Sunday, 04 March 2018 00:00

የቢል ጌትስ የምንጊዜም ተወዳጅ መፅሐፍ

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(2 votes)


    ማስታወሻ
አሜሪካዊው ቢሊዬነርና ችሮታ አድራጊው ቢል ጌትስ፤ በከፍተኛ የንባብ ፍቅራቸው ይታወቃሉ። የማይክሮሶፍት መስራቹ ባለፀጋ፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 50 መፃሕፍት ማንበባቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። (እኛ ዕድሜ ልካችንንም ላናነበው እንችላለን!) ደሞ ማንበብ ብቻ አይደለም፡፡ የወደዱትንና የመሰጣቸውን በ “Gates notes insider” ብሎጋቸው ላይ ለሌሎች ያጋራሉ፤ ያስተዋውቃሉ - የመፅሐፍ ቅኝት በመፃፍ፡፡
ባለፈው ጃንዋሪ መጨረሻ ላይ የ10 መፃህፍት ደራሲና የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ፕሮፌሰር የሆነው ስቲቨን ፒንከር የፃፈውን “Enlightenment Now” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ አንብበው፤ “አዲሱ የምንጊዜም ተወዳጅ መፅሐፌ” በሚል ርዕስ ለተከታዮቻቸው የመፅሐፍ ቅኝት (review) አጋርተዋል፡፡
ቢል ጌትስ የንባብ ልማዳቸውን አስመልክተው በቅርቡ ለTime ሲገልፁ፡- “ለእኔ በጣም ያዝናናኛል። ብዙ ሥራ እሰራለሁ፤ እናም እንደ ማበረታቻ ሽልማቴ ነው፡፡ ነገር ግን መጠንቀቅ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ያለዚያ አማዞን ወይም ኔፍትሊክስ ቪዲዮ መመልከት፣ የመፅሐፍ (ንባብ) ጊዜዬን ሊሰርቅብኝ ይችላል” ብለዋል፡፡
“Enlightenment Now” በተሰኘው መፅሐፍ ላይ የፃፉትን ቅኝት ከዚህ በታች ተርጉመን አቅርበነዋል፡፡
*       *      *
የስቲቨን ፒንከር “The Better Angles of Our Nature” በአሰርት ዓመት ውስጥ ካነበብኳቸው መፃህፍት ሁሉ ምርጡ መፅሐፍ ነው እያልኩ ለዓመታት ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ አንድ ሰው የሚያነበው አንድ መፅሐፍ ብቻ ጠቁም ብባል እሱን ብቻ ነበር የምጠቅሰው፡፡ ፒንከር በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ ሰላማዊ በሆነ ዘመን ላይ እየኖርን መሆናችንን ለማብራራት፣ ጥንቅቅ፣ ያለ ትክክለኛ ጥናት ተጠቅሟል፡፡ በዕድገት ዙሪያ እንዲህ ጥርትና ግልፅ ያለ ማብራሪያ አይቼ አላውቅም፡፡
አሁን ግን ስለ “Better Angles” ብዙ ማውራት እተዋለሁ፡፡ ወድጄ አይደለም፡፡ ፒንከር ራሱን በልጧል። “Enilghtment Now” የሚለው አዲሱ መፅሐፉ የሚደንቅ ነው፡፡
“Better Angles” በሚለው መፅሐፉ፤ በታሪኮች ውስጥ ጦርነትን ለመከታተል የተጠቀመበትን ዘዴ፤ በ“Enligment Now” የተከተለ ሲሆን በ15 የተለያዩ የዕድገት መለኪያዎች ላይ ተጠቅሞበታል (የኑሮ ጥራት፣ ዕውቀት፣ … ለመሳሰሉት) ውጤቱም፤ ዓለም እንዴትና ለምን የተሻለ የመኖርያ ሥፍራ እየሆነች እንደመጣች ሙሉ ስዕል ማቅረብ ነው፡፡
