Sunday, 04 March 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

  “ለሱ ብላክ ሌብል … ለኔ ብላክ ሊስት”
               
    ሰውየው ጥጋበኛ ነው፡፡ ግማሽ ጠርሙስ ብላክ ሌብል እንደ ጨለጠ በውስጡ ያንቀላፋው አውሬ ተገላበጠ፡፡ አስተናጋጁን አስር ጊዜ እየጠራ፣ በውሃ ቀጠነ መከራውን ያሳየው ጀመር፡፡ አስተናጋጁ ቢቸግረው … “ጌታዬ፤ ሌላ ሰው ልጥራሎትና ያስተናግድዎ…” አለው፡፡ አቶ ጥጋቡ የበለጠ በሸቀ፡፡ በአስተናጋጁ ላይ እየዛተ፤
“ብላክ ሊስት ውስጥ እንደገባህ እወቅ” … በማለት አስፈራራው፡፡ …
አስተናጋጁ … አንገቱን ደፍቶ፣ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ እንዳጣመረ፣ እጅ ነስቶ ዞር አለ፡፡ …
ዕድሉን እያማረረ፣ ዕንባውን ጠብ እያደረገ፣ ወደ ውጭ ወጣ፤ ሰማይ ሰማዩን እያየ፡-
“ምነው አምላኬ፤ ምን አጥፍቼ ነው? … ለሱ ብላክ ሌብል፤ ለኔ ብላክ ሊስት ያዘዝክልኝ?” በማለት ሲነጫነጭ የግዜር መንፈስ ወደ ጆሮው ተጠግቶ፡-
“ለሰው ፍርድ አትጨነቅ፣ ሰውየው በኔ ብላክ ሊስት ከሰፈረ ቆይቷል” አለው፡፡
እግዜር እውነቱን ነበር፡፡ አቶ ጥጋቡ አላወቀም እንጂ የማይድን ህመም በሰውነቱ ውስጥ ተተክሏል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲመረመር ለመኖር የቀረው ዘጠኝ ወራት ብቻ ነበር፡፡
…“የግዜሩ በለጠ!!” ይላሉ … እንዲህ አይነት ነገር የገጠማቸው፡፡ … “የራሷን ቂጥ ዞራ ማየት ያልቻለች ዝንጀሮ፤ በጓደኞቿ ትስቃለች” የሚባለውም የዚሁ ቢጤ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ከአቅምህ በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ ስለ ምን ሌሎችን ሰዎች ታስከፋለህ? … ቆም ብለህ ብታስብ … የሌሎች መከፋት በዋናነት የሚጎዳው አንተን ራስህን ነው፡፡ ሆን ብለህ አድርገኸው ቀርቶ በአጋጣሚ ወይም በስራ ሰበብ ሌላውን ሰው በድለህ ካልተሰማህ ወይም ካልተፀፀትክ ጤነኛ አይደለህም፡፡
“መጥፎ ዜና፤ ለነጋሪው እንኳን አይመችም፡፡ “Bad news affects the teller” … የሚለን ሼክስፒር … ስድብና ማስፈራራት ሲሆንበት እንዴት ይታዘበን ይሆን?
አርስቶትል መልካምና ቅን ስነ ምግባርን ዩዲሞኒያ (eudaimania) በማለት ይጠራዋል፡፡ ሲያብራራውም፡-
“ዞሮ ዞሮ የመኖር ወይም የዕውቀትና የጥበብ ዓላማ ደስታ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ደስታን ይሻል፡፡ ደስታ ደግሞ ከመልካም ተግባር የሚመነጭ ነው፡፡” በማለት ነው፡፡ (All knowledge and every persuit aims at some good, … what is the highest of all goods achievable by action? … it is happiness, they identify living well and doing well with being happy”
*       *     *
የሞራል ፍልስፍና (Morality) አካል ከሆኑት ሁለት የተለያዩ ግብረሰቦች (Egoism and Alturism) አንደኛው ሌሎችን ማስቀደም (altruism) የሚለው እሳቤ ነው፡፡ አልትሩይዝም ባጠቃላይ፤ “የሌሎችን ሰዎች ፍላጎት እናስቀድም፣ ሌሎችን አስቀደመን ማለት ሌሎች እኛን አስቀደሙን እንደማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ራሳችንን መጉዳት አይደለም፡፡ የሌሎችን ፍላጎት አለመቃወም ወይም በመንገዳቸው ላይ አለመቆም ማለት እንጂ፡፡” … ይለናል፡፡
አልትሩይዝም ምንም እንኳ የጎላ ልዩነት ባይኖራቸውም ሳይኮሎጂካል አልትሩይዝም  (Psycological altruism) እና ኤቲካል አልትሩይዝም (Ethical altruism) በተሰኙ ሁለት ክፍሎች ይመደባል፡፡ … “ሰዎች እርስ በራሳቸው እንዲረዳዱ ተፈጥሯቸው ራሱ ያስገድዳቸዋል” በማለት የሚሞግተው የመጀመሪያው አስተሳሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ሰዎች የሌሎች ወንድሞቻቸውን ፍላጎት እንደራሳቸው ማሰብና መተጋገዝ አለባቸው” የሚል ቁም ነገር ይነግረናል፡፡ ለዚህም፡-
