Sunday, 04 March 2018 00:00

“ከሁሉም ያልጠበቅሁት በሽብር መከሰሴን ነው” (ናትናኤል መኮንን- ከ6 ዓመት እስር በኋላ)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 • ወጣቶች እኛን ለማስፈታት ህይወታቸውን አጥተዋል
   • ትግሉን እቀጥላለሁ፤ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ
   • ለዚህች አገር ችግር መፍትሄው ውይይት ነው
   • ህውሓት አላፊ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ዘላለማዊ ነው

    ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የጀመሩት በ1993 ዓ.ም ሲሆን የቀድሞውን ኢዴፓ መድህን፣ (አሁን ኢዴፓ) በመቀላቀል ነበር፡፡ አቶ ናትናኤል መኮንን፤ በምርጫ 97 የአራት ፓርቲዎች ጥምረት በሆነው ቅንጅት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን የቅንጅት አመራሮች ሲታሰሩ፣ እሳቸውም ለ1 ዓመት ከ10 ወር ታስረው ተፈትተዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም በ”አንድነት” ፓርቲ ውስጥ ከመሥራችነት አንስተው፣
እስከ አመራርነት ድረስ ያገለገሉ ሲሆን በ2004 ዓ.ም በአሸባሪነት ተከስሰው፣ ከ6 ዓመት ተኩል በኋላ ክሳቸው ተቋርጦ ሰሞኑን ተፈትተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከመምህሩንና ፖለቲከኛው ናትናኤል መኮንን ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፤ እንዴት ለእስር እንደተዳረጉ፣ስለ ወህኒ ቤት ቆይታቸው፣ ስለ ቤተሰባቸው ሁኔታ፣ ስለ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ ችግሮች እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ጠይቃቸዋለች፡፡

    በምርጫ 97 ማግስት፣ ለሁለት ዓመት ገደማ ታስረው ቢፈቱም፣ ትግሉን ቀጠሉበት ማለት ነው?
በምርጫ 97 ጊዜ በቅንጅት አመራሮች መካከል ማለትም በእነ አቶ ልደቱ፣ በኢ/ር ኃይሉና  በሌሎችም መካከል የነበረው ሽኩቻና እሰጥ አገባ፣ቅንጅትንም ትግሉንም ለውድቀት ዳርጎታል ብዬ ስለማምን ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ስለዚህ ከዚያ ሁሉ መከራ፣ ግርፋትና እስራት ከወጣሁ በኋላ ሰላማዊ ትግሉ መቀጠል እንዳበት ራሴን አሳምኜ ነበር፡፡ እናም ከሌሎች እህቶችና ወንድሞች ጋር ትግሉን ቀጥዬ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ በወቅቱ በተቃውሞው ጎራ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች፤ እርስ በርስ መሻኮታቸውን ትተው፣ በሰላማዊ ትግሉ ከገፉ፤ የገዢውን ፓርቲ አመለካከትም ሆነ እርምጃ መግታት ይችላሉ ብዬ ስላመንኩኝ፣ “አንድነት” ፓርቲን በማዋቀርና በማደራጀት ጉልህ ሚና ተጫውቼአለሁ፡፡ ከመስራቾቹና ግንባር ቀደም ከሆኑት አንዱ ነበርኩ፡፡
በአመራር ደረጃም ሰርተዋል?
አዎ! የአንድነት የማዕከላዊ ምክርት ቤት አመራር ሆኜ፣ በ2004 ዓ.ም በሽብርተኝነት ተከስሼ፣ እስክታሰር ድረስ የምችለውን ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡
እንዴት ነበር ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ?
