Tuesday, 13 March 2018 13:10

‘ዶክተሩ’ እና ‘ታካሚው

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
(ታካሚው ዶክተሩ ዘንድ ይቀርባል፡፡)
ሀኪም፡— ጤና ይስጥልኝ፣ ቁጭ በል፡
ታካሚ፡— ጤና ይስጥልኝ ዶክተር፡፡
ሀኪም፡— አይዞህ፣ ዘና በል፡፡ እስቲ ምንህን እንደሚያምህ አስረዳኝ፡፡
ታካሚ፡— ዶክተር፣ ዶክተር ምን የማያመኝ ነገር አለ! የቱን ነገሬህ የቱን ልተወው! የማያምህን ንገረኝ ብትለኝ ይሻለኝ ነበር፡፡
ሀኪም፡— ግዴለም፣ ቀስ ብለህ ምን እንደሚሰማህ፣ የትኛው የአካል ክፍልህን እንደሚሰማህ ንገረኝና መፍትሄ እናገኝለታለን፡፡
ታካሚ፡— ራሴን ዶክተር፣  ራሴ በቃ የእኔ አይመስለኝም፡፡ የሌላ ሰው ጭንቅላት በውሰት የተከሉልኝ ነው የሚመስለኝ…ብቻ ቀን ከሌት ለደቂቃ እረፍት አይሰጠኝም ነው የምልህ፣ ዶክተርዬ!
ሀኪም፡— እሺ ዘርዝረህ ንገረኛ፡፡
ታካሚ፡— በአንድ ወገን ይጀምረኝና… ብቻ እየተንደረደረ፣ እየተንደረደረ፣ ምን አለፋህ… ይዞረኛል፣ ይሽከረከረኛል ነው የምልህ! ዶክተር ንገረኝ ካልከኝ እንደው ጭንቅላቴ የስታዲየም የሩጫ ሜዳ የሆንኩ ነው የሚመስለኝ፡፡
ሀኪም፡— አሁንም እኮ እንዴት እንደሚያምህ፣ የሚሰሙህን ስሜቶች አላስረዳኸኝም…ራስ ምታት ብቻ ነው? ያዞርሀል?
ታካሚ፡— ያዞርሀል ብቻ፣ ዶክተር! ያዞርሀል ብቻ! ይሽከረክረኛል ነው የምልህ…ሲፈልግ ደግሞ ዶማውን፣ መዶሻውን፡ ዲጂኖውን ሰብስቦ ይፈልጠኛል፣ ይፈረክስኛል…
ሀኪም፡— ግዴለም…ቀለል አድርገህ አስረዳኝ፡፡ እንዴት ነው የጀመረህ?
ታካሚ፡— ምክንያቱን ማለትህ ነው ዶክተር?
ሀኪም፡— ምክንያቱን ታውቀዋለሀ እንዴ?
ታካሚ፡— አንዴት አላውቀው ዶክተር፣ እንዴት አላውቀው!
ሀኪም፡— በእርግጥ ታውቀዋለህ?
ታካሚ፡— የሚያንገበግበኝ እኮ እሱ ነው፡፡ ማወቄ ነው እኮ የሚያብሰለስለኝ!
ሀኪም፡— እስቲ ንገረኛ…ለመሆኑ መቼ ነው የጀመረህ?
ታካሚ፡— ዶክተር እሷን ጥያቄ እለፈኝ…
ሀኪም፡— ለምን፣ ምንም አይነት የጤና እክል ቢሆን እኮ መቼ እንደጀመረ ካላወቅን አስፈላጊውን ህክምና ለማድረግ ትንሽ ያስቸግራል፡፡ ሁለት ሦስት ሳምንት ይሆናል?
ታካሚ፡— ዶክተር! ዶክተር! እኔ የጀመረኝ በካላንደር ካልሆነ ማስረዳት ያስቸግራል…ብዙ ዘመን ሆኗል፡፡
ሀኪም፡— ነ…ው!  እሺ ይሁን፣ ምክንያቱ ምንድነው?
