Sunday, 04 March 2018 00:00

‘ክብ’ ኳስ ‘ስታንከባልለን’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  “እንዴት ከረማችሁሳ!”
አንድ ጊዜ ያወራናት ‘በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተች’ ነገር አለች…አዲስ አበባ ስቴድየም በግራ ጥላ ፎቅ በሌላኛው፣ በመሰረተ ትምህርት ዘመን የሆነ ነው፡፡ ሁለት ተመልካቾች በሆነ  ነገር ይጋጫሉ፡፡ ቃላት ሲመላለሱ ይቆዩና መጨረሻ ላይ አንደኛው ሌላኛውን ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ሰው የመሀይምነትን ጥቁር መጋረጃ ይቀዳል፣ አንተ መልስህ ትሰፋለህ፣” ይለዋል፡፡ በዘንድሮ ቋንቋ ቀውጢ ነው የተፈጠረው፡፡ ግን አባባሏ አሪፍ አይደለች! ያኔ እናትን፣ አባትን፣ ቤተዘመድን እያነሱ መዝለፍ እንደ ዘንድሮ አልነበረማ! አልነበረም ብቻ ሳይሆን አለ ለማለትም የሚያስቸገር ነው፡፡ ዘንድሮ ምን እንደተፈጠረ አንድዬ ይወቀው፡፡
እናላችሁ… ያኔ በኳስ ችሎታቸው ምን የመሳሰሉ ተጫዋቾች፤ ከጨዋታ በኋላ አይደለም ስለ መኪና መግዛትና ስለ ቤት መሥራት ሊያስቡ፣ የሻወርና የአውቶብስ ይቸግራቸው ነበር፡፡ እንኳን ፎር ስታርና ፋይቭ ስታር ሆቴል ገብተው ሊመገቡ፣ ቤታቸው የሚያገኟት ምግብ ከማንኛውም ተራ ኢትዮዽያዊ ቤት ከምትገኘው የተለየች አይደለችም፡፡ ዘንድሮ ነገሮች እንዲህ ሊለወጡ!
“እኔ የምለው ያ የአጎትህ ልጅ ሥራ ጀመረ?”
“ሥራ ቢሉሀ ሥራ ነው!””
“ምን አይነት ሥራ ነው የሚሠራው?”
“ኳስ!”
“ኳስ ማለት…?”
“ኳስ ማለትማ ኳስ ተጫዋች ሆኗል ማለቴ ነው።”
ከት ብሎ መሳቅ… ትን እስኪለው ድረስ፡፡
“መቼም ዘመዴ ነው ብለህ ነው … እንዲህ ከፍ፣ ከፍ የምታደርገው፣ የእኔም ትንሹ ሙቹ እኮ ገና በአምስት ዓመቱ፣ ቀኑን ሙሉ ኳስ ሲራገጥ ነው የሚውለው፡፡”
“ለሳቁ ትደርስበታለህ፣ ይልቅ ደሞዙን ብትጠይቀኝ ይሻላል፡፡”
“ለኳስ ደሞዝ ይከፈል ጀመር እንዴ?”
“አዎ፣ ወደ መቶ ሀያ ነው፣ መቶ ሠላሳ ሺህ ብር ይከፈለዋል፡፡”
ዝምታ፡፡ ረጅም ዝምታ፡፡
“አልገባኝም፡፡”
“እኔም አልገባኝም፡፡ ግን እውነቱ የአጎቴ ልጅ በወር ያን ያህል ነው የሚከፈለው፡፡ እንደውም አነሰኝ ብሎ ሌላ ክለብ እየፈለገ ነው አሉ፡፡
ለኳስ! ለእኛይቱ ኳስ!  አዎ፣ ለእኛይቱ ኳስ፡፡
ይህን መሰል የንግግር ልውውጥ፤ በስንት ሰዎች መካከል ይደረግ እንደሆነ አንድዬ ይወቀው፡፡ ግን ኳስ አካባቢ የሚነገረው የፍራንክ መጠን፣ ብዙዎችን ማስደንገጥ ብቻ አይደለም፣ ያስገርማልም፡፡ ኳሳችንን ከምስራቅ አፍሪካና ከመላዋ አፍሪካ ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ክፍያው ነው፡፡  
“ስሚ እጮኛሽ ምንድው የሚሠራው?”
“ኳስ ተጫዋች ነው፡፡”
“እኔ የጠየቅሁሽ ሥራው ምንድነው ነው እንጂ፣ ምን ጨዋታ ይወዳለ አልኩኝ እንዴ?”
“ነገርኩሽ አኮ፣ ሥራው ኳስ ተጫዋች ነው፡፡”
“እና እሱ ቅሪላ እያለፋ፣ አንቺ ከየት አምጥተሽ ነው እንዲሀ ያማረብሽ!”
