Tuesday, 13 March 2018 13:24

“በትግል ነው የታሰርኩት፤ ለትግል ነው የተፈታሁት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ሁሉም የኔ ናት የሚላት፣ የሁሉም አገር መሆን አለባት

የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ መደበኛ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ሊወጣ አንድ ወር ከ18 ቀናት ሲቀሩት ባለፈው ሰኞ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ከእስር ተለቋል፡፡ ለእስር ስላበቃው ጉዳይ፣ስለ ማረሚያ ቤት ቆይታው፣ስለ ፖለቲካ ህይወት ጅማሬው፣ ስለ አገሪቱ የፖለቲካ ቀውስና መፍትሄዎቹ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
ወጣት ዮናታን ተስፋዬ (የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህ/ግ/ኃላፊ)

እስቲ እንዴት ወደ ፖለቲካ ህይወት እንደገባህ ንገረኝ?
እንደ አብዛኛው ወጣት ወቅታዊ ጉዳዮችን እከታተል ነበር፡፡ በተለይ ከ1992 ዓ.ም በኋላ የነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለየት ያለ መልክ ነበራቸው፡፡ እኔም ነፍስ አውቄ መጠየቅ ስጀምር እንደ አጋጣሚ የ1996 እና 1997 ዓ.ም ተከታትለው የመጡ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ህብረት እና ቅንጅት መንግስት ሊሆኑ የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ያኔ እኔ፣ አሁን የካቲት 12 የተባለው በቀድሞ ስሙ መነን ነበር የምማረው። ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነው የቅንጅትንና የህብረትን እንቅስቃሴ እከታተል የነበረው፡፡ በቤት ውስጥም ጥሩ ግንዛቤ ስለነበራቸው እነ ጦቢያን የመሳሰሉ መፅሄቶች ይመጡ ነበር፡፡ እነሱን በስፋት የማንበብ ዕድሉ ነበረኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ፖለቲካውን ለመረዳት ጥረት አደርግ ነበር፡፡ በኋላም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ 97 ላይ የቅንጅትና የህብረትን የምረጡን ቅስቀሳ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ አግዝ ነበር፡፡ ከዚያም የአንድነት መመስረት ሲመጣ ዩኒቨርሲቲ ሆኜ በቅርበት እከታተል ነበር፡፡ እደግፍም ነበር፡፡ በኋላ በ2004 ዓ.ም አካባቢ ሰማያዊን ለመመስረት ሲጠነሰስም ሁኔታውን ሳይ መስራቾቹ ወጣቶች ናቸው፤ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን እንደ የነፃነት ታጋዮች ነበር የሚንቀሳቀሱት፤ በሚያዘጋጁት ሰላማዊ ሰልፍ እሳተፍ ነበር፡፡ በኋላ ኢ/ር ይልቃል የተወሰኑ ልጆችን አነጋግሮን ወደ ፓርቲው እንድንገባ፣ ከዚያም ወደ አመራርነቱ እንድንመጣ አድርጎናል፡፡ በወቅቱ ለመብትና ለነፃነት ነበር የምንታገለው እንጂ ለፖለቲካ ትግል አልነበረም፡፡ በዚህ መልኩ ነው 2005 ዓ.ም ላይ ፓርቲውን የተቀላቀልኩት፡፡
በወቅቱ ሰማያዊ ፓርቲ የነበረው የትግል ስልትና ራዕይ ምን ነበር?
