Print this page
Tuesday, 13 March 2018 13:46

የሁለቱ ዕውቅ ደራሲያን የጋራ ጭብጥ

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ሦስት መጽሐፍትን ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም አበርክቶልናል፡፡ ያውም በጭብጥና በመቼት አደራደራቸው እንዲሁም በገጸ ባሕርይ አወቃቀራቸው ዋና ትኩረታዊ ነጥባቸውን ሳይለቅቁ፡፡
አንድ የድርሰት ሰው እንደ “ፈጣሪ” ሊታይ ይችላል፡፡ አልቦ-ሥጋ ፍጥረቶችን ያበጃል፡፡ ከሸክላ ባይሆንም ከምናባዊ እስትንፋስ ብቻ፡፡ ተደራሲያኑ በምናባቸው ያይዋቸዋል፡፡ በምናብ የማሳየት ብቃቱ ከፈጣሪው አገላለጽ ጋር ይቆራኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፤ በአንድ መጽሐፉ የገለጸው ይህንን ያጠነክርልናል፡፡ ይስማዕከ እንደሚለው፤“እኔ ፈጣሪ ነኝ፤ ነገር ግን እንደ ታላቁ ፈጣሪ ፍጡሮቼን አላሰቃይም”፤ ፈጥሮ የሚያሰቃይ ፈጣሪ አምላክነቱን የሚያጠያይቅ ሐሳብ ይዞ፣ ራሱን ከምድር ፈጣሪ ጋር ሲያወዳድር ተመልክተነዋል፡፡
ይስማዕከ ወርቁ እና ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴን ሊነፃፀሩ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች የዶ/ር ዓለማየሁ ሦስተኛ መጽሐፍ ‹‹መርበብት››ን በማነብበት ሰዓት ከአዕምሮዬ ጥግ ብቅ አለ፡፡ ዶ/ር ዓለማየሁ በሶስቱም መጽሐፍት “ሲሳይ”ን ፈጥሮታል፡፡ ሲሳይ በተለይም በሙያው ከፈጣሪው (ከደራሲው) ጋር መቀራረብ ስለሚታይበት፣ አንባቢው ሲሳይን እና ዶ/ር ዓለማየሁን መለየት ቢከብደው አያስገርምም። በሦስቱ መጽሐፍት ውስጥ የምናገኘው “ሲሳይ” ይዞት የመጣውን ገጸ ባሕርይ /ውክልና/ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ወጥ የሆነ ምሥልን እናገኝ ይሆን? በቤተሰብ ኃላፊነቱ፣ በሙያ ሥነ-ምግባሩ፣ በችሎታው፣ በሥንፍናው፣ በጉብዝናው፤ በእምነቱ…?
ሦስቱም መጽሐፍት ምስጢር ናቸው። የአጻጻፍና የትረካ ፍሰታቸው፤ ከስሜት ጋር የተያያዙ ልብ አንጠልጣይነት ልማዳቸው፤በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በርካታ ገጾችንና “ካልጨረስኩህ አልለቅህም” አይነት ጣዕማቸው ያመሳስላቸዋል፡፡
ቀደም ሲል ይስማዕከ ወርቁን የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በተለይ በዶ/ር ዓለማየሁ ሦስተኛው መጽሐፍ “መርበብት” እና በይስማዕከ ስምንተኛው መፅሐፍ “ክቡር ድንጋይ” (ይመስለኛል) መካከል የተሳሰረውን የጭብጥ መስመር ለመለየትና ተቃርኖአቸውን ለመመልከት ስለወደድኩ ነው፡፡
ይስማዕከ “ክቡር” ሲል የሚጠራውን “ድንጋይ”፤ ከዲያቢሎስም ይሁን ከማይታይ “መንፈስ”፤ “ጥበብ”ን እና ልማትን እንዲሁም ሥልጣኔን የምናገኝ ከሆነ፤ “ክቡሩን ድንጋይ” የሙጥኝ ልንልና ልንገለገልበት ይገባል ባይ ነው፡፡ ሰለሞን ጠቢቡ ይጠቀምበት ነበር የሚባለውን መናፍስትን የማስገዛት “ጥበብ”ን ጨምሮ፤ ይስማዕከ አይኑንና ምላሱን ሳያሽ፣ በመናፍስት የሚገኙ ጥበቦችን መጠቀም እንዳለብን ይመክራል፡፡
