Sunday, 04 March 2018 00:00

የፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ቃለ ምልልስ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 15/2010 ባካሄደዉ ስብሰባ የአመራር ሽግሽግ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዉ እንዲያገለግሉ ወስኗል፡፡ ይህን ዉሳኔ በማስመልከት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ከኦ.ቢ.ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ከኦ.ቢ.ኤን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ እንዲቀርብላችሁ በተደጋጋሚ ባቀረባችሁት ጥያቄ መሰረት ቃለ ምልልሱን ተርጉመን እንደሚከተለዉ አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

    ‘የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ፤ የድርጅታችን አሰራር መሠረት በማድረግ የአመራሮችን ሁኔታ አስመልክቶ አንዳንድ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ከተፈጠረው ሁኔታ በመነሳት፤ ድርጅታችን የሕዝባችንን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር እስካሁን የሄደዉ አካሄድ ምን እንደሚምስል እና ትግሉን ብስለትና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዴት መምራት ይችላል በሚል መንፈስ መልሰን መላልሰን ስንመለከተው ነበር፡፡
በዚህ አካሄድም ግልጽ የሆነ ነገር ተፈጥሯል። ሕዝባችን እንደክልል ራሱን በራሱ ማስተዳደርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ከመፈለጉ የተነሳ ጥያቄዎችን ሲያነሳ ነበር፡፡ በሌላ መልኩም በፌደራል ደረጃ የሃላፊነት ድርሻ በመወሰድና በወሰደውም ልክ የአመራርነት ድርሻ እንዲኖረው ጥያቄ ነበረው፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ የሕዝባችን ብቻ ሳይሆን የድርጅታችንም ጥያቄ ነበር፡፡ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የአመራርነት ሚናችንን በተገቢዉ መንገድ በመወጣት ለህዝባቸን ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ መስጠት እንዳለብን እናምናለን። ይህንን ከግብ ማድረስ ይገባናል፡፡ ለስኬታማነቱም ከሕዝባችን ጋር በመሆን ረዥም የትግል ጉዞ በማድረግ እዚህ ደርሰናል፡፡ ይህ ማለት ግን ትግሉ በዚህ አበቃ ማለት አይደለም፡፡ ትልቁ ትግል ከፊታችን ያለው ነው። ከዚህ በመነሳትም በፌዴራል መንግስት ውስጥ የአመራርነት ሚና በብቃት መወጣት አለብን ስንል ክልላችንን በመዘንጋት መሆን የለበትም፡፡
እዚህ ላይ ማሰብ ያለብን አብይ ጉዳይ ሃላፊነትን መቀበል አለብን ብለን ማሰብ ብቻ ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን ዕድል፣ እንዴት አድርገን ልንሰራበት እንደምንችል በማጤን፣ በበሰለ አካሄድ የወደፊቱን ግብ ማየት ነው እንጂ ሀላፊነትን መቀበል ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ጉዳዩን ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ የተሰጠንን ዕድል በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም መውደቅ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በሕዝባችን ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም፤ በመሆኑም ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ በማየት ልንሰራ ይገባል፡፡ ሕዝባችን በፌዴራል መንግስት ተገቢዉን የሃላፊነት ድርሻ ማግኘት አለብን ብሎ ሲጠይቅ ጥያቄው የሞራል ጥያቄ ነው፡፡ ድርጅቱም በዚህ ጥያቄ ተገቢነት ያምናል። በፌዴራል ደረጃ የሚቀመጠው አመራር ለኦሮሞ ሕዝብ የተለየ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያመጣል ብለን አናስብም፡፡ አንድ ሰው ከመካከላችን በመውጣት ሀገሪቱን መምራት ይችላል ብንል እንኳ፤ የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነትና በፍትሐዊነት ይመራል፡፡ የታገልነውም ለዚህ ነው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ወክሎ እንደመቀመጡ መጠንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ክብርና ጥቅም በማስጠበቅ፣ እኩልነት በሀገሪቱ እንዲሰፍንና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ መስራት አለበት፡፡
በሌላ በኩል የኦሮሞን ክብር ማስጠበቅ የምንችለው፣ ሰርቀን ለሕዝባችን በማምጣት ሳይሆን ለፍትሐዊነትና ለእውነት የምንስራ መሆናችንን፣ በተሰጠን ዕድል ሰርተን በማሳየት ብቻ ነዉ፡፡
በቀጣይነት የሚነሳው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ጥያቄ እንዴት መመለስ እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው በግልጽና በጥልቀት በመወያየትና በመደማመጥ፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር ያለዉ ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት ሲመለከት ቆይቷል። ይህን ችግር ለመፍታት የአመራሩ ድርሻ ቁልፍ መሆኑ ተሰምሮበታል። ከዚህ በመነሳት እንደ አመራር ያለንን ፑል በመጠቀም፣ ከምንጊዜውም በላይ በአንድ ልብና ሃሳብ ጠንክረን team spirit (collective leadership ፈጥረን) በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።
ከግብ የምናደርሰው የህዝባችንን ጥያቄ ስለሆነ፣ በክልል ያለውን አመራራችንን እንዴት እናስቀጥል፣ በፌዴራል ደረጃ ያለንን ተልዕኮስ እንዴት ከግብ እናድርስ የሚለውን ሃሳብ አፅንኦት ሰጥተን ተመልክተነዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ ያለውን ብቻ በማየት በክልል ያለውን ጉዳይ የምናንጠባጥብ ከሆነ ውድቀት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ አንድ ሰው አይደለም፤ ሀያ ሰው በፌዴራል ደረጃ ወንበር ቢያገኝ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም፡፡ ስለሆነም በሁለቱም አቅጣጫ ተመልክተን አንድም ክልላችንና ሕዝባችን ያሉባቸውን ችግሮች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትና ንክኪ፣ ራስችንን ችለን ማስተዳደር መቻል ትልቅ ድል ነው፡፡