በወቅቱ የነበረው ራዕይ እስከማስታውሰው ድረስ በእውቀት የሚመራ፣ ተግባር ተኮር የትግል ስልትን ተጠቅሞ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አንድ እርምጃ ማራመድ ነበር፡፡ ዝም ብሎ ኢህአዴግን በመጥላት ከስልጣን ለማውረድ መንቀሳቀስ ሳይሆን የፖለቲካ መድረኩን ማፍታታት ነበር፤ አንዱ አላማችን። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ምርጫ ገብቶ ተወዳድሮ፣ መፎካክር የሚቻለው የሚል እምነት ነበረን፡፡ እነዚህ ነገሮች ሳይስተካከሉ ፖለቲካ ማካሄድ ይከብዳል። ለዚያ አላማ ነበር ብዙ ሰልፎችን፣ የአደባባይ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ስንንቀሳቀስ የነበረው፡፡ ህብረተሰቡ ወደ ፖለቲካው ተደፋፍሮ መግባት የሚችለው ምህዳሩ ሲሰፋ በመሆኑ፣ ይሄን ሁኔታ ለማምጣት ነበር ስንታገል የነበረው። የትግል ስትራቴጂያችንም፤ በፊት ከሚታወቀው ጋዜጠኞችን እየጠሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ይልቅ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ስብሰባዎችን፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ መንግስት የፖለቲካ መድረኩን እንዲከፍት ነበር ስትራቴጂ ነድፈን ስንታገል የነበረው፡፡
በዚህ ስትራቴጂያችሁ ምን ያህል ውጤታማ ሆናችኋል?
የፖለቲካ ውጤት ሂደቱ ነው፡፡ ብዙ ሂደቶችን የተራመድን ይመስለኛል። ለምሳሌ መነቃቃትን ፈጥረናል፡፡ ህዝቡም ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮችም ከ97 በኋላ የተፋዘዘውን ለማነቃቃት ሞክረናል፡፡ ፓርቲዎች ተግባር ተኮር እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መነቃቃት ፈጥረናል፡፡ አሁንም ድረስ ዘልቀው የምናያቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች፣ ከ97 በኋላ ተቀዛቅዞ በነበረው ሁኔታ ላይ ሰማያዊ እንደ ክስተት ምንም የፖለቲካ ልምድ ባይኖረንም መነቃቃት ፈጥረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምርጫ 2007 ላይ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥም አዲስ ትውልድ ወደ ፖለቲካ መድረኩ እንዲመጣ በማድረግ፣ በዚህም የ60ዎቹ የሚባለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን አዲስ ትውልድ እንዳለ ማሳየት ችለናል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ተስፋ መስጠት ሆነ ማነቃቃት ችለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን በወቅቱ ህዝቡም ለምርጫው ብዙም ስሜት አልነበረውም። የመጣው ውጤትም ስሜት የማይሰጥ ይበልጥ በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር። እኛ ከዚያ በኋላ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ህጎችም ላይ እንቅስቃሴ ለማድረግም ሞክረናል፡፡ አሁን ፓርቲው በዚያ ደረጃ ቀጥሏል ለማለት ቢቸግረኝም በወቅቱ ግን በአጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን የፖለቲካ ድብታ ለመግፈፍ ጥረት አድርጓል፡፡ ህዝቡ ከዚያ ድብታ ወጥቶ እንዲነቃቃ በማድረግ ረገድ እኛም የተወሰነ ድርሻ ተወጥተናል የሚል እምነት አለኝ። ለህዝቡ ተስፋ በመስጠት በተወሰነ ደረጃ አስተዋጽኦ ያደረግን ይመስለኛል፡፡ ይሄ በእርግጥ ውጤት ነው ተብሎ የሚኮራበት አይደለም፡፡ ትግሉ ዛሬም ይቀጥላል፡፡
