጥ ነው የከተቱኝ። በተደጋጋሚ በአደባባይ ደብድበውኛል። በጣቢያም ተደብድቤያለሁ፣ በድብደባም ከጆሮዬ ደም እስከ መውጣት ደርሷል፡፡ የያዙኝ ሰዎች ደህንነቶች እንደሆኑ ያወቅሁት ራሱ ጣቢያ ከገባሁ በኋላ ነው። አብረውኝ የማተሚያ ቤት ሰራተኞች፣ ፎቶ ኮፒ አድራጊዎች ጭምር ነበር ለሰልፉ ወረቀት አዘጋጅታችኋል ብለው ያሰሯቸው፡፡ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ፤ እነሱ አይመለከታቸውም ብልም የሚሰማኝ አልነበረም። እንደተያዝኩ በማግስቱ መገናኛ ቤተልሄም ፕላዛ አካባቢ ወደሚገኝ  የደህንነት ቢሮ ተወሰድኩ፡፡ በኋላ መኪናቸውን ቀይረው የካ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ፡፡ የካ ወስደውኝ ከወንበር ጋር አስረው በአደራ አስቀመጡኝ። በኋላ ደግሞ መጥተው ወደ ኮልፌ ወሰዱኝ፡፡ በበነጋው ቅዳሜ ቀን ፍ/ቤት አቀረቡኝ፤ የ7 ቀን ቀጠሮ ተሰጠብኝ፡፡ የተከሰስኩበት ጉዳይም ህገ ወጥ ሰልፍ ለማድረግ የሚል ነበር፡፡ በጣቢያ በጣም ይደበድቡኝ ነበር፡፡
ልንጠራ ያሰብነው ሰልፍ ለመስከረም 21 ቀን 2004 ተጠርቷል፡፡ ሁሉም ያውቀዋል። ስንደበደብ ምን ፍለጋ እንደነበር አልገባንም ነበር። በኋላ መስከረም 13 ቀን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ተዛውረን፣ መስከረም 15 ቀን ደግሞ ሌላ ፍ/ቤት ቀርበን ጉዳያችንን አስረድተን የዋስ መብት ተፈቀደልን። ከዚያ የያዘን አካል “ይሄ እኛን አይመለከትም” በሚል ወደ ፌደራል ፖሊስ አዛወረን፡፡ ያንኑ ቃላችንን በድጋሚ ተቀበሉን፡፡ በኋላ ለዋስ ብይን በተቀጠርንበት ቀጠሮ ላይ አራዳ ፍ/ቤት መስከረም 18 ቀን 2004 እንድንቀርብ ተደረገ፡፡ በሽብር ተጠርጥረዋል የሚል ክስ ቀርቦብንም  28 ቀን የምርመራ ቀጠሮ ተሰጠ። ይሄ እንግዲህ ለኔ እስከ ዛሬም እንቆቅልሽ የሆነብኝ ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ ፍ/ቤት ዋስትና ፈቅዶልን፣ በሌላ ፍ/ቤት በሽብር የተከሰስንበት ታሪክ ነው ያለው፡፡
በማዕከላዊ በነበርንበት ወቅት ለ2 ወራት ለብቻዬ ታስሬያለሁ፡፡ ከቤተሰብ ጋር በዚህ ወቅት ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ ምግብ ፖሊስ ያቀብለኛል፤ ከማን እንደመጣልኝ እንኳ ሳላውቅ ነበር የምመገበው፡፡ የማላውቀው ሰው አመጣልህ የተባልኩትን ምግብ ነበር ለመብላት የምገደደው፡፡  
በአሁኑ ወቅት የፓርቲ ፖለቲካ ተዳክሟል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ በተለይ ከ1997 ምርጫ በኋላ ምን ይመስላል?