በተለይ የኢኮኖሚ ጥያቄን በመለከተ፤ ድርጅታችንን በማጠናከርና የመንግስት መዋቅርን በመገንባት ላይ አትኩረን ከሰራን፣ ከምን ጊዜውም በላይ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ዋናው ትኩረት ኦሮሚያ ላይ መስራት ነው። የስልጣናችን ምንጭ ሕዝባችን ስለሆነ ወደፊትም ወደ ፌዴራል ሄደን የምንሰራው ሥራ በግለሰብ የሚሰራ ስላልሆነ፣ ይህ ሕዝብ ዕውቅና እስካልሰጠውና እሰካልደገፈው ሁለት ሰውም ይሁን ሀያ ሰው ሄዶ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን ደግሞ ማምጣት የምንችለው በቤታችን ውስጥ የምንፈልገውን ነገር መስራት ስንችል ነው፡፡ በነፃነት ጠንክረን ኦሮሚያ ውስጥ ስንሰራ፣ የሕዝባችንን ችግር መፍታት እንችላለን። በተለያየ መልኩ እንቅፋት እየኖነብን፣ መሮጥ የምንችለውን ያህል እንዳንሮጥ የገደበን ነገር ቢኖርም፤ አሁን ባለን አቅም መሮጥ የሚያስችለን ነገር አለን ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ጠንካራ አመራር በክልላችን ሊኖረን ይገባል፡፡ ብዙ በጅምር ተንጠልጥለው ያሉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሕዝባችንን አንድ የማድረግ ስራዎች ይቀሩናል፡፡
የመንግስትና የድርጅት አደረጃጀት ጠንካራና ለሕዝቡ የሚቆረቆር መሆን አለበት። ይህንን ድርጅት ለማጠናከር የተለያዩ ትግሎችንና እርምጃዎችን እየወሰድን እዚህ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ጠንካራ ሆኖ የወጣ አይደለም፡፡ አሁንም በተለየ መንገድ ማጠንከር ያስፈልጋል። ዝም ብለን በሩን ክፍት አድርገን፣ ሁላችንም፣ የምንሄድ ከሆነ ተያይዘን እንወድቃለን። አሁን ባለበት በአንድ ልብና ሃሳብ ጠንክረን ከሰራን ከላይ የምንሰራው ስራም ዉጤታማ ይሆናል፣ ረዥም መንገድም ይጓዛል፣ በመንገድም አይቀርም፡፡ ይሄንን የሚያስተጓጉል የሚሞክር ሊኖር ይችል ይሆናል፤ በሕዝብና በጠንካራ ድርጅት ከተደገፈ ግን ምንም አይሆንም፤ ስለሆነም በኦሮሚያ ላይ የሚሰራው ስራ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ የሆነ አመራር ኦሮሚያ ላይ ሊኖረን ይገባል፡፡ ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ማን የት ቢጫወት የበለጠ ውጤት ያመጣል አንደሚባለው ማየት አለብን፡፡ ከዚህ በመነሳት ካለን የአመራር ፑል፣ ማንን የትና እንዴት ብናዘጋጅ ይሻላል ብለን አንዱን በማንሳትና ሌላውን በመተው ሳይሆን በአንድ ሃሳብና በቡድን፣ ለአንድ ግብ ብንስራ ተያይዘን ረዥም መንገድ መጓዝ እንችላለን። ሕዝባችን ከእኛ የሚጠብቀውንም ነገር ከግብ ማድረስ እንችላለን።
ከዚህም በመነሳት የህዝባችንን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ በሚያስችለን መልኩ አንድ አንድ ማስተካከያዎችን አድርገናል፡፡ ያደረግነው ማስተካከያ በፌዴራል ደረጃ የኦህዴድ ሚና የጎላ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለን፡፡ ድርጅቱ በፌዴራል አመራርነት ዉስጥ በሚገባ ሚናውን እንዲወጣ ስንታገል ነበር፤እየታገልንም ነው፥ ለወደፊትም እንታገላለን፡፡ይሄም ጥያቄ ዉስጥ አይገባም፡፡ የሚሆነዉም ዲሞክራቲክ በሆነ መልክ ነው፡፡ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ማን የት ቢተካ የበለጠ ዉጤታማ እንሆናለን በማለት አይተናል። በሌላ በኩል እንደ መስፈርት የሚነሱ አንድ አንድ ጉዳዮች ከወዲሁ በተሟላ መልክ እንድናደራጅ ትኩረት ሰጥተን ተወያይተን ወስነናል፡፡ አንድ አንድ ለውጥም አድርገናል፤ ለምሳሌ ማናችንም ከማናችን በልጠን አይደለም፤ ነገር ግን ማን የት ቢሆን በይበልጥ ዉጤት ማምጣት ይችላል? እና የድርጅቱን አላማ ከግብ ማድረስ ይችላል በማለት አይተናል፡፡