“እድሜ ለእሱ፣ በወር እኮ መቶ ሺህ ብር ነው ደሞዙ፡፡”
ጓደኛ ሆዬ፤ ድንጋጤዋ እንዲለቃት ስምንት ጊዜ ታማትባለች፡፡ ሰማንያም ብታደርገው በቀላሉ የሚለቅ ድንጋጤ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…የእሱና እሷ ነገር ካነሳን፣ ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው በዕድሜ ገፍቷል፡፡ አንዴ አግብቶ ፈቷል፡፡ በዚህ ላይ ጤና የለም፡፡ “ይሄ ሪህ እኮ አስቸገረኝ” “ምን እባክህ፣ ስኳሩ እየበጠበጠኝ…” ነው ሁልጊዜ፡፡ እና የሆነ ጊዜ “በቃ ሌላ ሚስት ላገባ ነው፣” አለ፡፡ ለሚያውቁት ሰበር ዜና አይነት ብቻ ሳይሆን እንደ ‘ብታምኑም፣ ባታምኑም’ አይነት ዜና ነበር፡፡ እናላችሁ…አንዱ ጓደኛ ምን ይለዋል.. “ምን እዳ አለባትና ነው አንተን የምታገባው! አንዴ “ጀርባዬን እሺልኝ፣” አንዴ “ሙቅ ውሀ በላስቲክ ስጪኝ፣” እያልክ መከራዋን ልታበላት ነው፡፡ ሌላኛው ጓደኛው ደግሞ ምክር ሰጠው… “ስማ፣ ምከረኝ ካልከኝ አንተ የምታስፈልግህ ሚስት ሳትሆን ቀለብ ከቤት የሆነች የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ ነች፡፡” ይሄ፣ እንደ ‘ጥቆማም’ መሆኑ ነው።  (ቂ…ቂ…ቂ…)
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እዚህ እድለቢስነት በተንሰራፋባት የዓለም ክፍል… የአገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች እድለኞች ናቸው። በጣም እድለኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶች “በሌለ ነገር ገንዘብ መዛቅ” በሚሉት ዘርፍ፤ ይህ ያህል ደሞዝ መዛቅ እድለኝነት ካልሆነ ምን ሊሆን ነው!
ግን አለ አይደል…ኳሳችን የሚወጣበትን ግማሹን ያህል እንኳን ባይሆን አንድ አሥረኛውን ለውጥ ማሳየት አለመቻሉ ያው ቅሽምና ነው፡፡
ብዙዎቹ ክለቦች እኮ ከኳስ የሚያገኙት የሜዳ ገቢ፣ ምናምን የመሳሰሉ ብጥስጣሽ ነገሮች እንጂ እንደሚያፈሱት ገንዘብ ‘ኢንካም ጄኔሬቲንግ’ የሚባል ነገር አላቸው ሲባል አንሰማም፡፡ ስሙኝማ…ኮሚክ ነገር እኮ ነው፡፡ መንደሮች ሁሉ የመጸዳጃ ቤት ያለህ እያሉ፣ ውህ እያሉ፣ መውጫ መግቢያ መንገድ እያሉ፣ አለቆቹ “በጀት የለም” ሲሉ ከርመው “ታዲያ ለኳስ ይህን ያህል የምትከፍሉት ከየት አምጥታችሁ ነው?” ቢባሉ፣ ምን ይመልሱ ይሆን!
እንዲህም ሆኖ ግን… የኳሳችን ስእል ለማየት የሚጓጉለት አልሆነም፡፡ ወሬው ለመስማት የሚጓጉለት አልሆነም፡፡ የምር ግን… አንድ እግር ኳስ ግጥሚያ ተካሂዶ “ጨዋታው በሰላም ነው የተጠናቀቀው” ማለት ቀዳሚ ዜና መሆን አለበት እንዴ!  ታዲያ ምን ሊሆን ነበር! መጀመሪያ ነገር በእግር ኳስ  ጨዋታ ‘ሰላም’ ወይም ‘ረብሻ’ የሚባሉ ቃላት ጎልተው ሲወጡ፣ የሆነ ነገር ተበላሽቷል ማለት ነው፡፡ ዋናው ዜና መሆን ያለበት የቡድኖቹ የሜዳ ላይ የኳሱ እንቅስቃሴ መሆን ሲገባው፣ የተጨዋቾችና የአሰልጣኞች የዲሲፕሊን ጕድለትና የደጋፊዎች ረብሻ ሲሆን፣ የሆነ ነገር ተበላሽቷል ማለት ነው፡፡ ኳሳችን ላይ ብዙ ብልሽት የሚመስሉ ነገሮች እያየን ነው፡፡ ከሳምንት ሳምንት፣ ከወር ወር ከመሻሻል ይልቅ የብልሽቱ ነገር መልኩን ሲለዋውጥ እያየን ነው፡፡
እግር ኳሳችን ጠንካራ፣ በጣም ጠንካራ አመራር የሚያስፈልገን ሰዓት ነው፡፡ ስልጣኑን ለመንሸራሸሪያና የዶላር ውሎ አበል ለመሰብሰቢያ ሳይሆን የእውነትም ስፖርቱን ለማሻሻል ከልባቸው የሚፈልጉ አመራሮች የሚያስፈልገን ሰዓት ላይ ነን፡፡   
በቀደም አንድ የስፖርት ፕሮግራም ላይ አንደኛው ተወዳዳሪ ከውድድሩ ራሳቸውን እንዲያገሉ ሽማግሌ ሁሉ እንደተላከባቸው ሲናገሩ ነበር፡፡ ምን! እንዴት አይነት ነገር ነው! ይሄ አባባል እኮ እውነት ከሆነ ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገርን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄን ያህል የስልጣን ጥማት አለ እንዴ! ጭራሽ በአማተርነት ለማገልገል የሚደረግ ምርጫ ላይ ልቀቅልን ብሎ ነገር ምን ማለት ነው!
