Sunday, 11 March 2018 00:00

ኢህአዴግ ቀልድ ማቆም አለበት!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

“--በመፍትሔ ረገድ ገዢው ፓርቲ የሚያስቀምጠው ‹‹የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴን›› ሲሆን፤ ተቃዋሚዎች ግን የኢህአዴግ የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ለውጥ አ ያመጣም ይላሉ፡፡ በ እነሱ በኩል እንደ መ ፍትሔ የሚነሳው ‹‹የብሔራዊ እርቅ›› እና ‹‹የሽግግር መንግስት ምሥረታ›› ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም በተቃዋሚዎች የሚሰነዘሩትን እነዚህን መፍትሔዎች አይቀበላቸውም፡፡--”

አሁን የምንገኝበትን ሁኔታ በደንብ ለመረዳት የቻልን አልመሰለኝም፡፡ ድፍን ቅል ሆኖ እያስቸገረን ነው፡፡ ሆኖም ከፊታችን ያለው ችግር፤ ታሪክ ለቦዘን ማስታገሻ ብሎ ያቀረበው የእንቆቅልሽ ጨዋታ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ጉዳዩ ሐገርን የተመለከተ ወሳኝ ጥያቄ እንጂ ሥራ ፈት አዕምሮን ለማጫወት የተፈጠረ መልስ የሌለው ጥያቄም አይደለም፡፡ ሆኖም ለጊዜው የምናውቀው፤ ጥያቄ መኖሩን እንጂ መልሱን ወይም የጥያቄውን ምንነት አይደለም። እንኳን መልስ ሰጪዎቹ፤ጥያቄ አቅራቢዎቹም ጥያቄውን በደንብ የሚያውቁት አይመስልም። በአመጽ እንቁላል ውስጥ ያለ እና መልኩ ገና የማይታወቅ አዲስ ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩ፤ ጥያቄው እንቁላሉን ሰብሮ ለመውጣት አልቻለም፡፡ እርሱ ሰብሮ ባይወጣም፤ በምሁራዊ መነጽር ቅርፊቱን ዘልቀን ለማየትም አልቻልንም፡፡ ግን ከገጠመን ችግር ተነስተን፤ ከፊታችን የቆመው አዲስ ባህርይና መልክ ያለው ጥያቄ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ የሚታወቁ ሰዎች የሚያቀርቡትን ያልታወቀ ጥያቄ ለመረዳት ጥረት እያደረጉ ያሉት የሚታወቁ መልስ ሰጪዎች፤ አዲስ ባህርይ ያለውን ጥያቄ በተለመደው ምላሽ ለመሸንገል ሙከራ እያደረጉ ነው፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት በዚህ ሁኔታ እየታመሱ አልፈዋል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ያለው ሁኔታ አልጣመንም። ነገር ግን እንዲመጣ የምንፈልገውን ነገር በውል አናውቀውም። ስለዚህ ተቸግረናል፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ሁከት፤ በጠላነው ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ጥሩ ነገሮች በሙሉ ማጥፋትና  የምንፈልገውን ነገር ለመለየት የምናደርገውንም ጥረት ማደናቀፍ ብቻ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ የፖለቲካ ማህበረሰብ ረጋ ማለት ያስፈልገዋል፡፡ ረጋ ብሎ፤ ‹‹የሁሉንም ልብ የሚያረካ የፖለቲካ ማህበረሰብ ምን ዓይነት ነው?›› ብሎ ጠይቆ፤ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እኔ በዚህ ጽሁፍ ለማድረግ የምሞክረው ይህን ነው፡፡ ሆኖም ጥረቴ መልስ ፍለጋ አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ ጥረቴ ጥያቄውን ለመረዳት ሙከራ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ችግሩ የት እንዳለ ለማወቅ የሚያስችል ብርሃን መፍጠር ነው -- ከተሳካልኝ፡፡
ታዲያ ይህን ሥራ ለመጀመር ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ ችግር እና መፍትሔ በሚል የሚያቀርቧቸውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እርሱን አደርጋለሁ፡፡ ከዚያም ችግሩን ለመረዳት ጥሩ ጥረት ያደረጉ አንድ ፀሐፊ የሚሰጡትን ትንታኔ ተንተርሼ የመሰለኝን አስተያየት አቀርባለሁ፡፡ ይህ ችግሩን ለመረዳት የሚያስችል በር ይከፍትልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በር ባይከፈትም ዝም ብሎ ጩታ ከማከክ ይሻላል፡፡
