Tuesday, 13 March 2018 13:41

የሱስ ተስፋ?

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(13 votes)

ከተማ አድጋለች ለማለት ግዴታ ፎቅ መገጥገጥና መኪና በትራፊክ መጨናነቅ አለበት?... ወይስ ስራ ያላቸው ሰዎችን ጠዋት ወጥተው ማታ ሲመለሱ መቁጠር ያስፈልጋል?... አዎ የከተማ እድገት ረቀቅ ባለ የእብድም አይነት ሊለካ ይችላል እኮ … እያልኩ ወደ ባቡር ገባሁኝ፡፡ እንደዚህ እያልኩ እንዳስብ ያደረገኝ ወጣትም አብሮኝ ገብቶ ከእኔ ፊትለፊት ተቀመጠ፡፡… እብድ መሆኑን ገና ባቡሩ ሳይመጣ ነበር ያወቅሁት፡፡ እብደቱ በትክክል የቱ ጋ እንደሆነ ግን አላውቅሁም፡፡… ጎኔ ተቀምጦ ሲያወራኝ ነበር። የሚያወራው እየጮኸ አይደለም፡፡ የሚያወራው ከራሱ ወይም ከስልኩ ጋር አይደለም፡፡
ባቡሩ እስኪመጣ ወንበሩ ላይ ቁጭ እያልኩ እየተነሳሁ፣ እየተንጎራደድኩ፣ ብጥስጣሽ ሀሳብ እያነሳሁ እጥላለሁኝ፡፡… ድንገት ከጎኔ ቁጭ ብሎ አገኘሁት፡፡
“የያዝከው መፅሐፍ አርዕስት ምንድነው የሚለው?” አለኝ፡፡ ሰክሯል፡፡ ግን በድርሰትና ፊልም ላይ አበሻ ሲሰክር ማሳየት ያለበት ድርጊት ወይ ተውኔት ፈፅሞ አያንፀባርቅም፡፡ ማበዱን አውቄያለሁ፣ ግን የቱ ጋ እንደሆነ ያበደው ልይዘው አልቻልኩም፡፡
“የቪክተር ጄ እስቴንጀር መፅሐፍ ነው፤ ስለ ፈጣሪ ህልውና የሚመረምር የሳይንሳዊ አቀራረብ ያለው…” (መፅሐፍ ነው)… ብዬ ሳልጨርስ…
“ማን ይዘቱን ጠየቀህ? የጠየቅሁህ አርዕስቱን ነው” ብሎ አሸማቀቀኝ፡፡ ለምን እንደተሸማቀቅኩም አልገባኝም፡፡ ይዘቱን ለማንም ተንትኜ ማስረዳት በምችልበት ጥልቀት ተውጬ የቆየሁበት መፅሐፍ ነው፡፡ ግን አርዕስቱን አልያዝኩትም፡፡ አርዕስቶችን መያዝ አልችልም… የሰዎችን ስምም ጨምሬ፡፡ ሰዎችን በአኳሃናቸው በቀላሉ ምን አይነት እንደሆኑ መመደብ እችላለሁ፡፡ ስማቸውን ግን ደጋግመው ነግረውኝም ማስታወስ አይሆንልኝም፡፡… ከሰዎች ስም በደንብ የምይዘው መፅሐፍት ደርሰው ያስነበቡኝን ነው፡፡ የሚገርመው የደራሲዎችን ስም ሳስታውስ የመፅሐፉ አርዕስት ግን ይጠፋኛል፡፡
“ለምን ትደነግጣለህ፤ አላውቅም ብትል ነውር አይደለም!” ብሎ የባስ አበሸቀኝ፡፡ ባቡር የሚጠብቁ ሰዎች ብዙ አይደሉም፡፡ ኮሪደሩ ላይ ተፈነጣጥረው ቆመዋል፡፡ የመፅሐፉን አርዕስት አለማወቄን እንዲሰሙብኝ አልፈለኩም፡፡ የመፅሐፉን አርዕስት ሽፋኑን ገልጬ ተመለከትኩኝ፡፡ እብዱ ወደ ሌላ ርዕስ ተሻግሯል፡፡ በኪሱ ግማሽ ሊትር የሚይዝ የፕላስቲክ የውሃ መያዣ አውጥቶ ተገነጨ፡፡ ከተጐነጨ በኋላ ኮምጣጤ እንደጠጣ ሰው ፊቱን በመንገሽገሽ አጨማተረ፡፡… ወደ እኔ ጠርሙሱን ዘርግቶ እንድጎነጭ ጋበዘኝ፡፡…የአበሻ አረቄ መሆኑን ለየሁት፡፡ ፈፅሞ እንደማልፈልግ ለማሳየት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መንጎራደድ ጀመርኩኝ። እንዲያዋራኝ አለመፈለጌን መግለፄም ጭምር ነው፡፡ እኔም ትንሽ ቀምሻለሁ ግን ደረጃ መዳቢ የሚያውቀውን መጠጥ ነው፡፡ ቢራ፡፡ እሱንም ከሦስት አላልፍም፡፡
