Sunday, 04 March 2018 00:00

ኢትዮጵያ ገና ፈተና ላይ ነች

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(6 votes)

  “--ሐገራችን የቤተ ክርስቲያን ሻኩራና የቄሶች ጽናጽል፤ የመስጊድ ሙዐዚኖች አዛን፣ የጀማ መንዙማ፤ የህጻናት የቡረቃ ጩኸት፣ የትምህርት ቤት ደወል፣ የጎረምሶች እና የኮረዳዎች የፍቅር ዜማ፤ የገጣሚዎች ቅኔ እንጂ የጥይት ጩኸት፣ የሙሾ እና የረገዳ ራሮታዊ ድምጽ የሚሰማባት ሐገር እንዳትሆን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ሐገራችንን የሰይፍ ሳይሆን የሐሳብ ፍጭት የሚሰማባት ዴሞክራሲያዊት ሐገር ማድረግ ይገባናል፡፡ በወጉ ካልታሰበበት፣ በስሜት ከሚነዳ፣ በቂም ከታሰረ የፖለቲካ አመለካከት ራሳችንን ጠብቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡--”
      
    የእኛ ፌደሬሽን ገና አልተደላደለም፡፡ የተለያዩ ፌደሬሽኖች ፀንተው እንዲኖሩ ለማድረግ የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች ገና በወጉ አልተሰሩም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ እና ሪፐብሊካዊ ሐገር ፀንቶ ለመኖር የሚያስችላትን እውነተኛ ትምህርት መማር የጀመረች ይመስላል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ትልቅ ፌደራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሐገር ለመሆን አሁን ከፊቷ የተደቀኑትን የተለያዩ ፈተናዎች ማለፍ ይኖርባታል። እንደ እኔ ግምት ኢትዮጵያ አሁን የተደቀቃኑባትን ፈተናዎች በአስተዋይነት  ማለፍ ከቻለች፤ እየሰፋች የምትሄድ ፌደሬሽን (ኮንፌደሬሽን) መሆን የምትችል ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹እየሰፋች የምትሄድ ፌደሬሽን (ኮንፌደሬሽን)›› ያልኩት፤ እንደ አሜሪካ ‹‹የባላገር ቀይ ህንዳውያን›› መሬት እየተነጠቀች ሳይሆን፤ በብልጽግና፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ በታሪካዊ ሁኔታዎች እና በአፍሪካ ህብረት ራዕይ ድጋፍ በአካባቢዋ ያሉ ትናንሽ መንግስታትን የምታሰባስብ ሐገር መሆን የምትችል ይመስለኛል ለማለት ነው፡፡ ሆኖም በአስተዋይነት ፈተናውን ማለፍ ካቃታት ወይም መሪዎችዋ እና ህዝቧ በሰፊ ራዕይ ይዘው መንቀሳቀስ ካልቻሉ፤ በእጃቸው ያለውን አጓጊ ዕድል አምክነው፤ በቀላሉ ሊቀለበስ የማይችል ትርምስ ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ወሳኝ ሐገር ነበረች፤ አሁንም ነች፡፡ የኢትዮጵያ ነገር የገባቸው እና የታያቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው አለመረጋጋትና የሰላም ችግር አሳስቧቸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያንና መንግስት ለሠላምና መረጋጋት ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰሩ ባለፈው ሣምንት ጥሪ ቅርበዋል፡፡