ከመታሰርህ በፊት በማህበራዊ ገፅህ የምትፅፋቸው ፅሁፎች አወዛጋቢ ነበሩ፤ “ወደ ብሔርተኝነት ያዘነበሉ ናቸው፣ ከፓርቲው ጋርም አይጣጣሙም፣ ህግም የሚጥሱ ናቸው” የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘሩ ነበር፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
አሁን በዚያ ጉዳይ ላይ በዝርዝር መናገር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሰማያዊ ፓርቲ ባለው ፕሮግራም ላይ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በጥቅል የተቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ይህን በማኒፌስቶው ላይ ለማብራራት የተሞከረበት ሂደት አለ፡፡ ከምርጫው በኋላ ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስላል? ኢህአዴግ በ25 ዓመት ውስጥ የነበረው ሚና ምንድን ነው? አዳዲስ ማንነቶችን የመፍጠር እንቅስቃሴ እንዴት መጣ? ለምሳሌ ከዚህ ቀደም አማራ የሚል እንቅስቃሴ የተለመደ አይደለም፤ አሁን ግን አለ፡፡ ሌሎችም የብሔረሰብ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይሄን ጉዳይ ሰማያዊ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በተለያየ አግባብ ነበር የሚረዱት፤ እኔና መሰሎቼ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የምንረዳበት መንገድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከአንድ አለት የተፈለፈለ ወጥነት ያለው ነገር አይመስለኝም - እኔ፡፡ የተለያዩ ማንነቶችን አሰባስቦ የያዘ፣ እያደገ ያለ ሂደት ይመስለኛል - ኢትዮጵያዊነት፡፡ ሀገሪቱም ለሁሉም የምትሆን፣ ሁሉም የኔ ናት የሚላት እንድትሆን የሚለው ነበር መሰረታዊ የክርክራችን መነሻ፡፡ ይሄን ሃሳብ ይዘን ስንነሳ፣ ብሔራዊ ማንነት ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡ ፓርቲዎች ህብረ-ብሄራዊ እንዲሆኑ መሻት ነበረን፡፡ በዚህ ያልተደሰቱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ሰዎች የፍረጃ መንገድን ሲከተሉም አይቻለሁ፡፡ እኔ አሁንም የማምነው፤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ብሔረሰቦች ማሳተፍ በሚችል መልኩ የተዋቀረ የፖለቲካ ብሄራዊ ድርጅት ያስፈልጋታል፤ ብሔራዊ ድርጅቶችም ያስፈልጓታል ብዬ ነው፡፡ ካናዳ ኩዩቤክ ውስጥ የኩዩቤክን ማህበረሰብ የወከለ ድርጅት አለ፣ እስራኤል ውስጥ ሃይማኖትን የወከለ ድርጅት አለ፡፡ ስለዚህ እኛም ሀገር እንደዚህ አይነት ሰፊነት ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያስፈልገናል። ይሄ ሃሳብ የብዙዎች እንዲሆን ነበር በፌስቡክም ሆነ በሌሎች መንገዶች ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ በፓርቲው ውስጥም በዚህ ረገድ የሀሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ግን ይሄ እኔ የማምንበት ጉዳይ ነበር፡፡ በአጠቃላይ እኔ ወደ ፓርቲው ስገባ፣ ለነፃነት የሚደረግን ትግል አስቤ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ፓርቲው ያንን የትግል ቀለሙን ሲያጣ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ስለነበሩ፣ ምርጫዬን በማምንበት መንገድ በማድረጌ ነው በደብዳቤ ከፓርቲው ኃላፊነት የለቀቅሁት፡፡
በመጨረሻም ለእስር የተዳረግኸው በፌስቡክ በምታደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት ነው፤ በዚህ መንገድ እታሰራለሁ ብለህ አስበህ ነበር?