እኔ መፅሐፉን በጣም ስለወደድኩት በዝግታ ነው ያነበብኩት፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሰው በፍጥነትና በቀላሉ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡ ብዙ ሺ መረጃዎችን ቀልብ በሚስብ፣ አይረሴና ለመገንዘብ ቀላል በሆነ መንገድ ማጋራት ተሳክቶለታል፡፡
መፅሐፉ የሚጀምረው ወደ አብርሆተ - ህሊና ዕፁብ ሃሳቦች መመለስ እንደሚገባ በመሞገት ነው - ምክንያታዊነት፣ ሳይንስና ሰብዓዊነት እንደ ቅዱስ ፀጋዎች ይወደሱ ወደነበረበት ዘመን፡፡
እኔ ምክንያታዊነት፣ ሳይንስና ሰብዓዊነት የሚሉ ዕሳቤዎችን ሙሉ በሙሉ እደግፋለሁ፤ ነገር ግን በጣም ትኩረቴን የሳበው፣ እያንዳንዶቹን የዕድገት መለኪያዎች የሚፈትሹት 15 ምዕራፎች ናቸው። ፒንከር፤ ታሪካዊ አዝማሚያዎችን በመተንተንና ያለፈውን ጊዜ በአውድ ውስጥ ለማስቀመጥ መረጃ በመጠቀም ረገድ በእጅጉ ተዋጥቶለታል። በመፅሐፉ የሚያቀርባቸው ብዙዎቹ መረጃዎች ለእኔ እንግዳ አይደሉም - በተለይ ጤና እና ኤነርጂን በተመለከተ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱን ጉዳይ በጥልቀት ስለሚረዳቸው፣ የፈለገውን ጉዳይ ትኩስና አዲስ በሚመስል መልኩ ማቅረብ ሆኖለታል፡፡
የመጀመሪያ የመረጃ ምንጮች ውስጥ ጠልቆ ለመግባትና ያልተጠበቁ የዕድገት ፍንጮችን በርብሮ ለማግኘት ያለውን ትጋት (ፍቃደኝነት) አደንቃለሁ። እኔ አስደናቂ የድህነትና የህፃናት ሞት ቅነሳ ወደ መሳሰሉ ጭብጦች አዘነብላለሁ፤ ምክንያቱም እንደ ህብረተሰብ እንዴት ባለ ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ለመፈተሽ ማለፊያ መመዘኛዎች ናቸው፡፡ ፒንከር፤ እነዚህን ዘርፎች አንስቷቸዋል፡፡ በእነዚህ ብቻ ግን አልተወሰነም፤ ብዙ የማይታወቁ ርዕሰ ጉዳዮችንም ተመልክቷል፡፡
ከመፅሐፉ ውስጥ ዓለም እንዴት እየተሻሻለች እንደመጣች የሚያሳዩ አምስት በእኔ የተመረጡ (ተወደዱ) ማስረጃዎችን (መረጃዎችን) እነሆ፡-  
በመብረቅ አደጋ ተመታችሁ የመሞት አጋጣሚያችሁ በክፍለ ዘመኑ መገባደጃ ላይ ከነበረው በ37 እጅ ቀንሷል - ይሄም የሆነው ዛሬ የመብረቅ አደጋ በጣም ጥቂት በመሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም የተሻለ የአየር ሁኔታ የመተንበይ አቅም በማግኘታችን፣ የደህንነት ትምህርት በመሻሻሉና ብዙ ሰዎች በከተሞች ውስጥ ስለሚኖሩ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1920 ዓ.ም ልብሶችን ለማጠብ በሳምንት የ11 ሰዓት ተኩል ጊዜ ይፈጅብን የነበረ ሲሆን  በ2014 ዓ.