‹‹መንግስትና የሐገሪቱ ህዝብ ችግሩን በመግባባት እንደሚፈቱ እምነት አለኝ›› ያሉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ መሃመት ፋኪ፤ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል መግባቱን በአወንታ ጠቅሰው፤ ‹‹የኢትዮጵያ መረጋጋት ለህዝቧ፣ ለቀጣናውና ለመላው አፍሪካ በእጅጉ አስፈላጊ ነው›› ብለዋል፡፡ ለዚህም መንግስትና ሁሉም የሐገሪቱ ባለድርሻዎች ሁሉ በኃላፊነት ስሜት እንዲቀሳቀሱ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም አመለካከት ማህጸን ነች፡፡ ‹‹የኢትዮጵያኒዝም›› ፍልስፍና መሠረት ነች፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻም በዚህ ሣምንት የምናከብረው የአድዋ ድል ነው፡፡ የአድዋ ድል ለአፍሪካ አህጉር ያለው ትርጉም ትልቅ ነው፡፡  ኢትዮጵያውያን ዛሬ የያዝነውን የብሔር፣ ብሔረሰብ መልክ ይዘን መቆየት የቻልነው በአድዋ ድል ነው። መምህሩ ጓኛዬ እንደሚለው፤ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንድ የሚያደርግ የሥነ ልቦና ቅርስ (ለምሣሌ፤ ከነጮች ጎን ሲቆሙ ያለ መሳቀቅ ሥነ ልቦና) የተፈጠረው በአድዋ ድል ነው፡፡
ዛሬ የምንኮራበትና የምንጣላበት የኢትዮጵያ ብሔር - ብሔረሰቦች ማንነት ተጠብቆ የዘለቀው በአድዋ ድል ነው፡፡ በዚህ ስሌት የአድዋ ጦርነት መሪ አጤ ምኒልክ፤ ለብሔር - ብሔረሰቦች ማንነት ተጠብቆ መቆየት ባለውለታ ናቸው፡፡ እርግጥ በዚሁ ጎዳና ክስ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ሊመሰገኑም የሚችሉ ናቸው፡፡ አጤ ምኒልክ፤ ለብሔር - ብሔረሰቦች ማንነት ተጠብቆ መቆየት ባለውለታ መሆናቸውን የሰማ አዝማሪ፤
ምኒልክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ፤
ቋንቋ እና ባህሉ፣
ጣሊያን ይሆን ነበር፣ ይህን ጊዜ አበሻ፤ ሊል ይችላል፡፡
ከፈለገ ይበል፡፡
እንዲያውም፤ ነገሩን ትንሽ ገፋ አድርገን፤ ‹‹እውነተኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የካቲት 23 ነው›› ለማለት እንችላለን። ኢትዮጵያ የብሔር - ብሔረሰቦች ሙዚየም መሆን የቻለችው በአድዋ ድል ነው፡፡ ታሪክ ቋሚ ምጸት መሥራት ስለሚወድ፤ ‹‹ኢትዮጵያን የብሔር-ብሔረሰቦች እስር ቤት ያደረጋት የአድዋ ድል›› የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ቢገጥሙኝ ቅር አይለኝም። እኛ ፖለቲከኞቹ እንቸገር ይሆናል እንጂ ታሪክ እንዲህ ያሉ በርካታ ‹‹የፈናጅራ›› ክንውኖችን ስለሚያውቅ በምፀተኛ ታሪክ ግራ አይጋባም፡፡
ነገር ግን የአድዋ ድል ኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን አፍሪካን ፈጥሯል፡፡ የአድዋ ድል ባይኖር አፍሪካ - አፍሪካ ለመሆን ብዙ ዘመን ትጓዝ ነበር። የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት ትግል ቀንዲል ነው። የጥቁር ህዝቦችን ህሊና እና እጅ ከቅኝ አገዛዝ ካቴና ያላቀቀ ዓለም አቀፍ አንድምታ (ብዙዎች በስህተት እንድምታ ይላሉ) ያለው ድል ነው፡፡ የድሉን አንድምታ ለመረዳት፤ ‹‹ኢትዮጵያ በአድዋ ተሸናፊ ብትሆን ኖሮ›› ብሎ ለማሰብ መሞከር ነው። ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ያሸነፈችው ኃይል፤ ከዚያ ቀደም በጥቁር የአፍሪካውያን ሊሸነፍ ይችላል ተብሎ የማይታሰብ ኃይል ነበር፡፡ ኢትየጵያ በዚያ ቅኝ ገዢ ኃይል ተሸንፋ ቢሆን ኖሮ፤ እርሷም ሆነች የተቀረው አፍሪካ እስከ ዛሬ ድረስ በቅኝ አገዛዝ ሊቆዩ ይችሉ ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊመሰረትና እንደ አሁኑ ወደ አፍሪካ ህብረት ሊሻገር አይችልም ነበር፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የአህጉሩ ሐገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማድረግ ዕድል አይኖረውም ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ባይኖር ኖሮ፤ የአፍሪካ ሐገራት ከቅኝ አገዛዝና ከአፓርታይድ አስተዳደር ነጻ ለመውጣት የሚያደርጉት ትግል ለብዙ ዘመናት ይራዘም ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ፤ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ የወጣችው ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ ከሦስት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡
ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካን ለመቀራመት በ1984-85 ዓ.ም በበርሊን ያካሄዱት ጉባዔ፣ በአፍሪካ ቅኝ አገዛዝን አጸና፡፡ የዚህን ጉባዔ መንፈስ በተግባርና በአስተሳሰብ የታቃወመችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ የአድዋ ድል በፈጠረው የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ፤ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር በመጀመሪያ የተገላገለችው ጋና ነበረች፡፡ ጋና በ1959 ነጻ ወጣች። በዛው ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረተች፡፡ እናም ከ1950ዎቹ (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ነጻነታቸውን ያገኙ ሐገራት ቢኖሩም፤ በርካታ ሐገራት ነጻ የወጡት በ1960ዎቹ (በብዛት) እና በ1970ዎቹ ዓ.ም ነበር፡፡ ነጻነትን በመቀዳጀት የመጨረሻዎቹ የሆኑት፤ ዝምባብዌ (በ1980) እና ደቡብ አፍሪካ (በ1994) ነበሩ - ዝምባብዌ ከቅኝ ገዢዎች፤ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ፡፡ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለዝምባብዌ ነጻነት አኩሪ ተጋድሎ አድርጋለች፡፡ በአጠቃላይ የፀረ - ቅኝ አገዛዝና የጸረ -አፓርታይድ ትግል መነሻ፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ተራሮች የተበሰረው ድል ነው፡፡ ያለ አድዋ የአፍሪካ ነጻነት ትግል እስከ ዛሬ ሊያዘግም ይችል ነበር፡፡ የአድዋ ድል የአፍሪካን የነጻነት ትግል መንፈስ ሲያቀጣጥል፤ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በድንጋጤ አርበድብዷል፡፡ አንዳንዶች የአፍሪካን ታሪክ ለመረዳት የአድዋ ድልን መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት ለዚህ ነው፡፡  
ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሣ መሃመት ፋኪ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሰበኝ›› ሲሉ ለወግ - ለአደባባይ ብለው አይመስለኝም። በርግጥም ያሳስባቸዋል፡፡ ሆኖም አሁን የፈጠርነው ፌዴሬሽን በደንብ እንዲጸና ልዩነቶችን የሚያርቅና ህብረትን የሚያጠናክር ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል - ወሬ አይደለም ሥራ፡፡ ሆኖም መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በደንብ የሚፈተንበትና ራሱን አረጋግጦ (አሻሽሎ) ለመዝለቅ ጥረት የሚያደርግበት ጊዜ መሆኑ ከወዲሁ ያስታውቃል፡፡ (ጎበዝ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ‹‹የማርያም ሰዓት›› መጠየቅ አይቻልም?)
