Tuesday, 13 March 2018 13:42

የመገረምን ጥግ ማለፍ…

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ singofbird@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

የፓትሪክ ሰስኪንድ ‹‹ግሬኖል››፤ እንደ አልበርት ካሙ ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ መሉ ስልጣን ያለው ንጉስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ግሬኖል በንባብ ብቻ ጉንፋን በሚያስይዝ የግማትና ጥንባት የሚሰነፍጥ ትርኪምርኪ የዓሳ ጭንቅላቶች መሀል ወድቆ የተገኘ አንድ ጉስቁል ፍጡር ነው፡፡ ሆኖም ሁለቱም ገፀባህሪያት በአንድ የንባብ ትውውቅ ብቻ በነፍሳችን ጥልቅ ስርቻ የሚፈጥሩት የሕይወት ንዝረት ከወትሮው የዘልማድ ኑረት አናጥቦ፣ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚያስቆዝም ልዩ ኃይል አለው፡፡
ያገሬ ሰው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይላል፡፡ በፓትሪክ ሰስኪንድ “Das Perfume” (በተሾመ ዳምጠው ጉድ ሲናጥ-- በሚል ተተርጉሟል) አመፀኛ ልብ ወለድ ውስጥ እንዲህ ሆነላችሁ፡- ጊዜው በ1770ዎቹ በፈረንሳይ ሀገር ውስጥ ነው፡፡ የዚህ ልብ ወለድ ዋና ገፀባህሪ ‹ግሬኖል› በተወለደበት ቅፅበት እቱት እንደ ሌሎቹ አራት ወንድምና እህቶቹ የተከማቹ የበሰበሱ የዓሳ ጭንቅላቶች መሃል ጥላ ልትገድለው ስትሞክር እጅ ከፈንጅ ተያዘች፡፡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአደባባይ ለዚህ ድርጊቷ በስቅላት ተቀጣች፡፡
ሕፃኑ በቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች በጎነት ለቅጥር ሞግዚቶች ተሰጠ፡፡ በቀጠለው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ የውርደት፣ የሃፍረት፣ የውድቀት ሰንሰለት እየተመላለሰበት፣ ከሞግዚት ሞግዚት እየተንከራተተ አደገ፡፡ በሁሉም ነገር ችላ የተባለ፣ ማንም ለቁምነገር የማይፈልገው፣ ሰዋዊ መስተጋብሮችን ሁሉ በጭካኔ የተነጠቀ ምንዱብ ሰው ሆነ፡፡ ይሄም በኋላ ላይ ያረገዘውን ድብቅ ቂም እንዲጸንስ አደረገው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ለሕይወት ስሜት አልባ፣ ገልጃጃ ይመስል የነበረው ለጋ ታዳጊ፤ አንድ የፀደይ ዕለት ድንገት ‹‹አፈር›› አለ፡፡ ቀጥሎ ዝም ያለው የምናብ ዓለም ሕሊና ሊገምተው እስከማይችለው ጥግ እስኪተረማመስ ድረስ የተፈጠረው ምስቅልቅል የተጀመረው በዚህች የማሽተት ልዩ ቅፅበት ነበር፡፡
ልዩ የማሽተት መክሊት ባለቤት መሆኑን ያወቀው ግሬኖል፤ በዙሪያው የተሰበሰቡ በሺህ የሚቆጠሩ ግማት፣ ክርፋት፣ ጥንባት፣ ቁናሶችን ሁሉ በአዕምሮው እየተነተነ መመዝገብ ጀመረ። ግሬኖል ከቆዳ አለስላሽነት እስከ ሽቶ ቀማሚነት በተሸጋገረባቸው ዓመታት ይሄው የማሽተት ስል ደመነፍሱ ይበልጥ እያደገ ሄደ፡፡ በዙሪያው ያለው ዓለም ሁሉ የከበበውን ሚሊዮናት ቁናስ፣ ግማት፣ ክርፋት፣ ብስናት ሁሉ በአዕምሮው የሚመዘግበው ግሬኖል፤ እሱ ግን ለራሱ አካላዊ ጠረን እንደለሌለው ተገነዘበ፡፡ በሽቶ ቅመማ ልሂቃን መናሃሪያነት ወደምትታወቀው ግራሰ ከተማ ሄዶ፣ ለራሱ እጅግ ልዩ የሆነውን ሽቶ ከመሥራቱ በፊት ለ7 ዓመታት በዋሻ ውስጥ ለብቻው አሳለፈ፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ግሬኖል የተነጠቃቸውን ክብር፣ ሞገስ፣ ፍቅር እንቶፈንቶዎች የሚያስመልስበት፣ ከዚህ በፊት ማንም ያልሰራውን ልዩ ሽቶ የመስራት ውጥን ያዘ፡፡ ይህንን ልዩ ሽቶ ለመስራት የበርካታ ልጃገረዶች ጠረን የግድ ያስፈልጋል፡፡ በግራሰ ከተማ ውስጥ ያሉ ልጃገረዶች ሁሉ ያሉበትን በጠረናቸው አማካኝነት ጠንቅቆ የሚያውቀው ግሬኖል፤ አንድ በአንድ ሃያ አምስት ልጃገረዶችን በጭካኔ እየገደለ ባዘጋጀው ሰም ጠረናቸውን መዘበረ፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናነበው ግሬኖል፤ በዕውንና በቅዠት ዓለም መካከል የሚዋልል የማይጨበጥ(illusionist) የተረት ዓለም ሰው ይመስላል፡፡ ይሄው ሀሳብ በመጽሐፉ ገጽ 98 ላይ በጥሬው ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ የግሬኖል ታሪክ ከአፈ-ታሪክ እስከ እውናዊ ሕይወት እየዋለለ፣ የንባብ ህሊናችን ብዙ ቅጥሮችን እንዲጥስ ያስገድዳል፡፡ የእውነታ ዓለምና የምናብ ዓለም የሃሳብ ድንበሮች ተጥሰው ሕይወት በነውጡ መሃል እንኳን ዝርግ ገፅታን ይዛ ትታያለች፡፡ ግሬኖል እንደ ካሊጉላ፤ ይህች ዓለም የተገነባችበትን ልክ ያልሆነ አወቃቀር የሚቃወም ይመስላል፡፡ ሆኖም ለግሬኖል የዚህ ተቃውሞውም ሆነ የመፍትሔ እርምጃው መነሻም መድረሻም ጠረንና ሽቶ ብቻ ነው፡፡
ግሬኖልን ጠጋ ብለን በየዋህነት ስንረዳው፣ እኛ ለምንኖርበት ዓለም በመጠኑ የቀረበ የሲሲፐስ መንታ ፍጥረትነት ይነበብበታል፡፡ ግሬኖል ዘመኑን ሙሉ የኖረው ልክ ትናንት በጎልማሳነት ዕድሜ ወደ ሕይወት በእንግድነት እንደተጠራ ሁሉ ግር እየተሰኘ ነው፡፡ አኗኗሩ ከሺ ዓመታት በፊት የሆነውን፣ ከሺ ዓመታት በኋላ የሚሆነውን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሰው ለምንም ያለመጓጓት በታከለበት ሁኔታ ነው። እንዲያውም መኖር ግዴታው ስለሆነ ብቻ የሚኖር ይመስላል፡፡ በመጨረሻ ግሬኖል ከተረሳና እንደ ትንኝ ከተናቀ ማንነት ተነስቶ ጠባቧን የግራሰ ዓለም፣ በአንዲት ጠብታ ሽቶ ብቻ በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ቻለ፡፡
በሕይወት ስድ አወቃቀር በግፍ የተደፈጠጠ ሰብዕ፤ ለግብስብሱና ብልጭልጩ ዓለም ግድ የለሽ መስሎ በማሽተት ልዩ መክሊቱ ሲያሸምቅ (ሲያደባ)፤ ነፍስ በጠረን ስም አፍንጫ ጫፍ ተንጠልጥላ ለሕልውና ስታቃስት፤ ውበት ቁብ ትኩረት አጥቶ ለጠረን ሲባል በጭካኔ ሲሰዋ፤ ዝብርቅርቁን ተከትሎ ጠባቧ ዓለም ስትናወጥ ... እንደገና አንድ ሙሉ ስልብ፣ ገልጃጃ፣ ስንኩል ኑረት የገበሩለት የብልቃጥ ሽቶ ከመስቀያ ገመዱ ሲያስጥል፤ መልሶ ሰውን ያክል ፍጡር እንደ ብስኩት፣ እንደ አንዳች ትንግርት በሚያስብል ሁኔታ ቀረጣጥፎ ሲያስበላ…ግር እየተሰኙ ማንበብ … ህም…እውነትም ‹‹ጉድ ሲናጥ››!!…
ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በትርጉም መጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈራት ምጥን ሐተታ፤ ‹‹…‹ጉድ ሲናጥ› የሰው ልጅ ሕልውና አፍንጫ ጫፍ ተንጠልጥላ ሁለመና በጠረን ኃይል ስር የሚወድቅበትና እንኳን ሊሞከር ታስቦ የማያውቅ ድንቅ ስራ ነው።›› ይላል። መጽሐፉ ለህትመት እንደበቃ በጀርመን ሀገር ለ9 ተከታታይ ዓመታት የሽያጭ ሰንጠረዡን ተቆጣጥሮት ነበር፡፡
እኔም አልኳችሁ… ይህንን ልዩ ጣዕም ባለው ትረካ የቀረበ መጽሐፍ አንብበው ሲጨርሱ፣ ደራሲውንና ለኛ ባዕድ ከሆነው ጀርመንኛ ቋንቋ የተረጎመልንን ተሾመ ዳምጠውን (“የእፎይታ” ተርጓሚ መሆኑን ልብ ይሏል) አለማመስገን ከቶውንም አይቻልም! አትጠራጠሩ፤ የመገረምን ጥግ ጥሳችሁ ስታልፉ፣ ከዚያ ወዲያ መገረም አይኖርም፡፡ ይህንን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ የተሰማኝ ይሄው ነበር፡፡ እኒህ ጀርመናዊያን ግን ምን ዓይነት ትንታግ ብዕረኞች ናቸው! ሔርማን ካርል ሔሰ፣ ፍራንዝ ካፍካ፣ ቶማስ ማን፣ ወልፍጋንግ ጎተ… አሁን ደግሞ ፓትሪክ ሰስኪንድ፡፡ ህምምምም…

 

Read 891 times