ከ1997 በኋላ ኢህአዴግ ካሮትና ዱላ ይዞ ነው ወደ ጨዋታ ሜዳ የገባው፡፡ የ97 ምርጫን ተከትሎ፣ የፓርቲ አመራሮች የታሰሩበት አጋጣሚ ነው የተፈጠረው። አብዛኛው ህዝብ የ1997 ዱላ አርፎበታል፡፡ በወቅቱ በዝዋይ ብቻ 11ሺ የቅንጅት እስረኞች እንደነበሩ አንዱ ኃላፊ ዝዋይ በነበርንበት ጊዜ በኩራት ሲናገር ሰምቼዋለሁ፡፡ ይሄ በወቅቱ ለለውጥ የተነሳ ህዝብ፤ በእስር በድብደባ፣ በግድያ መሸማቀቁን ያሳየናል፡፡ ከዚያ በኋላ ህዝብ በፖለቲካው ጉዳይ ቢቀዛቀዝ የሚገርም አይደለም። ሁለተኛው ኢህአዴግ ወደ ጨዋታው ይዞ የገባው ካሮት ነው፡፡ በቀላሉ ሊደለሉ የሚችሉትን በመደለል፣ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲፈራርሱ አድርጓል፡፡ እኔ ነኝ የዚህ ፓርቲ ባለቤት በሚል የሰውን መስዋዕትነት ያረከሱ ሰዎች በሀገራችን አሉ። እነሱ በሰው ስሜት ላይ ያሳረፉት በደል እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከነዚህ አንፃር የፓርቲ ፖለቲካ በሀገራችን ባይቀዛቀዝ ነበር የሚገርመው። ኢህአዴግ እኮ አሁን የፈፀመው ሳይቆጠር፣ አንዴ ባንክ በሌለበት ቦታ እየገደለ ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ተገደሉ እያለ፣ በገደላቸውና ባፈሰሰው የንፁሃን ደም ለፍርድ መቅረብ የሚገባው ነበር፡፡ ለፍርድ መቅረብ ይገባው የነበር ስርአት ነው፣ ለፍርድ አቅራቢ ሆኖ የተገኘው፡፡ ለዚህ የህዝቡ ትግልና የፓርቲዎች መኮላሸት ተጠያቂው አሁንም ኢህአዴግ ነው፡፡
ኢህአዴግ በ2002 ምርጫ  ፓርቲዎች ተዳክመው ባሉበት እንኳ ትንሽ ሲንቀሳቀሱ ይሸበር ነበር፡፡ በወቅቱ የመድረክ የኮልፌ ቀራኒዮ የምርጫ አስተባባሪ ሆነን ስንንቀሳቀስ፣ በምርጫው ዕለት የኢህአዴግ አባላት በሕገ ወጥ መንገድ መራጩን ሕዝብ፣ኢህአዴግን እንዲመርጥ ሲያስገድዱ እጅ ከፍንጅ በማስያዛችን እኛ ነበር የታሰርነው፡፡ ከ1997 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ምንም ሰልፍ አልተጠራም ነበር፡፡ ይሄን ዝምታ ለመስበር በማሰብ ነበር እኛ በ2004 ዓ.ም ሰልፍ ያዘጋጀነው። ሰልፉን ለማካሄድ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋር ሳይቀር እውቅና እንዲሰጡን ጠይቀን፣ በፀሐፊያቸው በኩል የሰጡን ምላሽ፣ “በዚህ ላይ የመወሰን ስልጣን የለኝም፤ጥያቄውን ለበላይ አካል አቅርቤዋለሁ” የሚል ነበር፡፡ የሰልፋችንን ጥያቄም በወቅቱ ለአቶ መለስ ዜናዊም ጭምር አሳውቀን ነበር፡፡ እኛ በወቅቱ ፍቃድ ሳይሆን ማሳወቅ በቂያችን ስለነበር፣ ወደ ሰልፍ እንቅስቃሴ ነው የገባነው፡፡ በወቅቱ ደግሞ የአረብ ሀገራት የለውጥና የትግል  እንቅስቃሴ ይካሔድ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ስላልጣማቸውና ወደ ሀገራችን ይገባል በሚል ስለፈሩ፣ እኛን ለማስፈራራትና ሰልፋችንን እንድናቆም ሊያስገድዱን ሞክረዋል፡፡ ማስፈራራቱ የማይሰራ ሲሆን ደግሞ አስረውናል፡፡
ከእስር ቤት መልስ የሀገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዴት አገኘኸው?
አሁን ህዝቡ ለውጡን እኔ አመጣዋለሁ ብሎ በራሱ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ እገሌ ፓርቲ ይምራኝ እያለ አይደለም፡፡ ልክ እንደ 1997 ሁሉ በርካታዎቹ ወታደራዊ ካምፖች ወደ እስር ቤት ተለውጠው አይተናል፡፡ በርካቶች “አይደገምም” የሚል ቲ-ሸርት አድርገው አይተናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አይደገምም የሚል ቲ-ሸርት ባደረጉ ወጣቶች ፊት ቆመው ንግግር ማድረጋቸው ለእኔ አሁንም ድረስ ያስገርመኛል፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እንጂ ተግባር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምን ያህል በካድሬዎቻቸው እንደተወናበዱ መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚያ ወጣቶች ሰርቀው፣ አጭበርብረው አይደለም፣ የነፃነት ትግል ስላደረጉ ነው ታስረው፣የተሃድሶ ስልጠና ተሰጣቸው የተባለው፡፡ አሁንም ህዝቡ ለመንግስት በቂ መልዕክት በሚያስተላልፍ ደረጃ እየታገለ ነው። መብቱንና ነፃነቱን እየጠየቀ ነው። በዚህ መሃል እየተካሄደ ያለው ትግል መቀናጀት ይጎድለዋል፡፡ ግቡ ሊለይ ባልቻለ መልኩ፣ አንዳንድ ጊዜ በቋንቋና በዘር ተለይቶ ሲካሄድ እንመለከታለን። ይሄ እንደ ሃገር ጉዳት አለው፡፡ ሊካሄድ የሚገባው፣ ሃሳብ በሃሳብ ሊሸነፍበት የሚችል ትግል ነው፡፡ የሀሳብ የበላይነት እንዲመጣ እንጂ የዘር የበላይነት እንዲመጣ መታገል ብዙ አያራምደንም፡፡  
አገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ የምትወጣው እንዴት ነው ብለህ ታስባለህ?