ችግር እና መፍትሔ
ሦስቱ የፖለቲካ ተዋናዮች (ህዝቡ፣ ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች) ችግር ብለው የሚያነሷቸው ነገሮች አሉ፡፡ በህዝብ ወገን ሊመደቡ የሚችሉ ቡድኖችና ዜጎች በተናጠል የሚያነሷቸው ችግሮች አሉ፡፡ ታዲያ ቡድኖችና ዜጎች በተናጠል የሚደርስባቸውን ችግር በደንብ ያውቁት ይሆናል እንጂ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱትን (አንዳንዴም የመጋጨት ባህርይ ሊኖራቸው የሚችሉ ፍላጎቶችን) ጥያቄዎች አቀናጅተው፣ ሐገራዊ ቅርጽ ያለው የችግር እና የመፍትሔ ቀመር ሊፈጥሩ አይችሉም። በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱትን ችግሮች በማጣጣምና በማቻቻል መፍትሔ ሊሆን የሚችል የፖሊሲ ሐሳብ ሊያቀርቡም አይችሉም፡፡ ይህ ሥራ ሊሰራ የሚችለው ፍላጎቶችን አስማምቶና አጣጥሞ የፖለቲካ ቀመር የመፍጠር ሚና በሚጫወቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ወይም ቅሬታዎች የመተንተን ኃላፊነት ያለባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ታዲያ የሐገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹ችግር እና መፍትሔ›› በሚል የሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ወይም ሐሳቦች ምንድን ናቸው የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ዘወትር እንደሚባለው፤ ችግሩን በትክክል ለመረዳት መቻል፤ ከመፍትሔ የሚያደርስ ጎዳናን ይጠርጋል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን እንመልከት፡፡
በገዢው ፓርቲ እይታ በህዝቡ ዘንድ እንደ ችግር የሚነሱ ጉዳዮች ተብለው የሚቀርቡት፤ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች፤ እንዲሁም የፀረ - ዴሞክራሲያዊነት ችግሮች ናቸው፡፡ ገዢው ፓርቲ ለእነዚህ ለተጠቀሱት ችግሮች መንስዔ አድርጎ የሚያቀርባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነርሱም፤ የኪራይ ሰብሳቢነት፤ ለሥልጣን ያለ የተዛባ አመለካከት ናቸው። የሐገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የፈጠራቸው የህዝብ ፍላጎቶችም አሉ ይላል፡፡ እነዚህም ‹‹ጠያቂ ህብረተሰብና ልማቱ የቀሰቀሳቸው ተጨማሪ የልማት ፍላጎቶች›› የሚላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹የተቋማት አለመጠናከር›› በሚል የሚጠቅሰው ችግርም አለ፡፡ እነዚህም ችግሮች በግንባሩ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ በሚታዩ ‹‹የመርህ አልባ ግንኙነት፤ የህዝበኝነት፣ የቡድንተኝነትና የሙስና›› ችግሮች መባባሳቸውን ያስረዳል፡፡ የተዘረዘሩትን ችግሮች ጠቅለል አድርጌ ሳያቸው፤ ‹‹ሥልጣን ህዝብን ማገልገያ ወይም የለውጥ መሣሪያ መሆኑን ዘንግቶ፤ የግል ጥቅም ማስከበሪያ መሣሪያ የማድረግ ችግር›› ሊቀመሩ ይችላሉ። በበኩሌ፤ ‹‹ለሥልጣን ያለ የተዛባ አመለካከት›› የሚለው ጉዳይ፤ በኢህአዴግ በኩል ለሚነሱ ሁሉም ችግሮች መንስዔ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የሚዘረዝሯቸው ችግሮች አሉ፡፡ ‹‹ችግሩ በህዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣ ድርጅት አለመሆኑ ነው›› ከሚል ግራ አጋቢ ሐሳብ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ ‹‹ገዢው