ኢትዮጵያ ውስጥ በምን መንገድ ልትታሰር እንደምትችል መገመት አይቻልም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል እንዲቀጥል ማበረታታችን ቀርቶ በጋዜጣ ብቻ መረጃ በማስተላለፋቸው ብቻ እየተመሰከረባቸው የሚታሰሩ እንደ ውብሸት ታዬ፣ እስክንድር ነጋ ያሉ ነበሩ፡፡ በዚያ ወቅትም ሆነ አሁንም ድረስ የማምንበትና ህዝቡ ማድረግ አለበት የምለው ሰላማዊ ትግል እስከሆነ ድረስ ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ ሰላማዊ ትግል ማለት በምርጫ መንግስትን መለወጥ ማለት አይደለም፡፡ በምርጫ መንግስትን መለወጥ ማለት የፖለቲካ ትግል ነው። እኛ ገና ለፖለቲካ ትግል አልበቃንም፡፡ ሰላማዊ ትግል የምንለው ግን በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ፣ በህንድ፣ በአሜሪካ የጥቁሮች ትግል የተደረገበት መንገድ ነው፡፡
አፋኝ ህጎች፣ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ህጎች ሲወጡ፣ እነዚህን ህጎች በመጣስ የሚደረግ ትግል ነው ሰላማዊ ትግል፡፡ ለምሳሌ ጥቁሮች ነጮች ካፌ ገብተው እንዳይጠቀሙ ኢ-ፍትሃዊ ህግ ተደንግጎ ነበር፡፡ ጥቁሮች ይሄን መብታቸውን ለማስከበር ይሄን ኢ-ፍትሃዊ ህግ በመጣስ ነበር ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ የነበረው። ሮዛ ፓርክስ የጥቁሮች የትግል ቀንዲል የሆነችው በህግ የተከለከለውን፣ በአውቶብስ ውስጥ ጥቁሮች የማይቀመጡት ቦታ ላይ ተቀምጣ ነው፣ ኢ-ፍትሃዊ ህጉን በተግባር የተቃወመችው፡፡ ህጉን በመጣስዋ ታስራ ነው፣ ያንን ሁሉ የነፃነት ትግል ማቀጣጠል የቻለችው። ስለዚህ በሰላማዊ ትግልና በፖለቲካ ትግል መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀን መረዳት አለብን፡፡ የፖለቲካ ትግል የሚደረገው ሁሉም ነገር ሰላም ሲሆን፣ ምቹ ህግና ስርአት ሲኖር ነው፡፡ አፋኝ ህጎች በሌሉበት ሁኔታ ነው፣ እንደ ልብ ተወዳድሮ ለህዝብ ራስን እጩ አድርጎ ማቅረብ የሚቻለው፡፡ አምባገነን በሆነ ስርአት ውስጥ ህግ መጨቆኛ ሲሆን መጨቆኛ ህጎችን በመቃወም ትግል ማድረግ ለኔ ሰላማዊ ትግል ነው፡፡ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይሄን ትግል ማድረግ በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ መንግስት ህዝቡ ትክክል ነው ብሎ አምኖ ቆራጥ የሆኑ ማሻሻያዎችን እስኪያደርግ ድረስ የሚመጣብንን ዋጋ ሁሉ እየከፈልን፣ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እኔም ይሄን ነገር በመስበኬና ይሄን በተግባር ለማድረግ በመንቀሳቀሴ ነው የታሰርኩት። ፕ/ር መስፍን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት አይነት ሰው ነው ያለው፡- ታስሮ የተፈታ፣ የታሰረና ለወደፊት የሚታሰር። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል መታሰርንም ይፈልጋል፤ እየታሰርክ ስትታገል ነው የህሊና የበላይነት የሞራል የበላይነት ይዘህ መብትህን የምትጠይቀው፡፡ ስለዚህ መታሰራችንን በፀጋ የምንቀበለው ነው፤ አሁንም ደግመን መታሰር ካለብን በምናምንበት የሰላማዊ ትግል መታሰር ችግር የለውም፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር የፖለቲካ ትግል ላይ ልንገናኝ የምንችለው የህዝብን መብት መልሶ፣ ምቹ የፖለቲካ መድረክ ሲፈጥር ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ፣ የአሜሪካ የጥቁሮች መብት እንቅስቃሴ በእነዚህ ሂደቶች ነው ያለፈው፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ ምን ታዘብክ?
