Sunday, 18 March 2018 00:00

አቶ በቀለ ገርባ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

• ከመታሰሬ ከአንድ ወር በፊት እንደምታሰር አውቅ ነበር
          • ህዝቡ ራሱ በመረጣቸው መሪዎች መተዳደር ይፈልጋል
          • ኦህዴድንና ግለሰብ አመራሮችን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል

    የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርና በቅርቡ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ከተለቀቁ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ስለ እስራቸው ጉዳይ፣ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

    አሁን ከእስር በተፈቱበት መልኩ ከእስር እፈታለሁ ብለው ገምተው ነበር?
እኔ በዚህ ሁኔታ እንፈታለን የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ይልቅ ተስፋ አድርጌ የነበረው ከመጀመሪያ አንስቶ የተከሰስንበት ጉዳይም ምንም መሰረት የሌለውና ማስረጃም ያልቀረበብኝ በመሆኑ በመጀመሪያ ብይን ላይ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከሚለቀቁት አንዱ እሆናለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ አንድም የሰው ማስረጃ አልቀረበብኝም፣ የቀረቡብኝ የሰነድ ማስረጃዎችም በብይኑ ላይ ውድቅ ተደርገዋል፤ ስለዚህ በብይኑ መፈታት ነበረብኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ በኋላም የክስ አንቀፁ ከሽብር ወደ ወንጀል ተቀይሮ ተከላከል ስባል በዋስ እወጣለሁ የሚል እምነት ነው የነበረኝ፡፡ ያ ሁኔታ ከተስተጓጎለ በኋላ ጉዳዩ የፖለቲካ እንጂ የፍትህ አለመሆኑን ነው የተረዳሁት፡፡ ከዚህ አንጻር በህዝቡ ጫና ይፈቱናል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ አንድ ጊዜ መደበኛውን የፍትህ ስርአት አዛብተው ከቀጠሉ ወደ ኋላ አይመለሱም፣ በዚያው ይገፉበታል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ምክንያቱም የዋስትና ገንዘብ ካስያዝኩ በኋላ ሳልፈታ ለ7 ወር ሲዘገይ፣ ሌላ ጉዳይ እንደሆነ ነው የተረዳሁት፡፡ እናም  በህዝቡ ግፊት እንዲህ ተንበርክከው ይፈቱናል ብዬ አልጠበቅሁም።
በሽብር ተከሰው ለ4 ዓመት ታስረው ከተፈቱ ከጥቂት ወራት በኋላ ተመልሰው ወደ እስር ቤት ሲገቡ ምን ተሰማዎት?
የአሁኑም ሆነ በመጀመሪያ የታሰርኩባቸው ጉዳዮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እንዲያውም የመጀመሪያው ከዚህ የበለጠ አስቂኝም ነበረ። እዚሁ አዲስ አበባ እያለሁ፣ ደሞዝም ከማስተምርበት ዩኒቨርሲቲ እየተቀበልኩ፣ ክፍል ገብቼ ተማሪዎችን እያስተማርኩ፣ ከአዳማ አዲስ አበባ እየተመላለስኩ ስሰራ ባለበት ሁኔታ ነበር፣ ኬንያ ሶሎሎ የሚባል ቦታ ሄዶ የኦነግ ተዋጊ ለመሆን ስልጠና ወስዷል የሚል ክስ የቀረበብኝ፡፡ በወቅቱ ክሱ ቢያስገርመኝም የማሰሪያ ሰበብ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ከተፈታሁ በኋላም አሜሪካ ሄጄ ነበር። ከአሜሪካ ተመልሼ የመጣሁትም ለመታገል ነበር፡፡ መታሰርም እንደሚኖር እያወቅሁ ነው የተመለስኩት፡፡ እዚህ ሆኜ መታገል፣ በሀገሬ መኖር፣ በሀገሬ ኢ-ፍትሃዊነትን እየታገልኩ በሰላማዊ ትግል ምርጫን ማሸነፍ፣ በሰላማዊ ትግል ስልጣን መያዝ ይቻላል በሚል እምነት ነው የተመለስኩት፡፡ በዚህ መሃል በድጋሚ መታሰር እንደሚኖርም አውቅ ነበር። በነገራችን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰሬ ቢያንስ ከ1 ወር በፊት ሊያስሩኝ እንደሚችሉና ለማሰር እንደወሰኑ አውቅ ነበር፡፡ በዚያ ሰዓት ሀገር ለቅቄ መውጣት እየቻልኩ ነው፣ ሃገር ውስጥ የቆየሁት፡፡ ለህዝቡ የትግል ፅናትን ማሳየትና ማስተማር ይቻላል በሚል ነበር ያንን ያደረግሁት፡፡
በእስር ላይ ሳሉ የጤንነትዎ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገር ነበር፡፡ አሁን ጤንነትዎ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?
አንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ ተደማምሮ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ደሞ እኔ ግፊት ነበረብኝ፡፡ በዚህ ምክንያት አይኔ ውስጥ የደም መፍሰስ ነገር ነበር፡፡ ይህ የደም መፍሰስ ሁኔታ እይታዬን ጎድቶታል፡፡ ማንበብ እስኪሳነኝ የደረስኩበት ሁኔታ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ጫና ምክንያትም ወደ መንግስት ሆስፒታል ተወስጄ ነበር፡፡ እነሱ ስላልቻሉ ወደ ግል ህክምና ተቋም ተወስጃለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ለውጥ አለኝ፡፡ ከእስር ከተፈታሁ በኋላም ህክምናዬን እየተከታተልኩ ነው፡፡ አሁን የጤናዬ ሁኔታ ጥሩ በሚባል መልኩ ተሻሽሏል፡፡
እርስዎ ታስረው በነበረበት ወቅት በጎንደር ሰላማዊ ሰልፈኞች ምስልዎትን ይዘው በመውጣት ለእርስዎ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ ያን ጊዜ  ምን ተሰማዎት?
አጋጣሚው እጅግ በጣም የሚገርም ነው። እንዴት ባለ ሁኔታ እዚያ ደጋፊዎች ላፈራ እንደቻልኩ በወቅቱ ገርሞኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በትዕይንቱ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው የተንፀባረቀው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ያለ ኢ-ፍትሃዊነት ለሌላውም ጠንቅ ነው የሚለው የእነ ማርቲን ሉተር ኪንግ አባባል በግልፅ የተንፀባረቀበት ነው፡፡ ለፍትህ የሚታገሉ ሰዎች ችግር ሲገጥማቸው፣ ወደ ሌሎችም መዛመቱና ድጋፍ ማግኘታቸው አይቀርም፡፡ የመብት ታጋዮችንም ስም እያነሱ አጋርነት ማሳየት በእውነቱ አርቆ አስተዋይነት ነው። ለሀገር አንድነትም ይሄ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ እኔ በሁኔታው በጣም ነው የተደሰትኩበትና የኮራሁበት፡፡ በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ መለመድና እንደ ምሳሌም መወሰድ ያለበት ነው። የትም ቦታ ያለ ወገናችን ወገን ነው፤ የትም ቦታ ያለ ታጋይ የሁላችንም ታጋይ ነው፣ የትም ቦታ ያለ ኢ-ፍትሃዊነት ደግሞ ለሁሉም ፀር ነው የሚለው አስተሳሰብ፣ የበሰለ ህዝብ አስተሳሰብ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለወደፊትም ይህ አስተሳሰብ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባው ነው፡፡
ከእስር ከተለቀቃችሁ በኋላ ከህዝብ የተደረገላችሁን ከፍተኛ አቀባበል ጠብቃችሁት ነበር?
