Sunday, 04 March 2018 00:00

ሴቶች ማሳቅ አይችሉም

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

 … ሴቶች ቆንጆ ናቸው፡፡ ወይ ምስኪን ናቸው … ወይ ነዝናዛ ናቸው፡፡ ታከብራቸዋለህ አልያም ትንቃቸዋለህ፡፡ እቀፋቸው ያሰኝሀል፡፡ አባብላቸው ያሰኝሀል፡፡ “ሁሉም ነገር ቀርቶ እነሱ ብቻ ደስ ይበላቸው” ያሰኝሃል፡፡ “ልብሷን አውልቃ ባያት” ብለው ያስመኙሀል፡፡ በጥፊ ባቃጥላቸውም ያሰኙሀል፡፡ ያለስለቅሱሃል፡፡ … ሴቶች ብዙ ነገር ያደርጉሃል፡፡ ሴቶች ግን ፈፅሞ ምንም ቢሞክሩ አያስቁህም፡፡ ይስቁብህ ይሆናል እንጂ ፈፅሞ አያስቁህም፡፡
*         *          *
የት እንደምንሄድ ሳትነግረኝ ነው እጄን ይዛ ወደ ሀያ ሁለት የበረረችው፡፡ ምሳ ስንበላ ጀምሮ በጣም ምቾት አልተሰማትም ነበር፡፡ … ድራም አበዛች። እጄን ልክ እንደ ቄስ እጅ፣ በአክብሮት ከአንጓው ጀምራ እስከ አይበሉባው ስትስም፣ ተመልካች እያየ ስለመሰለኝ፣ ቀስ ብዬ ነጠቅኳት፡፡ ፍቅር በድብቅ እንጂ በግልፅ ሲተወን፣ አትራፊው ተዋናዮቹ ሳይሆኑ፣ ሳይከፍል የሚመለከተው ታዛቢ ነው፡፡
ቀስ ብዬ ነጠቅኋት፡፡ እንዳይከፋት አንድ ጊዜ ከንፈሯ ላይ ሳም አደረኳት፤ አፌን እንዳትጎርሰው ተጠንቅቄ፡፡ አይኗ ላይ ቅሬታ ተወልዶ ከማደጉ በፊት፣ ታፋዋ መሃል ሸጉጣው የነበረውን አንድ እጇን አንስቼ ሳምኩት፡፡ የሳምኩት የእሷን እጅ ሳይሆን በስህተት የራሴን መሆኑን ባሳረፍኩት ምራቅ ቅዝቃዜና እሷ ቅሬታዋ በሳቅ ሲተካ ነበር ያወቅሁት። እጇን ጥዬ ወደምጠቀልለው ፖስታ ተመለስኩኝ፡፡ ሳቋን ጨርሳ የፍቅር ፊቷን መለሰችው፡፡
“ፍቅር ካንተ ይዞኛል” የሚል ፊት አላት፡፡ መውደድን እወዳለሁኝ፡፡ ግን የእሷ የፍቅር ፊት ያስፈራኛል፡፡ … ለእኔ የማይገባ ይመስለኛል፡፡ … ምናልባት ገና የእኔ መሆኗ አላሳመነኝም፡፡ ጥልቅ ፍቅር ውስጥ በዚህ ፍጥነት መግባት መቻሌን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ … ደግሞ እኔ ጎኗ አለሁ። እሩቅ አይደለሁም፡፡ … “ፍቅር ካንተ ይዞኛል” የሚለው ፊቷ፤ “ያንተ ብሆን ኖሮ” የሚልም ይመስላል፡፡ … ከጀርባዬ ሌላ ሰው እንደሌለ ማረጋገጥ ያምረኛል፡፡ … ግን ደግሞ ደስ የሚል ኩራት ይሰማኛል፡፡