ም በሳምንት ወደ 1 ሰዓት ተኩል ወርዷል፡፡ ከትልቁ የዕድገት ዕቅድ አንፃር ሲታይ፣ ይሄ ከጉዳይ የማይጣፍ ትንሽ ነገር ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የልብስ ማጠቢያ ማሽን መምጣት፣ ለሰዎች ትርፍ ጊዜ በመስጠት፣ የኑሮ ጥራትን አሻሽሏል - በአብዛኛው ደግሞ ሴቶች ሌሎች ህልሞችን እውን ያደርጉ ዘንድ አግዟቸዋል፡፡ የተገኘው ትርፍ ጊዜ በሳምንት ግማሽ ቀን ያህል ሲሆን መፅሐፍ ከማንበብ እስከ ፊልም መመልከትና አዲስ የንግድ ስራ መጀመር የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ለማከናወን ይውላል፡፡
ዛሬ በሥራ ላይ የመሞት አጋጣሚያችሁ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ በአሜሪካ በየዓመቱ ከሥራ ጋር በተያያዘ አደጋ 5 ሺ ሰዎች ይሞታሉ። እ.ኤ.አ በ1929 ዓ.ም ግን - የህዝብ ብዛቱ ከዛሬው በ40 በመቶ ያነሰ በነበረበት ወቅት፣ 20 ሺ ሰዎች በሥራ ላይ በሚያጋጥሙ አደጋዎች ሞተዋል፡፡ በዚያን ዘመን ሰዎች፤ በስራ ቦታ የሚያጋጥሙ ሞት የሚያስከትሉ አደጋዎችን፤ ቢዝነስን ለማከናወን የሚወጣ ወጪ አካል አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ዛሬ የተሻለ ዕውቀት ተቀዳጅተናል፤ እናም የብዙዎችን ህይወት ለአደጋ ሳናጋልጥ፣ ነገሮችን የምንገነባባቸውን ስልቶች ቀይሰናል፡፡
የዓለም አማካይ የአዕምሮ የማሰብ ችሎታ (IQ) በየአስር ዓመቱ በ3 ነጥቦች ገደማ እያደገ ነው፡፡ ለተሻለ የአመጋገብ ሁኔታና ንፅህናው ለተጠበቀ አካባቢ ምስጋና ይግባቸውና፣ የህፃናት አዕምሮ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እየዳበረ ይገኛል። ፒንከር በክፍል ውስጥና ከክፍል ውጭ ለሚደረግ ብዙ ጥልቅና ሂሳዊ አስተሳሰብም ዕውቅና ይሰጣል። የስልካችሁን የቤት ስክሪን በከፈታችሁ ወይም የምድር የውስጥ ለውስጥ ባቡር ካርታን በተመለከታችሁ ቁጥር ምን ያህል ምልክቶችን እንደምትተረጉሙ አስቡት። የዛሬው ዓለማችን ረቂቅ ሀሳብን፣ ከለጋ ዕድሜ ጀምሮ ያበረታታል፤ ብልህም እያደረገን ነው፡፡
ጦርነት ህገ ወጥ ነው፡፡ ይሄ ሃሳብ ግልፅና የሚታወቅ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በ1945 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከመፈጠሩ አስቀድሞ አገራትን እርስ በርስ ጦርነት ከመግጠም የመግታት ሃይል የነበረው ተቋም አልነበረም። ከአንዳንድ የተለዩ አጋጣሚዎች በቀር የዓለም አቀፍ ማዕቀቦችና የጣልቃ ገብነት ማስፈራሪያዎች፣ በአገራት መካከል ጦርነት እንዳይከሰት በመግታት ረገድ ውጤታማነታቸውን አሳይተዋል፡፡
እኔ ብዙ ጊዜዬን በማሰብ የማጠፋውን ጉዳይ ፒንከር በመፅሐሃፉ አንስቶታል፡፡ ይኸውም በተጨባጩ ዕድገትና ስለ ዕድገት ባለው ግንዛቤ መካከል ያለውን ክፍተት የሚመለከት ነው፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ህዝቦች ረዥም ዕድሜ፤ እየኖሩ ነው፤ ጤናማና ደስተኛ ህይወት እየመሩ ነው፡፡ ታዲያ እውነታው እንዲህ ከሆነ ዘንዳ… ለምንድን ነው በርካታ ሰዎች ሁኔታዎች እየከፉ መጥተዋል ብለው