ያው ሥራዬ መምህርነት ነበር፡፡ የምሰራው ደግሞ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኝ አንድ የግል ት/ቤት ነበር፡፡ ዕለቱ የ2004 ዓ.ም የመጀመሪያው የስራ ቀን ነበር፡፡ ስራ ውዬ፣ በትራንስፖርት ከጓደኞቼ ጋር እየመጣሁ ሳለ፣ አዋሬ አካባቢ ስንደርስ፣ የያዝነው የህዝብ ትራንስፖርት መኪና ከኋላም ከፊትም ተከበበ፡፡ እኔ ገምቻለሁ ምክንያቱም በዛን ሰሞን ሰዎች እየተያዙ የነበሩ፡፡ እናም በማንኛውም ሰዓት እስር ሊገጥመኝ እንደሚችል እጠብቅ ነበር፡፡  እስሩ እንደሚመጣ ብጠብቅም በሽብር ወንጀል እከሰሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው ስርዓቱ ጠንካራ ታጋዮችንና ድርጅቶችን፣ ለእምነቱና ለአስተሳሰቡ ፅኑ አቋም ያለውን ግለሰብና የፖለቲካ ሰው ከማሰር እንደማይመለስ አውቃለሁ፤መግደልም እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ ከእነዚሁ ሁሉ ያልጠበቅሁትና ያልገመትኩት ግን በሽብር መከሰሴን ነው፡፡ ይሄ በጣም የደነገጥኩበት አጋጣሚ ነው፡፡
በተያዝክ ወቅት ብቻህን ነበርክ?
ስያዝ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ አሁን የትኛው ጣቢያ፣ ጋዜጠኞች እንደነበሩ አላስታውስም፡፡ ካሜራ ነበር፤ በትንሹ 15 እና 16 የሚሆኑ ደህንነቶችና ፌደራል ፖሊሶች ነበሩ፡፡ “በሽብር ተጠርጥረሃል፤ እጅ ስጥ” ሲሉኝ መገረምና ያለማመን ስሜት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር እጄ የተያዘው፡፡ በወቅቱ እኔና መሰሎቼን ሰላማዊ ታጋዮች፣ ሽብርተኛ ብሎ ሲይዘን፣ መታዘብ የቻልኩት፣ ሥርዓቱ ምን ያህል እንዳበደ ነው፡፡ ይህን የምለው መንግስት በወቅቱ ምን እንደምንሰራ፣ እንቅስቃሴያችን ምን እንደነበር፣ ሌላው ቀርቶ ለሰላማዊ ትግል የነበረንን ፅኑ አቋም ጠንቅቆ እያወቀ፣አሸባሪ ብሎ ሲይዘን ነው፡፡
በማዕከላዊ ቆይታህ ምን ገጠመህ?
የመከራና የስቃዩ ጊዜ የነበረው በማዕከላዊ ነው፡፡ ማዕላዊ እያለሁ እጅግ የሚዘገንኑ የግርፋት አይነቶች፣ መኖርን የማያስመኙ ስቃዮች ተፈፅመውብኛል፡፡ ቶርቸር ተደርጌያለሁ፤ ገልብጠው ገርፈውኛል፣ ተሰቅያለሁ፤ ያላየሁት መከራ የለም፡፡
ተሰቅያለሁ ሲሉ --- እንዴት ነው?
 ለ21 ሰዓታት ያህል ሁለት እጄ በካቴና ወደ ላይ ተወጥሮ፣ በጣቴ ብቻ ቆሜ፣ ከባድ ጊዜ አሳልፌያለሁ። ያንን ቁስልና ህመም መሸከም ከባድ ነበር፡፡ ግርፋትና ስቃዩ ሲበዛብኝ፣ “እንደ አህያ እየበላሁ አልገረፍም ወይ ግደሉኝ አለበለዚያ ራሴን እገድላለሁ” ብዬ ምግብ ሳቆም፤ “እኛ አንገድልህም እስትከስል ግን እንገርፍሃለን” ሲሉኝ፣ ለስድስት ሰባት ቀናት ምግብ አቁሜ፣ ህይወቴ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኜ እንኳን ፖሊስና መርማሪዎች ደጋግፈው እየወሰዱ ይገርፉኝ ነበር። ይሄ የጭካኔያቸውን ጥግ ያየሁበት ነው። እየገረፉኝ፤ “የጠየቅንህ ከባድ ነገር አይደለም፤ ከአሸባሪው ግንቦት 7  ጋር ግንኙነት አለኝ ብለህ እመንልን፤ ይህን እምቢ ካልክ ኤርትራ በመሄድ የቦንብ ስልጠና ወስዶ፣ አዲስ አበባን ለማፈንዳት ሲንቀሳቀስ ያዝነው ብለን እንከስሃለን” በማለት በተደጋጋሚ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ብቻ በማዕከላዊ፣ ነፍስና ስጋዬ አልተለያዩም እንጂ የመከራውን አይነትና ብዛት ማስታወሱ ራሱ ስቃይ ነው፡፡ ማእከላዊ ሁለት ወር ስቆይ፣ “ሳይቤሪያ” በሚባለው ቀዝቃዛው ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ፡፡
ወደ ቃሊቲ ስትዘዋወሩ፣ አንፃራዊ እፎይታ ታገኛላችሁ ይባላል….?