ሆኖም ፈተናው በኛ ብቻ የወደቀ አይደለም። ሁሉም ፌዴሬሽኖች የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል፡፡ የአሜሪካ ፌደሬሽንም ከጆርጅ ዋሽንግተን እስከ አብርሃም ሊንከን ብዙ መከራ  ኣይቷል፡፡ ሆኖም አሜሪካ አስተዋይ መሪዎችና ብልህ ህዝቦችን የታደለች ሐገር በመሆኗ፣ ችግሮቹን በየጊዜው እየተሻገሩ ከዚህ ደርሰዋል፡፡ የአሜሪካ ፌዴሬሽን አባላት ቁጥርና የግዛቱ ስፋት እያደገ ሲሄድ አይተናል፡፡ የአሜሪካ ግዛቶች ከ13 ተነስተው ወደ 48 አድገዋል፡፡
እንደምናውቀው፤ የጆርጅ ዋሽንግተን (1789-97 ዓ.ም እ.ኤ.አ) አሜሪካ ባለ 13 ግዛቶች ነበረች። ሌሎቹ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የተጨመሩ ናቸው፡፡ ሆኖም ግዛቶቹ የተለያየ ባህርይ ያላቸው ነበሩ፡፡ የመጀመሪያዎቹ 13 ግዛቶች እንኳን በሁለት ቡድን የሚመደብ ልዩነት ነበራቸው፡፡ ልዩነቱ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ በሚል የሚታይ ነበር፡፡ የሰሜኑ አሜሪካ በዋናነት ኑሮውን በንግድ፣ በዓሣ ልማትና በበቆሎ ምርት የተመሠረተ ህዝብን የያዘ ነበር፡፡ የደቡቡ ደግሞ በሰፋፊ የትምባሆ፣ የሸንኮራ አገዳና (ወደ ኋላ) የጥጥ እርሻ ላይ የተመሠረተ ኑሮ ያለው ህዝቦችን የያዘ ነበር፡፡
ከዚህ ሌላ ደቡቡ ጭልጥ ባለ ሞቃታማ የሐሩር አውራጃ አካባቢ የሚሠሩ የበርካታ ባሮችን ጉልበት የሚጠቀሙ ግዛቶችን የያዘ ነበር፡፡ ደቡቡ የባርያ ጉልበት የሚጠቀሙ ትልልቅ እርሻዎች ያሉበት ክፍለ-ሐገር ሲሆን፤ ሰሜኑ ፋብሪካዎች፣ ባንኮችና ለተለያየ ሥራ የተቋቋሙ ቢሮዎች በብዛት የሚገኙበት ሆነ፡፡ ይህ ልዩነት አደጋ መጎተት ጀመረ፡፡ ታዲያ ይህ አልበቃ ብሎ፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ ሌላ ሦስተኛ ቡድን መጣ፡፡ ሦስተኛው ቡድን ‹‹ሚድል ዌስት›› ወይም ‹‹ዋይልድ ዌስት›› (መካከለኛው ምዕራብ ወይም እብዱ ምዕራብ) የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡
ዛሬ አሜሪካ ለተባለችው ሐገር ጥንስስ በመሆን ያገለገሉት የመጀመሪያዎቹ 13 ግዛቶች በሙሉ በአትላንቲክ ውቂያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ነበሩ፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ግዛቶች በስተምዕራብ፤ የባላገሮቹ ህንዳውያን ሰፊ የአደን ግዛት ሆኖ ያገለግል የነበረ አካባቢ ነበር፡፡ እንደ ሚሲሲፒ፣ ኦሃዮና ሚሶውሪ ያሉ ታላላቅ ወንዞች መፋሰሻ የሆነ እና የነጩ ዘር እግር ረግጦት የማያውቅ የተንጣለለ ግዛት ነበረ። ነጩ ዘር ግን አያርፍም፡፡ የሚሲሲፒ ሸለቆን ተሻግሮ ‹‹ሐገር ማቅናቱን›› ቀጠለ፡፡
ይህ አካባቢ ባላገሩ በትናንሽ መንደሮች የሰፈረበት፤ ሥልጣኔ የሚሉት ጉድ ያልደረሰበት፤ ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚሉ አደገኛ እረኞች የሚናኙበት፤ በሰፊ የሳር ምድር የሚግጡ ከብቶችን የሚዘርፉ ሰዎች የሚያውኩት አካባቢ ነው፡፡ በእንጨት የታጠሩ ለገበያ የሚያገለግሉ ከተማ ቀመስ ቦታዎች ያሉበት፣ ህግ የማያውቁና የማይገዛቸው ነጮች የሚኖሩበት፤ ሁሉም ሰው በድህነት የሚኖርበት፤ ማጭበርበር የበዛበት እና መሣሪያ የሌለው ሰው ከቶ ሊኖር የማይችልበት ሰፊ ግዛት ነበር፡፡ ለዚህ ነው፤ ‹‹ዋይልድ ዌስት›› ሲሉ የሚጠሩት፡፡
