Print this page
Sunday, 18 March 2018 00:00

ኢህአዴግ አቅቶታል፤ እስቲ እኛ ቤቱን እናጽዳለት!

Written by  ማርቆስ ረታ
Rate this item
(5 votes)

 “--ቀድሞ ነገር ኢ-ፍትሐዊ ሥርዓት መገንባትን ምን አመጣው? ኢህአዴግ አመራሩን/አባሉን ለኢ-ፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ
በሚደረገው ትግል መስዋዕትነት እንዲከፍል መጠየቁና አዎንታዊ ምላሽ መጠበቁ ምን ይባላል? ሰው ፍትህ ለቸገረው ይታገላል፤ ለተጨቆነ ይታገላል፤ አድልዎን ለማጥፋት ይታገላል፤ እኩልነትን ለማረጋገጥና ችጋርን ለማጥፋት ይታገላል። እንዴት ሰው ፍትሐዊ ያልሆነ ሥርዓት ለመገንባት እታገላለሁ ይላል?--”

   የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ተቀምጧል አሉ፤ እንደገና። ሊቀመንበር ለመምረጥ ነው ተብሏል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ጸድቋል፤ እንደገና። ኢህአዴግ ውስጡ ችግር አለ፤ ከአባል ግንኙነቶችና አደረጃጀት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። ከሕዝብ ጋር ያለው ችግር ይታወቃል። ሕዝብ ይጮኻል፤ ኢህአዴግ ምንም ሊያደርግለት አልቻለም። ምክንያቱም ፖሊሲ ሳይለውጡ ወይም ሳያሻሽሉ ያገርና የሕዝብ ችግር መፍታት አይቻልም። ኢህአዴግ ለውጥ አመጣለሁ እያለ ከመፎከር በቀር ትርጉም ያለው ሥራ ለመስራት አልቻለም። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ፖሊሲ አመንጭቶ የመተግበር ስልጣኑ በአበዳሪዎች እጅ ገብቷል። ይህን አልነገረንም፤ የተመዘገበው እድገት በኢህአዴግ ትክክለኛ ፖሊሲዎች የተገኙ ናቸው ሲል፣ ልክ ፖሊሲዎቹን ራሱ ያመነጨ፥ እንደፈለገም ሊቀይራቸው የሚችል መስሎ ሲታይ ኖሯል። ሆኖም ፖሊሲዎቹን ልቀይር ቢል፣ እውነተኛ ባለቤቶቹ አይፈቅዱለትም። ስለዚህ መቼም ቢሆን የህዝቡን ችግር ሊፈታ አይችልም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢህአዴግ በአበዳሪዎቹ መዳፍ ሥር ገብቶ የሚገኝ፥ አለቆቹ በግድ የጫኑበት፥ የአገርና የሕዝብ መከራ ምንጭ የሆነውን ፖሊሲ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ፣ የራሱ አስመስሎ ለማቅረብ ሲሞክር የኖረ አሳዛኝ ድርጅት ነው። ሆኖም ኢህአዴግ ራሱን በአበዳሪዎች ቁጥጥር ሥር በማስገባቱ አገራችንንም ለባዕዳን የቅኝ ግዛት ኃይሎች አሳልፎ ሰጥቷል። ስለሆነም እሱ ከአለቆቹ ነጻ ለማውጣት፣ እኛም ራሳችንንና አገራችንን ከመሪር አገዛዙ ለማውጣት የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። የመጀመሪያው ሥራ የኢህአዴግን ቤት ማጽዳት ነው። ለዚህም የድርሻችንን እነሆ።      
መግቢያ
መሪዎቹ ባለፈው ታህሳስ ወር ከግምገማው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ከሰማይ በታች ሳይነሳ የቀረ አግባብነት ያለው ጉዳይ የለም ማለታቸው ይታወሳል። ሆኖም የፖሊሲ ለውጥ፥ ማሻሻያ ሲባል አልሰማንም። የአገራችን የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የገንዘብ ተቋሞች ጉዳይም ሳይረሳ አልቀረም መሠል። በርግጥ አዳዲስ ሀሳቦችን አለመቀበል አመራሩ ራሱን በድክመት ከገመገመባቸው ነጥቦች አንዱ ሆኖ ቀርቦ ነበር።
በርግጥ የመንግሥት ስልጣን ይዣለሁ የሚል አመራር ችግሮችን ለመፍታት ተነስቶ ሲያበቃ፣ ፖሊሲዎቹን ይዘነጋል ለማለት ቢከብድም ኢህአዴግ የተጀመረውን ማስቀጠል አለብኝ በማለቱ ዋናውን የለውጥ መሣሪያ ሳይጠቀም በምን መንገድ ለውጥ እንደሚያመጣ አልታወቀም። ሆኖም የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እንከን የለባቸውም፥ ችግሩ የአመራር ድክመት ነው የሚለው ድምዳሜ፣ የግምገማውን ትኩረት በአመራሩ ዙርያ ብቻ ወስኖ በማስቀረት የፖሊሲዎቹ እውነተኛ ይዘትና የሚያስከትሏቸው ውጤቶች ሳይፈተሽ እንዲቀር አድርጎታል። በሌላ በኩል አንድ መሪ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ የሚሰጥ መሆን እንደሚገባውና ኢህአዴግ ውስጥ ያለው አመራር ይህን ማድረግ ባለመቻሉ፣ የአመራር ውድቀት ማጋጠሙን የተገነዘበና ለውጥ ማምጣት አለብን የሚል ኃይል ተፈጥሯል። ከግምገማው በኋላ የኢህአዴግ አመራር ከደረሰባቸው ድምዳሜዎች አንዱም አገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በፈጠረው ተስፋና የፖለቲካ ችግሮች በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች የሚል ነበር። ከዚህ ድምዳሜ በስተጀርባ የድርጅቱ የቆየ እምነቱ አለ፤ ኢህአዴግ የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለበትም የሚል። በዚህ ጽሑፍ እንዲያውም የኢህአዴግ ዋነኛ ችግር ፖሊሲዎቹ መሆናቸውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተያዘውን መንገድ በምሳሌነት በማንሳት አስረዳለሁ። በመቀጠል የኢህአዴግ አመራር አለብኝ የሚለው ዋነኛ ችግር የአመራር ድክመት ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ለእውነተኛው ችግር የሚቀርቡ፥ ነገር ግን በግምገማው ሳይነሱ አልያም በማብራሪያው ሳይጠቀሱ የቀሩ የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅርና የአባል ድርጅቶችን ግንኙነት የሚመለከቱ ነጥቦችን አነሳለሁ። በመጨረሻም ኢህአዴግ የእውነት ለኅብረተሰባዊ ለውጥ የተሰጠ ከሆነ፣ ከአለቆቹ የገንዘብ ተቋማት ተቀብሎ በአገራችን ላይ የጫናቸውን ፀረ-ድኻ ፖሊሲዎች ፈትሾ ለማስተካከል መድፈር እንዳለበትና የምር እታደሳለሁ ካለም፣ ራሱንም ውስጡ በበቀለው የአገራዊነትና ሕዝባዊነት መንፈስ ለመቃኘት መድፈር እንደሚገባው እጠቁማለሁ።
1.1 የኢህአዴግ የእርሻና የምግብ ዋስትና ፖሊሲ
ኢህአዴግ የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም ሲል ራሱን የትክክለኛ ፖሊሲዎች ባለቤት አድርጎ ያቀርባል። ምን ያህል እውነት ነው? የእርሻውን ዘርፍ ባጠቃላይና በተለይም የምግብ ዋስትናን የሚመለከቱ ፖሊሲዎቹን በምሳሌነት በማንሳት እንመዝነው።
ኢህአዴግ “ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሚስጥር ነው” ማለቱን ገና አሁን መጀመሩ ቢሆንም እስቲ ኢትዮጵያን ብቻ የሚመለከት አንድ ያደባባይ ሚስጥር እናንሳ። ኢህአዴግ አለኝ በሚለው ፖሊሲም ሆነ በሚያቀርበው የኢኮኖሚ እድገት ዜና፥ በማንም ምስክርነት ሊቀየር ያልቻለ፣ ሁሉም የሚያውቀው አንድ እውነታ ቢኖር፣ ያገራችን ሕዝብ የሚበቃውን አምርቶና በልቶ፣ ተመስገን ብሎ እንዲያድር አለመደረጉ ነው።
