Print this page
Sunday, 04 March 2018 00:00

ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይጠበቃል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 የዛሬ ሁለት ሳምንት ግድም ከጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው የመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የሚተካ አዲስ
ጠ/ሚኒስትር በቅርቡ ይመረጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተተኪው ጠ/ሚኒስትር ሥልጣን የሚረኩበት፣አገሪቱ በዘርፈ ብዙ ችግሮች እየታመሰችና በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ለ6 ወር የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ ማግስትም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ለመሆኑ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይጠበቃል? ሀገሪቱን ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ለማውጣትና ለማረጋጋት ምን ማድረግ ይገባቸዋል? ይሳካላቸውስ ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

            “ሁሉንም በአንድ ዓይን የሚያይ መሆን አለበት”
              አባገዳ በየነ ሠንበቶ (የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ)

   እርግጥ ነው አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለወጠ እንጂ ስርአቱ ያው ነው፡፡ ቢሆንም አሁን የሚሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሃገሪቱን ህዝብ በሙሉ “ይሄ የኔ ነው፣ ያ የእከሌ ነው” ሳይል በአንድ ጥላ ስር፣ በአንድ አይን ሁሉንም የሚያይ መሆን አለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ማለት ጥላ ማለት ነው፤ ሰው ጥላ ስር ይቀመጣል፡፡ ጥላ ስር የሚቀመጠው እንዲያቀዘቅዘው ነው፡፡
የፀሃይ ሃሩር በሚኖርበት ጊዜ ሰውም እንስሳውም ጥላ ይፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን የተነሳው የሚፋጅ እሳት ነው። ከዚህ በፊት አይተን የማናውቀውን ነው እያየን ያለነው። ስለዚህ ያንን እሳት ለማቀዝቀዝ እንደ ዋርካ ጥላ ሆኖ፣ ጫጩቶቿን እንደምታቅፍ ዶሮ፣ ክንፉን ለሁሉም ዘርግቶ፣ ለዚህ ሃገር ህዝብ በሙሉ ከለላ መሆን መቻል አለበት፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ በዚህ መንገድ ይሄን ህዝብ ማረጋጋት ይኖርበታል፡፡
 ይህቺ ሃገር ካለኛ፣ እኛም ካለሷ የለንም። ጠ/ሚኒስትሩ ሰላም መፍጠር አለበት፡፡ የጦር ሃይሉንም ሆነ ህዝቡን ማረጋጋት ይጠበቅበታል፤ ሃገር በጦር መሣሪያ አትገዛም፡፡ ሃገርና ህዝብ የሚገዛው በትህትና ነው፡፡ የጦር አባላቱም እኛም፣ የአንድ እናት ልጆች ነን፡፡
የወለደችንን እናት እናውቃታለን፤ ምናልባት የማናውቀው አባታችንን ነው፡፡ ሁላችንም ከአንድ ማህፀን ነው የወጣነው። ስለዚህ አሁን የሚሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሁሉንም በአንድ ጥላ ስር አድርጎ፣ እንደ ዣንጥላ እላያችን ላይ ከለላ መሆን አለበት፡፡
ሰው የሀገር ፍቅርና አንድነት እንዲኖረው፣ ሰብአዊ ክብሩ እንዲጠበቅ የሚሠራ መሆን አለበት - አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡ እንደ አቶ ለማ፣ እንደ ዶ/ር አብይ ከአፋቸው ጥሩ ነገር የሚወጣው መሆን ይገባዋል፡፡ “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚል ተረት አለ፡፡ ጣፋጭ ፍትፍት ቢቀመጥ፣ ፍቅር ከሌለ አይበላም። ሰውን በፍቅር መግዛት ያስፈልጋል፡፡ አንደበት ሁሉን ያበርዳል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አንደበተ መልካም መሆን አለበት፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሄን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት አለበት፡፡ ምክንያቱም ወጣቶቻችን ከኛ ትዕዛዝና ተግሳፅ አይወጡም። እናውቃቸዋለን፡፡ የሃይማኖት አባቶችን፣ አባገዳዎችን ያከብራሉ፡፡ እነዚህ አባቶች፣ ሃገሩን ማረጋጋት አይከብዳቸውም፡፡ ወታደሩ የሃገሪቱን ዙሪያ ይጠብቅ፤ ከተማ መሃል ምንም አይሠራም፡፡
የቤቱን ጉዳይ ለመካሪዎች መተው ነው የሚያዋጣው፡፡ ወታደሩም የኛው ልጆች ናቸው፤ ወጣቶቹም የኛው ልጆች ናቸው፡፡ እኛ ይሄ ኮማንድ ፖስት የሚሉትን ነገር አልወደድነውም። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ይሄን ማወቅ አለበት፡፡ የእሬቻ በዓል በሰላም የተጠናቀቀው እኮ በኮማንድ ፖስት አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ ሃገሪቱን ማረጋጋት አያቅተንም፡፡
በጦር ማስተዳደር ለመንግስቱ ሃይለማርያምም አልበጃቸውም፡፡ የደርግ ወታደሮች ብዙ ሰው ጨርሰው፣ መጨረሻ ላይ ወደ ህዝቡ ነው ተመልሰው የገቡት፡፡ በእውነት የኢትዮጵያ ህዝብ የዋህ ነው፤ በቀላሉ ይመለሳል፡፡ ኮማንድ ፖስት አያስፈልገውም፡፡ ህዝቡ፤ የሽማግሌዎች፣ የአባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ቃል ጠባቂ ነው፡፡