“እና መልስልኛ” አለኝ ከተቀመጠበት ሆኖ፡፡
“ምኑን ልመልስልህ?” አልኩት፡፡ እብድ መሆኑን እርግጠኛ ብሆንም በእብድና በማጅራት መቺ መሀል ግልፅ ልዩነት የማያሳይ አይነቱ ቢሆንስ ብዬ ሠጋሁ፡፡ በአንዱ ካባ ሌላኛውን የሚሰሩት መሀል ሊሆን መቻሉ መጠርጠር ስላለበት፡፡
“የምጠይቅህን ጥያቄ--”
“የማይሆን ጥያቄ እንዳትጠይቀኝ እንጂ ችግር የለም” አልኩት፡፡ ገንዘብ ስጠኝ እንዳይለኝ ማስጠንቀቄ ነበር፡፡… እብድ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኛለሁ፡፡ እብዶች ደግሞ ገንዘብ ሳይጠይቁ ማበድ አይሆንላቸውም፡፡ “እሺ ጠይቀኝ” አልኩት፡፡
“ተስፋ ሱስ ነው እንዴ?” አለኝ፡፡ ባቡሩ ሲመጣ አየሁት፡፡
“እኔ’ጃ” አልኩት፡፡
ባቡሩ መሰስ ብሎ አጠገቤ ደረሰ፡፡ ውስጥ ብዙ ያልተያዘ ወንበር ይታየኛል፡፡ በሩ ሲከፈት ገባሁኝ። ስቀመጥ ከፊትለፊቴ ተከትሎኝ መጥቶ ተቀመጠ። ትንሽ ሳልፈራው አልቀረሁም፡፡ ግን የሚያስፈራ ነገርን ለማድረግ አቅም ያለው አይመስልም፡፡ አቅሙ ድሮ ተንገዳግዶ እንደ ወደቀ መቅረቱ አኳሃኑ ላይ ያስታውቃል፡፡
“እንዴት እኔ’ጃ ትለኛለህ?!...እኔ ለምሳሌ ሱስ አለብኝ፡፡ የመጠጥ፣ የሲጋራ፣ የጫት … ብቻ በአፍ የሚገባ ነገር ሱስ አለብኝ፡፡…የእንጀራ ሱስም አለብኝ፡፡…ግን የሳብስታንስ ሱስ እንጂ የተስፋ ሱስ የለብኝም።… ወላ የተስፋ….የሀሳብ… የባህል…ገለመሌ ሱስ የለብኝም።… አንተ ምን አይነት ሱስ ነው ያለብህ?” አለኝ፡፡ ሰው እንዲያደምጣቸው ባቡር ውስጥ የሚጮሁት አይነት ኋላቀር ሰካራሞች አይደለም፡፡ … “አንተ የወሬ ሱስ ነው ያለብህ” ብዬ ላስቀይመውም እችላለሁኝ፡፡ ግን በማስቀየም ረገድ እኔ በቀላሉ ጎል ሊቆጠርብኝ ይችላል፡፡ እሱ የሚዋረድ ነገር ያለው አይመስልም፡፡ እኔ ግን ብዙ እንዳይሰደቡብኝ የምጠብቃቸው እሴቶች አሉኝ፡፡ ስለዚህ መንገድ ባልከፍት ይሻላል በሚል…
“እኔ የንባብ ሱስ ነው ያለብኝ” አልኩት፡፡ ክብርን የሚጨምር እንጂ የማይቀንስ ሱስ መምረጤ ነበር፡፡
“እኮ የባህል ሱስ ተጠቂ ነህ - ያው ነው፤‹ማንበብ ሰው ያደርጋል› የሚለው ህልም ሱሰኛ ነህ…አዎንታዊ ሱስ ነው- ግን ፈዛዛ አድርጎሀል” አለኝ፡፡