ልክ ነው፡፡ በቃሊቲ አንፃራዊ እረፍት ነበረን። ድብደባውና በየጊዜው እየወጡ መገረፍ የለም። ነገር ግን ቃሊቲ ከወረድን በኋላ እኛን መጠየቅ የሚፈልግ የትኛውም ሰው፤ አይፈቀድለትም ነበር። ይህን መብታችንን ተገፈን ነው የከረምነው፡፡ እኔ ከባለቤቱና ከልጆቼ በስተቀር ሌላ ወዳጅ ዘመድ አይጠይቀኝም ነበር፡፡ ከአራት አምስት ሰዎች ጋር ነበር፤ ለረጅም ጊዜ የታሰርኩት፡፡ እዛም ሆነን ደሞ ትግል አለ፡፡
ምን አይነት ትግል?
ሰብአዊ መብት ሲጣስ እንመለከታለን፡፡ የመብት ጥሰቱ ቀጥታ እኛ ላይ ባይሆንም የተለያዩ እስረኞች ላይ ጥሰት ሲፈፀም፣ ሲገረፉና ሲሰቃዩ እንቃወማለን፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተሰብ ይቀጣል፡፡ ከአንድ ወር እስከ አራት ወር ከቤተሰቤ እንዳልገናኝ ተቀጥቻለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ለተከታታይ አራት ወር፣ ከቤተሰቤ እንዳልገናኝ ተቀጥቼ፣ ልጆቼና ቤተሰቦቼ ሲያለቅሱ ቆይተዋል፡፡ እኔ ቃሊቲም ቂሊንጦም ዝዋይም ታስሬያለሁ፡፡ እስር ቤቶቹ ውስጥም እስር ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ቅጣት ቤቶች፣ እስር ቤት ውስጥ ያሉ እስር ቤቶች ይባላሉ። እያዘዋወሩ ሲያስሩኝ የነበረው በቅጣት ቤቶቹ ነው። በዚያ ቦታ የነበረው አያያዝ የከፋ ነው፡፡ እንደ ልብ አንንቀሳቀስም። እንደ ሌላው እስረኛ፣ ቤተሰባችን እንደ ልባችን አይጠይቀንም። ሌላው ቀርቶ፣ ሻይ ቡና እንኳን በቅጡ አናገኝም ነበር፡፡ እነዚህን መብቶች፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ሴት ልጅ የደፈሩ፣ ነፍስ ያጠፉ እስረኞች ሲያገኙ፣ እኛ ተነፍገን ነው የቆየነው፡፡
በድብደባው ወቅት የደረሰብዎት ከፍተኛ ጉዳት አለ?
ማዕከላዊ በነበርኩበት ጊዜ በደረሰብኝ ድብደባ፣ የቀኝ ጆሮዬ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ታምቡሩ ተቀዶና ኢንፌክሽን ፈጥሮ፣ በጆሮዬ ፈሳሽ ይፈስስ ነበር። ለአራት አመታት ያህል በጆሮዬ ምክንያት ሆስፒታል ተመላልሻለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ጆሮዬ በግማሽ ነው የሚሰማው፡፡ ሌላው በደረሰብኝ ድብደባ፣ የእግሬ አጥንት መሰንጠቅ ደርሶብኝ፣ ለሶስት ወር ያህል እያነከስኩ ነበር የምሄደው፤ አሁን የዳነ ይመስለኛል፡፡
ከ6 ዓመት እስር በኋላ ከቤተሰብ ጋር ተቀላቅለዋል። የልጆችዎና የቤተሰብዎ ስሜት ምን ይመስላል? እርስዎ በታሰሩ ወቅት ቤተሰብዎ በምን  ይተዳደር ነበር?