ከሌላው አገር ሁሉ ተለይታ “እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የተባለላት አገራችን፥ ከሌላው ሕዝብ ተለይተው እግዚአብሔር “ምግባቸውን ሰጣኻቸው” የተባለላቸው ልጆቿ የሚበሉትን ለመለመን፣ ካመት ዓመት ባለስልጣኖቿ  እጆቻቸውን ለፈረንጆች ምፅዋት ዘረጉ ሲባል፣ ሰሚ ተመልካቹን ‘አምላካቸው ወዴት አለ?’ ለማሰኘት ያለመ የጠላት ሥራ ይመስላል። በዚያ ላይ ከሷ ሌላ ማንም አገር ያለማቋረጥ እጆቿን ለምግብ ርዳታ ዘረጋች ሲባል አለመሰማቱ፣ ‘እውነትም ጠላት አለቆቿን ቢያሞኛቸው’ ነው ያሰኛል። ባይሆን ታዲያ በቂ መሬት እንዳለን ይታወቅ የለም? እነሆ ሳውዲ አረቢያ ዜጎቿን ለመቀለብ የኢህአዴግ መንግሥት “የመጣል ያክል” በተባለለት የሞተ ዋጋ ከሚቸበችበው መሬት ተከራይታለች። ውሃም ቢሆን ከዝናቡ በተጨማሪ ብንፈልግ ጠልፈን የምናመርትበትን እግዚአብሔር ሰጥቶናል። እነሆ ግብጽ እንኳ ከኛ ፈልቆም ዘንቦም ከሚጎርፍላት ውኃ፣ ለራሷ በልታ ለሌላም ትሸጣለች። [ራሺያ የአውሮፓ ምርት አገሯ እንዳይገባ ማዕቀብ በጣለች ጊዜ ለፍራፍሬ አቅራቢነት ግብጽን መምረጧ ይታወቃል።] አሁንማ ጭራሽ ፍራፍሬዋን፥ (አፕል ተብርቱኳን) ወደኛው መላክ ጀምራለች። እንግዲህ እኛ መሬቱም ሆነ ውኃው ሳይቸግረን ለራሳችን የሚበቃ ያክል እንኳን ማምረት ያልቻልንበት ምክንያት ምንድነው? ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ እንዲበላ አደርጋለሁ ሲል የተናገረ የኢህአዴግ መንግስት፣ ሌሎች አገሮች እዚህ ድረስ መጥተው የሚያደርጉትን ማድረግ፥ ማለትም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚበቃ የምግብ እህል አገር ውስጥ ማምረት እንዴት ያቅተዋል? በዚያ ፋንታ የትም የተመረተ እህል በምጽዋት ብር እየሸመተ ማስገባቱን ለምን መረጠ?
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ቢያንስ ሁለት አማራጭ መንገዶችን ሊከተሉ ይችላሉ። አንዱ የዓለም ገበያን እንደ መፍትሔ የሚያቀርበው፥ ለዓለም ገበያ እያመረቱ ከዚያውም እየሸመቱ መብላትን የሚመክረው [የኒዮ ሊበራል] መንገድ ሲሆን፥ ሁለተኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ በራስ አገር ውስጥ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ መንገድ ነው። የመጀመሪያው አማራጭ የገበያ ኃይሎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይችላሉ ከሚል እምነት የሚንደረደር ሲሆን፤ የምግብ ዋስትናንም በዓለም ገበያ አማካይነት በዓለም ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያልም ነው። ስለሆነም ገበሬው ለገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርትና ያን ሸጦ በሚያገኘው ገንዘብ ደግሞ ለራሱ የሚሆነውን ምርት እንዲገዛ የሚመክር ነው። ሁለተኛው የምግብ ሉዓላዊነት አማራጭ በበኩሉ፤ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት እያንዳንዱ አገር ባለው የተፈጥሮ ሀብት ለራሱ የሚመገበውን ለማምረት ሲችል ብቻ የሚሳካ መሆኑን፥ እያንዳንዱ ማኅበረሰብም ሆነ ቤተሰብ ለራሱ የሚፈልገውን የምግብ ዓይነት በሚፈልገው መጠን እንዲያመርት ሲደረግ የምግብ ዋስትናው እንደሚረጋገጥ ያስረዳል። ይህ አማራጭ እንደ አገር ነጋዴ መሆን ሳያስፈልግ ሰርቶ፥ አርሶና አርብቶ፥ በልቶ ማደር ሊባል ይችላል። በአንጻሩ ገበሬው ለገበያ በተለይም ለዓለም ገበያ እንዲያመርት ሲደረግ፣ ባንድ በኩል ለምርቱ ደህና ገዢና ደህና ዋጋ የማግኘት ዕድሉ፥ እንዲሁም ለራሱ የሚያስፈልገውን ምርት የሚገዛበት ዋጋ ተለዋዋጩን የዓለም ሁኔታ ተከትሎ መዋዠቁ እንደማይቀር ይታወቃል። እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና የተፈጥሮ ሁኔታዎች በዓለም ገበያ ላይ፥ ብሎም በገበሬው ገቢና እንጀራ [የምግብ ዋስትና] ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ስለሆነም ኑሮው መቼም ከስጋት ሊላቀቅ አይችልም። ገበሬው ለራሱ የሚመገበውን አምርቶ ቢሆን ኖሮ፣ ቢያንስ በልቶ ማደር እንደሚችል ግልጽ ነው።
ዛሬ በኢህአዴግ ፊታውራሪነት በአገራችን የሚተገበረው የገበያው መንገድ፣ የምግብ ዋስትናችንን ጉዳይ ከዓለም ገበያ ጋር የሚያቆራኘው አማራጭ ነው። አተገባበሩም የገበሬውን ፍላጎት የሚከተል አይደለም።  ይልቁንም የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከዓለም ገበያ ጋር ማቆራኘቱ፣ አምራቹን ገበሬ ከከተሜው እኩል የምግብ እህል ሸማች ሆኖ እንዲሰለፍ ስለሚያደርግ፣ በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ሊረጋገጥ አለመቻሉ ነው።
የግብርናውን ዘርፍ በትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደሚመራ የሚታወቅ ሲሆን የዕቅዱን ትግበራ የሚቃኘው እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2012 የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የፈረሙትና በስፋት የማይታወቀው “ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና የቡድን 8 አዲስ ዕቅድ” [G8 New Alliance for Food Security and Nutrition in Africa] የተሰኘው ስምምነት ነው። በባራክ ኦባማ ሰብሳቢነት የአፍሪካ አገራት መሪዎችና የድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች በተገኙበት በተካሄደ ስብሰባ የተቀረጸው ስምምነት፣ ቡድን 8 አገራት ርዳታ ሊያቀርቡ፥ ምዕራባውያን ኩባንያዎች ኢንቨስት ሊያደርጉ፥ የአፍሪካ አገራቱ [ያኔ ጋና እና ኢትዮጵያ] በበኩላቸው፤ ለግሉ ዘርፍ የሚመቹ የፖሊሲ ማሻሻያ ሊያደርጉ ቃል የገቡበት ነበር። ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ 15 ዝርዝር እርምጃዎችን ያቀፉ አራት ግዴታዎችን ይጭናል፦ 1) የግሉ ዘርፍ በዕጽዋት ዘር ማባዛትና ስርጭት ላይ እንዲሳተፍ ማስቻል [አዲስ የዕጽዋት ዘር ሕግ ማውጣትን ይጨምራል] 2) የግሉን ዘርፍ ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚከለክሉ እንቅፋቶችን መቀነስ [የማዳበሪያና ጸረ ተባይ ኬሚካሎች የሚመለከቱ የፖሊሲ ማስተካከያዎች ማድረግን ይጨምራል] 3) በእርሻው ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የመሬት ይዞታ መብቶችን ማጠናከር፤ 4) የግብርና ብድር አቅርቦት መጨመር።
በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የዕጽዋት ዘር ገበያውን ለግሉ ዘርፍና ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የተመቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን መውሰድ ነበረባት። በመሆኑም የኢትዮጵያ የዕጽዋት ዘር አቅርቦትና ገበሬው የሚያመርተውን የሚወስኑ፥ ለገበሬው የሚቀርቡ ግብአቶችንና አቅራቢዎቹን፥ ገበያውንም ሁሉ የሚመለከቱ ህጎችና ደንቦች ወጥተዋል። የውጭ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት ‘የዕጽዋት ዘር’ እንደ ተራ ሸቀጥ በየሱቁ እንዲቸረቸር የሚያስችሉ “ቀጥታ የዘር ሽያጭ” የተባለ አሠራር ሁሉ ተዘርግቶላቸዋል። [የስምምነቱ ዓላማ በኢትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ 2.9 ሚ. አነስተኛ አርሶ አደሮችን ከድኽነት ማውጣት ሲሆን ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው የፖሊሲ ለውጦች ግን የጊዜ ገደብ ያልተበጀላቸውና የሁሉንም ገበሬ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ህይወት የሚነኩ መሆናቸውን በአዲሱ የዕጽዋት ዘር ሕግ ለመረዳት ይቻላል። ለምሳሌ በስምምነቱ መሰረት፣ በፍጥነት የወጣው አዲሱ የዕጽዋት ዘር ሕግ፣ ጤፍን ጨምሮ የአገራችንን የዕጽዋት ዘር በሙሉ በድንጋጌዎቹ ስር የሚያስገባ ሲሆን የቀድሞው ግን የተመዘገቡ የዕጽዋት ዘርን ብቻ የሚመለከት ነበር።] ስምምነቱ ትኩረቱን ሁሉ በዓለም ገበያ ላይ ካደረገው ዕቅድ ትግበራ ጋር ተቀናጅቶ የሚፈጸም ሲሆን ሕጎቻችንንም ከአፍሪካ አህጉራዊ ውሎች ጋር እንዲስማሙ የሚያደርግ ነው። በዚያ መሠረት ገበሬው የማይፈልገውን እንዲያመርት ከመገደዱም በላይ እንደለመደው ያገሩን ነባር የዕጽዋት ዘር ለማምረት እንዳይችል የሚያደርጉ የፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል። በዚያው ስምምነት መሠረት የዕጽዋት ዘርና የማዳበሪያ ገበያው ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ምዕራባዊያን ድርጅቶች ክፍት ከመደረጉም በተጨማሪ ገበሬው የዕጽዋት ዘርን ያክል ነገር እንደ ኦሞና ሳሙና ከየሱቁ እንዲገዛ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል። ምርጥ ዘራችሁ ይቅርብኝ አልፈልግም፥ ነባሩን ያገሬን ዘር ዘርቼ እበላለሁ የሚለውንም ነባሮቹና «የገበሬው» የሚባሉት “ምርጥ” ዘር በመደበኛው የዕጽዋት ዘር ገበያ አማካይነት ለገበሬው ስለማይደርሱት ወደደም ጠላ ገበሬው የማይፈልገውን የዕጽዋት ዘር እየገዛ እንዲዘራ፣ መሬቱንም ያልፈጠረበትን የማዳበሪያ ሱስ እንዲያስለምድ ተደርጓል። ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያስፈልጋል በማለት የሚከራከሩ ወገኖች፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና ነባሩን አዝርዕትና ያለ ማዳበሪያ ቢዘራ ሊገኝ የሚችለውን የምርት መጠን አናሳነትን፣ ማዳበርያና ምርጥ ዘር ሲተባበሩ ከሚሰጡት ከፍተኛ መጠን ጋር በማነጻጸር ያነሳሉ። ሆኖም ለገበሬው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀርቦለት የሚያመርተው ለራሱ የሚፈልገው ሳይሆን ለዓለም ገበያ የሚሸጥ በመሆኑ ያሳሰባቸው የሕዝብ ቁጥር ጉዳያቸው እንዳልሆነ በድርጊት ያረጋግጡታል።   
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በኢህአዴግ ፖሊሲና በገበሬው ፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት የሚያስረዳ፣ በዝናብ አጠር አካባቢ የተስተዋለውን ሁኔታ የሚመለከት አስተያየት ሰጥተው ነበር። [ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት] የኢቴቪ ጋዜጠኛው አርሶ አደሩ የሚቀርብለትን የዕጽዋት ዘርና ማዳበርያ የመግዛት ፍላጎቱ ቀንሷል መባሉን ጠቅሶ ምክንያቱን ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ. . . በዝናብ አጠር አካባቢ ያለው ገበሬ የሚቀርብለትን የዕጽዋት ዘር ገዝቶ እንዳይከስር ስለሚፈራ፥ በእጁ ያለችውን ምርታማነቷ አነስተኛ ቢሆንም ችግር መቋቋም የምትችለውን ዘር ለመዝራት እንደሚመርጥ፥ ማዳበሪያም እንደዚሁ እንደሚያስፈራው ገልጸው፥ ችግሩን ለመፍታት [ችግር የተባለው ምርጫው መሆኑ ነው] ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ እዚያ ያለው ባለሙያ ደግሞ አሳምኖ መሄድ አለመቻሉን ከጠቀሱ በኋላ፤ ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች የሚሆን ዘር ማቅረብ ባለመቻሉ ዝናብ አጠር ግብርና ለብቻው መሆን እንዳለበት፤ ካልሆነ ግን ኮሜርሻላይዝ ማድረግ እንደሚያስቸግር ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ፖሊሲውና ገበሬው አልተገናኙም። በግንዛቤ ማስጨበጫ ለማገናኘት መሞከርም ገበሬውን ደንቆሮ ከማለት አይተናነስም።  የመሬቱንና ያካባቢውን ባሕሪ ከማንም በላይ ጠንቅቆ የሚያውቀው ዝናብ አጠር አካባቢ ያለው ገበሬ፤ በተለይ ለአካባቢው የሚሆን ዘር ከምርምር ተቋሞች ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት እድል ቢያገኝ አይጠላም። ሆኖም ከውጭ የሚመጣውም ሆነ ካንዱ የምርምር ተቋም ገብቶ የወጣና በውድ ዋጋ የሚሸጠው ዘር እንደማይሆነው ነጋሪ አይፈልግም። ደግሞስ የገዛ መንግሥቱ የሚሆነውን በማቅረብ ፋንታ የማይሆነውን አሳምኖ እንዲቀበል ለማድረግ ከሞከረ፣ ገበሬው ለራሱ ማሰብ እንዳለበት አያጣውም። ታዲያ ለአካባቢው የሚስማማ ዘር በማቅረብ ፋንታ ገበሬው የማይሆነውን ዘር ተቀብሎ እንዲወስድ ለማድረግ ባለሙያው ምን ብሎ ሊያሳምነው ይችላል? ባለሙያው ተሳክቶለት ገበሬውን ለማሳመን ቢችልም የተቀየሰው መንገድ የገበሬውን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ይልቅ ገበሬውን የዕጽዋት ዘርና ማዳበሪያ ሻጭ ድርጅቶች፣ ደንበኛ ብሎም ጥገኛ እንዲሆን ያስገድዳል።
እንግዲህ የኢህአዴግ መንግሥት እንደሚለው፤ በርግጥ የፖሊሲ ችግር ከሌለበት የአገራችንን ዋነኛ የምግብ እጥረት ችግር በዘላቂነት በመፍታት ፋንታ ገበሬው የማይበላውን እንዲያመርት፥ የማይሆነውን እንዲዘራ እያስገደደ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለዓለም ገበያና ለምጽዋት ቋሚ ጥገኝነት የሚዳርግ ፖሊሲ የተከተለበት ምክንያት ምንድነው?