እንዳልሰማሁ በመስኮቱ አሻግሬ ወደ ውጭ ማየት ጀመርኩኝ፡፡ በመስታወቱ ነፀብራቅ የእብዱ ፊት ላይ ያለው ቆዳ እንደ መሬት የተሰነጣጠቀ መሰለኝ፡፡ ግንባሩ በአንድ በኩል ተጠርምሶ የጎደጎደ ይመስላል። በፊት ለፊቱ ሲታይ የተጠረመሰው ግንባሩ በመስታወቱ እንደተንፀባረቀው ሆኖ ትንሽ የላብ ወዝ ይጨመርበታል፡፡ ትንሽ ፈቅ ብላ አንዲት ሴት ጆሮዋ ላይ ማዳመጫ ደቅና ስልኳን ትነካካለች። በመስታወቱ ነፀብራቅ እየተጫወተች ያለችውን ጌም ለየሁት፡፡… እኔን አንድ ሳምንት ከመፅሐፌ ሊቆራርጥኝ የነበረ ሀይለኛ ሱስ ያለው ጌም ነው፡፡
“ማንበብ ሙሉ ሰው ካደረገህ በኋላስ…ምን ታደርጋለህ?” አለኝ፡፡
“እፅፍ ይሆናላ”
“የባህልና የተስፋ ሱስ ተጠቂ ነህ… አዘንኩልህ… እንዳንተስ አያድርገኝ!” ብሎ ለባቡር የሚሆን ትንሽ ምራቅ ጢቅ አደረገ፡፡ በጥንቃቄ፡፡
“እሺ” አልኩት፡፡… አዲስ አይነት የእብድ ዝርያ እየተፈጠረ መሆኑንና በመፅሐፍት መሀል አንዱ በሌላው ላይ ብልጫ እንደሚያሳየው፣ እርሱ ደግሞ ከከተማ እብዶች አዲስ መሆኑን አሰብኩኝ፡፡ ትንሽ እንደ ምስባክ ባለ ከፍታ ላይ ራሴን አድርጌ ነበር የማስተውለው፡፡ … እሱም ግን በቀላሉ የማይሸነፍ ነው፤ በወደቀበት ሆኖ እኔን እንደ ትቢያ አድርጎ ለመግለፅ ይፍጨረጨራል፡፡
“በነገርህ ላይ…በዘላቂነት የሚኖሩት የአንተ አይነቶቹ ሱሰኞች ናቸው…፡፡ በባህል በሀይማኖት…በመናፍስትና በማይጨበጥ ተስፋ ሱስ የተጠቁት። የእኛ አይነቱ ጉበቱን ጨርሶ ይሞታል፡፡ የእናንተ ተስፋ አአምሮአችሁን በርዞትም እንደታመማችሁ ሳታውቁ ሸምግላችሁ ልትሞቱ ትችላላችሁ፡፡… በህይወት ለመቆየት የእናንተ ሱስ ይጠቅማል… ሀቀኛ ለመሆንና የእውነተኛ ህይወትን ያለ ሽንግላ ለመኖር ግን የእኔ ሱስ ነው የሚበልጠው፡፡…ገና የተሻለ መፅሐፍ ወደፊት አነባለሁ ብለህ ነው በተስፋ በመኖር ላይ ያለኸው፤ አይደለም?” አለኝ። መልስ ሳልሰጥ አደመጥኩት፡፡
“…አንተም የተሻለ መፅሐፍ ለማንበብ ትኖራለህ… ደራሲውም የተሻለ እፅፋለሁ እያለ ወረቀት እየበከለ ይቀጥላል፡፡… ተስፋችሁ በፍፁም ሊጨበጥ አይችልም፡፡ ከተጨበጠ ደግሞ ቶሎ የጨበጣችሁትን ለቃችሁ ሌላ ፍለጋ መንጠራራት አለባችሁ፡፡ … እኛ እና እናንተ ይኼ ነው ልዩነታችን።… እኛ የተሻለ ጣዕም ያለው አረቄ ለመጠጣት አይደለም መለኪያ የምንጨብጠው፡፡ … በቃ የተጨበጠ ሱስ ነው የኛ። አረቄ እንዲያሳስበኝ … ወይ በማህበረሰቡ ውስጥ ጠቃሚ ስፍራ እንዲያሰጠኝ አይደለም የምጠጣው፡፡ የምጠጣው የተስፋ ሱስ እንዳይዘኝ ስል ብቻ ነው፡፡ … መጠጥ ባቆም ስኬታማ የመሆን ተስፋ ይይዘኛል፡፡ … በዓለም ላይ ወደር ባልተገኘለት ፍቅር የምትወደኝ ሚስት የማግባት ተስፋ እንደ ህመም ይጠናወተኛል፡፡ … ልጆች ወልጄ ወደፊት የሰው ልጅን ስም የሚያስጠሩ እንዲሆኑ ለማድረግ ላልም እችላለሁ፡፡”