ከሌላው አባት የተለየሁ ነኝ ማለት ባይሆንም፣ ልጆቼን በጣም እወዳለሁ፡፡ በዚያው መጠን ትግሉንም እወዳለሁ፡፡ በቤቴ ለልጆቼና ለባለቤቴ የተለየ ፍቅርና አቅርቦት አለኝ፤ እንክብካቤም አደርጋለሁ፡፡ ከቤት ውጭ ደግሞ ትግሉን በደንብ አካሂዳለሁ፡፡ ለትግሉ የሚገባውን ዋጋ እከፍላለሁ። ለእኔ ልጆቼን ማጣት ከባድ ነው። ማዕከላዊ ተዘቅዝቄ እየተገረፍኩ እንኳን ልጆቼ ምን ሆነው ይሆን፣ የት ወድቀው ይሆን? ምን በልተው ይሆን? እያልኩ እነሱን አልም ነበር፡፡ ልጆቼን ደግሞ አስቢያቸው… በልጅነት አዕምሯቸው ምን ሊቀረፅባቸው እንደሚችል፡፡ ከተያዝኩበት ጊዜ ጀምሮ ከእናታቸው ጋር በየታሰርኩበት ቦታ  እየተንከራተቱ፣ እያለቀሱ፣ ዞር በሉ እየተባሉና የሰው ፊት እያዩ፣ በለጋ ዕድሜያቸው የትግሉ አካል ሆነዋል ተጎድተዋል - በስነ ልቦናም ጭምር ነው ጉዳታቸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከቤት ስወጣ እንኳን ተመልሼ የምመጣ አልመስል እያላቸው ይሳቀቃሉ፡፡ ከዚህ በላይ ጉዳት የለም፡፡ ኢኮኖሚን በተመለከተ ባለቤቴ እንደኔው መምህርት ናት፡፡ ትሰራለች፤ ግን ተጋግዞ መኖርና ለብቻ ጫናን መሸከም ልዩነቱ ሰፊ ነው፤ ነገር ግን ወገኖቼ፣ የትግል አጋሮቼ፣ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ… ባለቤቴን ልጆቼን አይዟችሁ በማለትና በመደገፍ፣ ለእኔ የሞራል ስንቅ ሆነውኛል፣ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የእነሱ ድጋፍና አይዟችሁ ባይነት፣ ሞራሌን ጠብቆ፣ በትግሉ እንድፀና አድርጎኛል፡፡
በቃሊቲ የእስር ቆይታዎ፣ ጊዜዎትን የሚያሳልፉት እንዴት ነበር?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ለሌላው የተፈቀደው አብዛኛው መብት፣ በሽብር ወንጀል ለተከሰስነው የፖለቲካ እስረኞች የተፈቀደ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የምናነባቸው መፅሐፍት ከውጭ እንዲገቡልን አይፈቀድልንም፡፡ አልፎ አልፎ በኃላፊዎቹ በጎ ፈቃድ፣ ከግቢው ቤተ - መፅሐፍት አንዳንድ መፅሐፍት እየወሰድን እናነባለን፡፡ የፖለቲካ መፅሐፍት አይፈቀድም፡፡ ከቤተ መፅሐፍቱም ልቦለድ መፅሐፍት ናቸው አልፎ አልፎ የሚፈቀዱት፡፡ ለሌላው የተፈቀደው በግቢው የሚሰጠው የትምህርትና የሙያ ስልጠና ለእኛ አይፈቀድም፡፡ ነገር ግን ጊዜያችንን በአገሪቱ ጉዳይ ላይ በመወያየትና፣ በመነጋገር እናሳልፍ ነበር፡፡
እርስዎ ከማን ጋር ነበር የታሰሩት?
እርግጥ ከእነ አንዷለም ጋር አብረን አልታሰርንም፤ ነገር ግን ከኦሮሞ ልጆች፣ ከእስላም መፍትሄ አፈላላጊ አባላት ከእነ አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ከእነ ኦልባና ሌሊሳ፣ ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ድርጅት የመጣ አህመድ በሽር ከተባለ ሰው ጋር አብረን ስለታሰርን፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ ሰብሰብ ብለን እንወያይ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሰውነታችንን ለማፍታታት ግቢ ውስጥ እንዘዋወራለን፤ ስፖርት ለመስራት እንሞክራለን፡፡
የአመጋገብ ሁኔታስ እንዴት ነበር?