ታዲያ ለህግ መገዛት የማይሹ ሰዎች በአካባቢው ሥርዓት ሲጠናከር የሚኖሩበትን ሥፍራ ለቅቀው ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ይዘምታሉ። ህግ አክብረውና አስከብረው መኖር የሚሹ ሰዎች (ሥልጡኖች) በቦታው ይጸናሉ፡፡ ዘርፎ በላዎቹ አካባቢውን በመልቀቅ ወደ ምዕራፍ ሲሄዱ አካባቢው መደበኛ እርሻ ሥራ የሚሰራበት ሐገር ይሆናል፡፡ ‹‹መካከለኛው ምዕራብ›› የሚባለው አካባቢ በሰሜን ምሥራቅ አሜሪካ በሚገኙ ከተሞች ከምናገኛቸው ጮሌ ነጋዴዎች ወይም አገልግሎት ሰጪዎች፤ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙት አራሾች ለየት ያሉ ፍዝ የገበሬዎች የሚኖሩበት ግዛት ሆነ፡፡  
በ‹‹ሚድል ዌስት›› የሚኖሩት ገበሬዎች፤ የሚሲሲፒ ወንዝን ቁልቁል ቀዝፈው ወደ ደቡብ በመሄድ ምርታቸውን መሸጥ ቢችሉም፤ ከቴክሳስ እና ከሜክሲኮ የሚያገኙትን ተፈላጊ ዕቃ ሸምተው ሽቅብ እየቀዘፉ ይዞ መምጣቱ ይከብዳቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ደህና መንገድ እና ዘመናዊ የውሃ ትራንስፖርት አልነበረም፡፡ የሞተር ጀልባ አይታወቅም፡፡ ታዲያ አሜሪካውያን እነዚህን ሦስት የተለያዩ ግዛቶች በማስተባበር ፌደሬሽኑን ለማጽናት የቻሉት በኢንዱስትሪ አብዮት ድጋፍ ነበር፡፡ የአሜሪካ ፌዴሬሽን የኢንዱስትሪ አብዮት ውጤት ነው የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
የእኛ ፌደሬሽን ህብረት በምን የሚታገዝ ፌዴሬሽን እንደሆነ አላውቅም፡፡ በዚህ ረገድ ይሁነኝ ተብሎ የሚሠራ ነገር ካለ አላውቅም፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ፌዴሬሽን በረከት የተባለው የኢንዱስትሪ አብዮት አደጋ ይዞ መጥቷል። የኢንዱስትሪ አብዮት፤ በደቡብና በሰሜን መካከል ይታይ የነበረውን ልዩነት ይበልጥ አጉልቶታል። በዚህም የሐገሪቱን ህብረት የሚፈታተን አደጋ አስከትሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፤ በአሜሪካ ፌዴሬሽን ላይ ችግር የሥነ ህዝብ ጉዳይ አለ፡፡ አሜሪካ ስደተኞች በነጻት የሚገቡባት ሐገር በመሆኗ፤ ድህነትና ሥራ አጥነት ከአውሮፓ ምድር የሚያፈናቅላቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አሜሪካ ይመጡ ነበር። ይህ የህዝቡን ህሊናዊ ሁኔታ አዘበራረቀው፡፡ በርግጥ ከኢንግላድና ከአየርላንድ የሚፈልሱት፤ በቋንቋም ሆነ በአስተሳሰብ ከአሜሪካ ህዝብ የተለዩ አልበሩም። ሆኖም ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከፖላንድ የሚመጡት ስደተኞች የአሜሪካ ህዝብን ጥንቅር አዠጎረጎሩት። ይህን ችግር በመረዳትም ነጻ ስደት እንቅስቃሴው እንዲቆም ተደርጓል፡፡  
እንግዲህ እንደምታዩት ከሦስት ቡድን ይከፈሉ የነበሩት (የደቡቡ፣ የሰሜኑና የመካከለኛው ምዕራብ) የአሜሪካ ግዛቶች፤ በኢንዱስትሪ አብዮት በረከት ይበልጥ የተሳሰሩ ቢሆንም፤ ይህም የፌዴሬሽኑን ህብረት ያጠናከረው ቢሆንም፤ በሌላ በኩል የኢንዱስትሪ አብዮት ልዩነት እንዲጠናከርም አድርጓል፡፡