አንዱ አገራዊ  መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሲፈጠር ነው። እንደሰማሁት ኢህአዴግ ከሚደራደራቸው ድርጅቶች ጋር በብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ብሏል፤ ግን ይሄን ሲል ማድረግ ያለበት አብረውት ከሚደራደሩት ውስን ፓርቲዎች ጋር ሳይሆን ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በሰላማዊም ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ከሚታገሉት ጋር ነው መሆን ያለበት። በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ ኃይሎች ተካተው፣ በግልፅ ውይይት ተደርጎ፣ የሀገሪቱ ችግር በግልፅ መፍትሄ ካልተቀመጠለት እንደ ሀገር ለኛ አደጋ ነው፡፡ በሚደረገው ሂደት የሚመጣውን ውጤትም ኢህአዴግ ለመቀበል ከወዲሁ ዝግጁ ሆኖ ነው፣ ወደ ብሄራዊ ውይይቱ መግባት ያለበት። ውጤቱ የሽግግር መንግስት ምሥረታ የሚያስከትል ከሆነም መቀበል ግዴታው ነው፡፡
ብሄራዊ መግባባት በህገ መንግስቱ በተለይም በአንቀፅ 39 ጉዳይ፣ በሰንደቅ አላማ፣ በሀገር ዳር ድንበር፣ በፌደራል አወቃቀር ጉዳይ ያስፈልጋል። ለምሳሌ መንግስትና ህዝብን ያላግባባው አንዱ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነው፡፡ የአርማ ጉዳይ በዋናነት አላግባባም፡፡ ለምን በግድ ተቀበሉ ይባላል፡፡ ደርግ እኮ አርማ ያለውን ባንዲራ ይጠቀም የነበረው ለፕሬዚዳንቱ ቢሮዎች ነው። በአድዋ ጦርነትም፣በ5 ዓመቱ አርበኝነት ጊዜም የሞአንበሳ አርማ ያለበት ባንዲራ አልነበረም በሰፊው ህዝብ የተያዘው፤ ሌጣው ባንዲራ ነበር፡፡ ለምን አርማ ተቀበሉ በሚል ህዝብ ይጨነቃል፡፡ ሌላው የአንቀፅ 39 ጉዳይ ነው። ይህም ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ አንዴ በህገ መንግስት ፀድቋል ተብሎ እድሜ ልክ የጭቅጭቅ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል የለበትም፡፡ የድንበር ጉዳይ በደርግ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ጊዜም በህገ መንግስት በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በኢህአዴግ ጊዜ በግልፅ አልተቀመጠም። ለምን አይቀመጥም? ምንድን ነው የተፈራው? ሌላው የፍትህ የደን ጥናትና የፀጥታ ስርአቱ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ የፍትህ የደኅንነቱና የፀጥታ ስርአቱ መሻሻል ያለበት ለኛ ብቻ አይደለም፤እነሱም እርስ በርስ ሲተሳሰሩ ይጠቅማቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢህአዴግ በአሁኑ ሰዓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በእኔ ዕምነት አዋጁ አስፈላጊ አይደለም። የሚያሳዝነው አዋጁ መታወጁ ሳይሆን ንፁሀንን ተኩሶ ከገደሉ በኋላ በስህተት ነው የሚል ምክንያት መስጠት ነው፡፡ በእኔ እምነት ይሄ ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ በሞያሌ ከተማም ይሁን በሌሎች የአገሪቷ ክልሎች ኢትዮጵያውያንን ተኩሰው የሚገድሉ የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች በአስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡
የፍርድ ሒደታቸው በግልፅ ተከናውኖ ውጤቱ በአስቸኳይ ለህዝብ መገለፅ አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህይወታቸውን ላጡት ሁሉ የተሰማኝን ልባዊ ሀዘን እየገለፅኩ፣ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡  

Read 7271 times