አቀባበሉ ያልተጠበቀና ከፍተኛ ነበር፡፡ በተለይ የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት በዚህ ደረጃ ተቀብለው፣ እውቅና ሰጥተው እንዲህ አይነት መድረክ ማዘጋጀታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ እነሱም አንድ እርምጃ ወደፊት እየተራመዱ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄ መለመድ ያለበት ነገር ነው፡፡ ህዝቡ እንዲህ ያለውን አቀባበል በአደባባይ ወጥቶ ማድረጉ ለፍትህ ያለውን ጥማት፣ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ያለውን ፍላጎት እንዲሁም ለውጥ እንዲመጣ ምን ያህል እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። ህዝቡ በዚህ ስርአት መሰላቸቱን፣ ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ እንደማይፈልግ ለማሳየት የፈለገ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ትክክለኛው የህዝብ ስሜት ነው፡፡
እርስዎ ከመታሰርዎ በፊትና ከተፈቱ በኋላ በኦሮሚያ ያለውን የህዝብ እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
ህዝቡ በጣም በተደራጀና ግልፅ በሆነ መንገድ ፍላጎቱን ማሳየት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያውን ትልቅ ፍላጎት ያሳየው በ1997 ምርጫ ነበር፡፡ ያኔ ገዥው ፓርቲን እንደማይፈልግ በግልፅ አሳይቷል። ከዚያ በኋላ የተደረጉ ሙከራዎችም የህዝቡን ፍላጎት ሊያሟሉ ያልቻሉ ነበሩ፡፡ ህዝቡ በቃልም በተግባርም አሁን ደግሞ በመብት ረገጣው በቃኝ እያለ እንዳለ ነው የተገነዘብኩት፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት በጥቃቅን ቡድኖች ነበር የሚንቀሳቀሰው፤ አሁን ግን ህዝቡ እንደ ህዝብ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ህዝቡ አዲስ ነገር፣ አዲስ ስርአት የማየት ፍላጎት እንዳለው ነው የሚያሳየው። አዲስ ትውልድ እየመጣ፣ አሮጌውም መንገድ እየለቀቀ ያለ መሆኑን የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ ይሄን የለውጥ ፍላጎት ሃገሩን እያስተዳደሩ ያሉት እንዴት እንደሚቀበሉት ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት፡፡
የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄና ፍላጎት ምንድን ነው ይላሉ?
ህዝቡ ፖለቲካዊ ጥያቄ ነው የሚጠይቀው። በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ይፈልጋል፤ ራሱ በመረጣቸው መሪዎች መተዳደር ይፈልጋል፤ ይሄን እድል እስካሁን አላገኘም፡፡ ይሄን ፍላጎቱን በተለያየ መንገድ አሳይቷል፡፡ ምርጫ እየተባለ አመት እየተቆጠረ፣ በሚሊዮን ብር እየተረጨ፣ ለዓለም ህዝብም ምርጫ ተካሂዷል በሚል የሚቀለደው ቀልድ እንዲቆም ህዝቡ ይፈልጋል፡፡ ህዝቡ እስካሁን ራሴ በመረጥኳቸው መሪዎች ነው እየተዳደርኩ ያለሁት ብሎ ማመን ያልቻለበት፣ አሁንም ገዥዎች በኃይል እላዩ ላይ የተጫኑበት አድርጎ የወሰደ በመሆኑ ጥያቄው በዚህ ዙሪያ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ሁሉም ነገር የሚመነጨው ማለትም ዲሞክራሲያዊ፣ ሰብአዊ መብቶች የሚባሉት ሁሉ ከዚሁ እውነተኛ የምርጫ ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ግልፅ የፖለቲካ ጥያቄ እንጂ መልካም አስተዳደር ምናምን አይደለም። መልካም አስተዳደር ከጤናማ የፖለቲካ ስርአት ነው የሚመነጨው፡፡ አሁን ህዝቡ እያለ ያለው፣ ”እያስተዳደራችሁኝ ያላችሁት በህጋዊ መንገድ አይደለም” ነው፡፡
የኢህአዴግ መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እየሰራሁ ነው ቢልም ትርጉም ያለው ለውጥ ግን ማምጣት አልቻለም፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ያልቻለው ለምን ይመስልዎታል?