በጥቅሉ እስር ቤት የስቃይ ቦታ ነው፡፡ ሰዎች ሲደበደቡ፣ ክብራቸው ሲዋረድ እንመለከታለን፡፡ ፍ/ቤት በነበረው ሂደትም ዳኛ፣ አቃቤ ህግ ባለበት ፖሊስ ከእነ ሙሉ ትጥቁና ክላሽንኮቭ መሳሪያው ገብቶ ነው የሚጠብቀው፡፡ ይሄን መታዘብ ይቻላል። እንግዲህ እስር ቤት ብዙ ነገር ይፈፀማል፤ ነገር ግን ያንን እያወራን ነገ በቆራጥነት በሚደረግ ትግልና ታጋይ ላይ ሃዘኔታ እንዲያድርበት ማድረግ አያስፈልግም፤ ስለዚህ እኛ የምንከፍለው ዋጋ መከፈል ያለበት ነው፡፡ ዝም ብሎ አየር ላይ የሚመጣ ነፃነትና መብት የለም፡፡ ዓለም ላይ የተደረጉ የነፃነትና የመብት ትግሎች ዋጋ ሳያስከፍሉ፣ ዝም ብለው ፍሬ አላፈሩም፡፡ እኔ ተምሬያለሁ፤ ራሴን ልለውጥበት የምችልበት ብዙ ምቹ ሁኔታዎች አሉኝ፤ የትም ሀገር ሄጄ መስራት እችላለሁ፡፡ ግን ነገስ? … ሃገር፣ ማንነት የሚባል ነገር አለ፡፡ እነዚህን ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ የሚከፈለውን ከፍዬ መታገል እንዳለብኝ አምኜ ነው የምታገለው፡፡ ሰላማዊ ትግል የሚደረገው መከራን፣ ሰቆቃን ለማስቀረት ነው፤ ይሄን ለማስቀረት ደግሞ መከራ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
ብዙ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ለእስር መዳረጋቸው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በእስርህ ወቅት ምን ታዘብክ?
አሁን ከተፈታነው በእጥፍ የሚበልጥ “የፖለቲካ እስረኛ” አሁንም በየእስር ቤቱ አለ፡፡ በግንቦት 7፣ በኦነግና በሌላም ሰበብ የታሰሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነሱን ትተን ነው የወጣነው፡፡ በዚህም ዛሬ ከእስር የወጣነው የህሊና እረፍት የለንም፡፡ እኔ ከብዙዎቹ ጋር ለመማማር ሞክሬያለሁ፡፡
በእስር ላይ ያሉ ሰዎች “አንድ ቀን እንወጣለን” ብለው ተስፋ ያደርጋሉ?
አዎ! አብዛኞቹ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ብዙዎቹ ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችሉ ናቸው። ህሊናቸው ንፁህ ነው፡፡ ከቂም በቀል የፀዱ ናቸው። የሀገሪቱን ሁኔታ የምትፈራው ማረሚያ ቤት ያለውን ሁኔታ አይተህ ስትወጣ ነው፡፡ በማረሚያ ቤቶቹ ያለው የፖለቲካ እስረኛ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በሌላ ወንጀል ተፈርዶበት ወደ ማረሚያ ቤቱ የገባው ሌላው ታራሚ፣ ሳይወድ በግዱ የገባበትን ጉዳይ ረስቶት ለስርአቱ እየተፈጠረበት ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ አሸባሪ ተብለው ታስረው የሚያያቸው ሰዎች፣ ቀርበው ሲረዷቸው በጣም ጤናማ፣ ለሰው ልጅ መልካም አሳቢ ሆነው ስለሚያገኛቸው፣ ንፁሃን መሆናቸውን ሲያውቁ ይረበሻሉ፡፡ ከብዙዎቹ የፖለቲካ እስረኞች ጋርም ሀገራችንን እንዴት መልካም ማድረግ እንደምንችል እንወያይ ነበር፡፡
በምን ሁኔታ ነው ከእስር የተፈታኸው?
የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች አፈታት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ግልፅነት የለውም፡፡ ሁሉንም ሰዎች ለምን እንዳላካተተ እንቆቅልሽ ነው የሆነብኝ። ከኋላዬ ትቻቸው የወጣሁ እስረኞች፣ ህሊናዬን እረፍት ይነሱኛል፡፡
የይቅርታ ደብዳቤ ፈርም አልፈርምም የሚል ውዝግብም ተፈጥሮ ነበር?