መፈለግ ደስ ይላል፡፡ …. ድሮ ፍቅርን በተመለከተ እኔ ፈላጊ ነበርኩ፤ ከመፈለጌና የሚፈልገኝን ከማጣቴ የተነሳ ሴቶችን ከሆኑት በላይ ብርቅ አድርጌ ነበር የምቀበላቸው፡፡ በአለሙ ላይ ከወንድ እኩሌታ ሴቶች እንዳሉ በማያውቅ ካብ ላይ ነበር የማስቀምጣቸው፡፡ “ምነው ባደረገኝ የበርሽን አፈር፣ አንቺ ስትረግጭኝ እኔ እንድንፈራፈር” የሚለው ዘፈን፣ ትርጉም የሚሰጠው ለኔ ብቻ ነበር።
በጣም ብርቅ መሆንን ቢሹም … ከሚገባው በላይ ብርቅ ስታደርጋቸው ግን ሴቶች ይደነግጣሉ፡፡ … ይደነግጡና ያስደነገጣቸውን ይርቃሉ፡፡ … “ፈፅሞ ሴት የማያውቅን ወንድ እንወዳለን” ቢሉም፣ በጣም አጋኖ የሚያመልካቸው ግን ምቾት ይነሳቸዋል። … እንደዛ በፈላጊነት አለም ብዙ ስለተንገላታሁ፣ በተመላሽ እኔም ለዚህች ሴት ብርቅ መሆኔ ጨነቀኝ። ደስ የሚል ጭንቀት፡፡ “እውነት ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ግን አይመስለኝም፤ ግን እውነት ባደረገልኝ” የሚል ፍርሃትና ምኞት ተደባለቀብኝ፡፡ የእሷን እጅ ለመሳም ብዬ፣ የራሴን ስሜ የተሸማቀቅሁት ለዛ ነው፡፡
እሷ ግን ሳቀችብኝ፡፡ በድርጊቴ የተሰማኝን መሸማቀቅ በኋላ ብቻዬን ስሆን በደንብ አፍርበታለሁኝ “… የራሴን እጅ ሳምኩኝ?! ….
ብዕር አውጥታ ፖስታ የማይጠቀልለውን እጇን ዘርግታ፣ ጠረጴዛው ላይ እንደ ወረቀት ... የመዳፌን የአሻራ መስመር ተከትላ ፃፈች፡፡ እጅ ፅሁፏ ቆሎ የሚባል አይነት ነው፡፡
“Do you really love me?” ይላል፡፡
ወዲያው የምመልሰው መልስ በቅርቡ ሳነበው ከነበረ መፅሐፍ ላይ እንዴት እንደተከሰተልኝ አላውቅም፡፡ ገፀ ባህሪው የሆነ ዲቴክቲቭ ነገር ነው። እና “ምን ጥርጥር አለው?” ብሎ የተጠየቀውን ጥያቄ፣ እርግጠኝነት ለመግለፅ ሲፈልግ፡- “Is the pope catholic?” ደጋግሞ ይላል፡፡ ዲቴክቲቩ እንዳጋጣሚ ጥሩ ሰዓት ላይ ትዝ ስላለኝ፣ በውስጤ ኩራት ተሰማኝ፡፡ በእሷ ትንሽ እጅ ላይ ዳር እስከ ዳር ፃፍኩት፡፡ አንብባ በጣም ተደሰተች፡፡ ከአንድ ሰው ጋር ልታስተዋውቀኝ እንደምትፈልግ የነገረችኝ ከዛ በኋላ ነበር፡፡ ምሳ በልተን እንደጨረስን፣ከነበርንበት ቦታ እስከ ሀያሁለት ታክሲ አስቁማ አነጋገረች፡፡
*         *          *
…በታክሲው ውስጥ እያለን፣ከማን ጋር እንደምታስተዋውቀኝ ነገረችኝ፡፡ ከታላቅ እህቷ ጋር ነው፡፡ የሚገርመው እንደዛ ቀጠሮ አክብራ፣ እኔን ለማስተዋወቅ እየበረረች የሄደችበት እህቷን ፈፅሞ እንደማትወዳት፣ ከዚህ ቀደም ደጋግማ ነግራኛለች። ስለ ቤተሰቧ ብዙም ማውራት አትፈልግም፡፡ ወሬዋ እንዳጋጣሚ አሳብሮ ወደ ቤተሰቧ ከተሻገረ፡፡ አባቷ “He’s a raging alcholic” በሚል አጭር ሀረግ ታጠቃልለዋለች፡፡ ታላቅ እህቷን ደግሞ “She’s a soft spoken bitch with an angles voice” ብላ ወሬውን ትዘጋዋለች፡፡