ፓርቲ የሚያቀነቅነው የጎሳ ፖለቲካ፤ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል አከላለል፤ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ፤ የሲቪክ ተቋማት በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻልና መዳከም፤ የሥራ አስፈጻሚው አካል በሐገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ህይወት ውስጥ ፍፁም አድራጊና ፈጣሪ መሆን፤ የገዢው ፓርቲ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት›› ወዘተ አሁን ለገጠሙን የተለያዩ ችግሮች መነሻ ናቸው ይላሉ፡፡
በርግጥ ሁለቱም ወገኖች ከሚያነሷቸው ችግሮች ውስጥ ያልጠቀስኳቸው ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ነገሮቹ በጥቅሉ ሲታዩ፤ የችግሩን መንስዔዎች በተመለከተ በሁለቱም ወገን የሚሰጡት አስተያየቶች ያን ያህል ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ሁለቱም ወገኖች የሚያነሷቸውን የተለያዩ የሚመስሉ ችግሮች፤ በምክንያትና ውጤት አስተሳስሮ አንድነት መፍጠር ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ልዩነታቸውን ጠብቀው የሚቀሩ ወሳኝ ነጥቦች መኖራቸው አይቀርም፡፡
‹‹በህዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን ያልመጣ ድርጅት›› የሚለው ኢህአዴግ የሚቀበለው ክስ አይደለም። እንዲሁም ‹‹ገዢው ፓርቲ የሚያቀነቅነው የጎሳ ፖለቲካ ወይም በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል አከላለል አሁን ለተፈጠረው ችግር ዳርጎናል›› በሚል በተቃዋሚዎች የሚሰነዘረውን አስተያየትም አይቀበለውም፡፡ ገዢው ፓርቲ፤ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቧቸውን እነዚህን ሁለት አስተያየቶች ‹‹በጥሬው›› ባይቀበላቸውም፤ በእነዚህ ጉዳዮች ጭምር መቀራረብ መፍጠር ይቻላል፡፡
ገዢው ፓርቲ በምርጫ ማግስት የተነሳበትን ተቃውሞ ሲተረጉም፤ ምርጫን ከማጭበርበር ጋር አያይዞ ባያየውም፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታዩት የአመጽ ዝንባሌዎች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ፤ መቀሌ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ ‹‹ህዝቡ የመረጠን ችግር የለባችሁም ብሎ አይደለም፡፡ ይልቅስ ተመክሮ ተዘክሮ ችግሮቹን ያሻሽላል በሚል እምነት ነው›› ብሎ ነግሮናል፡፡ ይህን ተቃዋሚዎች ‹‹በህዝብ ምርጫ ወደ ሥልጣን ያልመጣ ድርጅት›› በሚል ከሚያነሱት ችግር ጋር አወራርሰን ማየት እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል፤ ገዢው ፓርቲ የፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን መቶ በመቶ ማሸነፉን መጀመሪያ አካባቢ እንደ ስኬት ቢቆጥረውም፤ አሁን ያን አቋሙን ቀይሯል፡፡ አሁን ‹‹የኢትዮጵያ ነባራዊ ብዝሃነት በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል የሚችል አይደለም›› በሚል ፓርላማው መቶ በመቶ በአንድ ፓርቲ አባላት መያዙ ችግር መፍጠሩን ተገንዝቧል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ የፌደራል አከላለሉ የብሔር መስመርን የተከተለ መሆኑን እንደ ችግር አይወስደውም፡፡ ይሁንና ለብሔራዊ አንድነት ጉዳይ ተገቢ ትኩረት አለመሰጠቱ ችግር መሆኑን ተቀብሏል። በዚህ አኳኋን ሁለቱ ወገኖች በችግሩ መንስዔ ላይ እንዲቀራረቡ ለማድረግ ብንችልም በመፍትሔ ረገድ ማቀራረብ አንችልም፡፡ ስለዚህ በመፍትሔ ረገድ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡  