ይህን እየፈቀዱ ፖሊሲያችን ምርጥ ነው ማለት፥ ይህን እያደረጉ ኒዮ ሊበራሊዝምን እጠላለሁ ማለት ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ኒዮ ሊበራሊዝም ማለት በዜጎች ኑሮ ውስጥ የመንግሥት ሚና ውሱን መሆን አለበት፥ ነጻ ገበያ ይስፋፋ፥ ድንበሮች ለዓለም ገበያ ክፍት ይሁኑ የሚል አስተሳሰብ ነው። ኢህአዴግ እገነባዋለሁ የሚለው የገበያ ሥርዓትና ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ ገበያ የማስተሳሰር ዓላማው መንግስትን የሃብታም ንብረት ጠባቂ የሚያደርግ ነው። ሆኖም ኢህአዴግ ካፒታሊዝምን እየገነባም ቢሆን ልማታዊ ነኝ ይላልና፥ ልማታዊ መንግሥት ማለት ደግሞ ከተራ መንግሥታዊ ዘበኝነት የተሻለ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ከሆነ፣ ኢህአዴግ ይህን ከማድረግ ማን ከለከለው? የኒዮ ሊበራል ኃይሎችን “ምክር” እና ትዕዛዝ ካልሰማና ካልተከተለ በቀር ማንም ከልካይ የለውም። የኒዮ ሊበራል መርህ አራማጅ አገሮች/ድርጅቶችን ጫና የማይቋቋም፥ ይልቁንም አጥፊ ትዕዛዛቸውን የሚቀበል መንግሥት ደግሞ ቢያንስ የግብርናውን ዘርፍ በሚመለከት መሪነቱን ተነጥቆ የዘበኝነት ሚናውን ፈቅዶ ተቀብሏል ማለት ነው።
እዚህ ላይ አንዲት ነጥብ በቅንፍ አስቀምጬ እንዳልፍ ይፈቀድልኝ። [ዛሬ ኋላ ቀር ሲል ተሳድቦ ላሰልጥን የሚል ደፋር፥ ድኻ ሲል አዋድቆ ላበልጽግ የሚል ጥጋበኛ በዝቷል። ለብልጽግናውም ሆነ ለስልጣኔው የሚቀርብልን መፍትሄ ዘራችን እንዳይበዛ መሆኑ  ደግሞ ይገርማል። ሳር ቅጠሉ አትዋለዱ ባይ ነው። የቤተሰብ ምጣኔ ለኢኮኖሚ ዕድገት ይጠቅማል፤ አለመውለድ ዘመናዊነት ነው።]
 ኢህአዴግም በበኩሉ፤ ስልጣንን ለዝርፊያ ብንጠቀምበትም የኢኮኖሚ እድገት አምጥተናል፥ የተጀመረውን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ ይዘናል፤ ይኸውም አገራችን ለውጭ ኢንቨስተር የተመቸችና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረግ ነው ብሎናል። ታዲያ በፈጣን እድገት አስጎምዢውም ሆነ በአዘማኙ ሁሉ አለብን ለሚሉት ችግር ማስረጃ ተብሎ የሚጠቀስብን በአገራችን ስም ለምጽዋት የተዘረጋው የባለስልጣኖቻችን እጅ መሆኑን ልብ ማለት ነው. . . ስለሆነም ከአሁን በኋላ ስማችን ከምግብ ዕጦት ጋር ተነሳ ብለን ልንቆጭ አይገባም። በፍጹም! ይልቁንም ስማችን ከዕጦት ተያይዞ መነሳቱን ብንሰማ መንግሥት የመረጠውን የተሳሳተና፥ ፈረንጅ-ሰራሽ የእርሻ ፖሊሲ ማስታወስና የተሻለ ማድረግ እንደምንችልም መገንዘብ ይስፈልጋል።
ዋናው ነጥብ ግን የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እንከን የለባቸውም፥ ችግሩ የአፈጻጸም ነው የሚለው የተለመደው ክርክር ስህተት መሆኑን ለማየት መቻላችን ነው።
1.2 የፖሊሲዎቻችን እውነተኛ ባለቤቶች እነማን ናቸው?
ከዐድዋ ድል በኋላ በቁጭትና ስስት ኮርኳሪነት ኢትዮጵያን ለመውረር ከመነሳትዋ በፊት ኢጣሊያ በአገራችን ላይ የከፈተችው የወሬ ጦርነት ነበር። ዋናው ክስ፣ የባርያ ንግድን ማስረጃ በማድረግ ታቀርበው የነበረው ኢትዮጵያን አልሰለጠነችም የሚለው ክስ ነበር።  ክሱ በወቅቱ አውሮፓውያን በአፍሪካና እስያ ሕዝቦች ላይ አለን ይሉት በነበረው የበላይነትና የማሰልጠን መብት ላይ የተመሠረተ ነበር።  አውሮፓውያን ሁሉ የሚያምኑበትና የሚመሩበት አስተሳሰብ አውሮፓዊ ካልሆነው ዓለም ጋር ያለውን የባህል ተለያይነት፣ የበላይ/በታች መለኪያ አድርጎ የራሳቸውን የሰለጠነ/የበላይ፥ የሌላውን የበታች የሚል ነበር። በመቀጠል ሁሉም ባህል የአውሮፓውን እንዲመስል ሊሻሻል ይገባል፤ ህጎቹ፥ አሰራሮቹ ሁሉ ሊቀየር ይገባል። ይህን የማድረግ ኃላፊነቱንም ለራሳቸው ሰጥተው፣ በጉልበት ቅኝ የሚገዙትን ሕዝብ ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ ውለታ እንደዋሉለት ያደርጉ ነበር። የጣልያንም ክስ ዓላማና ግቡ ይኸው ነበር። ሊበሏት ያሰቧትን ቆቅ እንዲሉ አልሰለጠነችም ማለቷ ‘ላሰልጥን’ ለማለት፥ ለማሰልጠን ደግሞ ቅኝ መያዝ ይገባኛል ለማለት ነበር። ሞከረች፤ አልሆነም። ይመስገነው!