“ለራስህ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን አንተም ለሌሎች አድርግ፡፡” … የሚለውን ወርቃማ ህግ በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡
በነገራችን ላይ የኢጎኢዝም (ራስ ወዳድነት) እና አልትሩይዝም (ቅድሚያ ለሌሎች)ን ንፅፅር አስመልክቶ፣ በአንድ የፍልስፍና መጽሃፍ ላይ የአብርሃም ሊንከንን አጋጣሚ እንደምሳሌ አስቀምጦታል፡፡
ሊንከን ከጓደኛው ጋር በጨቀየ የገጠር መንገድ ሲጓዝ የጋሪውን ጎማ ጭቃ ይይዝበታል፡፡ እሱን እያላቀቁ ሳሉ አንዲት አሳማ ግልገሎቿን አግተልትላ፣ መንገዱን ስታቋርጥ፣ ግልገሎቿን ጭቃው ይይዝባታል፡፡ እናት አሳማ ግልገሎቿን ለማስለቀቅ ስትታገል የተመለከተው ፕሬዚዳንት፤ ወደዚያው ሄዶ፣ ግልገሎቹን ነፃ በማድረግ ይሸኛቸዋል፡፡ ወደ ጋሪው ሲመለስ ጓደኛው፡-
“ይሄ ሌሎቹን የማስቀደም፣ የደግነት ተግባር (አልትሩይዝም) መሆኑ ነው፡፡” ቢለው …
“በጭራሽ!” በማለት ነበር የመለሰለት፡፡
“ታዲያ ምንድነው?” … ሲለው …
“ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ለነሱ ሳይሆን … ለራሴ ስል ያደረግሁት!! እንደዛ እየተቸገሩ እያየሁ ዝም ብል ወይም አልፌአቸው ብሄድ ቀኑን ሙሉ አይመቸኝም፡፡ … የህሊና ሰላም፣ የመንፈስ ነፃነት አይኖረኝም” … አለው፡፡ … የሊንከን ሁኔታ፤ “ማናቸውም ሰው ግላዊ ፍላጎቱን ለመሙላት ወይም ስሜቱን ለማርካት ሲፈልግ ብቻ ነው ሌላው ደግ የሚውለው” ከሚለው የኢጎኢዝም ሁለት ክፍሎች (theses) የመጀመሪያ የሆነው ሳይኮሎጂካል ኢጎኢዝም (psycological egoism) ከሚያራምደው … (all acts are basically selfish) አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ይመስላል፡፡
የኢጎኢዝም ሁለተኛው ቴሲስ (Ethical egoism) ከመጀመሪያው የሚለይበት ቀጫጭን ምክንያቶች አንዱ፤ ሰዎች ቀና ማድረግ ካልፈለጉ፣ ያለማድረግ ምርጫ አላቸው፣ ይህ ሲሆን ግን ውስጣዊ ፍላጎታቸው ወይም ስሜታቸው የሚፈልገውን ማሳካት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ራስ ወዳድነትም ቢሆን የሚኖረው ሌሎች ሲኖሩ ነው፡፡” ባይ ነው፡፡
በፍቅር፣ በደግነት - በማስተዋል ለታነፅከው
ምስጋናና መልካም ምኞት ላንተ ይሁን ለቅኑ ሰው፡፡
ውብ ርህሩህ ሃሳቦችህ ካንደበትህ የፈለቀ፣
የብዙዎችን ቀን አበሩ ውሏቸውን አደመቁ፡፡
ለስንቱ ቀና ጎዳና - ብርሃን የሆኑለት ፋና፣
ያንተም ፀሐይ ጮራ ይውጣ - ዕድል በመንገድህ ይቅና
ዛሬና ትናንት ነገም - አንድ ነህና!!
ወዳጄ፡- ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን ስንመለስ… ያ ምስኪን አስተናጋጅ መንፈሱ ስለ አቶ ጥጋቡ ሹክ ስላለው ነገር እያሰበ በጣም በማዘኑ፣ እራሱን እንደ ጥፋተኛ ቆጠረው፡፡ ስራውን እንደ ጨረሰ በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው ቤተ እምነት ጎራ ብሎ ተንበረከከ፡፡ ለአቶ ጥጋቡ ምህረት እንዲወርድለት ፀለየለት፡፡ መልዕክቱ የደረሰው መንፈስም እንደ በፊቱ ወደ ጆሮው ተጠግቶ…
“ይኸ ነገር አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው እንደሚሉት አይሆንም ወይ? ቢለው … አስተናጋጁ፡-
“እባክህ ከኔ ዕድሜ አስር ዓመት ቀንሰህ ስጠው” በማለት አጥብቆ ለመነው፡፡ ይህን ሲሰማ ልቡ የተነካው መንፈስ፣ በአስተናጋጁ ርህራሄ እየተገረመ፤ “ሰው በመፍጠሬ ለካስ አልከሰርኩም” ሲል አሰበ፡፡
አስተናጋጁንም፡-
“ላንተ ስል ከጥቁር መዝገቤ ላይ ጨርሶ ብሰርዘው ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አጋጣሚ ሆኖ አንተ ዕድሜ ልትለምንለት ወደዚህ ስትመጣ፣ እሱ ወደ ቤቱ ሲሄድ መኪናው ተገልብጦ አልፏል” አለው፡፡
አስተናጋጁም ፍፁም ያልጠበቀው ነገር ድቅን ስላለበት በእጅጉ ደነገጠ፤ አዘነ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮም እዛው ቤተ እምነቱ ጊቢ ውስጥ በምንኩስና ለመኖር ወሰነ፡፡ እግዜር ደግሞ ወደ መኖሪያው ተመልሶ፣ ጥቁር መዝገቡን አወጣና፣ የጥጋቡን ስም ሰርዞ፣ የራሱን ስም ፃፈ!!
ሠላም!!

Read 975 times