ሀያ ሁለትን አልፈን ቦሌ ሚካኤል አካባቢ አወረደን ታክሲው፤እየወረድን … እየከፈለች፣ ማውራቷን አላቆመችም፡፡ ወሬዋ እህቷን ከእሷ ጋር ተባብሬ፣ እንድጠላላት ይመስላል፡፡ አንድ ፎቅ ላይ ወጣን፡፡ ቤቱ  ልጆቻቸውን ኬክ በሚያበሉ ወላጆች ተጨናንቋል፡፡ ልጆቹ ፊታቸውን ኬኩ ውስጥ ነክረው፣ በመሀል ቀና እያሉ ያለቅሳሉ። ወንዶቹ ወላጆች፤ በቀጫጭን እግሮቻቸው ላይ ሰፋፊ ቁምጣ አጥልቀው፣ ኬክ እየበሉ ከሚያለቅሱ ልጆቻቸው ጋር “ሰልፊ” ይነሳሉ፡፡ … የማትወዳትን እህቷን የሚያስናፍቅ ታኢብ፣ የስጋ ዝምድና ተብሎ ይጠራል፡፡
“አሚ ተጫወች” አልኳት፡፡ … ጭልጥ ብላ ትካዜ ውስጥ ስትገባ፡፡ የፍቅር ፊቷ በትካዜ ተውጧል፡፡ ጣቶቿን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣ ተመለከተቻቸው። የመስታወቱን ጠረጴዛ በጣቶቿ እየነካካች፣ምናባዊ ፒያኖ ስትጫወት ቆየች፡፡ … ድንገት እንደዛ ትካዜ ውስጥ ሆና ሳያት፣ የእውነት ብትወደኝ ደስ የሚለኝ መሰለኝ፡፡
“…ፍቅር ማለት ማዘን ነው …” የሚለው የቀድሞ እምነቴን ጠራርጌ፣ ከአስቀመጥኩበት መሀደር አውጥቼ በደንብ አስተውለው ጀመር፡፡ … ኤሚ እምወዳት ስለምታሳዝነኝ ነው፡፡ … በዛ ላይ ግልፅም ናት፡፡ እንደ ሴቶች ድብቅ አይደለችም፡፡ … ግን ምን የሚደበቅ ነገር አላቸው ሴቶች፡፡ … ራቁታቸውን ከቆሙ በኋላ የሚደበቅ ነገር የላቸውም፡፡ … ምስኪን ናቸው … ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ፡፡ … መወደዳቸው፤ በየደቂቃው ካልተረጋገጠላቸው ይሸማቀቃሉ፡፡ …
እጆቿን በድጋሚ አንስቼ (ሁለቱንም) ሳምኳቸው፡፡ ቅድም እጇ ላይ የጻፍኩት የእስክሪፕቶ  መልዕክት በከፊል ደብዝዟል፡፡ … እጇን ስስመው ፅሁፉ እንዳይጠፋ ተጠንቅቄ ነበር፡፡ … እህቷ ስልክ ደውላ፣ ፎቁና የኬክ ቤቱ ስም ተነገራት፡፡
*         *          *
ኤሚና ሊዲያ እህትማማች አይመስሉም። በቁመትም፣ በውበትም፣ በገፅታ ፍካትም ታላቅየው የእኔዋን ትበልጣታለች፡፡ ትልቅየዋ ለታናሿ እንዳይተርፍ፣ ከመሀፀን የዝርያቸውን ፀጋ ዘርፋ የወጣች ነው የምትመስለው፡፡ ምናልባት የሁለቱ ጥል፣ ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል -- ብዬ ለማሰብ ቅፅበቱ አይበቃም፡፡ ለበኋላ አስቀመጥኩት፤ ሀሳቡን።