ታካሚ፡— ምክንያቱማ ዶክተር፣ ምክንያቱማ በአጠቃላይ ሰው… ሰው የሚባል ፍጡር፣ በተለይ ደግሞ ይሄ ስልጣን ላይ ተቀመጦ፣ ዳሌውን አስፍቶ…
ሀኪም፡— ቆይ! ቆይ! ቆይ! ይኸውልህ ስለ በሽታህ እናውራ፡፡
ታካሚ፡— ስለ በሽታዬ እኮ ነው ያወራሁት ዶክተር። እንዲህ የሚያደርገኝ ሰው እያልኩህ እኮ ነው
(ዶክተሩ የሆነ ቀይ መብራት ሳይበራበት አልቀረም።)
ሀኪም፡— እሺ ለእሱ ምርመራዎች አዝልሀለሁ…ሌላስ የሚያምህ አለ?
ታካሚ፡— ሌላማ ሆዴን ነው የሚያመኝ ዶክተር፡፡
ሀኪም፡— ሆዴን ስትል… እንዴት ያደርግሀል?
ታካሚ፡— ዶክተር፣ ዶክተር እንደው ፈጣሪ ያሳይህ የእኔም ሆድ፣ ሆድ ሆና በሽታ ይላክባታል! ከእነ መኖሯ አይደለም ሌላው፣ እኔ የማላውቃት ሆዴ በሽታ ይላክባታል!
ሀኪም፡— ቁርጠት ነው?
ታካሚ፡— ቁርጠት በለው፣ ግዝገዛ በለው፣ ጭቅጨቃ በለው…
ሀኪም፡— የቱ አካባቢ እንደሆነ ልታሳየኝ ትችላለህ…
ታካሚ፡— ዙሪያውን ዶክተር፣ ዙሪያውን! ዶክተር የአዲስ አበባ መንገዶች ሲቆፈሩ አይተህ አታውቅም
ሀኪም፡— አይቻለሁ…
ታካሚ፡— እንዴት ትርምስምሱን እንደሚያወጡት አይተሀል አይደል!
ሀኪም፡— አይቻለሁ አልኩህ እኮ!
ታካሚ፡— በቃ የእኔ ሆድ ማለት የአዲስ አበባ መንገድ በለው፡ ይቆፈራል፣ ይቆፈራል…
ሀኪም፡— ይቅርታ፣ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…
ታካሚ፡— ደስ ይለኛል፣ ዶክተር፡፡
ሀኪም፡— ባለ ትዳር ነህ?
ታካሚ፡— ዶክ...ዶክተ…
ሀኪም፡— ይቅርታ፣ መጠየቅ አልነበረብኝም መሰለኝ
ታካሚ፡— እንደሱ ሳይሆን ዶክተር፣ እንደሱ ሳይሆን…
ሀኪም፡— መመለስ የለብህም፣ ወደ ጉዳያችን እንመለስ…
ታካሚ፡— ዶክተር ምን መሰለህ፣  ለበሽታዬ አንዱ ምክንያት፣ አንዱ ምክንያት…
ሀኪም፡— ግዴለም፣ እሱን ተወውና ሆዴን ላልከኝ ስለሚሰማህ ስሜት በደንብ አስረዳኝ…
ታካሚ፡— ዶክተር፣ መናገር ስለምፈልግ ነው…እንዳልከው ትዳር ነበረኝ…
ሀኪም፡— እሱ አሁን አስፈላጊ አይደለም…
ታካሚ፡— ዶክተር፣ የእኔ በሽታ ሰው ነው ብዬህ የለም፣ ሚስቴን ነጠቁኝም፣ አስነጠቁኝም…
ሀኪም፡— አሀ፣ ተለያይተሀል ማለት ነው?