ዶ/ር ዓለማየሁም በሦስተኛ መጽሐፉ ይዞት የተነሳው ሐሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ በሐሳብ ይዘታቸው ከመመሳሰላቸው የተነሳ፣ መናፍስትን ለጥበብ መጠቀም አለብን የለብንም ወደሚለው ክርክር መግባታችን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን እንኳን የማይታየውን ይቅርና የሚታየውንም ለማመን ለተቸገረ የአሁን ትውልድ፣ ይህ ጉዳይ ከጸጉር ሥንጠቃ አነሰ የሚባለውን “የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ ርዕዮተ ዓለም ግብግብ”ን ማስታወሱ አይቀርልንም፡፡
የሰው ልጅ መንፈሱን ሲክድ፤ ከነፍሱ ጋር ሲጣላ የማይታዩ ፍጥረታትን መካዱና ከማይታዩ ፍጥረታት ጋር መቆራረጡ የግድ ነው፡፡ ከነፍስ ጋር መቆራረጥ የሚታየውን ዓለም ቁርኝት ማዛበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በመንፈስና በነፍስ ጠንካራ ግለሰቦች ሲኖሩን የሚታየውን አሜኬላ የማሽቀንጠር፤ የሚታየውን አረንቋ የማጽዳትና ወደ ምድራዊ ሥልጣኔ የአብሮነት ልምምዳችን የሚያሳልጥልን ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ጸጋ-በረከት ነው፡፡
የሚታዩ ፍጥረታት ሰውን ጨምሮ፤ መሬቱ፣ ውሃው፣ ጫካው፣ ሰማዩ፣ አራዊት ለማዳው፤ ማዕድኑ፤ ተራራው፣ ዋሻው ወዘተው ጋር የምናደርገው ትስስር በውስጣችን ባለው “ዓለም” ልክ የሚሰፈር ይመስለኛል፡፡ አንድ ማሕበረሰብ በአካባቢው ያለውን የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ጸጋ ለመጠቀም፤ አግባብነትና ሕጋዊነት ባለው መስፈሪያ የሚመዝናቸው ሆኖ ሲገኝ፣ ውጤቱ በጅምር አስተያየትም ሆነ በአጠቃቀም ደረጃ ሰው የመሆንን ትርጉም ጠቋሚ ናቸው፡፡ አግባብነት ሥንል ከሥር መሰረቱ ሁሉን አቀፍ የሆነውን የነገሮች አፈጣጠር ሥልት ከነምክንያቱ ማጤንን ያመላክታል፡፡ ሥልት ክህሎትን እውቀትን/ጥበብን ይጠይቃል፡፡ ሕጋዊነት ሲባል ደግሞ መዳረሻ ሚዛኑን ይጠቁመናል፡፡ መፍትኄ አምጥተናል…? እኩልነትን አስፍነናል…? ሕጋዊነትን ገንብተናል…? መተካካትን እውን እድርገናል--? ወዘተ እያልን ማብራራት እንችላለን!
ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው/ራሳችንን ስንመዝነው/ የሁለንተኑ አስተያየትና አጠቃቀማችን በድርጊትና በውጤት ደረጃ እኛነታችንን ይገልጻሉ። በ“መርብበት” መጽሐፍ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የምናስተውለው መዳረሻም ለአካባቢያችን የምንሰጠውን ትኩረት በመፈተሽ ምን ላይ እንደምንገኝ ማሳየት መቻሉን ነው፡፡
“መርብበት”ይሁን ያለፉት የደራሲው ሥራዎች ይህንን ጉዳይ ሳያነሱት አላለፉም፡፡ ሲሳይ በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ በየትኛውም ገጠመኝ ይሁን ክስተት ኢትዮጵያን ያስባል፡፡ በውጪ ካለችው ኢትዮጵያ ውስጥ በውስጡ የበቀለችው ኢትዮጵያ ሰፊ ምድር ናት፡፡ ጥልቅ ዋሻ ናት፡፡ ትልቅ ክምር ናት፡፡ አያልፋትም፡፡ ያለፋታል፡፡ ይጠይቃታል። ይመክራታል፡፡ ይመሰክርላታል፡፡ ያፍርባታል፡፡ ይኮራባታል፡፡ ያለቅስባታል፡፡ ያለቅስላታልም…!