በዚህም መሰረት ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲሰራ እኔ ደግሞ ምክትል ሆኜ እንድሰራ ወስነናል፡፡ ይሄን ስናደርግ ለህዝባችን ግልፅ ሊሆን የሚገባው ምንም ነገር ተፈጥሮ አይደለም። ነገር ግን የህዝባችንን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የተጠቀምንበት ስልት እንጂ፡፡ ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ እድር አይደለም ወይም ማህበር አይደለም። ፖለቲካ ደግሞ በሁሉ አቅጣጫ መመልከትን ይጠይቃል፡፡ የህዝብ ፍላጎትን ያማከለና የድርጅቱን ዓላማ ከግብ ያደርሳል ብለን ያሰብነውን ሁሉ አድርገናል፡፡ በዚህ ዕይታ ነው ይሄን ማስተካከያ ያደረግነው፡፡ እንደዚህ ሲሆን አንድና ሁለት ሰው ማዘጋጀት ሳይሆን ወደ ፌዴራል አመራር የሚሄድ አካል በቡድን እንዲሰራ በማሰብ ጭምር ነው። ለፌዴራል የሚሄድ አካል እንዴት መሰራት እንዳለበት፤ ምን መስራት እንዳለበት ግንዛቤ በመያዝ፣ ይሄን ማስተካከያ አድርገናል፡፡ በክልል የሚቀረው አካል ምን መስራት እንዳለበት አንድ ሁለት ብለን አስቀምጠናል። ሁለቱም አካላት ደግሞ በመደማመጥ፤ በመተጋገዝ ይሰራሉ ብሎ ድርጅቱ አምኖበት፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀጣዩን ስራ በማጤን ወስኗል፡፡
ይህ ማለት ድርጅቱን ስመራው እንደቆየሁት አሁንም እመራለሁ፤ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ በጅምር ተንጠልጥሎ ያሉ የቤት ሥራዎች አሉን፡፡ ተንጠልጥሎ ያለ ሥራን ትቶ መሄድ ደግሞ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ እንደ እኛ ሃሳብ ጅምር ስራዎችን በክልሉ እየገነባን ባለነው ቲም/ቡድን/ በርትተን ብንሰራ ይበልጥ የተሳካ ይሆናል። ወደ ፌዴራል የሚሄደው ቡድን በዚህ ደረጃ የህዝባችንን ፍላጎት ያስከብራል፡፡ ይሄንን ስናደርግ በስልጣን ስሌት የምናየው ከሆነ፤ አንዱ ወንበር ካንዱ ይበልጣል፡፡ ይሄ ደግሞ በታሪክ ሲገጥመን ለመቀበል ማናችንም ትልቅ ጉጉት ይኖረናል፡፡ ነገር ግን እንደ ግለሰብ ወንበር በመመኘት ብቻ ህዝባችን ዋጋ የከፈለበትን ጉዳይ ከግብ እናደርሳለን ብለን ማሰብ አይቻልም። በይበልጥ የት ሆነን ብንሰራ፣ ህዝቤ ዋጋ የከፈለበትን ከግብ አደርሳለሁ ብሎ በማሰብ እንጂ፡፡ ለእኔ ትልቁ ስኬት ዋጋ ከፍለን እዚህ ያደረስነዉን ትግልና በኦሮሚያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ትግል ከግብ ማድረስ ሲቻል ነው፡፡ የተለያዩ ጫናዎችና ሙሉ ትኩረታችንን የሚበትኑ ጉዳዮች ከቆሙ፣ በሙሉ ኃይል ዛሬ ላይ ከምናደርገው ሩጫ በሁለትና ሶስት እጥፍ ማፍጠን እንችላለን፡፡ ሌት ተቀን ሙሉ ኃይላችንን በመጠቀም በኦሮሚያ የጎላ ለዉጦች እናመጣለን ብዬ አምናለሁ፡፡
በሀገራች ደረጃ ያለዉን ቸግር ለመፍታት በምናደርገዉ እንቅስቃሴ፣ በክልል ያለውን ችግር በመሰረቱ ካልፈታን፣ እንደ መዋጮ አስር ሰውና ከዚያ በላይ ወደ ፌዴራል አመራር በመላክ ቀጣይነት ያለዉ መፍትሄ ልናመጣ አንችልም። መጀመሪያ ክልላችን መሰረቱ የጠነከረ መሆን ይገባዋል፤ በሁለት እግሩ መቆም ይኖርበታል፤ ካሁን በኋላ የሚሆነው ጠንካራ ትግል ነው፡ ዝም ብለን ለአጭር ጊዜ ኃላፊነት ወስደን መመለስ ከሆነ፣ ማንም ሰው የፈለገበት ቦታ መሄድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የተገኘውን ዕድል ዘላቂ ለማድረግ አስበንበት፣ እስትራቲጂክ በሆነ መንገድ መስራት ይኖርብናል። በተለይ በክልል ደረጃ ፍፃሜ ሳያገኙ የቆዩ የቤት ስራዎችን ሙሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሙሉ አድርገን ማናችንም በፈለግን ቦታ፤ ደረጃ መስራት እንችላለን፡፡ በክልል ደረጃ ተጨባጭ ለዉጥ ካመጣን፣ ጠይቀን ሳይሆን ተጠይቀን መስራት እንችላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን ብዙ የቤት ስራ አለብን፤ ድርጅታችንን ጠንካራ ድርጅት ማድረግ አለብን፤ በጣም ብዙ ነገር ማስተካከል አለብን፡፡ በራሱ የሚተማመን፣ ቀን ከሌሊት ሰርቶ ስር-ነቀል ለውጥ የሚያስገኝ ጠንካራ ክልላዊ መንግስት መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ የህዝባችንን የሞራልና ኢኮኖሚ ጥያቄ የመመለስ አቅም በቂ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል፡፡ በኦሮሚያ ያለን የሰው ሀብት፣ የተፈጥሮ ሀብት በማቀናጀት ለውጥ ማምጣት አለብን። ለዚህ ደግሞ አሁን ባሰብነው መንገድ ከሰራን ረጅም መንገድ ያስኬደናል ብለን ስለምናምን፣ በአንድ አቋም መፅናት ነዉ ያለብን፡፡
መርሳት የሌብን ነገር ቢኖር፣ በአንዳንድ አሉታዊ ንክኪዎች አንተ እንዲህ አድርግ፣ አንተ ደግሞ እንዲህ ሁን ብሎ ዛሬ በሚታየዉ መልኩ የምንሰራ ከሆነ ህዝባችንን አሳፍረናል፤ የፈሰሰዉን ደም ዋጋ አሳጥተናል ማለት ነዉ። ስለዚህ በዚህ አንሰራም። ለህዝባችን ቃል በገባነዉ መሠረት እንጂ፡፡ ዛሬም ነገም ቃላችንን አንሸራርፍም፡፡ የምንሰራዉም ማንንም በመስማት ሳይሆን ህዝባችንን በመስማት ይሆናል፡፡ ይህ አቋም አይሸራረፍም፡፡ እዚህ ያደረስነዉን ወደኋላ የሚመልስ የለም፡፡ ዋናዉ ጉዳይ ግን ሁሉም ነገር በብልኃት፣ ዲሞክራቲክና በተደራጀ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በተናጠል የሚሰራ አመራር የለም፡፡ ሁሉም በቡድን መንፈስ ነዉ የሚሰራዉ፡፡ በዚህ መልክ ተግባብተን እየሠራን ነዉ፤ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ይበልጥ አጠንክረን በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ አቋም፣ በአንድ እይታ ተቀናጅቶ የሚሠራ አመራር መሆን አለብን። በዚህ መልኩ ኮሚቴያችን አምኖኝ ተቀብሎኛል። የኦሮሚያ ካቢኔዎች እንዲሁ በዚሁ መልክ ሀሳቡን ተቀብሏል፤ ይህን ደግሞ ማጠናከር ነዉ፡፡ አመራሩን ማብቃት አለብን፡፡ አንድ ሰዉ አንድ ሰዉ ነዉ፤ ጠንካራ አመራር ማፍራት አለብን፤ በምኞት ብቻ አላማችንን ማሳካት አይቻልም፤ ወደ ተግባር መቀየርና የትም ቦታ ሆነን መገኘት አለብን፡ በልጠን መገኘት አለብን፣ ዛሬ እዚህ ካልተሰራ ከየትም ሊመጣ አይችልም፡፡ ትልቅ ዕድል እጃችን ላይ ነው። ትልቅ እድል ነው፤ ለኛ ውድቀት አይደለም፡፡ ልንጠቀምበት ይገባል። እስከ ዛሬ ለህዝባችን ትልቅ ውጤት አስገኝተናል ብለን እናምናለን፡፡ ጠንክረን ሰርተን ከኦሮሚያ አልፈን ህዝባችን የተናቀበትን፣ ሌላን ማስተዳደር ይቅርና እራሱን እንደማያስተዳድር ተደርጎ የነበረውን የመቶ ዓመት ጥያቄን አልፈን፣ ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች ኦሮሞ ያስተዳድረናል የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዲሁ አልመጣም በሥራ እንጂ፤ ታሪክ ተቀይሯል ከመቶ ሃምሳ ዓመት በላይ የነበረብንን እድፍ ታጥበናል፡፡ በዚህ ደረጃ የኦሮሞ ታጋዮች በጋራ ትግል እዚህ ደርሰናል፡፡ቀጥሎም እንደዚያዉ ነው መሆን የምንመኘው፣ እውን ሆነን ምኞቱን ማረጋገጥ ያለብን የቤት ሥራ ነው፡፡
እኔ ዛሬ ብወድቅ ብቻዬን አልወደቅኩም፤ ህዝብን አከትለን ስለሆነ የምንቀመጥበት መቀመጫ የህዝባችን ማንነት እንጂ የግላችን አይደለም፡፡ የእኔ መውደቅ መድከም ለዚህ ህዝብ የሚያመጣዉ ተጽእኖ አለ፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በመደጋገፍና በመተጋገዝ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በተገኘው ዕድል መጠቀም እንጂ ወዲያ ወዲህ የምናይበት ጊዜ አይደለም። ማፈራረስ አይደለም የሚንፈልገዉ፤ መተቻቸት አይደለም የሚፈለግብን፤ በየትም በኩል የህዝባችንን ምኞትና ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ይሄንም ከግብ ለማድረስ የሰራንበት ጉዳይ ስለሆነ ህዝባችን በዚህ በኩል ልረዳን ይገባል፡፡