ጥሩ አይደለም፡፡ አይመችም፡፡ በጉጉትና በናፍቆት የምንጠብቀው በሳምንት አንድ ጊዜም ሆነ ሁለት ጊዜ፣ ከቤተሰባችን የሚመጣልንን ምግብ ነው፡፡ ስጋ፣ በዓላት ተጠብቀው፣ እንደ ነገሩ ነበር። በአዘቦት ቀን ወጡ ቅባት የለውም፤ እንጀራው ቀጭ ቀጭ የሚል ነገር ያለው፣ ከአሸዋ የተቀላቀለ የሚመስል ነው፡፡ ብዙ ሰው ጤናው የታወከ ነው። ደስ አይልም፡፡ ቅሬታ ስናቀርብ፣ አንድ ሰሞን ሻል ይልና ከዚያ ይመለሳል፡፡
ከስድስት ዓመት ተኩል እስር በኋላ፣ አገሪቱን በምን ሁኔታ አገኟት?
ሁለት ዓይነት ስሜት ነው ያስተናገድኩት። አንደኛው ህዝቡና ተቃዋሚዎች ያደረጉት ትግል፣ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርሶ፣ ማንገዳገድ የጀመረበትና በተለይ ከ1997 በኋላ ትግሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሆኖ አይቻለሁ። በዚያው መጠን ደግሞ አገሪቱ በብሔርና በዘር ተከፋፍላ፣ አስከፊ ያለመግባባትና ግጭት ሰፍኖባት ነው ያገኘኋት፡፡ በሌላ በኩል የተደራጀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተዳክሞ፣ የህዝብ ፍርሃት ተገስሶ፣ ወጣቶች ታንክ ፊት ቆመው መጮህና የነፃነት መዝሙር ማሰማት ቢችሉም፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራር የተዳከመና ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት የጠፋበት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
እንግዲህ በአገሪቱ ላይ ተስፋም አለ፡፡ ይሄውም ህዝብ ከፍርሃት ተላቅቆ፣ አምባገነንነትንና ጭቆናን እምቢ ብሎ አደባባይ መውጣቱ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ እኛም የተፈታነው በህዝቡ ትግልና ትግሉ ባመጣው ተፅዕኖ ነው፡፡ እኛን ለማስፈታት ወጣቶች ሞተዋል። ተገርፈዋል፡፡ የተፈታነው በመስዋዕትነት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍ ያለ አክብሮትና ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ እርግጥ ነው አሁንም በየእስር ቤቱ የቀሩ በርካታ የኢትዮጵያ ልጆች፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እነዚህም ወገኖች እንዲፈቱ እጠይቃለሁ፡፡
እርስዎ በአመራርነት የነበሩበትና የመሰረቱት “አንድነት” መፍረሱ ምን ስሜት ፈጠረብዎ? ወደፊትስ በትግሉ ለመቀጠል አስበዋል?
