Tuesday, 13 March 2018 13:13

“ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል?” ቢሉት ሲያስብ ዘገየ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

አንድ በወታደሮች ካምፕ የመዝናኛ ክበብ ዙሪያ የተፃፈ ሐተታ የሚከተለውን ቀልድ ነጥቧል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ የመኮንኖች ክበብ ውስጥ ከተራ ወታደር እስከ ጄኔራሎች ድረስ እየተዝናኑ ሳሉ፣ የዕንቆቅልሽ መሰል ጥያቄና መልስ ተጀመረ፡፡
የጨዋታ መሪው፤
“ለመሆኑ ወሲብ (የአልጋ ላይ ግንኙነት) ስንት ፐርሰንቱ ፍቅር ነው? ስንት ፐርሰንቱስ ሥራ ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
መኮንኖቹ እንደየ ማዕረግ ደረጃቸው ይመልሱ ጀመር፡-
ጄኔራሉ:- “ዘጠና ከመቶው ፍቅር፣ አሥር ከመቶው ሥራ ነው” አሉ፡፡
ኮሎኔሉ፡- “በእኔ ግምት ሰማኒያ ከመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሃያ ከመቶው ሥራ ነው፡፡” አሉ፡፡
ሻለቃው ቀጠሉ፡- “ለእኔ እንደሚሰማኝ ደግሞ ወሲብ ሰላሳ በመቶው ሥራ፤ ሰባ በመቶው ፍቅር ነው”
ሻምበሉ ደግሞ፤
“እኔ በበኩሌ አርባ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ፡፡ ስልሳ በመቶው ግን ፍቅር ነው፡፡”
መቶ አለቃው ጥቂት ስሌት ሠርተው፤
“እኔ ደግሞ ወሲብ ሃምሳ በመቶው ፍቅር፣ ሃምሳ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ”
አለ፡፡
ሃምሳ አለቃው ተነሳና፣
“የእኔ ከሁላችሁም ይለያል፡፡ ወሲብ አርባ በመቶው ፍቅር፤ ስልሳ በመቶው ሥራ ነው” አለ፡፡
አሥር አለቃው፤
“ሰላሳ በመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሰባ በመቶ ደግሞ ሥራ ነው” አለ፡፡
ይሄኔ ተራ ወታደሩ እጁን አወጣ፡፡
ዕድል ተሰጠው፡፡
“እኔ ከሁላችሁም አልስማማም፤ ለእኔ ወሲብ መቶ በመቶ ፍቅር ነው” አለ፡፡
ጄኔራሉም፣ ኮሎኔሉም፣ ሻለቃውም አጉረመረሙ፡፡
“እኮ ምክንያትህን አስረዳና?” አሉት፡፡
ተራ ወታደሩም፤
“ጌቶቼ፤ ወሲብ ሥራ ቢኖርበት ኖሮ ለእኛ ትተውልን ነበር!”
* * *
አስተሳሰባችን የልምዳችን፣ የትምህርታችን የተፈጥሮአችን ተገዢ ነው፡፡ ልምዳችን የቅርብ የሩቁን የማስተዋልና በትውስታችን ቋት ውስጥ የማኖር ውጤት መዳፍ ሥር ያለ ነው፡፡ ትምህርታችን ትምህርት የሚሆነው ወደ ዕውቀት መለወጥ ሲጀመር ነው! ዕውቀታችን ወደ የብልህ-ጥበብ (wisdom) የሚለወጠው አንድም በዕድሜ፣ አንድም የሚዛናዊ አመለካከት ባለቤት ስንሆን ነው! ሚዛናዊነት የጎረኝነት (Positionality) ተቃራኒ ነው፡፡ የወገናዊነት ፀር ነው! ወገናዊነት የኢ-ፍትሐዊነት መቆፍቆፊያ ሰንኮፍ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት ከማናቸውም ህገ-ወጥ ድርጊት ጋር፤ አንዱን-ሲነኩት-ሌላው ይወድቃል ዓይነት ግንኙነት አለው፡፡ (Domino-effect እንደሚባለው፡፡) ለችግሮች የምንሰጠው አጣዳፊ መፍትሔዎች ወዴት ያደርሱናል? ብሎ መጠየቅ ትልቅ መላ ነው፡፡ “የፊተኛውን ባልሽን በምን ቀበርሽው- በሻሽ፤ ለምን- የኋላኛው እንዳይሸሽ” የሚለውን ማውጠንጠን አለብን፡፡ በየለውጡ ውስጥ የአንድ የአገራችንን ገጣሚ ስንኞች ሥራዬ ብሎ ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡-
“ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ከምሮ እየናደ፣ ንዶ እየከመረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ
ጀመረ”
መውጫ መውረጂያችን በሥጋት የታጠረ ከሆነ፤ ከመረጋጋት ጋር እንራራቃለን፡፡ ያለ ሥጋት የምንጓዘው ለህሊናችን ታማኝ የሆንን እንደሆነ ነው! በስሜታዊነት ምንም ዓይነት ድርጊት መፈፀም የለብንም፡፡ ፅንፈኛ ሆነንም ማሰብ የለብንም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አሉታዊነትን
(Negativism) በፍፁምነት ማስወገድ አለብን፡፡ ለረዥም ጊዜ ሰቅዞ የያዘንን ሁሉ፣ በተቃውሞ በጋራ ከመጠርነፍ ዕምነት የግድ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ ነጋዴውን ሌባ ነው ብሎ አስቦ መጀመር፣ ባለሙያውን ከእኛ ጋር ካልሆነ ባለሙያ አይደለም ብሎ ማሰብ፣ ሰውን አላግባብ መፈረጅ፤ የእኔ ቦይ ውስጥ ካልፈሰስ የተሳሳተ ሰው ነው ብሎ መገምገም… እኒህና እኒህን መሰል አካሄዶች ሁሉ ከፀፀት አያፋቱንም!
ዛሬም ነገረ-ሥራችንን እንመርምር፡፡ ማህበረሰብ ለአመክንዮ እንጂ ለመላምት/ለግምት መጋለጡ ደግ አይደለም፡፡ ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ አሊያም ፓርቲያዊ ግልፅነት (Transparency) ወደድንም ጠላንም አስፈላጊ ነው! አለበለዚያ ዳፍንተኝነት (Obscurantism) ይወርረናል፡፡ ህብረተሰብ የሀገሪቱ አካሄድ ውሉ እንዳይጠፋበት ማድረግ ያለበት አመራሩ ነው፡፡ አመራር ተመሪውን አይከተልም፡፡ ያ ከሆነ ጭራዊ እንቅስቃሴ ወይም የድሃራይ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል- Tailist movement እንዲል መጽሐፍ፡፡ ደራሲ በተደራሲ ከተመራ፣ ገጣሚው በአጨብጫቢ-ታዳሚ ከተመራ፣ ዋናው ባለሙያ በበታቹ ተፅዕኖ ውስጥ ከወደቀ፣ መሪው በተመሪው እጅ ከተያዘ የመንተብ- decadence አንድ ድረጃ ነው! ከዚህ ተከትሎ ምርጫ ማጣት ይመጣል፡፡ የሚፈልገው ነገር ሁሉ ጭጋግ ውስጥ ይወድቅና አጥርቶ ማየት ይሳነናል፡፡ የቱን ልያዝ ዓይነት ድንግዝግዝ ውስጥ እንጨፈቃለን፡፡
ያኔ ነው እንግዲህ “ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል?” ቢባል ሲያስብ ዘገየ፤ የሚለው ተረት ጎልቶ የሚነበበው! ከዚህ ይሰውረን!!

 

Read 6872 times