የወሰነዉ ዉሳኔ የሌላ አካል ጫና አለበት ብሎ ለሚጠራጠር ማንም ሰው ግልፅ ሊሆን የሚገባው፣ በማንም ጫናና ተፅዕኖ አልሰራንም። ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡ እኔ መገፋት ያለበትን ገፍቼ፤ ማድረግ ያለብኝን አድርጌ፣ ዛሬ ላይ ደርሼ በማንኛውም አካል ግፊት የምወስን ከሆነ ይሄን ህዝብን መናቅ ይሆናል። የህዝቡንም ትግል ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ በፍጹም አናደርግም፡፡ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነገሮችን በፖለቲካ አይን መመልከት ነው፡፡ በቅድሚያ ማየት ያለብን፣ እኛ የምንፈልገው ቤታችንን ማድዳት ነው፤ ራሳችንን ነፃ ማድረግ ነው፤ ሌላ ነገር የለም፡፡
ይሄን በአጽንኦት መመለከት ይኖርብናል፡፡ ለኔ የማንም ሰው ግፊት/ ጫና/ አይደለም፤ ለህዝቤ ብሠራ ይበልጥ ውጤት ማምጣት እችላለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ዛሬም ነገም የጀመርነው ወደ ኋላ ሊንሸራተት ይችላል፤ የህዝብ ትግል ወደ ኋላ ይቀለበሳል ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን መስተካከል ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ዛሬ ወጥተን ለመታየታችን እኔ በግሌ የሰራሁት ልዩ ሥራ አለ ብዬ አላስብም፡፡ ለዚህ ክብር ያበቃን ይሄ ህዝብ ነው፡፡ እኔ በግሌ ከማንም በልጬ አይደለም፡፡ በዚህ ህዝብ ተማምነን ደግሞ ማድረግ የሚገባንን ነገር ያለ ፍራቻና መሸማቀቅ አድርገነዋል፡፡ የተማመነው በእነርሱ ነው፡፡ ክብርና ሞገስ ያጎናፀፈንንና ዕውቅና የሰጠንን ህዝብ ተማምነን ነው የሰራነው፡፡ ነገም በዚህ እይታ ነው የምንሰራው ዛሬም ቢሆን ይህን ህዝብ ለማዋረድ ብለን አይደለም፤ በቅድሚያ ግን ቤታችን ውስጥ ያላፀዳነው ነገር አለ፡፡ ያልሰራነው ነገር አለ። እሱን አልጨረስንም፤ ይህንን መዘንጋት የለብንም፤ ዛሬም ተንኮልና ሴራ አይሰራብንም ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ አቅማችንን ማጎልበት ይቀረናል። አንድነታችንን ማጠናከር ይቀረናል፡፡ ጠንካራ ለህዝብ የሚሰራና ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ድርጅት ለመገንባት ልንሰራ ይገባል፡፡ ኦህዴድን እንደ አዲስ ልንሰራው ይገባል ስንል፣ ይህንን ድርጅት ማንም ሊሰራው አይገባም ማለታችን ነዉ፡፡ እንደ ጀመርኩት እኔም መሥራት ይገባኛል ብዬ አስባለሁ። አብሮኝ ከሚሰራ ኃይልና አመራር ጋር መሥራት ይገባኛል ብዬ አስባለሁ። ይሄ ክልል፤ ክልል ብቻ አይደለም፤ ትልቅ ሐገር ነው፡፡ በዚህ ክልል ትልቅ ሀብት አለ። ግን አልሰራንበትም፡፡ ይህቺን ሀገር ለመለወጥ ኦሮሚያን መቀየር አለብን ብለን ነበር፡፡ እሱን ልንሰራ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ አቅማችን ሊበታተን አይገባም፡፡ ስለሆነም እዚህ ያለውን መሥራት ይገባናል። ለእኔ ህዝቤ ያንን መመኘቱ ክብር ነው፡ ክብርን ያጎናፀፈኝ ነው፡፡ ስለዚህ እኔም ይህን ክብር ሳይሸራረፍ ለማስጠበቅ፣ ትናንትና ህይወቴን ሰጥቼ እንደሰራሁት ሁሉ ነገም ለእሱ እሰራለሁ፡፡ ለእሱ ስሰራለትም የት ቦታ ውጤታማ እንሆናለን በሚለው አግባብ እኔም ሆንኩኝ ድርጅቴ አይተን ፈፅመናል። ስለሆነም አንዳንድ ነገሮች በዕድል እጃችን ይግቡ እንጂ በመሃከላችንና በጓዳችን ማስተካከል የሚገቡን አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ማለት ለማ ነገ ወደ ታሰበው ቦታ የመምጣት ዕድሉ ተዘጋ ማለት አይደለም፡፡ በጓዳችንና በቀዬአችን ያለውን ነገር ሁሉ አስተካክለን ከጨረስን፣ ሳንወድ የግድ መንገዱ አጭር ይሆናል፤ የሚል ግምት አለኝ፡፡