እንደሚታወቀው ከመረጃ እርቄ ነው የቆየሁት። ጓደኞቼም እንደዛው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ወቅታዊ ሁኔታውን ማጤን፣ ማንበብና ከትግል አጋሮቼም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር መወያየት ይኖርብኛል። ብዙ የደከምንበትና ዋጋ የከፈልንበት “አንድነት” ፓርቲ ለገዢው ፓርቲ ስጋት ሆኖ በመገኘቱ፣ እንዲፈርስ በመደረጉ በጣም አዝኛለሁ፡፡ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለዚህ ነው የተደራጀ የተቃውሞ ትግል ተዳክሟል ያልኩሽ። ይሄ ትግል መልሶ እንዲያንሰራራና የህዝቡን ትግል በተቀናጀ መልኩ መርቶ ውጤት እንዲመጣ፣ አቅጣጫ የሚያሳይ ጠንካራ ፓርቲ እንደሚያስፈልግ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ባሉ ደርጅቶች ውስጥ ገብቶ ለመታገልም ሆነ አዲስ ፓርቲ ለመመስረትመ ገና ብዙ ውይይትና ንግግር ማድረግ ያስፈልጋል፤ ትግሉን ግን እቀጥላለሁ፤ የሚጠበቅብኝን ዋጋ ከመክፈል ወደ ኋላ አልልም፡፡ እስካሁንም የታገልነው በዚህች አገር የዴሞክራሲ ልዕልና እንዲረጋገጥ፣ ስልጣን ከአንድ ፓርቲ (መንግስት) ወደ ሌላ በሰላማዊ መንገድ እንዲሸጋገር፣ አገሪቱ የነፃ ተቋማት ባለቤት ሆና፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ዜጎች በአገራቸው የፈለጉትን ተናግረው ፅፈው የሚኖሩበት አገር ለመገንባት ነው። እኔም ትግሉ ጫፍ ደርሶ ተሳክቷል ብዬ የማምነው ያኔ ነው፡፡ ይህ እስኪረጋገጥ ትግሉ ይቀጥላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “በፈቃዴ ስልጣን እለቃለሁ” ማለታቸው እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተመለከተ እለቃለሁ የሚሉት፣ መጀመሪያም ያልያዙትን ስልጣን ነው። መጀመሪያም ስልጣን ይዘዋል የሚል እምነት የለኝም፤ በግሌ፡፡ የእርሳቸው መውረድ በዚህ አገር ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ ብዬ አላምንም። ከኋላ ያለው አስተሳሰብና ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነ አመራር እስካልተቀየረ ድረስ የሚመጣ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ጉዳዩ የግለሰብ ጉዳይም አይደለም። እሳቸው ቢሄዱም መሰላቸው ነው የሚመጣው፤ በዚህ ለውጥ አይመጣም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም ስንመለከት፣ አገሪቱ እስካሁን የኖረችው ባልታወቀ አዋጅ ነው፡፡ አሁን አዋጁ፣ ህገ - ወጥ አፈናውንና ግድያውን ህጋዊ ማድረግ ነው፡፡ ትግሉን እያጧጧፈ የመጣው ህዝብ ላይ፣ የስነ ልቦና ጫናና ፍርሃት ለማንገስ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ አገሪቱ ላይ በተለይ ከ97 ዓ.ም በኋላ አፈናው፣ ግድያውና ወከባው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የቀጠለው፡፡ ይህንን በአዋጅ ህጋዊ ማድረግ ነው ዓላማው፡፡
ለዚህች አገር የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ ምንድን ነው ይላሉ?
ለዚህች አገር መፃኢ ዕድል መቃናት ትክክለኛው መፍትሄ ንግግር ነው፡፡ ንግግር ሲባል በ97ም ሆነ ከዚያ በኋላ የነበረው አይነት የይስሙላ ንግግር ሳይሆን እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣ፣ በዚህች አገር ላይ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን፣ ተቃዋሚዎች፣ ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በአገር፣ በዴሞክራሲና በሁሉም ጉዳዮች ላይ እውነተኛ ንግግር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ንግግር አዲስ አስተሳሰብና አገር መገንባት አለብን። ንግግሩ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ መንግስት ከአባል ድርጅቶቼ ጋር “ከሰማይ በታች ባሉ ሁሉም ጉዳዮች ላይ ንግግር አድርጌያለሁ” ብሏል፤ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ጋር በብሄራዊ ደረጃ መነጋገር አለበት፤ እሱ ብቻ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ሆኖ መቀጠል የለበትም፡፡ ንግግሩ፤ ህገ - መንግስቱን ጨምሮ ለአገሪቱና ለህዝቧ ደህንነትና የፍትህ ችግር መንስኤ በሆኑት በሁሉም ጉዳዮች ላይ መሆን ይገባዋል፡፡ ቂምና ቁርሾ በፈጠሩ፣ ህዝቡን እርስ በእርስ የጎሪጥ ያስተያዩ ሀሳቦች --- ለንግግር በግልፅ መቅረብ አለባቸው፡፡ አለባብሰን ሸፋፍነን እያለፍንና በአረም እየተመለስን ነው