Sunday, 04 March 2018 00:00

የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የ1.2 ሚ ብር መኪና ተበረከተላቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

   “ኢትዮጵያ የተሻለች እንድሆን የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ”

    በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፤ ከሃረርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዘመናዊ መኪና የተበረከተላቸው ሲሆን “ስጦታው ፈፅሞ ያልጠበቅሁት ነው” ብለዋል፡፡
1.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኒሳን ካሽካይ አውቶሞቢል በድንገት የተበረከተላቸው ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፤ የማህበረሰቡን መብት ለማስከበር በተደረገው ትግል ላይ የኔ ድርሻ ከሌላው የተለየ ሆኖ አይደለም፤ ነገር ግን ስጦታው ለሌላውም አርአያነት አለው” ብለዋል፡፡
“እኔ ምናልባት በሚዲያ ስለምታወቅ ይሆናል እንጂ ብዙዎች በሚያምኑበት አመለካከትና አደረጃጀት በርካታ ኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለዋል” ሲሉ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ኡስታዝ አህመዲን፤ ዛሬም በእስር ቤት ያሉ በርካቶች ናቸው፤ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል፡፡
በፖለቲካዊ ጉዳይ የታሰሩ በርካታ ዜጎች ዛሬም በእስር ቤት እንደሚገኙ የጠቀሱት ኡስታዝ አህመዲን፤ እነዚህን ሰዎች ማስታወስም ያስፈልጋል ብለዋል። የተበረከተላቸው ሽልማት በእስር ቤት ቆይታቸው ኑሮአቸው ለሚበተን ሰዎች አርአያነት ያለው ነው ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ መንግስት አሸባሪም ሆነ ሌላ መለያ፣ እየሰጠ ካሰራቸው ሰዎች ጎን በመቆም አለኝታነቱን ማሳየቱ መንግስትና ህብረተሰቡ ምን ያህል እየተራራቁ መሆኑን ያሳያል ያሉት ኡስታዝ አህመድ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስትም አመለካከቱን ቆም ብሎ መፈተሽ አለበት ሲሉም ምክረዋል፡፡
ቀጣይ  እቅዳቸውን በተመለከተም ሲናገሩ “ከዚህ በኋላ በሃይማኖትና በሌሎች በምሰራቸው ስራዎች ብቻ ሳልታጠር ኢትዮጵያ የተሻለች እንድትሆን አቅሜ በፈቀደ ሁሉ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የበኩሌን አስተዋፅኦ አበረክታለሁ” ብለዋል። በሃይማኖት አስተምህሮውም ሆነ በመብት ታጋይነት እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
ኡስታዝ አህመዲን በወዳጆቻቸው መኖሪያ ቤት በተዘጋጀላቸው የምሳ ግብዣ ላይ ለመሄድ ከቤታቸው በሚወጡበት ወቅት ባልጠበቁት ሁኔታ የመኪና ስጦታው እንደቀረበላቸው ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን በስጦታ ሥነስርዓቱ ላይም አባገዳዎች፣ የሃይማኖች አባቶችና የህብረተሰቡ ተወካዮች መገኘታቸው ተናግረዋል፡፡

Read 7835 times