ሊዲያ እህቷን አቅፋ ስትስም--ሽው ያለው የፀጉራ ሽታ አወደኝ፡፡ ድሮ እንደ ብርቅ የማያቸው የህልሜ ሴቶች ራሱ እንደዚህ ያለ ጠረን ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ከሻምፖና ቅባት ሳይሆን ከማንነቷ የመነጨ ጠረን መሰለኝ፡፡ ጥርሷ፤ መንግስተ ሰማይ በመርፌ ቀዳዳ አልፈው ለሚገቡ ሰዎች፤ ከህይወት በኋላ የሚሰጣቸውን የፅድቅ ጥርስ ይመስላል፡፡ ምግብ ተበልቶበትም … አላስፈላጊ ሳቅ ተስቆበትም የሚያውቅ አይመስልም። የኤሚ ጥርስ የተደረበ አለው፡፡ በቃ ወላጆች አንዷን አውስትራሊያ፣ ሌላዋን ሶማሊያ ወልደው ያሳደጓቸው እስኪመስል። … የሽንጥ ርዝመት-- የቆዳ ቀለም … ሊዲያ በተጫማችው ግልፅ ጫማ፣ የእግር ጣቶቿን (መሬት መሬት ለማየት ሳቀረቅር) እንዳጋጣሚ አየሁዋቸው፡፡ የእግር ጣቶቿ እንደ እጅ ጣት ረጃጅም ናቸው፡፡ ሁለቱ የእግሯ  ጣቶች ላይ የወርቅ ቀለበት አድርጋለች፡፡ … በጥሩ መሬት ላይ በጥንቃቄ የተራመደ እግር ነው፡፡
“ተዋወቂው ባሌ ነው” አለች፤ የኔዋ፡፡
ሊዲያ በአይኗ በደንብ አድርጋ አየችኝ፡፡ በቃኋት … መሰለኝ ብዙ ሳትቆይብኝ አይኗን ነቀለች፡፡ “Hi” አለችኝ፤ ለመጨበጥ እጇን ሳትዘረጋ፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ተፀይፋኝ እንደሆነ፡፡ … ግን እጇን ይቅርና እግሯንም ብትዘረጋ የምትጨበጥ አይነት ናት፡፡ እሷ ሰዎችን ወደ ታች ታይ እንደሆነ እንጂ ማንም እሷን ዝቅ አድርጎ ለማየት አቅም የለውም። ሁሉም ነገሯ እንደ ፀሐይ ነው፡፡ ቀና ብዬ፣ አይኗን ለማየት አፈርኩኝ፡፡ በራሴ ጊዜ እንደ ድሮው፣ በራስ አለመተማመኔ ሳልፈልገው ሄድኩኝ፡፡
“So this is your man?! --- ካሮንን በቃ ተውሽው ማለት ነው?” አለች ሊዲያ፤ በድጋሚ የክለሳ ግምገማ እያካሄደችብኝ፡፡  
“አዎ ደስ ይበልሽ፤ ትቼልሻለሁ” አለች ኤሚ፤ ፍርጥም ብላ፡፡
ሊዲያ ዝም ብላ ታናሽ እህቷን ስታያት ቆይታ፣ ወደኔ ድንገት ዞረችና፡-