“እና ታዲያ ይሄ ህልም ምን ችግር አለው፣ ሰካራምና የማህበረሰብ ሸክም ከመሆን አይሻልም?” አልኩት፡፡
ራሴ ሳልሆን ሱሰኛ ያደረገኝ የባህል አስተሳሰብ ነው፣ በአፌ ቀድሞ እየወጣ የሚያወራልኝ፡፡
“…በመጨረሻ ላይ እኔንም፣ አንተንም ሱሳችን ሳይሆን የሚሸከመን፣ ሞተን የምንቀበርበት ጉድጓድ ነው፡፡ የአንተ መፅሐፍትም ሆነ ማህበረሰብ የምትለው ከሞት ባሻገር አንተን አይሸከምህም። ንባብህም ሆነ የተስፋ ሱስህ ከመቃብር ባሻገር አማላጅ ሆኖ አይቆምህልም፡፡ … ለመኖር ብለህ የያዝከው ሱስ ከሞት የማያድንህ ከሆነ ከእኔ በምን ትለያለህ?”
“…አይ እኔ ከሞት ያድነኛል ብዬ አይደለም የማነበው” አልኩት ቆጣ ብዬ፤ ቀስ እያለ እኮ እግሬን ከታች እየቆረጠ ሁለታችንንም ወደ አንድ ወለፈንድ ፅንሰ ሀሳብ ድንክነት አምጥቶ ሊያስተካክለን ነው። … “ስማ አጎቴ፤ እኔ ማንበብ ስለምወድ ብቻ ነው የማነበው … እንትን እና እንትን ወይንም ሌላ ከፍ ያለ ግብ ስለማገኝበት አይደለም፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠኝን አእምሮ መጠቀም ስለምፈልግ ብቻ ነው፡፡ አንተም በተፈጥሮ የተሰጠህን ጉበት እንዳሻህ አድርገህ መጠቀም ትችላለህ፡፡ … አንተ መሞት ልትፈልግ ትችላለህ፤ እኔ ደግሞ መኖር እፈልጋለሁኝ ካላስ!”
መውረጃዬ ጋር መድረሴ በአንድ በኩል ደስ እያለኝ ተነሳሁኝ፡፡ … “በል ደህና እደር” ብዬ ለምን እንደሆነ ባልተገለፀልኝ ምክኒያት ልጨብጠው እጄን ዘረጋሁኝ። ወደፊት ደግሜ እንደማላገኘው እርግጠኛ ሆኛለሁ፡፡ ከመሞቱ በፊት በህይወት እያለ ልሰናበተው ፈለኩኝ፡፡ እጄን ስዘረጋ፤ በስጋ ደዌ በጎደለ መዳፍ ልጨብጠው እንደሞከርኩ ሁሉ የተዘረጋለትን ስንብት ተንገሸገሸው፡፡ … እንደ ወታደር ሰላምታ በቅንድቤ ልክ ጣቶቼን ግንባሬ ላይ አሳርፌ፣ ወደ በሩ፣ ብረቶቹን እየያዝኩ ተራመድኩ። በሩ ሲከፈት ቀስ ብዬ ወረድኩኝ፡፡ ባቡሩ ተነስቶ ሲንቀሳቀስ “ለከተማ እድገት የሚመጥነውን እብድ” በአይኔ ፈለኩኝ፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙሱን ጉልበቱ መሀል ይዞ ጎንበስ እንደ ማለት ብሏል፡፡ ከአፍንጫው ንፍጡን በእጅጌው ላይ ሲጠርግ እያለቀሰ መሆኑን አወቅኩኝ፡፡ አሳዘነኝ፡፡
…በቀዝቃዛው ምሽት በአስፋልቱ ላይ እየተራመድኩ፣ ንፋሱ አጭር አድርጌ በተቆረጥኩት ፀጉሬ በኩል እያፏጨ ሲያልፍ … አየሩን በረጅሙ በአፍንጫዬ አስገብቼ በአፌ ሳስወጣ … ህይወት ምን ያህል ሱስ እንደሆነብኝ አወቅሁኝ፡፡ በደመ-ነፍስ የማውቀውን አስተውዬ በደንብ ልብ አልኩኝ፡፡ የፈለገ ባነብም … ህይወት ግን ሊለቀኝም የማይችል፣ እንዲለቀኝም የማልሻው ሱሴ መሆኑ ተገለፀልኝ፡፡