ምናልባትም የደራሲው የሙያ ተመክሮ ለዚህ ሁሉ ሐተታ ምንጭ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ሆኖም በሙያው ከዕጽዋት ጋር የተቆራኘው ሲሳይ፤ ባሕሉን፣ ሐይማኖቱን፤ መንደሩን፤ ውሃውን፤ ቅርሱን፤ ፖለቲካውን ሕዝቡን በሚመለከት እንደ ሙያው የተካነበት ይመስላል፡፡ በየመሃሉ ወቅታዊ ውዥንብሮችንም አያልፋቸውም፡፡ ሊፈትሻቸው፣ ሊያርማቸው፣ ሊያሻሽላቸው ሲሞክር እናስተውላለን፡፡ በጥብቅ ይታገላል… እንደ ዜጋም እንደ ምሑርም፡፡ ከአንድ ምሑር የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ ጥጉን ይዞ በጠራራ ጸሐይ ፋኑስ ያበራውን ፈላስፋም እንድናስታውስ ያስገድደናል፡፡
በ”መርበብተ”- ሰለሞን “ጥበብ” እንጠቀምበት ወይንስ አሽቀንጥረን እንጣለው…? ይህ ጥያቄ ለይስማዕከ ወርቁ እና ለዶክተር ዓለማየሁ የሚቀርብ ይሆናል። ሁለቱም የየግላቸውን መዳረሻ በመጽሐፍቶቻቸው አሳይተውናል፡፡ የማይታየውን እንኳ ማመን እና መቀበል ላቃተው ትውልድ፣ እኒህ ግለሰቦች ምን አይነት መልክ ይኖራቸዋል? የሚለው ራሱን የቻለ ርዕስ ቢሆንም፤ ያገባኛል/ይመለከተኛል የሚለው ትውልድም የትኛውን መዳረሻ ሊዘግን ይችላል..? በምን አይነት መስመርስ ሊቀበለው ይችላል…? አቀባበል እና አጠቃቀሙስ በምን መልኩ ይወሰናል…? እንጠቅምበት/አንጠቀምበት የሚለውስ በየትኛው መመዘኛ ታይቶ ነው…? የሚሉ መሠል ጥያቄዎች ለእያንዳንዳችን የሚተዉ ይሆናሉ፡፡
በ316 ገጾች የተቀነበበው “መርበብት”፣ ከሁለቱ መጽሐፍቶቹ ጋር ተመሳስሎውን እና መለያየቱን ተሸክሞ፤ የውጭውን ዓለም ምልከታ በንጽጽር ሲያቀርብልን እናስተውላለን፡፡ እንደ ሲሳይ አመለካከት፤ አብዛኛውን ገጠመኝ ከአገሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማወዳደር ይቀናዋል፡፡ በአገር ውስጥም ቢሆን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ወቅታዊ ትኩሳትና አጠቃላይ ገጠመኞች ትኩረትን አግኝተው ተዳስሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ይስማዕከ ወርቁ እና ዶ/ር ዓለማየሁ አንድ ምንጭ የቀዳቸው ሁለት ወንዞች ናቸው፡፡ በግራ እና በቀኝ ትይዩ ሆነው የሚፈስሱ፡፡ ከምንጩ መጠጣትም ሆነ በወንዙ መፍሰስ የአንባቢ ድርሻ ነው። መልካም ንባብ!!

Read 3558 times