Sunday, 18 March 2018 00:00

ከሞያሌ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን በኬንያ በ10 ቦታዎች ተጠልለው ይገኛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 የኬንያ ቀይ መስቀል የምግብ እርዳታ እያደረገ ነው

     በሞያሌ በመከላከያ ሰራዊት አባላት 10 ሰዎች መገደላቸውንና 12 ያህል መቁሰላቸውን ተከትሎ ተደናግጠው ወደ ኬንያ የሸሹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከ10 በላይ በሚሆኑ አካባቢዎች ተጠልለው እንደሚገኙ የኬንያ ቀይ መስቀል አስታውቋል፡፡
ካለፈው ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ ከኢትዮጵያ ሞያሌ ግዛት ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ መሄዱን የገለፀው የኬንያ ቀይ መስቀል፤ እርዳታውን ተደራሽ ባደረገባቸው አካባቢዎች ብቻ ከ8500 በላይ ስደተኞችን መመዝገቡን ጠቁሟል፡፡  
በመጀመሪያው ቀን 2 ሺህ መመዝገቡን፣ በሁለተኛው ቀን 5 ሺህ እንዲሁም ረቡዕ እለት በጠቅላላው 8600 ያህል ስደተኞችን መመዝገቡን የገለፀው የኬንያ ቀይ መስቀል፤ በየእለቱ ቁጥራቸው የሚጨምረውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በማስተናገድ ተወጥሮ መሰንበቱን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስደተኞቹ በኬንያ ሞያሌ፣ ሶሎሎ፣ ሰሲ፣ ሶማሬ፣ ሲፋ፣ ማኢ፣ ኩኩብ፣ ጋታ፣ ዳምባላ ፋቻ በተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በየሰው ቤት ጥገኝነት በመጠየቅ ተበታትነው እንደሚገኙ የጠቆመው ቀይ መስቀል፤ ይህም አጠቃላይ ቁጥራቸውን በውል ለመለየት አስቸጋሪ እንዳደረገው አመልክቷል፡፡  
የኬንያ ቀይ መስቀል ለስደተኞቹ በዋናነት የምግብና የጤና አገልግሎት እያቀረበ መሆኑን ጠቁሞ፤ በተለይ ለህፃናት አልሚ ምግብ እየቀረበ ቢሆንም መጠለያዎቹ የዝናብም ይሁን የፀሐይ መከላከያ የሌላቸው በመሆኑ ስደተኞቹ መቸገራቸውን  አስታውቋል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ከቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ በሞያሌ ከተማ ሸዋ በር በተባለ አካባቢ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስና ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ 10 ሰዎች ገድለው፣ 12 ያህል ማቁሰላቸው የተገለፀ ሲሆን ኮማንድ ፖስቱ በበኩሉ፤ ግድያው የኦነግ ታጣቂ ኃይሎችን ለመያዝ በሚደረግ ጥረት መሃል በተሳሳተ መረጃ የተፈፀመ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ግድያውን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 5 የመከላከያ አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችን ያካተተ መርማሪ ቡድንም ወደ ስፍራው በማምራት ማጣራት እያደረገ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ጠቁሟል፡፡
የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ በሁኔታው የተደናገጡ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን የከተማዋ ከንቲባ ለቪኦኤ የገለጹ ሲሆን ኢቢሲ በበኩሉ፤ 39 ሺህ ያህል ሰዎች መሰደዳቸውን ዘግቧል፡፡ የተሰደዱትን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ እስካሁን ከፌዴራል መንግስት የተሰጠ መረጃ እንደሌለ ታውቋል፡፡    

Read 5782 times