በወቅቱ እንግሊዝ ጥጥ አብዝታ የምትፈልግ በመሆኗ፤ በደቡብ የሚገኙት አሜሪካ ግዛቶች ጥጥ በሰፊው እያመረቱ፤ ከአትላንቲክ ውቂያኖስ ማዶ በመላክ ደህና ሐብት ማካበት ችለው ነበር፡፡ ሆኖም ነገሩ በዚህ ሁኔታ ብዙ አልዘለቀም፡፡ ሳሙኤል ስላተር የተባለ አንድ አሜሪካዊ፤ በእንግሊዝ ሐገር እንዳለው ያለ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ሲገነባ፤ የደቡብ አሜሪካ ገበሬዎች ለእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በሰሜን-ምሥራቅ አሜሪካ ግዛት ለሚገኙ ነጋዴዎች የጥጥ ምርታቸውን መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚህም ለተወሰነ ጊዜ ሁለቱም ሐብታቸው እየደረጀ መጣ። ታዲያ ይህ ሁኔታ የህልውና ተደጋጋፊነት ፈጥሮ ህብረቱን ያጠናከረውን ያህል፤ ሰሜንና ደቡቡ በሐብትና በውሳኔ ሰጪነት አቅም እንዲለያዩ የሚያደርግ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ 
እንደሚታወቀው፤ በእንፋሎት የሚሰሩ ጀልባዎች ሲመጡ፤ ‹‹በሚድል ዌስት›› አካባቢ ያለው ህዝብ በሌላው የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ከሚገኘው ህዝብ ጋር ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ተጠናክሯል፡፡ በእንፋሎት የሚሰሩት ጀልባዎች የሚሲሲፒ ወንዝን በቀላሉ ሽቅብ - ቁልቁል መቅዘፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ በ‹‹ሚድል ዌስት›› አካባቢ የሚመረተውን ምርት ወደ ደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ በቀላሉ ማጓጓዝ አስችሏል፡፡ ቋሚ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠርም ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታም የከተማ ነዋሪው ርካሽ ምግብ፤ የገጠሩ ህዝብ ደግሞ የተለያዩ ሸቀጦችን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ከጀልባዎቹ በተጨማሪ ንግዱን ይበልጥ የሚያሳልጡ ካናሎችም ተሰርተው የመጓጓዣ ዋጋ ሲቀንስ፤ የሸቀጥም ዋጋ ቀነሰ፡፡ ይህም ተደጋጋፊነት ያለው ኢኮኖሚ መፍጠር አስቻሏል።
ደግሞ ቆይቶ ባቡር መጣ፡፡ ከ1827 ጀምሮ ባቡር ትራንስፖርት በአሜሪካ ሥራ ጀምሯል፡፡ ሆኖም በ1860 ዓ.ም በአሜሪካ የነበረው የባቡር መስመር 45 ሺህ ኪ.ሜ ደርሶ ነበር፡፡ ይህም በየዓመቱ እየጨመረ፤ ብዙ አካባቢዎችን ተደራሽ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያም የምትገነባቸው አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ የአየር ጉዞ መስመሮች ተመሳሳይ ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ግንባታ ገና ብዙ ሥራ ይፈልጋል፡፡ አዲሱ ‹‹የኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አብዮት›› ለፌደሬሽን ግንባታችን በረከት እና መርገም ሆኖ እያስጨነቀን ይገኛል፡፡
ታዲያ የኢንዱስትሪ አብዮት የአሜሪካን አንድነት የሚፈታተን አደጋ ያመጣው፤ በገበሬዎቹ ደቡባውያና በሰሜን - ምሥራቆቹ ነጋዴዎች መካከል የሐብት ልዩነት በመፍጠሩ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ደቡቦቹ ‹‹በእኛ ኪሳራ ሰሜኖቹ እየበለፀጉ ነው›› የሚል ቅሬታ ተፈጠረባቸው። ከገቢ ሸቀጦች በሚገኘው ቀረጥ ሰሜኑ ሐብት ማግኘቱ ለደቡቦቹ አልተዋጠላቸውም፡፡ ሰሜኖቹ ከደቡቦቹ በላቀ ፍጥነት ኃያልና ሐብታም ሆኑ፡፡ ስለዚህ ደቡቦቹ ከሰሜኖቹ ተገንጥለን የራሳችንን ሪፐብሊክ እንመሠርታለን አሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ጥያቄዎች ተነሱ፤