እብዱ እጄን ስዘረጋለት ለምን እንዳልጨበጠኝ ወዲያው ገባኝ፡፡ የእኔን እጅ እንደ ህይወት ሱስ ቆጥሮት እንዳይጋባበት … እንደ ወረርሽኝ ቢፀየፈውም … የተፀየፈው ግን እንዲያውም መሰናበቱን መሆኑ ከእሱ በላይ እኔን ገባኝ፡፡ መሞት ነው የማይፈልገው ግን በዚያው የመጠጥ ሱስ ምክኒያት ህይወት እየራቀው፣ ሞት እየቀረበው መምጣቱ ታውቆታል። ታውቆታል--- ወደ ህይወት ሱስ፣ ወደ መፅሐፍ ንባብ ከእንግዲህ እንደማይመለስ፡፡ መመለስ ይፈልጋል። ከእንግዲህ የመመለሱ ተስፋ የመነመነ እንደሆነም ጠንቅቆ አውቋል፡፡ … ፈፅሞ እብድ አይደለም፡፡ ድሮ እንደኔው አይነት ሰው ነበረ፡፡ ከሶስት ቢራና ከብዙ መፅሐፍት ንባብ ተነስቶ ወደ መጠጥ ሱስና ወደ መፅሐፍት ጥላቻ የሄደ ሰው አድርጌ ሳልኩት፡፡
የመጠጥን ሱስ ሊያሸንፈው የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ የመፅሐፍትና የተስፋ ሱስን የሚያሸንፍበትን ፍልስፍና ወደ መቅረፅ ሄደ፡፡ ያለው አማራጭ መቀበል ብቻ ስለሆነ … ሞትን ለመቀበል ደግሞ የህይወትን ሱስ መርሻ ምክኒያት ለራሱ መፍጠር አስፈለገው፤ ለእኔም ይሄንን የራሱን ትግል ነው እንደ አቋሙ አድርጎ ሊሰብከኝ የሞከረው፡፡ ግን እኔን ለመስበክ የሚሞክረው ሀሳብ ሲደመጥ፣ አሳማኝና ፍልስፍናው ያልተፋለሰ ቢሆንም … እኔን እንዳሳመነው ራሱን ማሳመን አልቻለም፡፡ … በአፉ ሲናገር ያሳመነኝ አጎንብሶ ሲያለቅስ ሳየው እውነቱ ተገለፀልኝ፡፡ ከህይወት ጋር የያዘው ሱስ፣ ከህይወት ጋር የያዘው ፍቅር አልለቀቀውም፡፡ … ከሞት የሚያገግምበት ምንም አማራጭ ባይኖረውም … ሞቱን በጉበቱ መጠን እየከረከመ በመጠበቅ ላይ ቢሆንም የህይወት ፍቅር አልለቀቀውም፡፡ ሞትን ለማጨት እየተዘጋጀ በድብቅ ከህይወት ጋር ገና ሲወለድ የያዘው ፍቅር አለቀቀውም። ምናልባት ከሞተም በኋላ አይተወውም፡፡ …
ይሄንን አሰብኩ፤ ስለ ከተማው ረቂቅ እብድ …፡፡ የእውነት ታሪኩ ይሄ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ ግን እንደዛ መሰልኩት፡፡ የመሰልኩት ምስል ከእውነተኛ ታሪክ በላይ የሚመስጥ መነካት ለመቀመም ስል … የሰራሁት አሳዛኝ የአንድ ገፀ ባህሪ ምስል እንደሆነ እያወቅሁም … ጉሮሮዬ ላይ የሀዘን ሳግ ሲቋጠር ይሰማኛል፡፡ ፈጠራ ሱስ ነው፡፡ ህይወት ፈጠራ ስትሆን እንደ መፅሐፍ ጥልቀት ትጨምራለች፡፡ ለገለጣትም ትነበባለች፡፡
በምናቤ ስዬው ከጨረስኩ በኋላ ስሙን ሳልጠይቀው መለየቴ ትዝ አለኝ፡፡ ስሙን ቢነግረኝ አልረሳውም ነበር፡፡ ድርሰቶች ላይ ያሉ ገፀ ባህሪያትን ስም አልረሳም፡፡ … የስጋ ለባሾቹ ስም ነው የማይያዘኝ።

Read 4339 times