-----------


            “እዚህ ደረጃ እንዴት እንደደረስን መፈተሽ አለበት”
             ስዩም ተሸመ (የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር)

   አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በመጀመሪያ ሊያደርግ የሚገባው፣ የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው የሚለውን ለይቶ ለማወቅ መጣር ነው፡፡ ወደ መፍትሄው ከመሄዱ በፊት የችግሩን መሰረታዊ መንስኤ ማስጠናትና መመርመር አለበት፡፡ አቶ ኃይለማርያም ስልጣን የለቀቁት በተደራረበ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግርና ቀውስ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ስልጣኑ የሚመጣው ሰው፣ በመጀመሪያ እንዴት እዚህ ደረጃ ደረስን ብሎ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡
ህዝብ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እየተጋጨ፣ ደሙን እያፈሰሰ፣ ጥያቄ የማቅረቡ ምክንያት የዲሞክራሲ ተቋማት ያለመኖራቸው ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡ የመብት ጥያቄ አለ፡፡ ህዝብ እንዴት ህይወቱን እየሰዋ፣ ወደ አደባባይ ወጣ የሚለውን፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር መመርመር አለበት፡፡ አሁን በሀገሪቱ ነፃና ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማት የሉም፡፡ ህዝቡ የተለየ ሃሳብ የሚያስተናግድበት፣ ብሶቱን ምሬቱን የሚገልፅበት ሚዲያ የለም፡፡ ሌላው ደግሞ በመንግስትና በማህበረሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ማገልገል የሚችሉ ሲቪል ማህበራት የሉም፡፡ እነሱ በሌሉበት የዲሞክራሲ መዋቅር መልሶ የሚገነባበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
የፖለቲካ መሪዎች በነፃነት እየተንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ የህዝቡን ድምፅ በአግባቡ ማስተላለፍ አልቻሉም፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ደግሞ ከ1997 በኋላ የመጡ የመንግስት ውሳኔዎችና አሰራሮች በሙሉ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በመሆናቸው ነው፡፡ ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር በዋናነት፣ ባለፉት 10 ዓመታት እንዴት የዲሞክራሲ መዋቅሮች ፈረሱ? ተፍረከረኩ? ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ከዚህ በመነሳትም እነዚህን የፈረሱ ተቋማት መልሶ መገንባት አለበት፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ የምንሰጥ ከሆነ፣ እነዚህ ምሰሶዎች መዋቀር አለባቸው፡፡ ደብዛቸው እንዲጠፋ ትግል ሲደረግባቸው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖችን መልሶ ድጋፍ ጭምር በማድረግ፣ ከውድቀታቸው አንሰራርተው፣ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታው ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ አለበት፡፡
የሲቪል ማህበራት ላይ የወጣውን መመሪያ፣ የፀረ ሽብር ህጉን፣ የሚዲያ አዋጁን በመፈተሽ የመዋቅር ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የሲቪል ማህበራት እንዲያንሰራሩ ማድረግ አለበት፡፡ በፀረ ሽብር ህጉ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች (ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ) ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ተደርጎ፣ ወደ ጫካ የገቡት ወደ ቤት እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ አጥተው ጫካ እንደገቡ ሁሉ ተስፋ አግኝተው፣ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን ምቹ መንገድ መሻት ያስፈልጋል። ገዥው ፓርቲ ለእነዚህ ቡድኖች ልባዊ ድጋፍ ሰጥቶ፣ መልሰው እንዲቋቋሙ በማድረግ፣ የጥላቻና የመፈራረጅ ምዕራፉን መዝጋት አለበት፡፡
እንደ ኢህአዴግ ባለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ ራስን በራስ ማጥፋት የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚህ ሂደት ታልፎ ግልፅና ገለልተኛ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ፣ ምናልባት እንደ 97 ዓ.ም ሽንፈት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይሄ ሽንፈት የማይቀር ቢሆን እንኳ ኢህአዴግ፣ እንደ “ስዋይን በርድ” (የወፍ ዓይነት) ነው መሆን ያለበት፡፡ ኮርያዎች ተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት ገዥው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ራሱን ለሽንፈት አጋልጦ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቢያደርግም አስቀድሞ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ከእስር ለቆ፣ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን አድርጎ ስለነበር፣ ምርጫውን ተዓማኒነት ባለው መልኩ ማሸነፍ ችሎ ነበር፡፡ ኮርያውያን ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት፣ ልክ አሁን እኛ በደረስንበት ደረጃ ላይ ወሳኝ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን በማድረጋቸው ነው፡፡
“ስዋይን በርድ” የምትባለው ወፍ ዝም ብላ ትኖርና፣ ልክ ልትሞት ስትል፣ ጥኡም ዜማ ታዜማለች፡፡ ኢህአዴግም እንዲህ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትርም እንደዚህች ወፍ ለራሱ ውድቀት የሚሰራ፣ ሀገሩን ያስቀደመ መሪ መሆን አለበት፡፡  