ለመሆኑ ቅኝ መግዛቱ ቢሳካላት ምን ልታደርግ ኖሯል? የታሰበ የተሠራውን ያጠና አልቤርቶ ሳባቺ [Ethiopian Under Mussolini ከሚለው መጽሐፉ] ይንገረን፦  
*የሙሶሊኒ ዓላማ የምስራቅ አፍሪቃ ግዛቱ በምግብ ራሱን እንዲችልና በሚተርፈውም ለአባት አገሩ [ኢጣሊያ] ቀለብ በማቅረብ፣ በዓመት ለምግብ እህል ግዢ የሚመደበውን 2.5 ቢሊዮን ሊሬ ወጪ እንዲቀንስ ነበር።
*በተጨማሪ ታዋቂዎቹን የኢትዮጵያን ምርቶች [ቡና፥ ቆዳ፥ የጥርኝ ዝባድ፥ ሰም፥ እህል] ለውጭ አገሮች በመሸጥ የሚገኘው ገቢም ለኢጣሊያ ኢኮኖሚ በጣም ተፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝለታል።  
*የአጭር ጊዜ ዕቅዱ ግን በግዛቱ ለሚገኙት የጣልያን ስደተኞች ማረፊያ በመስጠት ያገር ቤቱን የሥራ አጥነት ችግር መፍታት ነበር። በፖለቲካና በባህል ረገድም ኢትዮጵያ የኢጣሊያና የፋሽስት ስልጣኔን ወደ አፍሪካና እስያ ለማሰራጨት ማዕከል ተደርጋ ትታይ ነበር። *በተጨማሪ ምንም እንኳ ለኢጣሊያ ጥቅም ሲባል የታቀደ ቢሆንም ከሰብአዊ፥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መርሆች አንጻር የእርሻን ምርታማነት በመጨመር፣ ኢኮኖሚው  ከእጅ ወደ አፍ ወጥቶ ሞልቶ እንዲተርፈው በማድረግ የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ማሻሻል አስፈላጊ ነበር። የኢትዮጵያን እህል ለጣልያኖች በመሸጥ የባላገሩን አማካይ ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል። [ገጽ 95]
በዚያ መሠረት ግብርና ላይ ለመሠማራት ፈቃደኛ የሆኑ የኢጣልያን ዜጎች መምጣት ጀመሩ። ሲመጡ ብድር ይመቻችላቸዋል፤ መሬት (በሊዝ) ይሰጣቸዋል፤ ቤት መስሪያ ይሰጣቸዋል፤ የእርሻ ማሽን ይቀርብላቸዋል። ለጉልበት ሥራው ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አሉላቸው። ሁሉ ሙሉ፤ ሁሉ ዝግጁ። በአንጻሩ ያገሬው ሰው ከርስቱና ከቀዬው ይነቀላል። እንደ ነገሩ ካሳ ይከፈለዋል። ከዚያም ደመወዝ እየተከፈለው ለባለሃብቱ ከበርቴ በጉልበቱ እያገለገለ እየተገዛ ይኖራል። ፖሊሲው ኢትዮጵያዊውን በገዛ አገሩ የበይ ተመልካችና ሁለተኛ ዜጋ ያደርጋል፡፡
ይቀጥላል

Read 4665 times