እግረ ኳሱን ማን ይምራው፣ ማን አይምራው … ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኗል፡፡ ቤቱ መልኩን ከለወጠ ውሎ ቢያድርም የዘንድሮው ነገር የጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ማን እውነተኛ እንደሆነ፣ ማን እያበለ እንደሆነ መገመት እንኳን አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ “እሱ መግለጫ ለመስጠት ምን ስልጣን አለውና ነው፣ ለሚዲያ መግለጫ የሚሰጠው የሚባል ነገር ስንሰማ ለነገሮች መበላሸት ምንም ተጨማሪ ማረጋገጫ አያስፈልግም፡፡ መጀመሪያ የተባለው ስልጣን የሌለው ሰው፣ እንዴት መግለጫ ለመስጠት ደፈረ! ቀኖች አየጨመሩ በሄዱ ጊዜ ጥያቄዎቹም እየበዙ እየሄዱ ነው፡፡ ምን እየተካሄደ ነው? እውን ይሄ ሁሉ እሰጥ አገባ አመራር ላይ ወጥቶ፣ የኢትዮዽያን አግር ኳስ ለመምራት ነው?
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንድ ጊዜ ይሄ ስልጣን ለመያዝ የሚደረገው እንካ ስላንትያ…አለ አይደል…የሆነ ‘መፔት ሾው’ ምናምን የሚለውን ያስታውሰናል፡፡ ከጀርባ ሆነው ክሮቹን በፈለጓቸው አቅጣጫ ወዲህ፣ ወዲያ የሚጠመዝዙ ሰዎች አሉ እንዴ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከግለሰቦቹ አልፎ የቡድኖች ፍላጎት አለ እንዴ!
የሜዳ ላይ የተጫዋቾች ባህሪይም የሚገርም ነው፡፡ እንዴ ዳኛ የሚገፈትሩ ተጫዋቾች እኮ የቡድን መለያ ለብስው የሚገቡበት ጊዜ እኮ ነው! አይደለም ዳኛ መገፍተር ጫፉን መንካት እኮ ትልቅ የዲሰፕሊን ጉድለት ነው፡፡ ዳኛው፣ አይደለም አንድ፣ አንድ መቶ ግብ ለተቃራኒው ቡድን ከአግባብ ውጪ ቢሰጥ፣ በእግር ኳስ ህጉ ይጠየቃል እንጂ የተበሳጩ ተጫዋቾች፣ ነገር የሚያባብሱ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ፈረንጅ እንደሚለው ‘ህጉን በእጃቸው ሲያስገቡ’፣ ሀይ ባይ የጠፋው፣ ብልሽቱ ምን አይነት ደረጃ ላይ ቢደርስ ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በአሁኑ ጊዜ የስፖርት ጋዜጠኞቻችን፣ አንዳንዶቹ ያሉባቸው ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስለኛል፡፡ ልክ ወገን እንደያዙ ተደርገው ሲተቹ እንሰማለንና፣ ትንሽ ጠበቅ አድርገው ጥያቄ ካበዙ እውነቱ ላይ ለመድረስ አስበው ያደረጉት ሳይሆን ‘ሌላኛውን ወገን ለመጥቀም’ ያደረጉት እንደሆነ አይነት ሲታሰብ ምልክቱን አይተናልና!
ኳሷችን ላይ የሰፈርክ ምንም ሁን ምን ተጠራርገህ ሂድልንማ! ‘ክቧ’ ኳስ እኛንም ‘አንከባለለችን’ እኮ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5368 times