ታካሚ፡— አልተለያየሁም፡፡
ሀኪም፡— አልገባኝም፡፡
ታካሚ፡— ዶክተር፣ ሚስቴ ቤቴ ሆና፣ ከአንድ ማእድ እየበላን፣ ጎን ለጎን እየተኛን፣ ከእኔ ጋር አይደለችም…
ሀኪም፡— ምን መሰለህ፣ ሌሎች ታካሚዎች ስለሚኖሩ ጊዜ ላይበቃን…
ታካሚ፡— ጊዜህን አልወስድብህም ዶክተር፣ ሚስቴን አንድ ባለጊዜ ወሽሞብኛል…ያውልህ ጉዱ ዶክተር፣ ያውልህ ጉዱ!
ሀኪም፡— እሺ ወደ ጉዳያችን…
ታካሚ፡— ዶክተር አንዱ በሽታዬ አቅም ማጣቴ…ሚስቴን ይውሰዱብኝ
ሀኪም፡— ግዴለም አሁን ምርምራዎች አዝልሀለሁ…ከዛ ውጤቱን እናይና በፍጥነት የሚያሽሉህ መድሀኒቶች አዝልሀለሁ…
ታካሚ፡— ዶክተር…መች በሽታዬን ነግሬህ አጋመስኩና! ገና ምኑን ሰምተህ!
ሀኪም፡— ግዴለም…መጀመሪያ እነኚህን ምርመራዎች አድርግና ውጤቱን እያየን ደረጃ በደረጃ እናየዋለን፡፡
ታካሚ፡— ካልክ ይሁን ዶክተር…
ሀኪም፡— እሺ፣ ምን አናድርግ መሰለህ…የሽንት፣ የሰገራና የደም ምርመራ ይደረግልሀል፡፡
ታካሚ፡— አይ ዶክተር! አይ ዶክተር! እንዲሀ ቆመህ ስታየኝ ሰው መስዬሃለሁ፡፡
ሀኪም፡— አታስብ፣ ችግሩን አውቀን እንዲሻልህ ልናደርግ እኮ ነው…
ታካሚ፡— ዶክተር፣ ደም ምርመራ ነው ያልከኝ! ዶክተር፣ መጀመሪያ ነገር ምን ደም ተረፈኝና! ምን ደም ቀረኝና! በደም ስሬ ውስጥ እኮ ውሀ ነው የሚመላለሰው…
ሀኪም፡— ለምርመራ ያህል አይጠፋም…
ታካሚ፡— ከስንቱ ያቆራረጠኝ እኮ ደሜ ነው፣ ዶክተር!
ሀኪም፡— አ…አልገባኝም፡፡
ታካሚ፡— በየሄድኩበት “ደምህ ምን አይነት ነው?”  “ደምህ ከየት ነው? ከሰሜን ነው? ከደቡብ ነው? ከምዕራብ ነው? ከምስራቅ ነው?” እያሉ አይደል እንዴ በሽታ በበሽታ ያደረጉኝ!
ሀኪም፡— አሀ፣ እንደሱ ለማለት ፈልገህ ነው!…ግዴለም እኛ ዘንድ ደም ሁሉ እኩል ነው፡፡ (ይስቃል)
ታካሚ፡— እሱንማ አውቃለሁ፣… ይቅርታ ዶክተር፣ ጨቀጨቅሁህ፡፡
ሀኪም፡— ምንም ይቅርታ አያስፈልግም፣ ሥራዬ አይደል እንዴ…
ታካሚ፡— ዶክተር አሁን፣ አሁን ደግሞ በየሬድዮኑ፣ በየቴሌቪዥኑ የምሰማው ወሬ ያዞረኛል፣ ያንዘፈዝፈኛል…
ሀኪም፡— ግዴለም፣ እሱን በሁለተኛ ዙር ምርመራ ትነግረኛለህ…
(ታካሚም ደሙ ውስጥ ምን፣ ምን እንዳለ ለመለየት ወደ ላቦራቶር ሄደ፡፡ በልቡም ሆነ አፍ አውጥቶ “ደሞች ሁሉ እኩል ናቸው!’ የሚል መፈክር ለማሰማቱ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡)
ደህና ሰንብቱልኝማ! 

 

Read 2904 times