አይደለም በኦሮሚያ በዚህች ሀገር በየትኛውም ደረጃ ሰርተንም ሆነ መርተን ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ በሀገሪቱ GDP ውስጥ የክልሉ ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ እውነት ይህችን ሀገር መቀየር ከተፈለገ፣ በክልሉ ላይ ነው መሰራት ያለበት፡፡ ይሁን እንጂ እኛ ሀገሪቱን መቀየር አይደለም፣ የድሀውን ህዝብና ኦሮሞ ኑሮ መቀየር አይቻልንም፡፡ ዛሬም ለም መሬት ላይ ተቀምጦ፣ እየተራበና እየተጠማ ያለ ህዝብ አለን፡፡ መጀመሪያ እሱን መቀየር አለብን፤ ይህንን ከቀየርን ለወደፊትም ጊዜ አለ፡፡ ነገ በየትኛውም ቦታ ለማም ይምጣ ገመቹ፣ እሱ ምንም አይደለም፣ መንገድ ብቻ ይከፈት፤ መጀመሪያ እሱን እንቀይር፤ መንገድ ተከፍቶ የተሟላ አቅም ኖሮን፣ አንድነት ኖሮን ይህንን መጎናፀፍ የሚያስችለን አቅም ካለ፤ አይደለም ዛሬ ነገም ማንም በቀጣይነት ሊመጣበት ይችላል፡፡ ይህንን ልንዘነጋው አይገባም ስለሆነም በዚህ ደረጃ ልንሰራ ይገባል፤ አንድ ሰው አንድ ነው። አንድ ሰው ድርሻ የለውም ማለት አይደለም። ነገሮችን በመለወጥ ውስጥ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው፤ ያዉ አንድ ሰው ነው:: ከልብ የሚሰራ፣ ትልቅ ኃይል ከሥሩ ማደራጀት አለበት። በየትኛውም ጊዜ በማንኛውም ሰአት በሚመጣ ንፋስ የማይናወጥ ሰው ሊኖረን ይገባል እንጂ በግል ቢንጠላጠል ረዥም መንገድ መሄድ አይችልም፡፡
ስለዚህ ይሄን አውቀን ጠንክረን መስራት ይገባናል። ይህን ሁሉ እናደርጋለን ስንል ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሀገሪቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነው፡፡ እኛ በየትኛውም ደረጃ ኦሮሞ የአመራርነት ድርሻ ወስዶ ይምራ ስንል የኦሮሞ የበላይነት እንዲመጣ አይደለም፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት እንዲረጋገጥ ነው። ይህች ሀገር ሰላም አግኝታ ቀጣይ ሆና እንድትኖር ነው ኦሮሞ እየታገለ ያለው፡፡ ይህም ከግብ እንዲደርስ ከየአቅጣጫዉ በማየት መስራት ይጠይቀናል። ይህ ነው ግባችን፡፡ ለዚህ ደግሞ በየትኛውም ቦታ ይሁን ወደ ጨዋታው እስከገባን ድረስ የተሻለ የሚጫወትበት ቦታ ላይ መጫወት ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ፌደራል የምንልካቸው ሰዎች፤ ብቻቸውን ምንም መሥራት አይችሉም። ዕድላቸውን የሚወስነው እኛ የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ በሀሳብ እንደ ምሰሶ ካልደገፍናቸዉ፣ ቅርንጫፍ ሆነው ነዉ የሚቀሩት፡፡ እናም ምሶሶ እና ግንድ ላይ እንስራ። ግንዱ ጠንካራ ከሆነ፣ ቅርንጫፉ የትም መሄድ አይችልም፤ በዚህ ላይ በብስለት ልንሰራ ይገባል። ወደ ኃላ ማለት የለብንም ብለን ነው እነጂ የሚገባበት ቦታ ገብተን ለመስራት ማናችንም የምናቅማማበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ከዚህ ወደ ኋላ አንልም፤ ይህ ሲሆን ግን እኔ በግሌ ብቻዬን ወደፊት ወጥቼ፣ ሁሉንም ነገር አሳካለሁ ማለት አይደለም ፡፡ እንደ አመራር መሥራት የሚችሉትንም ማብቃት አለብኝ። ሌሎች ለነገ አመራርነት ብቁ የሆኑ፤ ፖለቲካው ገብቷቸው ሊሰሩበት የሚችሉ ቆራጥ፤ ተቆርቋሪ፤ ልባም፤ ሙሉ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን አምጥቶ በማለማመድ መሥራት ትልቅ ጥበብና አመራርነት ይጠይቃል፡፡ እንዲህ እየሠራን ነው የመጣነው፡፡