በመፍትሔ ረገድ ገዢው ፓርቲ የሚያስቀምጠው ‹‹የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴን›› ሲሆን፤ ተቃዋሚዎች ግን የኢህአዴግ የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ለውጥ አያመጣም ይላሉ፡፡ በእነሱ በኩል እንደ መፍትሔ የሚነሳው ‹‹የብሔራዊ እርቅ›› እና ‹‹የሽግግር  መንግስት ምሥረታ›› ነው። ገዢው ፓርቲም በተቃዋሚዎች የሚሰነዘሩትን እነዚህን መፍትሔዎች አይቀበላቸውም፡፡ ታዲያ ‹‹የብሔራዊ እርቅ››ን ቃል በቃል ባይቀበለውም፤ በቅርቡ በተለያዩ ምክንያቶች በእስር የቆዩ ሰዎችን (አንዳንዶች የፖለቲካ እስረኞች የሚሏቸውን) ለመፍታት መወሰኑን፤ የ‹‹ብሔራዊ እርቅ›› አጀንዳ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ እስረኞችን በምህረት እና በይቅርታ የመፍታት እርምጃን፤ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት እርምጃ እንጂ ‹‹የብሔራዊ እርቅ›› ጉዳይ አድርጎ አይገልፀውም፡፡ ስለዚህ በመፍትሔ ረገድ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች የመቀራረብ ሁኔታ አይታይም፡፡ አንዱ የችግሩ ቁልፍ መፍትሔ ‹‹የሽግግር መንግስት ምስረታ ነው›› ሲል፣ ሌላው ‹‹ጥልቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው›› ይላል። በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ሆኖ ለመናገር የሽግግር መንግስት ምሥረታ ጉዳይን ትቼ፤ ‹‹በጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ” ጉዳይ በመወሰን አስተያየት እሰጣለሁ።
ጥልቅ ተሐድሶ
ኢህአዴግ በታሪኩ ሁለት ተሐድሶዎችን አድርጓል። በ1993/94 የተካሄደው የመጀመሪያው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ፓርቲው በተለያዩ መስኮች ለፈጠራቸው አወንታዊ ለውጦች ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ግልጽ ፖሊሲዎች ተቀርፀው የወጡትና መተግበር የጀመሩት በመጀመሪያው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ሆኖ ከመጀመሪያው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ያገኘው ኃይል ከ15 ዓመታት በላይ ሊወስደው አልቻለም፡፡ ከ15 ዓመታት በኋላ በ2008 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባ። የሁለተኛው የተሐድሶ እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ምዕራፍ ክንውን ውጤታማ ባለመሆኑ፤ ፓርቲው እንደገና ራሱን ገምግሞ ዳግም የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ፤ ተጨባጭ ለውጦችን በጉጉት ይጠብቅ የነበረውንና ከእንቅስቃሴው ጠብ የሚል ነገር ያጣውን ህዝብ አስቀይሟል፡፡ ገዢው ፓርቲም ችግሩን ተረድቶ፣ በሁለተኛው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ዳግም ግምገማ ለማድረግ ተገዷል፡፡
ይህ የጥልቅ ተሐድሶ በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ የሚካሄድ ተሐድሶ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው የሐሳብና የዓላማ አንድነት ማጣት ውስብስብ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በሂደቱም የመንግስት ተዓማኒነትን የሚሸረሽሩና የህግ የበላይነትን የሚጎዱ በርካታ ችግሮች ታይተዋል፡፡ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ‹‹የጎራ መደበላለቅ›› የሚሉት ችግር በተፈጠረበት ሁኔታ የተካሄደ የተሐድሶ እንቅስቃሴ በመሆኑ፤ የህዝብ አመኔታ ለማግኘት ብርቱ ፈተና ያለበት እንቅስቃሴ ነው፡፡   