‹‹ደቡቦቹ ከዩናትድ ስቴትስ የመገንጠል መብት አላቸው እንዴ?››
‹‹ለአሜሪካ ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ግዴታ የለባቸውም እንዴ?››
‹‹እንዴ፤ እንዲሁ ብድግ ብሎ መገንጠል አለ እንዴ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ተነሱ፡፡
ሰሜኖቹ መገንጠል ህገ ወጥና የተሳሳተ ጥያቄ ነው አሉ፡፡ ደቡቦቹ ደግሞ ‹‹ስህተት ተባለ - ትክክል እኛ እንገነጠላለን›› አሉ፡፡ በመጀመሪያ የመገንጠል ውሳኔ ያደረገችው፤ ደቡብ ካሮሊና ነበረች -በዲሴምበር 1860 ዓ.ም፡፡ በኋላ አስሩ የደቡብ አሜሪካ ግዛቶች የእሷን ፈለግ ተከትለው ከህብረቱ ወጡ፡፡ የራሳቸውን አዲስ መንገስት ለማቋቋም በመወሰን ተገነጠሉ፡፡ ጃፈርሰን ዳቪስ የተባሉ ሰውን ፕሬዚዳንት አድርገው፤ ኮንፌዴሬት ስቴት ኦቭ አሜሪካ በሚል የተሰየመ ነጻ መንግስት መመስረታቸውን አወጁ፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹ደቡቡ ከፌደሬሽኑ የመገንጠል መብት የለውም›› የሚል አቋም የያዙት ሰሜኖቹ (ፌዴራሊስቶች)፤ የመገንጠል ውሳኔውን ተቃወሙ። የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ለአምስት ዓመታት የቀጠለ ጦርነት ተካሄደ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ዝነኛው እና ታላቁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ወደ ስልጣን የመጡት፡፡ አሜሪካ በክፉ ጊዜ ጥሩ ፕሬዚዳንት አገኘች፡፡ ሊንከን ቀደም ሲል በጠቀስነው ‹‹በሚድል ዌስት›› ግዛት በምትገኘው ኬንቱኪ ስቴት ይኖር ከነበረ ድሃ ቤተሰብ የተወለዱ ናቸው፡፡ ሊንከን ጦርነቱ ባርነትን በመቃወም የሚደረግ ጦርነት አለመሆኑን ተናገሩ፡፡ ይልቅስ፤ ደቡቡ እንደ ፈለገው ተነስቶ መገንጠል እንደማይችል ለማሳየት የሚደረግ ጦርነት መሆኑን ገለፁ፡፡ ሊንከን በ1863 ዓ.ም ባርነት ከምድረ አሜሪካ መወገዱን አወጁ፡፡ በደቡብ የሚገኙት ባሮች ነጻ ስለ መሆናቸ አዋጅ አስነገሩ፡፡ ብዙዎች ከደቡብ ኮበለሉ፤ ወደ ሰሜን መጡ፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነቱ ለሦስት ዓመታት ከተካሄደ በኋላ፤ ጌቲስበርግ በተባለ ሥፍራ የተደረገው ጦርነት ድሉ በመጨረሻ የሰሜኑ እንደሚሆን ግልጽ ምልክት ሰጠ፡፡ ሆኖም ሮበርት ሊ የሚሉት የደቡቡ ጀነራል ተስፋ ቆርጦ፣ ለሰሜኑ አዋጊ ጀነራል እጁን የሰጠው፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1865 ነበር፡፡ ይህ በሆነ በአንድ ሣምንት ውስጥ ሊንከን በነፍሰ ገዳይ በተተኮሰ ጥይት፤ በቲያትር ቤት ውስጥ ሞቱ። ሆኖም ሥራቸውን አጠናቀው ነበር፡፡ 
ይህን ሐተታ የማጠቃልለው፤ አብርሓም ሊከን ቀደም ሲል በተጠቀሰችው፤ ወሳኝ ድል በተገኘባትና ‹‹ጌቲስበርግ›› በተባለችው ሥፍራ ለተሰዉ ወታደሮች መታሰቢያ የሚሆን መካነ ዕረፍት ለመመስረትና በጦርነቱ የተሰዉ ዜጎችን ለማሰብ ተብሎ በተዘጋጀ ስነ-ሥርዓት ላይ ያደረጓትን ዘመን ተሻጋሪ ዝነኛና አጭር ንግግር ሙሉ ቃል በመጥቀስ ነው፡፡ ኖቬምበር 19 1863 ዓ.ም ሊንከን በዚያች ንግግራቸው እንዲህ አሉ፤