አዎ! ይቅርታ ፈርም አሉ፤ አልፈርምም አልኳቸው። መልሰው ሌላ ደብዳቤ ይዘው መጡ። ደብዳቤው፤ “በ5 ዓመት ውስጥ ካጠፋሁ እታሰራለሁ” የሚል ነበር፡፡ እኔ ይሄን አይቼ አላውቅም፡፡ ገደብ የሚወስነው ፍ/ቤት ነው፤ ስለዚህ ይሄ ኢ-ፍትሃዊ ስለሆነ ሃሳቡን አልቀበልም አልኳቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ተለይቼ ቀርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ሊያነጋግሩኝ ሞክረዋል ግን አልሆነም። በቃ የቀረኝ ጊዜ ከሁለት ወር ያነሰ በመሆኑ መደበኛ የእስር ጊዜዬን ለመጨረስ ወስኜ ባለበት ሰዓት፣ ድንገት ሳላስበው፣ ሰኞ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ጠዋት እንቅስቃሴ እያደረግሁ ሳለ፤ “ና እቃህን ይዘህ ውጣ” ተባልኩ፡፡ በዚያ መልኩ ነው ከእስር ቤት የወጣሁት፡፡ ድንገት ነው፤ ብቻዬን ነው የወጣሁት፤ ቤተሰቦቼ አያውቁም፣ በዕለቱም አድማ ስለነበር ትራንስፖርት እንደማይኖር አውቅ ነበር፡፡ ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ፈቅዶ፣ በዕለቱ ከቤተሰቦቼ ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡
ከዚህ በኋላም ለሃገሬ ማድረግ ያለብኝን ሁሉ ለማድረግ ነው ሃሳቤ፡፡ በትግል ነው የታሰርኩት፤ ለትግል ነው የተፈታሁት፡፡
አንተ ከመታሰርህ በፊት የነበረውን የሀገሪቱን ሁኔታና አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ታየዋለህ?
አስተዋይ መሪ ቢኖረን አሁን ባለንበት አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ምናልባትም ለሁሉም አካል ለሀገሪቷም የተሻለውን ውሳኔ ሊወስድ ይችላል፡፡ አሁን ያ አለመሆኑ ያስፈራኛል፡፡ እንደሚታወሰው በ97 የነበረው ሁኔታ ደረጃ በደረጃ አድጎ የመጣ ነበር፡፡ ይሄኛው ግን በድንገት የገነፈለ ነገር ነው፡፡ በ97 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፤ አሁን ደግሞ ትግሉን ህዝቡ ነው የራሱ ያደረገው። ፓርቲዎች በአደባባዩ ላይ የሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ እንደ ጥያቄ ቢቀበላቸውም፣ ጥያቄዎቹን የመመለስ ቁርጠኝነት የለውም፡፡ ቁርጠኝነቱ የሌለው ደግሞ እርስ በእርሱ ባለመስማማቱ ወይም በማንአለብኝነት ሊሆን ይችላል፡፡ ተቃዋሚዎችንም የማዳከም ስራ ይሰራል። ከዚህ አንጻር መንግስት ምን እንደሚፈልግ አልታወቀም፡፡ አሁን ያለነው አጣብቂኝ ውስጥ ነው። በዚህ መሃል መልካም አጋጣሚው ግን የህዝቡ አስተውሎት የተሞላበት እንቅስቃሴ ነው። በዚህ መሃል ምናልባት የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል። ይሄ ሁኔታ በአግባቡ ካልተያዘ ግን አጠቃላይ የሀገሪቱን ህልውና ሊፈታተን የሚችል ነገር ሊመጣም ይችላል፡፡
ከዚህ አጣብቂኝ እንዴት መውጣት የሚቻል ይመስልሃል?
ምናልባትም ድርድር አድርጎ ስልጣን ማጋራት፣ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሊሆን ይችላል፤ አማራጩ። ወሳኙ ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ድርድር ማድረግ ነው፡፡ በድርድር የምርጫ ሁኔታን ማስተካከል ይቻላል፡፡

 

Read 1388 times