በገዢው ፓርቲ ዘንድ የተሐድሶ አንቅስቃሴውን የሚጎዱ በርካታ የአመለካከትና የተግባር ችግሮች አሉ። ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ሊነሳ የሚገባው የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት በፀረ-ሙስና ትግሉ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳዩ በቂ እርምጃዎች አልወሰደም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሞከራቸው የፀረ-ሙስና ዘመቻዎች፤ የህዝቡን አመኔታ የሚሸረሽሩና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የበላይነት ያለው መሆኑን በሚያረጋግጥ ሁኔታ የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡ የፀረ-ሙስና ትግሉ፤ ‹‹ሙስናን መቀነስ እንጂ ማስወገድ አይቻልም›› ከሚል የባለሥልጣናት ገለጻ ጀምሮ፤ ትግልን በሚያኮላሹ የተለያዩ አመለካከቶችና ተግባራት የተሽመደመደ ነው፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚል የፊውዳል ዘመን አባባል እየተጠቀሰ፤ ‹‹ህብረተሰቡ ሙስናን የሚያበረታቱ ዝንባሌዎች አሉት›› እየተባለ ይነገራል፡፡ ‹‹የመንግስት ኃላፊነትን የሚይዙት እንዲህ ያለ ሙስናን የሚያበረታታ አመለካከት ካለው ህብረተሰብ የወጡ ሰዎች ናቸው›› ብለው የሚናገሩ ባለሥልጣናትም አሉ፡፡ ይህ አነጋገር ብዙ ሸማች ያለው፤ የተሳሳተና አደገኛ አነጋገር ነው፡፡ እነዚህ ንግግሮች የፀረ-ሙስና ትግሉን የሚያኮላሹና ‹‹የመንግስት ሐብት ቢዘረፍና ቢመዘበር አይግረምህ›› የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉ፤ ለሌቦች ጋሻ ሆነው የሚያገለግሉ ብሂሎች ናቸው፡፡
‹‹ሙስናን መቀነስ እንጂ ማስወገድ አይቻልም›› ይባላል፤ መንግስት ግብ አድርጎ መያዝ ያለበት፤ ሙስናን ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ዓላማን እንጂ የመቀነስን ዓላማን አይደለም፡፡ ምናልባት፤ ይህን ዓላማ አድርጎ ይዞ በተግባር ሳይሳካ ሊቀር ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ አፈጻፀሙን አይቶ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ለይቶ ለመሥራት መንቀሳቀስ ነው፡፡ በተረፈ፤ ሙስና የስርዓቱ ዋና መገለጫ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ‹‹ሙስናን መቀነስ እንጂ ማስወገድ አይቻልም›› ማለት ነውር ነው። ከስድብ መቆጠር ያለበት ንግግርም ነው፡፡ ‹‹የመንግስት ኃፊነት የሚይዙት እንዲህ ያለ ሙስናን የሚያበረታታ አመለካከት ካለው ህብረተሰብ የወጡ ሰዎች ናቸው››፤ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚል አመለካከት በህብረተስቡ ዘንድ አለ›› የሚል ዲስኩርም ከፖለቲካ ተዋስዖ መድረኩ መወገድ አለበት፡፡
እንደሚታወቀው፤ እላፊ ለመጠቀም በማሰብም ወይም መብታቸውን በገንዘብ ለመግዛት ተገደው ጉቦ ለመስጠት የሚሞክሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሁለቱም ወንጀለኞች ናቸው። ሁለቱም፤ የመንግስት ኃላፊነትን በያዙ ሰዎች ዘንድ ያሉ ችግሮችን የሚመለክቱ እንጂ በህዝብ ዘንድ ያሉ ችግሮችን የሚያሳዩ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም። አንደኛው፤ እላፊ ጥቅም በመስጠት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች መኖራቸውን ያመለክታል። ሁለተኛው፤ ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት በአግባቡ የማይሰጥና በዚህም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀስ የሥራ ኃላፊ መኖሩን ያመለክታል፡፡ መቼም ጉቦ ሳይሰጥ አገልግሎት ማግኘት እየቻለ ገንዘብ መስጠት የሚፈልግ ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ እላፊ ለመጠቀም አስቦ የሚመጣውም፤ ከመንገድ የወጣ ሥራ ለመስራት ፈቃደኛ የሆነ የሥራ ኃላፊ መኖሩን በመገመትና ተጨባጭ ተመክሮውም ይህን ስለሚያረጋግጥለት ነው። በሁለቱም አጋጣሚዎችም ችግሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ችግሩን የህዝብ አድርጎ የሚያቀርብ አመለካከት በጣም የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለዘመናት የሰፈኑት ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች በፈጠሩበት ጫና የተፈጠረውን የአመለካከት ችግር የሥነ ዜጋ ትምህርት  በማስረጽ ማስወገድ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡    
በተረፈ መንግስት፤ ‹‹እንዲህ እንዲህ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ካመነበት ሊፈቅድ ይችላል›› የሚል የአቀራረጽ ዘይቤ ካላቸው የህግ አንቀፆች ጀምሮ፤ ማናቸውም ለሙስና በር የሚከፍቱ ደንቦችና መመሪያዎችን ከማሻሻል ጀምሮ፤ ጥፋት ተሰርቶ ሲገኝ አስተማሪ ቅጣት በማስተላለፍ፤ ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ አደረጃጀት ያለው የፍትህ ስርዓት በመፍጠር ለፀረ-ሙስና ቁርጠኛ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል። ሆኖም በእስካሁኑ ሂደት፤ በመንግስትና በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ሰርቆ መኖርና የህዝብን ሐብትና ንብረት ለምዝበራ እያጋለጡ በስልጣን መቆየት እንደማይቻል ማሳየት አልቻለም፡፡ ሰርቀው መክበር የቻሉ የሥራ ኃላፊዎች በመንግስት አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ መታየታቸውም ሌሎችን ለዝርፊያ የሚያነሳሳ ነው፡፡ መንግስት በሚያውቀው ልክ እርምጃ መውሰድ ተስኖት እየታየ፤ ‹‹የሙስና ጉዳይ በጣም ውስብስብ ነው፤ ህብረተሰቡም ሊያግዘኝ ይገባል›› ብሎ ሊናገር አይገባም። የፌዴራል ዋናው ኦዲተር በየጊዜው የሚያቀርበውን በቢሊየን የሚቆጠር የችግር ሪፖርት፣ ስንት ጊዜ በሽንገላ እንዳለፈው እናውቃለን፡፡ የፀረ - ሙስና እና የሥነ ምግባር ኮሚሽንም፤ ‹‹የመንግስት ባለሥልጣናትን ሐብት መዝግቢያለሁ፤ አሁን ይፋ አደርገዋለሁ›› እያለ ሲፎክር ወደ አስር ዓመት የሚጠጋ ዘመን አሳልፏል፡፡
አሁን በሐገሪቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ከወንጀል የፀዳ የሥራ እንቅስቃሴ የለም ብለን እንድንገምት የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሙስና መደበኛ አሰራር መስሎ የሚታይበት ምህዳር ተፈጥሯል። በሺህዎች የሚቆጠሩ በተጭበረበረ የትምህርት ሰነድ፣ የመንግስት ኃላፊነት የያዙ ሰዎች  መኖራቸውን አይተናል፡፡ ይህ ችግር ከሚገመተው በላይ ግዙፍ መሆኑን ታዝበን ዝም ብለናል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚል የፊውዳል ብሂል እየጠቀሱ ማደናገር ተገቢ አይደለም፡፡ መቶ በመቶ ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የፀዳ የመንግስት አስተዳደር የመፍጠር ግዴታም የመንግስት እንጂ የህዝብ አይደለም። ዜጎች በእጅ መንሻና በጉቦ ለመሄድ የሚገደዱት ብልሹ አስተዳደር ሲኖር እንጂ ጉቦ መክፈል ደስ ስለሚላቸው አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲ በተሐድሶ እንቅስቃሴው ውጤታማ ይሆን ዘንድ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ የምንሰማቸው የሙሰኞች መዝሙር አዝማች የሆኑ መሰል አገላለፆች፤ ከተዋስዖ መድረኩ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡
ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚረጋግጥ ህገ መንግስታዊ መርህ በሌለበት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓት፣ እነዚያ ብሂሎች መፈጠራቸው አይገርምም፡፡ ይልቅስ የሚያሳዝነው ‹‹ግልጽነት እና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ስርዓት›› በምንለው የመንግስት አስተዳደር ውስጥ፤ (በብዙዎች ግምት ከቀድሞዎቹ መንግስታትም የባሰ) የሙስና ችግር መንሰራፋቱ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ‹‹ከአፍሪካ ሐገራት የባሰ ችግር የለብንም›› በሚል ሊሸነገል የሚችል አይደለም፡፡ ችግሩ የስርዓት ቀውስ ለመፍጠር ከሚችልበት አደገኛ ነጥብ ደርሷል፡፡ ይህን ችግር አምኖ መቀበል ሳይሆን ችግሩን የሚመጥን ሥራ መስራት አለብን፡፡
በተመሳሳይ፤ ‹‹የጥልቅ ተሐድሶው ስኬት የሚመዘነው ሰዎችን በማባረር አይደለም›› የሚለው አገላለጽም ተመሳሳይ ችግር ነው፡፡ ይህ አገላለጽም ሆነ ‹‹ሙስናን ማስወገድ የሚቻለው ለሙስና ምቹ ያልሆነ የፖለቲካል - ኢኮኖሚ በመፍጠር ነው›› የሚለው ድንጋጌ፤ ከላይ -ከላይ ሲታይ የአስተዋይ ሰው ድምዳሜዎች ይመስላሉ፡፡ በርግጥም ናቸው። ሆኖም  ‹‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ›› የሚባል ሁኔታ ውስጥ ለሚዳክር መንግስት ተገቢ ድምዳሜዎች አይደሉም። ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው፤ በ2008 ዓ.ም በተካሄደው ግምገማ ለውጥ ይመጣል ብሎ ይጠብቅ ለነበረው ህዝብ፤ ከግምገማ አዳራሽ የሚወጡት የድርጅቱ አመራሮች ይሰጡት የነበረው መግለጫ፤ ‹‹ለውጥ የምናመጣው አመለካከትን በመቀየር እንጂ ሰዎችን በመቀየር አይደለም›› የሚል ነበር፡፡
በዚህ መሰል የባለስልጣናቱ መግለጫ የበርካታ ህዝብ ስሜት ተጎድቷል፡፡ ኢህአዴግ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት እንዳይዝ አድርጎታል፡፡ አስተያየቱ የህዝብን ስሜት ብቻ ሳይሆን የተጠያቂነትን ጉዳይ አጥፍቶታል፡፡ ተጠያቂነት መቀለጃ ሆኗል፡፡ በግምገማው ማግስት አንዳንድ የመንግስት ጋዜጠኞች ጉድለት ከታየበት መሥሪያ ቤት ሄደው ባለሥልጣኑን ሲያናግሩ፤ ‹‹እሺ ለዚህ ጉድለት ተጠያቂው ማነው?›› የሚል ጥያቄን ያነሱ ነበር፡፡ ጥያቄው የወቅቱ ፋሽን ሆኖ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የሥራ ኃላፊዎች፤ ‹‹መሥሪያ ቤቱ፣ የቀድሞው አመራር›› የሚል ምላሽ ሲሰጡ፤ የተወሰነ ቅንነት ያልራቃቸው ደግሞ ‹‹እኔ ተጠያቂ ልሆን እችላለሁ›› የሚል መልስ ሲሰጡ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በሁሉም በኩል ተጠያቂ የተደረገ ሰው አልነበረም፡፡
በገዢው ፓርቲ የሂስና የግለ ሂስ ነገር ድርጅታዊ ባህል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የድርጅቱን ባህል ወደ መንግስት አሰራር ማምጣት አይችልም፡፡ የድርጅቱ አባላት በፓርቲ ተልዕኮ ለፈፀሙት ጥፋት በሂስና በግለ ሂስ ሊታለፉ ይችላሉ፡፡ ያ የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በመንግስት አሰራር ውስጥ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች መታየት ያለባቸው፤ ህገ መንግስታዊ በሆነው የተቀባይነት መርህ ነው። በዚህ አካሄድ የጥልቅ ተሐድሶው እንቅስቃሴ ሊሳካ አይችልም። ድርጅቱ ከባድ የአሰራርና የአመለካከት ግድፈት አለባቸው ብሎ የገመገማቸውን አባላት፤ በጥፋታቸው ልክ ተጠያቂ ማድረጉ ቀርቶ፤ በሌላ ቦታ እየመደበ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ እያደረገ ወይም ሌላ ከፍ ያለ የመንግስት ሹመት እየሰጠ፤ በአሁኑ ወቅት በጣም የሚያስፈልገውን የህዝብ አመኔታ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ሊታገልም አይችልም፡፡