------------


              “ሙሉ ሥልጣን ያለው መሆን አለበት”
                 ዶ/ር አለማየሁ ረዳ

    አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ቀድሞው የመወሰን ስልጣኑ የተዳከመ ከሆነ፣ ምንም አይነት ለውጥ አንጠብቅም፡፡ ያው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው፡፡
ከዚያ በመለስ ኢህአዴግ ያለፉ ስህተቶቹን አርሞ፣ ሙሉ ስልጣን ያለው ጠ/ ሚኒስትር ከሾመ ግን ከሁሉም በፊት በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምንጭ ገምግሞ፣ እርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ ኢህአዴግ ራሱ የገመገመው የመድብለ ፓርቲ ስርአት መዳከም ጉዳይ ነው። የመድብለ ፓርቲ ስርአት መጎልበት የሚችለው የተሳትፎ መድረኩ ሲሰፋ ነው፡፡ ይሄ መጎልበት የሚችለው ደግሞ ህብረተሰቡ ውስጥ ነፃ የውይይት ባህል መዳበር ሲችል ነው፡፡
ኢህአዴግ በመረጠው ሳይሆን ህብረተሰቡ የራሱን ጉዳይ ሲወያይ ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በሚዲያው ላይ የተጣለው እቀባ መነሳት አለበት፡፡ ሚዲያው በኃላፊነት እንዲሰራ መለቀቅ አለበት፡፡ ህብረተሰቡ በሚዲያ አማካይነት ነው ሃሳቡን መግለፅ የሚችለው፡፡ ሌላው የሲቪል ማህበረሰቡ ነፃ ሆኖ፣ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጎለብት ማድረግ አለበት፡፡ በዚህ ላይ የተጣለው እቀባም መነሳት አለበት፡፡ ይሄ ከሆነ ውይይቶች ይፈጠራሉ። ይሄ ቶሎ እርምጃ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
ወደ ስራ አፈፃፀም ስንገባ፣ የመልካም አስተዳደሩን ለማስተካከል፣ የባለስልጣን መንጋውን ማፅዳት አለበት፡፡ በብቃትና በችሎታ ላይ የተመሰረተ ምደባ መደረግ ይገባዋል፡፡ ሌላው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን የሚመለከት ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በመዋቅር ደረጃ ሊቀይር የሚችል የኢንቨስትመንት ስርዓት አልተዘረጋም፡፡ የታክስ ስርአቱ ችግር አለበት፡፡ በዚህ ላይ የዘርፉ ተዋናይና መንግስት መተማመን ስላለባቸው፣ ተከታታይ ውይይት ያስፈልጋል፡፡
የወጣቱ ስራ አጥነት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ይሄ ስራ ያጣ ወጣት ነው፣ ነገ ከነገ ወዲያ ድንጋይ የሚወረውረው፡፡ ስደት አላዋጣውም፡፡ “ስደትም ብሄድ እዚህም ብቆይ ሞት ነው” የሚል አስተሳሰብ እንዳያደብር ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ከምንም ተነስተው ሚሊየነር የሆኑ ግለሰቦች እየፈጠሩት ያለው ነገር ማቃለል የሚቻለው ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በመጀመሪያ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የህዝቡን እምነት ማግኘት አለበት፡፡


