Sunday, 04 March 2018 00:00

መድረክ አስቸኳይ የአገር አድን ድርድር እንዲያካሄድ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 ኢራፓ ለፓርቲዎች የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ ሊያዘጋጅ ነው

     የአራት ድርጅቶች ህብረት የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፤ ከገዥው ፓርቲ ጋር አስቸኳይ የሃገር አድን ድርድር እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ፡፡ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በበኩሉ፤ (ኢራፓ) በበኩሉ ኢህአዴግን ጨምሮ ከ35 በላይ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የብሔራዊ መግባባት ውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡
“ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ገዥው ፓርቲ ብቻውን ሊታደጋት አይችልም” ያለው መድረክ፤ ሁሉም በሀገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት አስቸኳይ የድርድር መድረክ መከፈት አለበት ብሏል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ ገብቷል፣ ልዩነቶች እየሰፉ በመሄዳቸው ቅራኔዎች ወደማይታረቁበት ደረጃ ደርሰዋል ያለው የመድረክ መግለጫ፤ ለዚህ መፍትሄው የህዝብ ወኪሎች ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ድርድር ማካሄድ ብቻ ነው ብሏል፡፡
ዜጎች ለአመታት የመብት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን፣ በዚህ የበርካቶች ህይወት እየጠፋ፣ የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎች በህግ እየተጠየቁ አለመሆኑን የጠቆመው መድረክ ከዚህ በኋላ በዚህ መንገድ መቀጠል አይቻልም፤ ከድርድር የሚመነጭ አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ኢራፓ ለብሔራዊ መግባባት ውይይት ጥሪ ካቀረበላቸው 60 ፓርቲዎች 35ቱ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ መላኩ መለሰ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ እና መኢአድ፣ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ መአህድ፣ኦብኮ፣ የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ፣ ኢዴህ፣ ቅንጅት የብሔራዊ መግባባት መድረኩ አካል ለመሆን ስምምነታቸው ከገለፁት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለኢህአዴግም ሆነ ለአጋር ድርጅቶቹ በደብዳቤ ጥሪ እያደረስን ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ ፓርቲዎች ህዝቡን የሚወክሉ እንደመሆናቸው፣ በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ያለመውን ጉባኤ በመጪው ቅዳሜ ለማሰናዳት ፓርቲያቸው ማሰቡን አስታውቀዋል።
ስብሠባው ህጋዊ እውቅና አግኝቶ እንዲካሄድ ፓርቲው ለኮማንድ ፖስቱ የፍቃድ ማመልከቻ እንደሚያስገባ አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

Read 6438 times