መንግስት ራሱ ችግር እያለበት መፍትሄ ማምጣት አይችልም፡፡ ይሄ መንግስት ፖሊሲ አውጥቶ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ነው የሚያስፈፅመው እንጂ ለህዝቡ በሚመች መንገድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባለ ስንት ዓመት ተዘለቀ? ይህ የመልካም አስተዳደር ችግር የመጣው ለህዝብ ወገንተኛ ባለመሆን፣ ለራስ ወገንና ጥቅም የሚሮጡ በመሆናቸው ነው፡፡ በመጀመሪያ እነዚህን ባለስልጣን ያፈራው ስርአቱ ነው፡፡ ስለዚህ ስርአቱ ላይ ነው ለውጥ መምጣት ያለበት። ባለስልጣንን እየነጠሉ ማባረርና ማሰር ዋጋ የለውም፡፡ በዚሁ ፓርቲ ፖሊሲ፣ አሰራር፣ ልምድ ውስጥ የሚገባ ማንም ሰው፤ አዲስ ማሻሻያ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስርአቱ በአጠቃላይ በሙስና ተዘፍቋል። በምትኩ ለሀገራቸው ቅን፣ ለህዝባቸው ሩህሩህና ለህዝባቸው ተገዢ የሆኑ ሰዎች ናቸው የሚያስፈልጉት፡፡
አንዳንዶች ከኦህዴድ አዲስ አመራር ለውጥ ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ ኦህዴድ እንደ ድርጅት ለውጥ ያመጣል፤ ይሄን ሃገር የመምራትም ብቃት አለው ብዬ ለማመን ያስቸግረኛል፡፡ ከአባላቱ አመላመል ጀምሮ ወደ ስልጣን የሚመጡበት አካሄድ፣ ከዚህ በፊት የነበራቸው ታሪክና የአሰራር ልምድ እንዲሁም እውቀት አንፃር ለዚህ ሃገር አመራር ብቃት ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን በኦህዴድ ውስጥ ብቃት ያላቸው፣ ለህዝባቸው የሚቆረቆሩ፣ ፍትህና ነፃነት የሚሹ ሰዎች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ እንደ ድርጅት ስመለከተው፣ እኔ ምንም ተስፋ የምጥልበት አይደለም፡፡ እዚያ ድርጅት ውስጥ ግን ተራማጅ የሆኑ ለውጥ ማምጣት የሚፈልጉ፣ ለዚህ ሀገር መልካም መሻቱ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አሁን ኦህዴድ ውስጥ የሚታየው ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ ግለሰቦችንና ድርጅቱን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡  
አሁን አገሪቱ የምትገኝበትን  የፖለቲካ ቀውስ እንዴት ያዩታል?
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ እኛ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ አለበት ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም አስቸኳይ አዋጅ መታወጅ የነበረባቸው በርካታ ጊዜያት አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በሚሊዮኖች ተፈናቅለው ባይተዋር በሆኑበት ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም። አሁን ምን ተፈጥሮ አዋጁ እንደታወጀ ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተብሎ የፖለቲካ እስረኞች እንዲወጡ ተደረገ፣ ህዝብም የመብት ታጋዮቻችን እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም ብሎ ሰፊ አቀባበል እያደረገላቸው ባለበት ወቅት ነው በህዝቡና በተፈቺዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመበጠስ በሚያስመስል መልኩ አዋጁ  የታወጀው፡፡ ይሄ አዋጅ ፀደቀ የተባለበትም መንገድ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው፡፡ ቁጥር ተሳስተናል፤ ይቅርታ በተባለበት ሁኔታ ነው አዋጁ ፀደቀ የተባለው። ይህ አወዛጋቢ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ነው ሃገር የበለጠ እየታመሰ ያለው፡፡ ከዚያ በፊት ያለው ሁኔታ አንፃራዊ መረጋጋት የሚታይበት ነበር፡፡ ሰዎች በስህተት እየተባለ የሚገደሉበት ሁኔታና የሚሰደዱበት አግባብ ነው የተፈጠረው፡፡ ሃገሪቱ ወደባሰ አጣብቂኝ እንድትገባ ነው የተደረገው፡፡
በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ምን ዓይነት ፖለቲካዊ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ብለው ያምናሉ?
አሁን ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስለኛል፡፡ የህዝቡ አርቆ አስተዋይነትና አብሮ የመኖር ባህል ነው እንጂ እንደ መንግስት አሰራር ቢሆን ህዝቡ በተፋጀና ሀገሪቱ ወደባሰ ቀውስ በገባች ነበር፡፡ አሁን ክልሎች እየጠነከሩና ሃገር እያስተዳደሩ ሲሆን በአንጻሩ ፌደራል መንግስቱ እየተዳከመ ያለ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ የፖለቲካ ቡድኖችና የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው፣ ውይይትና ንግግር አድርገው፣ መፍትሄ ማመንጨት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ገዥው ፓርቲም ይሄን ውይይት ለሁሉም አካላት መጋበዝና ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት ይመስለኛል፡፡   


Read 4166 times