-------------


             “አራት መሰረታዊ ለውጦች ይጠበቃሉ”
               ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

    ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር የሚጠበቀው ትልቁ ጉዳይ፣ አራት መሰረታዊ ለውጦችን እውን ማድረግ ነው፡፡ አንደኛ፤ ስርአትና ህጉን የጠበቀ፣ ሁላችንም ባንስማማበትም የምንግባባበት የፍትህ ስርአት መፍጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ቢጠፋ እንኳ መንግስትን ሳይቀር ከስሶ ማስተካከል የሚቻልበት ስርአት ከተመሰረተ የተሻለ ይሆናል። ሁለተኛ፤ ፖለቲካዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡ በዚህች ሀገር ማንም የማይገለልበት፣ ማንም ደግሞ የተለየ ጥቅም የማያገኝበት፣ ሁላችንንም በእኩልነት ሊያስተናግድ የሚችል፣ እያደገ የሚሄድ የፖለቲካ ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህን በአንድ ቀን መፍጠር አይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን መንገዱ መዘርጋት አለበት፡፡ ወደዚያ እየተጓዝን መሆኑን የሚያሳይ አረንጓዴ መብራት ማሳየት ይኖርበታል፡፡  
በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ማንም በሀገሪቱ ውስጥ የተለየ ተጠቃሚ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠቃሚ አይደለም እየተባለ የማይወቀስበት ስርአት መዘርጋት አለበት፡፡ ሰዎች በስራቸው ብቻ የሚያገኙበት የኢኮኖሚ ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
በአራተኛ ደረጃ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ፤ ለእነዚህ ሁሉ እንደ ጠባቂም፣ እንደ ዋና የሃሳብ ማንሸራሸሪያ የሚሆን ተዓማኒ፣ ገለልተኛ የሆነ፣ ዜጎችን የሚጠቅም የሚዲያ ስርአት መዘርጋት ነው፡፡ ይሄ የሚዲያ ስርአት ከተዘረጋ ሌሎችን ሁሉ እየጠበቀ፣ እያረመ፣ እያስተካከለ፣ ህዝቡ ሁሉ ሃሳቡን ስለሚገልጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ወይም በጎዳና ላይ ማመፅ ላያስፈልገው ይችላል፡፡
ስለዚህ በእነዚህ አራቱ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችል፣ የኢትዮጵያን የእድገት  ደረጃ፣ የህዝቡን ፍላጎትና ዓለም የደረሰበትን ለውጥ  እውን ለማድረግ  ብቃት ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ያስፈልገናል፡፡

Read 4620 times