Tuesday, 13 March 2018 13:21

አነጋጋሪው የአኵስም ጽዮን ሙዚየም ግንባታ ሊጀመር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለ 5 ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል

የሕንፃ ግንባታው ለአምስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ ለማስጀመር፣ የ160 ሚሊዮን ብር አዲስ ውል ተፈረመ፡፡
ጨረታውን በአዲስ መልክ በማውጣት፣ ባለፈው የካቲት 12 ቀን የግንባታ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና አሸናፊ የሆነው ተቋራጭ ድርጅት የስምምነት ውል ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ከድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ተክለ ሃይማኖት አስገዶም ጋር በመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት አዳራሽ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በመተማመን ያስጀመሩት ይህ ታሪካዊ ቤተ መዛግብት፣ የኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት ነው፤” ብለዋል፤ ለፍጻሜውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የቤተ ክርስቲያን አካላት እያንዳንዳቸው ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል፡፡
ቤተ መዘክሩን ለማጠናቀቅ 160 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ሙዚየም ግንባታ፣ በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ በቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ይፋ የተደረገ ቢኾንም፤ እስከዛሬ የግንባታው ሒደትና ወጪ አነጋጋሪ ሆኖ መዝለቁ ታውቋል፡፡
በአንድ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የሆነው “ዜና ቤተ ክርስቲያን” ጋዜጣ፣ “ለግንባታው ፕሮጀክት በውጭ ምንዛሬ 8.9 ሚሊዮን ዮሮ እና 25 ሚሊዮን ዶላር፣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ደግሞ ከ200 ሚሊዮን እና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ” ወጪዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሰ ሲሆን፣ የወጪው መጠን መለያየት በፕሮጀክቱ ላይ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ሲያስነሣ ቆይቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ለሙዚየሙ ግንባታ ርዳታ ለማሰባሰብ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ላለፉት 6 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ ቢሆንም፤ በሙዳየ ምጽዋት የታቀደውን ያህል ገንዘብ በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እስከ አሁንም የተሰበሰበው ገንዘብ ከ25 ሚሊዮን ብር ያልበጠ እንደኾነ የጠቆሙት ምንጮች፤ መሠረቱ ወጥቶ የቆመው ግንባታ ከተቋረጠም አምስት ዓመት ማስቆጠሩን ጠቁመዋል፡፡ “ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁበት ብረቱ እየዛገ፣ ብሎኬቱ እየፈራረሰ ነው፣” ይላሉ ምንጮቹ፡፡
በሌላ በኩል ዩኔስኮ፣ “የሙዚየሙ ሕንፃ ዲዛይን መካነ ቅርሱን የሚሸፍን መኾን የለበትም፤” በሚል ማሻሻያ እንዲደረግበትና ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችም ከመካነ ቅርሱ (ሐውልቱና የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን) መልኮች ጋር እንዲጣጣሙ ማሳሰቡን ምንጮቹ አክለዋል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ትብብር፣ የዲዛይኑ ማሻሻያ ተደርጎ ለዩኔስኮ ከተገለጸና ከተፈቀደ በኋላ ጨረታው ወጥቶ የግንባታው ውል እንደ አዲስ መፈረሙን አስረድተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ አስተዋፅኦውን የሚያስተባብረው ኮሚቴም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንደ አዲስ ተዋቅሮ በሥራ አስኪያጅ እንዲመራ የተደረገ ሲኾን፣ በሙዳየ ምጽዋት የሚሰበሰበው ርዳታም እንደ አድባራቱ የገቢ አቅም ወደ “ቁርጥ መዋጮ” መዞሩ ታውቋል፡፡
የ“ቁርጥ መዋጮው” ድልድል፣ በአድባራት በቂ ውይይት አልተካሔደበትም፤ ያሉት ምንጮቹ፣ ይህም የተፈለገው አስተዋፅኦ እንዳይገኝ ዕንቅፋት እንዳይሆን ስጋታቸው ገልጸዋል፤ የአድባራቱን አስተዳደር የማሳመን ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግና ቀድሞውንም በቂ ገንዘብ ሳይያዝ በተለጠጠ በጀት ግንባታውን መጀመሩ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ለቁጥጥርም ስለሚያዳግት ሊታረም ይገባል፤ ብለዋል፡፡

 

Read 1444 times