‹‹አባቶቻችን ከዛሬ ሰማንያ ሰባት ዓመታት በፊት፤ ከነጻነት ማህጸን የተጸነሰች፤ ‹‹ሁሉም ሰው በፍጥረቱ እኩል ነው›› ለሚል መርህ ተገዢ የሆነች አዲስ ሐገር በዚህ አህጉር እውን አድርገዋል፡፡ ዛሬ እኛ፤ ይህች ሐገር ወይም ከተመሳሳይ ማህፀን የተጸነሰ እና ‹‹ሁሉም ሰው በፍጥረቱ እኩል ነው›› ለሚል መርህ ተገዢ የሆነ ሌላ ማናቸውም ሐገር ፀንቶ መዝለቅ መቻል - አለመቻሉን ሊያረጋግጥ የሚችል ታላቅ የእርስ በእርስ ጦርነት በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡ ዛሬ ለዚህ ዓላማ ሲባል ታላቅ ተጋድሎ በተካሄደበት አውደ ግንባር ተገናኝተናል። ከዚህ አውደ ግንባር የተወሰነ ሥፍራ ከልለን፤ ከፍ ሲል በተጠቀሰው እምነት የቆመችው ሐገር ህልውና ዘላቂ ይሆን ዘንድ ክቡር ህይወታቸውን መስዋዕት ላደረጉ ሰዎች የመጨረሻ መካነ ዕረፍት የሚሆን ሥፍራ ለመወሰን እዚህ ተገኝተናል፡፡ ይህን ማድረግም ፍጹም ተገቢ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ነገሩን ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው፤ እኛ መካነ ዕረፍት ልንወስን፣ ሥፍራውንም ልንቀድስ እና ልንባርክ አንችልም። ምክንያቱም፤ በዚህ ሥፍራ ተጋድሎ ያደረጉት፤ ዛሬ በህይወት ያሉ እና የተሰዉ ጀግኖች፤ ከእኛ የመጨመር ሆነ የመቀነስ አቅም ከፍ ባለ ሁኔታ፤ ሥፍራው አስቀድመው ቀድሰውታል። ዓለም ዛሬ በዚህ ሥፍራ የምንናገረውን ነገር ከቀብ አይቆጥረውም፤ ነገ ከነገ ወዲያም ጨርሶ አያስታውሰውም፡፡ ነገር ግን እኒያ ጀግኖች በዚህ ሥፍራ ያደረጉትን ነገር ለዝንተ ዓለም አይዘነጋውም። ይልቅስ ዛሬ እኛ በህይወት ያለነው ሰዎች፤ በዚህ ሥፍራ ተጋድሎ ያደረጉት ጀግኖች፤ እስከዚህ ምዕራፍ ድረስ በታላቅ ክብር ያራመዱትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ቃል ኪዳን መግባት ይኖርብናል። ከእንግዲህ ወዲህ መሰራት የሚገባውን ነገር ወይም ከፊታችን ያለውን ቀሪ ሥራ ለማከናወን ቃል መግባት ይገባናል። እኒያ የክብር ሞት የሞቱት ሰዎች፤ ፍጹም በሆነ እምነት ያራምዱት የነበረውን ዓላማ ከዳር ለማድረስ በላቀ መሰጠት ለመሥራት ቃል መግባት ይኖርብናል፡፡ እኒያ የሞቱ ወገኖቻችን በከንቱ እንዳልሞቱ ለማረጋገጥ በታላቅ ቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል፡፡ በፈጣሪ የታመነችው ይህች ሐገር፤ ከምድረ ገጽ ሊጠፋ የማይችል አዲስ ነጻነትን እንድትወለድ ማድረግ ይኖርብናል፡፡››
በ122ኛው የአድዋ ድል ክብረ በዓል ማግስት የምንገኘው ኢትዮጵያውያን፤ ለሐገራቸው ነጻነት ሲሉ፤ ኢትዮጵያ በነጻነት ፀንታ እንድትኖር ሲሉ፤ በአድዋ ተራሮች የተሰዉ ጀግኖች አባቶቻችንን በማሰብ፤ አንዲሁም ለዴሞክራሲና ለሰብዐዊ መብት መከበር ሲሉ ክቡር ህይወታቸውን የገበሩ ወንድሞቻችንን በመዘከር፤ እነርሱ የሞቱለትን ክቡር ዓላማ ከዳር ለማድረስ ቃል ኪዳን መግባት ይኖርብናል፡፡ ሐገራችን የቤተ ክርስቲያን ሻኩራና የቄሶች ጽናጽል፤ የመስጊድ ሙዐዚኖች አዛን፣ የጀማ መንዙማ፤ የህጻናት የቡረቃ ጩኸት፣ የትምህርት ቤት ደወል፣ የጎረምሶች እና የኮረዳዎች የፍቅር ዜማ፤ የገጣሚዎች ቅኔ እንጂ የጥይት ጩኸት፣ የሙሾ እና የረገዳ ራሮታዊ ድምጽ የሚሰማባት ሐገር እንዳትሆን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ሐገራችንን የሰይፍ ሳይሆን የሐሳብ ፍጭት የሚሰማባት ዴሞክራሲያዊት ሐገር ማድረግ ይገባናል፡፡ በወጉ ካልታሰበበት፣ በስሜት ከሚነዳ፣ በቂም ከታሰረ የፖለቲካ አመለካከት ራሳችንን ጠብቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበን፤ በማስተዋል ለመራመድ መወሰን ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያ ፈተና ላይ ነች፡፡ ከፖለቲካ መሪዎችም ብዙ ትጠብቃለች፡፡  

Read 7709 times