Tuesday, 13 March 2018 13:45

የአፍታ ቆይታ ከድምጻዊው ጋር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• የምተዳደረው በሙዚቃ ሳይሆን በሂሳብ ባለሙያነቴ ነው
• እዚህ አገር የሙዚቃ ህይወት በጣም ፈታኝ ነው

ከ10 ዓመት በፊት አልበም ለማሳተም ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር ተዋውሎ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን አምስት ነጠላ ዜማዎችን በመልቀቅ ዕውቅንና ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ በመጨረሻ የለቀቀው “ተመለሽ” የተሰኘው ባህላዊ ዘፈኑ በእጅጉ ከመወደዱ የተነሳ በዩቲዩብ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘ ሲሆን በዚህ ዘፈን ምክንያትም በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ኮንሰርቶች እንዲሰራ ግብዣ ቀርቦለት፣ ለጉዞው እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ የዛሬው የአፍታ ቆይታ እንግዳችን የሂሳብ ባለሙያና ድምጻዊ አያሌው ንጉሴ (ያዩ)፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከድምጻዊው ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡

እንዴት ነው ወደ ሙዚቃ የገባኸው?
ሙዚቃን በት/ቤት ሚኒ ሚዲያና በቤተሰብ መምሪያ ነው የጀመርኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሙያው በጥልቀት ልገባ ችያለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ቤት ውስጥ በጣም ሙዚቃ አዳምጥ ነበር፡፡ ቤት ውስጥ ተገዝተው የሚመጡ ካሴቶችን እየከፈትኩ እያዳመጥኩ፣ አብሬ እያንጎራጎርኩ ነው ይበልጥ ወደ ሙዚቃው የተሳብኩት፡፡
መድረክ ላይ የማቀንቀን ዕድል ያገኘኸው እንዴት ነው?
ወደ ትልልቅ መድረክ መጣሁ የምለው እንግዲህ ከኤክስፕረስ ባንዶች ጋር ነው፡፡ የተለያዩ ባዛሮች ላይ በመጋበዝና በመዝፈን ነው እራሴን እያሳደግኩ የመጣሁት፡፡
ብዙ ወጣት ድምፃዊያን ወደ መድረክ ሲመጡ መጀመሪያ ላይ የአንጋፋ ድምፃዊያንን ዘፈን በመዝፈንና በምሽት ክበቦች ድምፃቸውን በመግራት ነው፡፡ በዚህ በኩል ያንተ ልምድ ምን ይመስላል?
በክለብ ደረጃ የቴዎድሮስ ታደሰንና የጥበቡን ሥራዎች እጫወት ነበር፡፡ በማድነቅ ደረጃ እነዚህን ድምፃዊያን አደንቃለሁ፡፡ ከሴቶች የፍቅርአዲስ አድናቂ ነኝ፡፡ ባህላዊ ዘፋኝ እንደመሆኔ፤ መሰረት በለጠንም በጣም አደንቃታለሁ፡፡ የሰራሁባቸው የምሽት ክበቦች ዋሊያ የሚባል ልደታ አካባቢ የነበረ ቤት፣ ቦሌ ደግሞ አበጋዝ የሚባል ምሽት ክበብ ሰርቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ወደ ሶስትና አራት የምሽት ቤቶች ሰርቻለሁ፡፡ በዚህም በርካታ ልምዶችን ቀስሜያለሁ፡፡
በሙዚቃ ህይወትህ ፈታኝ የምትለው ወቅት አለ?
እዚህ አገር በአጠቃላይ የሙዚቃ ህይወት በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ከፈታኝነቱም አልፎ አስቀያሚ ነው፤ ግን ታግሰሽ ካለፍሽ ፍሬው ደስ ይላል፡፡ ያንን ፍሬ ለማየት ከፍተኛ ትዕግስትና ተስፋ አለመቁረጥ ግን የግድ ነው፡፡ ጥንካሬው ከሌለ ሙያውን ጠልተሽ ሁሉ ጥለሽ ልትወጪ ትችያለሽ፡፡
ከ10 ዓመት በፊት አልበም ለማሳተም ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰህ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስካሁን ታትሞ ለአድማጭ ያልበቃበት ምክንያት ምንድን ነው?
እንግዲህ ለሙዚቃው ካለኝ ፍቅር የተነሳ ገና ተማሪ ሆኜ፣ በ1995 ዓ.ም አካባቢ ነው አልበም መስራት የጀመርኩት፡፡ እሱን ስጀምር ተማሪ እንደ መሆኔ በቤተሰብ ገንዘብ ነበር የጀመርኩት። ያኔ ስቱዲዮ ለመግባት በጣም ውጣ ውረድ ነበረው፡፡ እንዲያም ሆኖ አልበሙ አልታተመም። አልበሙ እንዲታተም ስምምነት ያደረግኩት ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር ነበር፡፡ ከዚያ የሙዚቃ ቤት ባለቤቱ፣ አምስት ዘፈኖች መርጠው አወጡና፣”እነዚህ አይሆኑም ቀይር” አሉኝ፡፡
ከዚያስ?
እንደነገርኩሽ ተማሪ ስለነበርኩ ከቤተሰብ የምሳና የትራንስፖርት እየተቀበልኩ፣ ከደብረዘይት አዲስ አበባ ተመላልሼ ነው፣ ስቱዲዮ እየገባሁ ሰርቼ የጨረስኩት፡፡ ከዚያ ሁሉ ችግር በኋላ አምስት ዘፈን ቀይረሽ፣ ግጥምና ዜማ አሰርተሽ፣ እንደገና ስቱዲዮ መግባት ለእኔ በዛን ወቅት በጣም ከባድ ስለነበር በዚህ ምክንያት ቀረ፡፡
አሁን አቅም ካገኘህ በኋላስ ለምን አላሳተምከውም?
አሁን ስታይው ሁሉም ነገር ተቀይሯል፤ ቴክኖሎጂው --- ቅንብሩ --- ከ10 ዓመት በፊት ያለውና የአሁኑ አይገናኝም፡፡ በዚህ ምክንያት ሳይታተም ቀረ ማለት ነው፡፡
እስኪ ስለተወዳዱልህ ነጠላ ዜማዎችህ ትንሽ አጫውተኝ?
መጀመሪያ ላይ ስለ መርሀቤቴ የሚገልፅ “መሬው” የተሰኘ ነጠላ ዜማ ነው የለቀቅኩት፡፡ ዜማና ግጥሙን እኔ ሰርቼ፣ ቅንብሩን ሙሃዘ ፀጋዬ ሰራው፤ ሚክሲንጉ በኤክስፕረስ ባንዱ ክብረት ዘኪዎስ ነበር የተሰራው፡፡ በመቀጠል “ድንገት መጣሽብኝ” የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ለቀቅኩኝ፡፡ ዜማውን እኔ ነኝ የሰራሁት፡፡ ቅንብሩን አማኑኤል ይልማ የሰራው ሲሆን ግጥሙ የአንጋፋው ገጣሚ ግሩም ሀይሌ ነው፡፡ ግሩም ሀይሌ እጅግ የማደንቃቸውና የማከብራቸው ባለሙያ ናቸው፡፡ በዚህ ዘፈንም ጥሩ እውቅናና ተቀባይነት አግኝቻለሁ፡፡ “የከበርሽ እንቁ” የተሰኘ ሌላው ስራዬ ጎንደር የተቀረፀ፣ የጎንደር ባህልና ትውፊትን ጠብቆ የተሰራ ስራ ነው። ዳይሬክተሩ ስንታየሁ ሲሳይ ነው፤ ይህ ነጠላ ዜማ ከ130 ሺህ ብር በላይ ወጥቶበታል፡፡ ዜማና ቅንብሩን የሰራው አሌክስ ይለፍ ነው፡፡ ይህም ዘፈን እጅግ የተዋጣላት ነበር፡፡
በ2009 ዓ.ም መስከረም ላይ “ተመላሽ” የሚል ዘፈን ሰራሁ፡፡ ከዚህ በፊት ሀብተሚካኤል ደምሴ ነፍሳቸውን ይማርና ሰርተውት ነበር፡፡ ዜማውን የሰራው የኔው አካሉ ነበር፤ አስፈቅጄ አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅሜ፣ አዲስ ግጥም በግሩም ሀይሌ አሰርቼ ለቀቅኩት፡፡ ይሄ ዘፈን በጣም ነው የተወደደው፡፡ በዩቲዩብ ከ1. ሚሊዮን በላይ ሰው ተመልክቶታል፤ ገብቶ ማየት ይቻላል፡፡
ይሄ ዘፈን በአውሮፓ ከተሞች ኮንሰርት የመሥራት ግብዣ አስገኝቶልሃል---
በትክክል፡፡ አሁን፤ ከሁለት ወራት በኋላ በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ለአንድ ዓመት የሚቆይ ኮንሰርት ለመስራት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ በአገር ውስጥም የተለያዩ ኮንሰርቶችን ለመስራት ግብዣዎች ቀርበውልኛል፡፡
ከሙዚቃው ውጭ የሂሳብ ባለሙያም ነህ …
አዎ፤ እውነት ነው፡፡ በአካውንቲንግ ሙያ በመንግስት መሥሪያ ቤት እየሰራሁ እገኛለሁ። የምተዳደረውና የምኖረው በዚህ ሙያዬ እንጂ ከሙዚቃው እስካሁን ያገኘሁት ጥቅም የለም፡፡ ወደፊት ነው ውጤቱን የማየው፡፡
በሂሳብ ባለሙያነትህ የተከበርክና የተዋጣልህ ነህ፡፡ ሙዚቃው በመንግስት ሥራህ ላይ ጫና አያሳድርብህም?