“ወንድሜ፤ እኔ አላውቅህም ግን ጥሩ ሰው ትመስለኛለህ፡፡ … እቺን ልጅ የምትሰማህ ከሆነ ምከራት … አባታችን ወደ ውጭ ትምህርት እንድትማር ፈልጎ ሊልካት ሲል እንቢ ብላለች፡፡ … ቀለበት ያሰረችለት እጮኛ፣ ከውጭ ቆይቶ ሊመጣ ሲል፣ ትዳርም አልፈልግም ብላለች፡፡ … አንተንም እንደው ለጊዜው ነው እንጂ ጥላህ ትሄዳለች፡፡ …እህቴን አታውቃትም፡፡ … ሰው ማስቀየም የሚያክል የለም፡፡ ለምን እንደዚህ እንደምታደርግ አላውቅም…” ብላ ስታወራልኝ፣ የራሷ ድምጽ እንዴት ራሷን እንደማያፈዛት እየገረመኝ ነበር፡፡ በድምጿ ውበት ምክኒያት የምትነግረኝን በሙሉ ተቀብያለሁኝ። … ቅድም ኤሚ ስለ እህቷ መጥፎነት የነገረችኝን ረሳሁት፡፡ ምናልባት በውበትም በዕድሜም  ታላቅየዋ ስለምትበልጣት፣ ንግግሯም በቀላሉ እውነትነቱ ተሰማኝ፡፡
እንዳፈዘዘችኝ ስታውቅ እጄን ያዘችኝ። … እያወራች እጄን ያዘችኝ፡፡ እጄን አያያዟ በወሬዋ ተመስጣ፣ እኔን ለመመሰጥ ቢመስልም፣ አጨባበጧ ጥንካሬዬንም እየለካች መሰለኝ፡፡ “… ብርሽን እመልስልሻለሁ፤ በራሴ ምርጫ ውስጥ ግን አትግቢብኝ … ራሴን ችዬ ለመኖር አቅም ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ያንችንም ሆነ የሼባውን ምክር አልፈልግም” ብላ አጭር ፀጉሯን በሁለት እጇ እየቆፈረች ማልቀስ ጀመረች፤ ኤሚ የኔ፡፡
ላፅናናት ግን አልቻልኩም፤ተይዣለሁኝ፡፡ እኔን እየደባበሰች ማውራት ትታ፣ ትልቅየዋ እጇን ጭኔ ላይ አሳረፈችው፡፡ … ሙሉ ለሙሉ ሰውነቴ መታዘዝ አቆመ፡፡ በአደገኛ ደረጃ እንደተቆጣጠረችኝ ስታውቅ በዛ የፅድቅ ግዛት ጥርሷ፣ እንደ ጅብ አሽካክታ ሳቀች። … ማሳቅ አይችሉበትም እንጂ መሳቅ የሚያክላቸው የለም፡፡
…ኤሚ ፀጉሯን አንጨብርራመ፣ እየቆፈረች ከተቀመጠችበት ድንገት ተነስታ፣ ተንደርድራ ወጣች፡፡ የወጣችው ታላቅ እህቷ ከመሳቋ በፊት ወይንስ በኋላ አላውቅም … ትንሽ ነፍሴን እንደ መሳት አድርጎኝ ነበር፡፡
ኤሚን ለመከተል የወጣሁት ትንሽ ዘግይቼ ነው፡፡ ከመውጣቴ በፊት ታላቅ እህትዋም ጭኔን በጨዋታ መልክ እየደባበሰች … “…እኔና እህቴ፣ በጣም እንቀናናለን … በሁሉም ነገር፡፡ … እሷ አሁን በኔ መቅናት አቁማለች …በጣም በልጫት ስለሄድኩ … እኔ ግን በእሷ፣ አሁንም እቀናለሁ፡፡ የሚቀናበት ነገር ባይኖር እንኳን እቀናለሁ፡፡ (“የሚቀናበት ነገር ባይኖር እንኳን--ስትል ጭኔን ቆንጠጥ አድርጋ፣ እኔን መሆኑን እንዳውቅ አድርጋኛለች) … እና ስለሷም ሆነ ስለሌላ ጉዳይ ለማውራት ከፈለክ ደውልልኝ” ብላ ቢዝነስ ካርድ ጠረጴዛው ላይ  አስቀመጠች፡፡
ብዙ ከቆየሁ በኋላ፣ “እወድሻለሁ” ብዬ ቃል የገባሁላትን ሴት ለመከተል፣ እያነከስኩ ወጣሁኝ፡፡ 

Read 4669 times