የሚያስቡት? ለምንድን ነው አዎንታዊ (ገንቢ) ዜናዎችን ችላ ብለን፣ አሉታዊ (አፍራሽ) የሆኑትን የሙጥኝ የምንለው? ፒንከር ለምን ወደ ጨለምተኝነት እንደምናስብና ይሄ ስሜታችን ስለ ዓለም ባለን አመለካከት ላይ እንዴት ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በማብራራት ረገድ ግሩም ሥራ ሰርቷል - ምንም እንኳን ሥነ ልቦናውን ይበልጥ በጥልቀት ቢመለከተው ብዬ ብመኝም ቅሉ፡፡ (በተለይ የሥነ ልቦና ባለሙያ ከመሆኑ አንፃር) አሁን በህይወት የሌለው ደራሲ ሃንስ ሮስሊንግ “Factfuiness” በተሰኘ አዲስና ግሩም መፅሐፉ፤ ይሄንን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ አብራርቶታል፡፡
በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ከፒንከር ጋር እስማማለሁ። ነገር ግን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በተመለከተ ብሩህ ተስፈኝነቱን ጥቂት ሳያበዛው አልቀረም፡፡ ሮቦቶች ፈጣሪያቸወን የሰው ልጅን፣ “ከጨዋታው ውጭ ያደርጉታል” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ለማድረግ ተጣድፏል፡፡ “Terminator” በሚለው ፊልም ላይ እንደሚታየው ዓይነት፣ አደጋ ላይ ነን ብዬ ባላስብም፡፡ ሮቦቶችን በትክክል የሚቆጣጠረው ማነው? የሚለው የፍርሃት ምንጭ የሆነ ጥያቄ - ተገቢ ነው፡፡ በርግጥ ገና እዚያ ጋ አልደረስንም፤ ነገር ግን የሆነ ጊዜ ላይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያለው ማነው? ማንስ ይቆጣጠረዋል? የሚለው ጥያቄ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምላሽ ሊሰጡት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ይሆናል፡፡
በአውቶሜሽን ዙሪያ የሚነሱ ትላልቅ ጥያቄዎች፤ ዕድገት ውስብስብና አስቸጋሪ ነገር ሊሆን እንደሚችል ምስክር ናቸው፡፡ ይሄ ማለት ግን በተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዝን ነው ማለት አይደለም፡፡
በ“Enlightment Now” መፅሐፍ መጨረሻ ግድም፣ ፒንከር እንዲህ ሲል ይሞግታል፡- “ፍፁም እንከን የለሽ የሆነ ዓለም ፈፅሞ አይኖረንም፤ የዚያን አይነቱን ዓለም መሻትም አደገኛ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ዕድገት ለማበልፀግ ዕውቀትን መተግበር ከቀጠልን ግን በምንቀዳጃቸው መሻሻሎች ላይ ገደብ አይኖርብንም፡፡”
ዓለም የተሻለ የመኖርያ ሥፍራ እየሆነች ነው፤ ምንም እንኳን ሁልጊዜ እንደዚያ ያለ ስሜት ባትፈጥርም። ትልቁን ስዕል ለማየት የሚያግዙን፣ እንደ ስቲቨን ፒንከር ያለ ብሩህ አሳቢዎች በማግኘታችን ደስተኛ ነኝ። “Enlightment Now” የፒንከር ምርጥ ሥራው ብቻ አይደለም፡፡ እኔም የምንጊዜም ተወዳጅ መፅሐፌ ነው፡፡      

Read 833 times