ይሄኛውንም ስራዬን በአግባቡ ነው የምሰራው፤ ምክንያቱም የምተዳደረው በሙዚቃው ሳይሆን በዚህኛው ሙያዬ ነው፡፡ ነገር ግን በመስሪያ ቤት ያሉ ጓደኞቼም አለቆቼም ለሙዚቃው ያለኝን ፍቅር ስለሚያውቁ በደንብ ይረዱኛል፡፡ ሙዚቃ በአብዛኛው ሌሊት ነው የሚሰራው፡፡ በዚያ ላይ አዲስ አበባ ተመላልሼ ነው የምሰራው፡፡ ሌሊት ሰርተሽ ጠዋት ደክሞሽ ጠውልገሽ ነው ሥራ የምትገቢው፡፡ ድካም በሚያጋጥመኝ ጊዜ አለቆቼና ጓደኞቼ ሥራዬን ሸፍነው እንዳርፍ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለመስሪያ ቤት አለቆቼና ጓደኞቼ ከፍ ያለ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
የአገሪቱን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዴት ትገልጸዋለህ?
የአገሪቱ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በጣም ከባድና አስቸጋሪ ነው፡፡ አንደኛ፤ ኢንዱስትሪው በተወሰኑ ሰዎችና በቲፎዞዎቻቸው የተያዘ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ለፍተሽ ደክመሽ፣ ለአንድ ነጠላ ዜማ ቪዲዮ ከመቶ ሺህ ብር በላይ እያወጣሽ፣ ሚዲያዎች አንቺን ለማበረታታትና ሥራሽ ለሰው እንዲደርስ ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ቲፎዞ አጃቢ ሊኖርሽ ይገባል። ወዲህ ደግሞ የቅጂ መብት አለመከበር አለ፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ዘርፉ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል። ሆኖም ስራውን ስለምንወደው እንቀጥልበታለን። እንደ አዲስ ሙዚቃውን ለሚቀላቀሉ ጀማሪዎች፣ መስመሩ በጣም የተጣበበ ነው፡፡
በሙዚቃው ዘርፍ ህልምህ ምንድን ነው?
የእኔ ህልም የግል የሙዚቃ ት/ቤት መክፈት ነው፡፡ ፍላጎቱም ተሰጥኦውም ኖሯቸው፣ መንገዱንና አካሄዱን አጥተው፣ ከእነ ህልማቸው የተቀመጡ ድምፃዊያንን ወደ አደባባይ ማውጣትና ዕድል መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ዛሬ እነዚህን ክሊፖች ሰርቼ ህዝብ ጋ ለመድረስ እጅግ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌያለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት መንገዱን አጥተው፣ ብቃታቸውን ይዘው የተቀመጡ፣
ምን ያህል ወጣቶች እንዳሉ ቤት ይቁጠራቸው።
ከ10 ዓመት በፊት ተሰርቶ ሳይታተም የቀረው አልበምህ ዕጣ ፈንታው ምንድን ነው?
እንደነገርኩሽ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ክፍተት አለ፤ እነሱን አስተካክዬ ለመስራት ስቱዲዮ ገብቻለሁ። ነገር ግን ቶሎ ለማጠናቀቅ በቂ ጊዜ የለኝም፡፡ አንድም የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፤ ሁለትም አሁን የውጭ ጉዞ ሂደት ጀምሬያለሁ፤ በመላው አውሮፓ ነው ኮንሰርት የምሰራው፡፡ አልበሙ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ በደንብ ተሰርቶ ለአድማጭ ይቀርባል፡፡
እንዴት ነው ለደብረዘይት አልዘፈንክም?
እንግዲህ ተወልጄ ያደግሁባት ከተማ በመሆኗ በጣም እወዳታለሁ፡፡ ለዚህም ደብረዘይትን የሚያወድስ ኦሮምኛ በአማርኛ የሆነ ዘፈን ከፀጋዬ ደንደና ጋር ለመስራት አስቤያለሁ፤ ዜማው አልቋል፡፡ ግጥሙን ፀጋዬ እየሰራ ነው፡፡ ከቻልኩ ወደ ውጭ ከመሄዴ በፊት ካልተቻለ ስመለስ እለቀዋለሁ ብያለሁ፡፡ በውጭ ጉዞዬም አንድ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን ለመልቀቅ አስቤያለሁ፤ ስመለስም አልበሜን እየሰራሁ ነጠላ ዜማዎችን በተከታታይ በመልቀቅ በደንብ ወደ ህዝቡ ዘልቄ ለመግባት እፈልጋለሁ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጋዜጣችሁ እንግዳ ስላደረገኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በስራ ቦታዬ ያሉ ጓደኞቼን፣ አብሮ አደጎቼን፣ ወላጆቼን ባለቤቴን መሰረት ተስፋን፣ አቀናባሪዎቼን፣ ግጥምና ዜማ የሚሰሩልኝን ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ከምንም በላይ ኃያሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡

Read 1941 times