እኔም በግሌ ዛሬ የዚህች ሀገር አመራር ብሆን፤ ማንም ያላገኘውን ዕድል እንዳገኘሁ ይሰማኛል። ይቅርና በኢትዮጵያ በአሜሪካ ውስጥ ሰው ለስልጣንና ለወንበር ብሎ ነው ይገዳደል የነበረው። ለግል ስም ከሆነ ማንም ያላገኘውን ዕድል ነው ያገኘሁት፡፡ ነገር ግን እኔ የምኖረዉ ለግል ስሜ ሳይሆን ለህዝቤ ነው፡፡ ለህዝቤ ደግሞ መሥራት በምችለው ቦታ ላይ ነው መሥራት ያለብኝ፡፡ ምክንያቱም ክብር፤ ሞገስና ፍቅር አጎናፅፎ ለዚህ ያበቃኝ የለማ የግል ብቃትና ችሎታ አይደለም፤ይህ ህዝብ ነው፡፡ የት ጋር ብሰራ ነው ዉጤት ላመጣ የምችለው የሚለውን አስቤ ከማንኛውም ነገር ነፃ በመሆን መሥራት አለብኝ፡፡ በሥልጣን ዕይታ ካየነው ማንም ሰው ያላገኘውን ዕድል ነው ያገኘሁት፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ዛሬ መቀበል ነው የሚገባኝ፡፡ እሱ ሳይሆን ግን እኔ የግል ክብር የለኝም። ክብሬ ከህዝቤ ጋር ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ክብር ሲያገኝ ነው፣ እኔም አብሬ የምክብረው፡፡ በዚህ መልኩ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ በዚህ ረገድ ህዝባችን ምንም ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም፡፡ ድርጅታችን የሚወስነው ውሳኔ ባለን እዉቀት፣ አቅማችን በፈቀደውና በተረዳነው መንገድ ሁሉ፣ ይህንን ህዝብ በሚጠቅም መንገድ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረስን በኋላ ሌላ አካል ፈርተዉ፣ በሌላ ትእዛዝ ይሰራሉ ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ሞኝ ነው፡፡ ኦህዴድ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ታዞ የሚሰራ ከሆነ ሞኝ ነው ማለት ነዉ፡፡ ለራሱ ይጠፋል እንጂ ይህን ህዝብ ማጥፋት አይችልም፡፡ የዚህን ህዝብ ትግልም ሊያጨልም አይችልም፡፡ የህዝባቸንን ትግል አናጠፋውም፤ ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ መሥራትና በበሳል መንገድ ነው መጓዝ ያለብን፡፡
ባለፉት ዓመታት ሲሰሩ የነበሩ ነገሮች ምንድናቸው? ከላይ ያለው ንፋስ ምን ይመስላል? በዚህ ውስጥ በምን ወቅት ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው? የሚሉትን በሰከነ መንገድ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ተረጋግተን በማየት ነው ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡ በመሆኑም ህዝባችን፣ የድርጅታችን አባላትና የመንግስት መዋቅርም ጥርጣሬ ሊገባቸው አይገባም፡፡ ይህ ስኬታማ እንዲሆን ተረዳድተን መሥራት ይገባናል፡፡ ትናንት በጋራ የጀመርነውን ትግል ከግብ ለማድረስ አውቀን በመግባባት ከፊታችን ለሚጠብቀን ትግል ዝግጁ ልንሆን ይገባል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው ለህዝባችን ጥቅም በማስብ እንጂ ሌላ ጉዳይ ኑሮን አይደለም፡፡ ለግለሰብ ወንበርና ጥቅም ተብሎ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ገለቶማ!
በክልሉ መ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የተረጎሙት
“ይህቺን አገር ለመለወት ኦሮሚያን መቀየር አለብን”

Read 4438 times