ያለነው፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር አያይዤ የማነሳው፣ በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብና ህውሓት የተለያዩ ናቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ ህውሓትን ወደ ስልጣን ለማውጣት፣ ልጆቹን መስዋዕት እንዳደረገ አምናለሁ፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥም እንደ ሌሎቹ ህዝቦች እንዳልተጠቀመም አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ህውሓት ለትግራይ ህዝብ የተለየ ጥቅም አምጥቶለታል ብዬ አላምንም፡፡ የትግራይ ህዝብ ከህውሓት ከተጠቀመው በላይ ህውሓት በትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ አንድም ወደ ስልጣን ወጥቶበታል፤ በኋላም ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እያጋጨ፣ ምሽግ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት አንድ የታወቁ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ፣እንደ ተራ የህውሓት ካድሬ ወርደው፤ “ህውሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። በቅርቡም ህውሓት፤ “ተቃዋሚዎች፤ ህውሃትንና የትግራይን ህዝብ ለመነጣጠልና ህውሃትን ለመምታት እየጣሩ ነው” የሚል አሳዛኝ መግለጫ አውጥቷል፡፡
እኔ ግን በግሌ ህውሓት አገሪቷ ላይ የዘር ፖለቲካ እንዳንሰራፋ፣ ኢትዮጵያን በፖለቲካም በኢኮኖሚም የሚጎዱ ስራዎችና እርምጃዎች እንደወሰደ አምናለሁ። ህውሃት የራሱን የቡድኑን ጥቅመ ከማስከበር ባለፈ መቼም ቢሆን የትግራይን ህዝብ እንደማይወክልም አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ከጫካ እስከ ዛሬ የትግራይን ህዝብ ምሽግ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው፡፡ ስለዚህ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ህውሃትና የትግራይን ህዝብ ለይቶ መመልከት አለበት፡፡ ምክንያቱም ህውሃት አላፊ ነው፤የትግራይ ህዝብ ግን ይቀጥላል። ህውሃት እንደ አንድ ስርዓት ነገ ይወድቃል፡፡ የትግራይ ህዝብ ዘላለማዊ ነው፡፡ ስለሆነም በትግል ላይ ያሉ ሀይላትም ሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር ያለውን የቆየና የጠበቀ ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። እኔ በግሌ ስልጣን ላይ ያለው ህውሐት፤ ምንም ያህል ቢያሰቃየኝ፣ የትግራይን ህዝብ ግን በክፉ አይቼው አላውቅም፡፡
የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እንደሚያስፈልገው አምናለሁ፡፡ በሚመጣው ሥርዓት የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ምኞት አለኝ፡፡ ምኞት ብቻ ሳይሆን እታገላለሁም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብም ለለውጡ መታገል አለበት፡፡ ህውሃት በስሙ የሚወስደውን እርምጃም ማውገዝ አለበት፡፡ በዚህ መንገድ ነው፤ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት የምንችለው፡፡
በመጨረሻ የሚያስተላልፋት መልዕክት …   
በመጨረሻ የምናገረው፤ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ ያለውን አጋጣሚና የመጨረሻ እድል፤ ለውይይትና ለንግግር በሩን በመክፈት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በውጭም በውስጥም ያሉ የፖለቲካ ታጋዮችና ለመፍትሄ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁሉ ጋብዞ፣ በአገሪቱ ህልውናና መፃኢ ዕድል ላይ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ በተረፈ አሁንም በእስር ላይ ያሉት በሙሉ መለቀቅ አለባቸው። ውይይትና ንግግር ከተጀመረ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞችና ስደተኞች አንድ ላይ ሆነው ነው መሆን ያለበት፡፡ ወገኖቼን፣ በእስር እያለን አብረውን በህሊና ቤተሰባችንን ሲደግፉና ሲንከባከቡ የነበሩትን፣ ትንሽ ዋጋ ከፍለን ብዙ ያከበሩንን ---- ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አሁንም በቀጣይ ለዚህች አገር ግንባታ የምችለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፡፡ ጓደኞቼም አቋማቸው ይሄው ነው፡፡ ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡

Read 3058 times