በዚሁ አግባብ በርካታ ግድፈትና ጥፋት የፈፀሙ አመራሮች በኃላፊነት ሲቀጥሉ አይተናል። አንዳንዶች ለግምገማ ሲቀመጡ፤ ‹‹በግምገማው ማጠቃለያ ጠንካራ ውሳኔ ጠብቁ›› ብለውን ወደ አዳራሽ ገብተው፤ በመጨረሻ ‹‹ችግር ያለባቸውን አመራሮች ገምግመናል። አመራሮቹ የአመለካከት ለውጥ አድርገዋል፡፡ ህዝቡን ለመካስ ቃል ገብተዋል›› በሚል ኃላፊነታቸውን ይዘው መቀጠል ችለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች የሚታዩበት የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ የህዝብ አመኔታን ሊያስገኝ አይችልም፡፡ ኢህአዴግ ቀልድ ማቆም አለበት፡፡
በአንድ ወቅት ኢህአዴግ ‹‹እንደ ታምራት ላይኔ ያለ ጠንካራ ታጋይ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በስኳር ተሸነፈ፡፡ አሁን ድርጅቱ እርሱን ይዞ መቀጠል አይችልም›› ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በህግ እንዲጠየቁ አድርጎ እንደነበር፤ እንኳን በጆሮ የሰማው በዓይኑም ያየው ሰው ሊጠራጠር ይችላል። ይህን አሰራር የለመዱ አንድ ሚኒስትር ዴኤታ፤ ባለፈው ዓመት በምክር ቤቱ ውስጥ የሙስና ወንጀል ጥያቄ ሲነሳባቸው፤ ‹‹ይህን ጉዳይ በዚህ መድረክ ባናየው ይሻላል›› በማለት ራሳቸውን ለመከላከል ሞክረዋል። ይህን ያሉበት ምክንያት ግልጽ ይመስለኛል። በፓርቲ መድረክ፤ እንደ ተለመደው ግለ ሂስ አድርገው፣ ከተጠያቂነት ለመዳን እንደሚቻል በማሰባቸው ሊሆን ይችላል፡፡
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመሩት እና የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ባስተላለፈው የውይይት መድረክ፤ የፖሊሲ ጥናት ተቋም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያካሄደው 800 ገፆች ያለው ሐገር አቀፍ ጥናት ቀርቦ ውይይት መደረጉን እናስታውሳለን። ያ ውይይት በህዝቡ ዘንድ የፈጠረው ስሜት ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ኢቴቪ ባልተለመደ ሁኔታ ለህዝብ ያቀረበው የዚያ ጉባዔ ውይይት፣ በህዝቡ ዘንድ የፈጠረው ትልቅ ተስፋ ነበር። ያ ተስፋ እና አመኔታ ገዢው ፓርቲ ለሚያካሂደው የፀረ-ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ትግል ትልቅ እገዛ ሊያደርግ የሚችል ነበር፡፡ ታዲያ በዚያ ውይይት ማጠቃለያ፤ አቶ ኃይለማርያም ‹‹አሁን ከዚህ አዳራሽ ስትወጡ ኔትወርካችሁን መከላከል ትጀምራላችሁ። አብሮ አደጌን፣ የፓርቲዬን አባል፣ የት/ቤት ጓደኛዬን አሳልፌ አልሰጥም ማለት ትጀምራላችሁ›› ያሉት ችግር ተፈጥሮ፤ የተሐድሶ እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከንቱ ትያትር ሆኖ  ተጠናቀቀ፡፡ ‹‹እባብ ያየ፤ በልጥ በረየ›› እንዲሉ፤ ኢህአዴግ ሐገሪቷን ከገባችበት ማጥ ሊያወጣት የሚችለው ሁነኛው መፍትሔ፣ “የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ” ነው ሲል አምኖ መቀበል የሚከብደው ሰው ብዙ ነው። ሆኖም ለጊዜው ኢህአዴግ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊነግረን አይችልም፡፡ ይሁንና ከኢህአዴግ በተለየ ጎዳና ችግሩን የሚተነትኑና የተለየ መፍትሔም የሚያስቀምጡ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ታዲያ ተቃዋሚዎች ከሚያቀርቡት ትንታኔና ‹‹የሽግግር መንግስት›› ከሚሉት አማራጭ ለየት ያለ ትንታኔና መፍትሔ የሚያስቀምጡት ሰዎች ምን ይላሉ? ሣምንት ጠብቁኝ፡፡

 

Read 3040 times